ትውልደ ኢትዮጵያዊ በሆኑ የእስራኤል ዜጋ አካውንትና በሌላ የዳያስፖራ አካውንት ላይ በድምሩ 4.3 ሚሊዮን ብር በማጉደል፣ በመንግሥት ላይ ጉዳት በማድረስ የተጠረጠሩ ሦስት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች ታሰሩ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ አቶ ዓለማየሁ ዲንቃ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጦር ኃይሎች ቅርንጫፍ የደንበኞች አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ ሲሆኑ፣ ውቢት ዓለማየሁና ፀጋአብ ሐጎስ የተባሉት ተጠርጣሪዎች ደግሞ የአንድነት ቅርንጫፍ ሠራተኞች ናቸው፡፡
አቶ ዓለማየሁ የእስራኤል ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊው አቶ ተስፋዬ ኪዳኔ ሒሳብ ላይ በሐሰተኛ ሰነድ 2,500,000 ብር ወጪ ሲደረግ ማፅደቃቸውን፣ የፌዴራል ፖሊስ የፋይናንስ ወንጀሎች ምርመራ ቡድን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት አስረድቷል፡፡
ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ደግሞ ስሙ ካልተጠቀሰ የዳያስፖራ ሒሳብ ላይ 1,800,000 ብር ተስፋዬ ንጉሤ ለተባለ ግለሰብ በመክፈልና በማጽደቅ ከባንኩ አሠራርና መመርያ ውጪ ተጠርጣሪዎቹ የማይገባ ተግባር መፈጸማቸውን ፖሊስ ገልጿል፡፡
ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣትና ሥራን በማይሆን መንገድ በመምራት ባንኩን ለከፍተኛ ኪሳራ መዳረጋቸውን ፖሊስ ለፍርድ ቤት አስረድቷል፡፡ በመሆኑም የሰውና የሰነድ ማስረጃ አጣርቶ ለሚመለከተው የፍትሕ አካል ለማቅረብ የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ተጠቀይቶባቸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን ስምንት ቀናት ብቻ በመፍቀድ ለጳጉሜን 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡