Tuesday, March 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ ጂቡቲ የምድር ባቡር መስመር የማስተዳደር ሥራ ግንባታውን ላካሄዱት የቻይና ኩባንያዎች ተሰጠ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከ3.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ በቻይና ኩባንያዎች ተገንብቶ መስከረም 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ሥራ ይጀምራል የተባለው የአዲስ አበባ ጂቡቲ ምድር ባቡር መስመር ለማስተዳደር፣ በጥምረት የቀረቡት ሁለት የቻይና ኩባንያዎች መመረጣቸው ተገለጸ፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት ሥራውን እንደሚረከቡ ይጠበቃል፡፡

በኢትዮጵያና በጂቡቲ መንግሥታት ስምምነት መሠረት የአዲስ አበባ ጂቡቲ የምድር ባቡርን አጠቃላይ የሥራ ሒደት ለማስተዳደር ከተመረጡት ኩባንያዎች፣ ግንባታውን እያከናወኑ ያሉት የቻይና ሬልዌይ ግሩፕና የቻይና ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ናቸው፡፡

ሁለቱ ኩባንያዎች የአዲስ አበባ ጂቡቲ ምድር ባቡር አገልግሎትን ከሦስት እስከ አምስት ዓመት ለሚሆን ጊዜ የኦፕሬሽንና የማኔጅመንት ሥራውን ተረክበው ያከናውናሉ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኩባንያዎቹ በኮንትራት ጊዜው ውስጥ የባቡርና የሐዲድ ጥገና ሥራዎችንም ጨምረው ይሠራሉ፡፡ ለዚህ አገልግሎታቸው ሊከፈላቸው የሚችለውን የገንዘብ መጠን ግን አልገለጹም፡፡

የአስተዳደር ሥራውን ለውጭ ኩባንያዎች ለመስጠት በወጣው ጨረታ አሸናፊ መሆናቸው ከተጠቀሱት የቻይና ኩባንያዎች ባሻገር የቱርክና የፈረንሳይ ኩባንያዎችም በጨረታ ተሳታፊ የነበሩ ቢሆንም፣ የአዲስ አበባ ጂቡቲ የምድር ባቡር የጋራ ኮሚቴ የቻይና ኩባንያዎቹን መምረጡ ታውቋል፡፡

የጨረታው አሸናፊ የሆኑት ተጣማሪዎቹ የቻይና ኩባንያዎች፣ ‹‹ያቀረቡት ሰነድ የእኛን ጥቅም የሚያስከብር ሆኖ በመገኘቱ የተመረጡ ናቸው፤›› በማለት ዶ/ር አርከበ ገልጸዋል፡፡ እንደ ዶ/ር አርከበ ገለጻ የኩባንያዎቹ ዋናው ሥራ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ደረጃ በደረጃ አጠቃላይ ሥራውን እንዲረከቡ ማብቃት ነው፡፡ ሌሎች የባቡር ፕሮጀክቶችም ላይ በተመሳሳይ የሚሠራበት አካሄድ ነው ብለዋል፡፡

‹‹እንዲህ ዓይነቱን ሥራ ለውጭ ኩባንያ መስጠት ቢሊዮን ብሮች ያፈሰስንበት  ፕሮጀክት በተቻለ መጠን ካልተረከብነውና እንዲሠራ ካላደረግነው ኢኮኖሚው ተጠቃሚ አይሆንም፤›› ያሉት ዶ/ር አርከበ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግሩ በአጭር ጊዜ እንዲከናወን ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡  

የኦፕሬሽንና የማኔጅመንቱን ሥራ እንዲህ ባለው መንገድ መስጠት ሊያስገኝ የሚችለው ጠቀሜታ ከፍተኛና የግድ እንደሆነ ያመለከቱት ዶ/ር አርከበ፣ ለዚህም ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው ብለዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ አየር መንገድ አኩሪ የመንግሥት ተቋም እንዲሆንና በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ቀዳሚ እንዲሆን ካስቻሉት አንዱና ትልቁ ምክንያት፣ አየር መንገዱ ሥራ ሲጀምር የማስተዳደር ሥራው ለውጭ ኩባንያ መሰጠቱ ነው፤›› በማለት እንዲህ ያለውን አሠራር ጠቃሚነቱን ለማጉላት ሞክረዋል፡፡ በወቅቱ ዕውቀቱና ቴክኖሎጂው ስላልነበር ቲደብልዩኤ የተባለው የአሜሪካ ኩባንያ ለበርካታ  ዓመታት አየር መንገዱን ሲያስተዳድር ከቆየ በኋላ፣ ኢትዮጵያውያን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ተመድበው ማስተዳደር የጀመሩት ከ35 ዓመታት በኋላ እንደሆነም ዶ/ር አርከበ አስታውሰዋል፡፡

በአዲስ አበባ ጂቡቲ የምድር ባቡር አገልግሎትም የማስተዳደሩንና የጥገና ሥራዎችን የተረከቡት ኩባንያዎች በአምስት ዓመታት ውስጥ ሥራውን ለኢትዮጵያውያን እንዲያሸጋግሩ ማድረግ ከባድ ቢሆንም፣ ይህ እንዲሆን እንሠራለን ሲሉ አክለዋል፡፡ በሥራው ላይ የሚሰማሩት ኢትዮጵያውያንና ቻይናውያን በጋራ በመሆን ነው፡፡ ለማኔጅመንትና ለኦፕሬሽን የሚወክለው ወጪ የባቡርና የሐዲድ ጥገናን ይጨምራል፡፡

አዲሱ የአዲስ አበባ ጂቡቲ ምድር ባቡር መስመር 756 ኪሎ ሜትር ርዝመት ሲኖረው የግንባታ ሥራውን እያጠናቀቁ የሚገኙት ቻይና ሬልዌይ ግሩፕ (CREC) እና ቻይና ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን (CCECC) የተባሉት ኩባንያዎች ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ጂቡቲ ምድር ባቡር የሐዲድ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ እየተጠናቀቀ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ዝርጋታ ጋር የተያያዙ ሥራዎች ብቻ እንደሚቀሩት ታውቋል፡፡ በመጪው ዓመት መስከረም መጀመሪያ ሳምንት አገልግሎት መስጠት ይጀምራል መባሉ ይታወሳል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች