በጋምቤላ ክልል በሕጋዊ መንገድ ሠፍረው ይኖሩ የነበሩ በአካባቢው አጠራር ‹‹ደገኞች›› የሚባሉ አንድ የስምንት ወር ነፍሰ ጡርና ባለቤታቸውን ቤታቸውን ላያቸው ላይ ቆልፈው በማቃጠል ሕይወታቸው እንዲያልፍ ማድረጉ የተረጋገጠበት ተከሳሽ፣ በ25 ዓመታት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ፍርድ ቤት ውሳኔ ሰጠ፡፡
የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የመሠረተውን ክስ ሲመረምር የከረመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በሰጠው ውሳኔ እንዳብራራው፣ በጋምቤላ ክልል ማጃንግ ዞን ጎደሬ ወረዳ ነዋሪ የሆነው ሙሉጌታ ኩንዴ ሸነክ የፈጸመው አሰቃቂ የነፍስ ግድያ ድርጊት፣ በዓቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ተረጋግጧል፡፡
ፍርደኛው ከመሬትና ይዞታ አጠቃቀም ጋር በተገናኘ፣ ‹‹አገራችንን ለቃችሁ ውጡ፣ የማትወጡ ከሆነ የኃይል ዕርምጃ እንወስዳለን፤›› ብሎ መዛቱንና በዛቻውም መሠረት ከግብር አበሮቹ ጋር ሆኖ የስምንት ወር ነፍሰጡር የነበሩትን ወ/ሮ አስቴር የቦና ባለቤታቸውን አቶ ገረመው ገሞታን ጳጉሜን 5 ቀን 2006 ዓ.ም. በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በመቆለፍ አቃጥለው እንደገደሏቸው፣ በሰውና በሰነድ ማስረጃዎች መረጋገጡን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ያስረዳል፡፡
ፍርደኛው ዜጎች በፈለጉበት ቦታ ተዘዋውረው የመኖርና ሀብት የማፍራት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን በመተላለፍ ቤታቸው እንዳሉ ጨካኝነትና ነውረኝነት በተሞላበት ሁኔታ በላያቸው ላይ በር በመቆለፍና ቤቱን እሳት በመለኮስ፣ ቤቱ ነዶ እስከሚያልቅ ድረስ ከግብር አበሮቹ ጋር ክላሽኒኮቭ ጠመንጃ ይዘው በመጠበቅ በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደሉ በ25 ዓመታት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ለሁለት ዓመት ከሕዝባዊ ተሳትፎው እንዲታገድም ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡