የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰሞኑን ባወጣው ማሳሰቢያ፣ እስራኤላውያን ወደ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች ከመጓዝ እንዲታቀቡ አስጠነቀቀ፡፡
በተለይ የአማራ ክልል ከተሞች የሆኑት ጎንደር፣ ባህር ዳርና ደብረ ታቦር ከመጓዝ እንዲታቀቡ አስጠንቅቋል፡፡
የአሜሪካ፣ የአውስትራሊያና የእንግሊዝ ኤምባሲዎች ተመሳሳይ መልዕክቶችን በኢትዮጵያ ለሚንቀሳቀሱ ዜጐቻቸው መግለጫ ማውጣታቸው የተለመደ ሲሆን፣ የእስራኤል መንግሥት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ያወጣው የጉዞ ማሳሰቢያ ግን ያልተለመደ ነው፡፡
የጉዞ ማሳሰቢያው የኢትዮጵያ መንግሥት በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ ማወጁንም ይገልጻል፡፡
በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር ከወልቃይት የወሰን ለውጥ ጥያቄ ጋር ተያይዞ የተነሳው ተቃውሞ፣ በበርካታ የአማራ ክልል አካባቢዎች በመስፋፋት በሥርዓቱ ላይ ወደ አመፅነት ተቀይሯል፡፡
ሰሞኑን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለመንግሥት የሚዲያ ተቋማት በሰጡት መግለጫ የመከላከያ ሠራዊቱ ፀጥታ እንዲያስከብር ማዘዛቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ የእስራኤል መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመከላከያ ሠራዊቱ ፀጥታ እንዲያስከብር መታዘዙን ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር አገናኝቶት ሊሆን እንደሚችል የሕግ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡
ለዚህ የሚሰጡት ምክንያት ደግሞ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 87 (3) ላይ፣ ‹‹የመከላከያ ሠራዊት የአገሪቱን ሉዓላዊነት ከመጠበቅ በተጨማሪ በዚህ ሕገ መንግሥት መሠረት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚሰጡትን ተግባሮች ያከናውናል፤›› የሚል ድንጋጌ አስቀምጧል፡፡
የአስቸኳይ አዋጅ የሚታወጀው ደግሞ በሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅራቢነት በፓርላማው ሲሆን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅም ‹‹የውጭ ወረራ ሲያጋጥም ወይም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለማቋቋም የማይችል ሲሆን…›› የሚሉ መሥፈርቶች እንዳሉ የሕግ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡