Sunday, April 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለ አራት ኮከብ ሆቴል ግንባታ 30 በመቶ ተጠናቀቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ65 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚያስገነባው ባለ አራት ኮከብ ዘመናዊ ሆቴል ግንባታ 30 በመቶ ተጠናቀቀ፡፡

የሆቴሉ ግንባታ የሚካሄደው በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት አቅራቢያ ሚሊኒየም የስብሰባ አዳራሽ ፊት ለፊት በሚገኝ 40,000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ነው፡፡ በጥር 2008 ዓ.ም. የተጀመረው የሆቴል ግንባታ በመፋጠን ላይ መሆኑን የገለጸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ግንባታው በተጀመረ በሰባት ወራት ውስጥ 30 በመቶ  ሥራው መጠናቀቁን ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

ሆቴሉ የአየር መንገዱንና የደንበኞቹን ፍላጐት የሚያሟላ መሆኑን የገለጸው አየር መንገዱ፣ አራት የተለያዩ ምግብ ቤቶች፣ ሁለት መጠጥ ቤቶችና 370 የመኝታ ክፍሎች እንደሚኖሩት አስታውቋል፡፡ ከአራቱ ምግብ ቤቶች መካከል አንዱ ግዙፍ የቻይና ምግብ ቤት መሆኑን፣ በመጠኑ ከአፍሪካ ትልቁ የቻይና ምግብ ቤት እንደሚሆን ተገልጿል፡፡ ሆቴሉ ሁለት የመዋኛ ገንዳዎች፣ የስጦታ ዕቃ መሸጫ ሱቆች፣ የቀረጥ ነፃ ሱቆች፣ ኬክ ቤቶችና ጂምናዚየም አሟልቶ እንደሚይዝ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ 2,000 ሰዎች የሚያስተናግድ የመሰብሰቢያ አዳራሽና ሦስት አነስተኛ የመሰብሰቢያ ክፍሎች ይኖሩታል ተብሏል፡፡

የሆቴሉ አጠቃላይ ወጪ 65 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ሲሆን፣ ግንባታውን በማካሄድ ላይ የሚገኘው አቪክ የተሰኘ የቻይና ኩባንያ ነው፡፡ የፕሮጀክቱ አማካሪ ሞረን አሶሼትስ ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት ስለሺ ኮንሰልት ከተባለ ታዋቂ አገር በቀል አማካሪ ድርጅት ጋር በመተባበር እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የሆቴሉ ግንባታ ከዕለት ወደ ዕለት በመፋጠን ላይ መሆኑን የገለጸው አየር መንገዱ፣ በታኅሳስ 2010 ዓ.ም. ግንባታው ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ አስታውቋል፡፡ ሆቴሉን መገንባት ያስፈለገበት ምክንያት አየር መንገዱ ደንበኞቹን የሚያስተናግድበት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል በማስፈለጉ መሆኑን አስረድቷል፡፡ አየር መንገዱ በጽሑፍ በሰጠው ምላሽ፣ ‹‹በኤርፖርቱ አቅራቢያ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሆቴል አገልግሎት መኖር አየር መንገዱ ለሚሰጠው ጥቅል የጉዞ አገልግሎት ወሳኝ ነው፤›› ብሏል፡፡

ሆቴሉ ወደ ሥራ በሚገባበት ወቅት የሚያስተዳድረው ማነው ለሚለው ጥያቄ በሰጠው ምላሽ፣ ከቻይና የሆቴል አስተዳደር ኩባንያ ጋር ድርድር በመካሄድ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡ የሆቴል ማኔጅመንት ውል ከተጠናቀቀ በኋላ ለሆቴሉ ስም እንደሚወጣለት የጠቆመው አየር መንገዱ፣ ሆቴሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገሪቱን እንደ አፍሪካ ምርጥ የቱሪስት መዳረሻ ለማስተዋወቅ ለሚያደርገው የማስተዋወቅ ሥራ ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው ገልጿል፡፡

ራዕይ 2025 በተሰኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ15 ዓመት የዕድገት መርሐ ግብር የተለያዩ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ የአቪዬሽን አካዳሚው በ100 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የማስፋፊያ ፕሮጀክት የተጠናቀቀ ሲሆን፣ የምግብ ማደራጃ፣ ግዙፍ የካርጐ ተርሚናልና የአውሮፕላን የጥገና ማዕከል ግንባታ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች