Friday, February 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበኦሮሚያ አመፅ ንብረት ለወደመባቸው ካሳ ለመክፈል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ እየተጠበቀ ነው

በኦሮሚያ አመፅ ንብረት ለወደመባቸው ካሳ ለመክፈል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ እየተጠበቀ ነው

ቀን:

–  በአማራ ክልል ንብረት እየወደመባቸው የሚገኙ ሪፖርት ማቅረብ ጀመሩ

በኦሮሚያ ክልል ተከስቶ በነበረው ሁከት ንብረት ለወደመባቸው ባለሀብቶች ካሳ ለመክፈል ሲካሄድ የቆየው ጥናት ተጠናቆ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ቀረበ፡፡ በአማራ ክልልም እየተካሄደ ባለው ሁከት ንብረት እየወደመባቸው የሚገኙ ባለሀብቶች ሪፖርት እያቀረቡ መሆኑ ታውቋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በተቀሰቀሰው ደም አፋሳሽ ግጭት 20 ኩባንያዎች የንብረት ውድመት ደርሶባቸዋል፡፡ የንብረቶቹ ባለቤቶች ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አቤቱታ አቅርበዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስተባባሪነት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የሚሳተፉበት ኮሚቴ ተዋቅሮ፣ የንብረት ውድመቱን እንዲያጠና ትዕዛዝ መሰጠቱን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በዚህ መነሻ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጉዳት ደርሶባቸዋል ያላቸውን 20 ባለሀብቶች መረጃ በመቀበል ማጣራቱን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጌታሁን ነጋሽ፣ ንብረት ለወደመባቸው ባለሀብቶች ካሳ ለመክፈል ሲካሄድ የቆየው ጥናት መጠናቀቁን ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡ በካሳ ማዕቀፍ ውስጥ ከተካተቱት ባለሀብቶች መካከል የአትክልት፣ የፍራፍሬና የአበባ እርሻዎች እንዲሁም ፋብሪካዎችና የልማት ድርጅቶች ይገኙበታል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ለደረሰው ውድመት ካሳ ለመክፈል የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ውሳኔ በሚጠበቅበት ወቅት፣ ከአማራ ክልል የንብረት ውድመት የደረሰባቸው ኩባንያዎች ካሳ እንዲከፈላቸው ጥያቄዎች ማቅረብ እንደጀመሩ ተጠቁሟል፡፡

ወራት ያስቆጠረው የአማራ ክልል ደም አፋሳሽ ሁከት በኦሮሚያ ክልል እንደሆነው ሁሉ በርካታ ሕይወት የጠፋበት፣ የአካል ጉዳት የደረሰበትና ንብረት የወደመበት ሆኗል፡፡

በዚህ ሁከት ጉዳት ከደረሰባቸው ከአሥር በላይ ኩባንያዎች ውስጥ ቆጋ ቪጂ አግሮ ዴቨሎፕመንት ኩባንያና በኢስመራልድ ጥላ ሥር የሚገኘው ኮንዶር እርሻ ይገኙበታል፡፡

ቆጋ ቪጂ በምዕራብ ጎጃም ዞን ውስጥ ይገኛል፡፡ ይህ ኩባንያ በቤልጂየም ባለሀብት የተቋቋመ ሲሆን፣ በውኃ ሥራዎች ላይ በተሰማራው ዱረብሊቲ ኩባንያ ጥላ ሥር ይገኛል፡፡ ኩባንያው ከአማራ ክልል 52 ሔክታር መሬት ተረክቦ በ68.7 ሚሊዮን ብር ካፒታል አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት ላይ ነበር፡፡

የኩባንያው የመስኖ ሥራዎች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ባንተአምላክ መንግሥቴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ማክሰኞ ነሐሴ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. በአካባቢው በተነሳ ሁከት በእሳት ወድሟል፡፡

‹‹በተፈጠረው ቃጠሎ የኩባንያው ንብረት ሙሉ በሙሉ ወድሟል፡፡ ምንም የሚነሳ ንብረት የለም፤›› ሲሉ የደረሰውን ውድመት ስፋት ተናግረዋል፡፡ ኩባንያው አደጋ እንደደረሰ ወዲያውኑ ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ሪፖርት ማድረጉን አቶ ባንተአምላክ ገልጸው፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃዎችም ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡

ቆጋ ቪጂ አትክልትና ፍራፍሬ ኤክስፖርት ማድረግ የጀመረው በ2006 ዓ.ም. ነበር፡፡

 ሌላኛው የሆላንድና የአሜሪካ ኩባንያ የሆነው ኮንደር ፋርም ነው፡፡ ይህ ኩባንያ ከባህር ዳር ከተማ ወደ አዲስ አበባ በሚወስደው መንገድ 13 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡

ኩባንያው ከክልሉ 150 ሔክታር መሬት በመረከብ በመጀመሪያው ዙር 35 ሔክታር መሬት ማልማት ችሏል፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት ኩባንያው 10.5 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ በማድረግ ወደ ሥራ በመግባት፣ ካለፈው ኅዳር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በየወሩ 250 ሺሕ ዩሮ ወደ ውጭ ከሚልከው አበባ ገቢ ማግኘት ጀምሮ ነበር፡፡

ከ2009 በጀት ዓመት ጀምሮ ኩባንያው በወር 500 ሺሕ ዩሮ ገቢ ለማግኘት የተለያዩ ሥራዎችን መሥራት ጀምሮ እንደነበር፣ የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይሌ ሰይፉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አቶ ኃይሌ እንደተናገሩት፣ ባለፈው ሳምንት ሰኞና ማክሰኞ በአካባቢው በተፈጠረው ሁከት አምስት ከባድ ተሽከርካሪዎች፣ 100 ሜትር ርዝመት ያለው የማቀዝቀዣ ማሽን፣ 500 ሰዓት ብቻ የሠራ 640 ኪሎ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው ጄኔሬተርና እርሻው ተቃጥለዋል፡፡ የቀሩ ንብረቶችም ላይ ዘረፋ መካሄዱን አቶ ኃይሌ ተናግረዋል፡፡

‹‹ማኅበራዊ ኃላፊነቶችን በሚገባ እየተወጣን ነበር፡፡ የዚህ ፕሮጀክት መኖር ለአካባቢው በጣም ጠቃሚ ነበር፤›› ሲሉ አቶ ኃይሌ ፕሮጀክቱ አካባቢውንም እየጠቀመ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

ኩባንያው ቃጠሎ እንደደረሰበት ወዲያውኑ ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንና ለሌሎች ለሚመለከታቸው አካላት ማስታወቁን አቶ ኃይሌ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ባህረ ለዚህ ኩባንያ 70 በመቶ የሚሆነውን ፋይናንስ ያደረገው ልማት ባንክ መሆኑን ገልጸው፣ የኩባንያውን ውድመት መስማታቸውን አስታውቀዋል፡፡

በአማራ ክልል በሚገኙ ሦስት ዞኖች 15 የአትክልት፣ የፍራፍሬና የአበባ ኩባንያዎች ኢንቨስት በማድርግ ላይ ይገኙ ነበር፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች በድምሩ 350 ሔክታር የሚጠጋ መሬት በማልማት ላይ የነበሩ ሲሆን፣ ከእነዚህ ኩባንያ ውስጥ ዘጠኝ ያህሉ በተፈጠረው ሁከት ውድመት አጋጥሟቸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ የካቤኔ አባል የሆኑት አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሚያቀርቡትን ቅሬታ እያዳመጡ ነው] 

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር በእጅጉ ስላሳሰበኝ ነው በአካል...

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የፈጠሩት አምቧጓሮ

ባለፈው ቅዳሜና እሑድ በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት 37ኛው...

የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ትግበራ የፈጠራቸው አሉታዊና አዎንታዊ ጎኖች

የአገሪቱ ንግድ ባንኮች በዓመት የሚሰጡት የብድር መጠን ላይ የኢትዮጵያ...

ቱግ ቱግ!

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ለመታደም የመጡ እንግዶችን ሸኝተን ከፒያሳ ወደ...