Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉ‹‹በመስተዋት ቤት ውስጥ የሚኖር ሰው መጀመርያ ድንጋይ ወርዋሪ መሆን የለበትም››

‹‹በመስተዋት ቤት ውስጥ የሚኖር ሰው መጀመርያ ድንጋይ ወርዋሪ መሆን የለበትም››

ቀን:

 በሚዛኑ አደራ

ከላይ የተመለከተው ምሳሌያዊ አነጋገር ወደ ጆሮዬ የገባው የሁለተኛ ደረጃ ትምህር ቤት ተማሪ እያለሁ ከዛሬ 40 ዓመታት ገደማ በፊት ነው፡፡ ጊዜው የደርግ መንግሥት የንጉሡን ሥርዓት ገርስሶ ሥልጣን የያዘባቸው የመጀመርያዎቹ ዓመታት አካባቢ ይመስለኛል፡፡ በወቅቱ በዚህ ምሳሌያዊ አነጋገር ርዕስ ሥር ከደርግ የተሰጠ መግለጫ ነበር፡፡ እንደማስታውሰው መግለጫው የተሰጠው ደርግ ኢዲ አሚን ዳዳ ይመሩት ከነበረው የኡጋንዳ መንግሥት ጋር ገብቶበት ለነበረው የዲፕሎማሲ ፍጥጫ የኡጋንዳን መንግሥት የተቸበት ነበር፡፡ የመግለጫው ቁልፍ ይዘትም ኡጋንዳ ራሷ በችግር ውስጥ ሆና እያለ ትንኮሳ ውስጥ መግባት እንደሌለባት የሚያስገነዝብ ነበር፡፡

ይህ ምሳሌያዊ አነጋገር ከዚያ በፊትም ከዚያ በኋላም አንብቤውም ሰምቼውም አላውቅም ነበር፡፡ እነሆ ዛሬ እኔው ራሴ ከ40 ዓመታት በኋላ ምሳሌያዊ አነጋገሩን በርዕስነት መርጬ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ ልጽፍበት ወሰንኩ፡፡

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ጀምሮ በሰሜን ምዕራብ የአገራችን ክፍል በተለይም በጎንደርና በባህር ዳር ከተሞች እንዲሁም አካባቢዎቻቸው ሕዝባዊ አመፅና ረብሻ ተቀስቅሶ ለብዙ ሰው ሕወይትና ንብረት ጉዳት ምክንያት መሆኑ፣ በመንግሥትም ሆነ ከመንግሥት ውጪ ያሉ ወገኖች ዘግበውታል፡፡ ከደረሰው የሰው ሕይወት ጉዳት ውስጥ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና የሲቪል የማኅበረሰብ አባላት እንደሚኙበት ታውቋል፡፡ በንብረት ጉዳቱም የመንግሥት፣ የድርጅቶችና የግለሰቦች ሀብት እንደሚገኝበት ተመልክቷል፡፡

ይህ ሁሉ ጥፋትና ውድመት መፈጸም ያልነበረበትና አሳዛኝ ነው፡፡ የበለጠ የሚያሳዝነው ግን የሕይወትም ሆነ የንብረት ጉዳት ከደረሰባቸው ውስጥ ሁከት በመፍጠርም ውስጥ ያልነበሩ፣ በፀጥታ አስከባሪነትም ያልተሰማሩ፣ ጉዳቱ እቤታቸው ድረስ ሄዶ ያጠቃቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ወገኖች የጉዳትና የጥቃት ሰለባ የሆኑበት ጥፋትና ምክንያት ደግሞ የመጡበት ብሔር እንደሆነ ተዘግቧል፡፡ እንዲያውም ከጥቃት የተረፉትም በአስቸኳይ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ በርካታ በራሪ ወረቀት እየተበተነባቸው እንደሆነ ይሰማል፡፡

በእርግጥ አንዳንድ ወገኖች (ተምረናል የሚሉት) ብሔርን መሠረት አድርገው ጥቃት የፈጸሙትን ያህል ይህንን ድርጊት በፅኑ አውግዘው ንብታችሁን ለመከላከል ከአቅማችን በላይ ቢሆንም ሕይወታችሁን እናድን ብለው፣ ተጠቂዎቹን ዋናው መኝታ ቤታቸው ሳይቀር ለእነሱ ለቀው ከሞትና ከድብደባ የተከላከሉ (ፊደል ያልቆጠሩት) ወገኖች እንዳሉም እየተነገረ ነው፡፡ የእናት ሆድ ዥንጉርጉር መሆኑ ነው፡፡

በጎው ነገር የኢትዮጵያዊነት መገለጫ በመሆኑ ይበል የሚባል ተግባር ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን ሰዎችን በዘራቸውና በብሔር ምንጫቸው ፈርጆ የጥቃት ዒላማ ማድረግና ለቀው እንዲወጡ መመርያ መስጠት የት ያደርሰናል? የአማራን ሕዝብስ ይጠቅመዋል ወይ?  ብሎ በሰከነ መንገድ መመርመሩ ተገቢነት አለው፡፡

ሲጀመር ይህንን ‹‹አካባቢን ካልተፈለገ ዘር የማጥራት›› ዕርምጃ እያስተላለፉና እያስፈጸሙ ያሉት የሃይማኖት አጥባቂ አማኞች፣ ለሰብዓዊ መብት ተቆርቋርቋሪና የአማራ ሕዝብ ጥቅምና ክብር ጠባቂ ነን የሚሉ ወገኖች መሆናቸው ይሰማል፡፡ ጥያቄው ነን የሚሉትን እየሆኑ ነው ወይ? የሚል ነው፡፡

እንደሚታወቀው ሃይማኖት በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረን የሰው ልጅ ክብር ሊሰጠው እንደሚገባ ይሰብካል፡፡ ታዲያ ይህ ድርጊት ከሃይማኖት አንፃር ምን ማለት ነው? ከሰብዓዊ መብት መርህም አንፃር ሲታይ ሰዎች ሁሉ እኩል መሆናቸው፣ እኩል ክብርና አያያዝ ሊሰጣቸው እንደሚገባ፣ እንዲያውም በዘራቸው፣ በሃይማኖታቸው፣ በፖለቲካ አመለካከታቸው፣ ወዘተ ምክንያት መድልኦና መገለል ሊደርስባቸው እንደማይገባ በግልጽ የተቀመጠ ጉዳይ ነው፡፡

የጥቃት ዒላማ የሆኑት ወገኖች ብሔራቸውንም ሆነ ዘራቸውን መርጠው የያዙት አይደለም፡፡ ሊለውጡትም የሚችሉት ነገር አይደለም፡፡ ይህ እንደ ጥፋት ተቆጥሮ ለጥቃት ሲዳርጋቸው እጅግ ያስቆጫል፡፡ ለሰብዓዊ መብት እቆረቆራለሁ የሚል ወገን ሊፈጽመው አይገባም ነበር ብቻ ሳይሆን ድርጊቱን ጮክ ብሎ ሊያወግዘው በተገባም ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ሰብዓዊ መብት ሲደፈር ያንገሸግሸናል ባዮቹ እነ ፕሮፌሰር መስፍን፣ እነ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባዔ፣ እነ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ምነው በዚህ ወቅት ብዕራቸው ደረቀ? ልሳናቸው ተዘጋ?  አልሰማንም እንዳይሉ በአልጄዚራ ሳይቀር ሽፋን የተሰጠው ጉዳይ ነው፡፡

የሃይማኖት አጥባቂነትና ለሰብዓዊ መብት መቆርቆርን ጉዳይ በዚህ ትተን ዕርምጃው ለአማራ ሕዝብ ይበጃል ወይ? ጥቅሙንስ ያስከብራል ወይ? የሚለውንም ማየቱ ተገቢ ነው፡፡ በታሪክ ሒደትና አጋጣሚ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ካንዱ የአገሪቱ ጫፍ ወደ ሌላው እየተዘዋወሩ ጎጆ ቀልሰው፣ ወልደው ከብደው መኖር ከጀመሩ ብዙ ዓመታት አስቆጥረዋል፡፡ በተለይም የአማራ ሕዝብ ከጫፍ እስከ ጫፍ በሚባል ደረጃ እንደ ጨው ተዘርቶ የሚኖር ሕዝብ ነው፡፡ በምዕራቡም በምሥራቁም፣ በሰሜኑም በደቡብም ቁጥሩ ይለያይ እንደሆነ እንጂ የአማራ ሕዝብ ያልሰፈረበት የኢትዮጵያ ክልል የለም (1999 የቤቶችና ሕዝብ ቆጠራ ማየት ይጠቅማል)፡፡ በጎንደርና በተወሰነ መልኩም በባህር ዳር እየተተገበረ ያለው አካባቢን ከሌላ ብሔር የማፅዳት ዕርምጃ በሌሎች ክልሎችም ተግባራዊ እንዲደረግ ዕድል ከተሰጠው ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ መገመት ይገባል፡፡ የዕርምጃችን ምንነትና ሊያስከትለው የሚችለው ውጤት አማትሮ ማየት ብልህነት ነው፡፡

ለነገሩ በተወሰነ የአማራ ክልል በጥቂት በጭፍን ጥላቻ በተሸበቡ ጉልበተኞች አርቆ አሳቢነት የጎደለው ዕርምጃ በማየት በሌላው የአገሪቱ ክፍል በሰላም ጥሮና ግሮ በሚኖረው የአማራ ተወላጅ ላይ የአፀፋ ዕርምጃ መውስድ ከመርህ አንፃር ተቀባይነት የለውም ብቻ ሳይሆን፣ ጥላቻን በጥላቻ መመለስና በጉልበተኞቹ ደረጃ ወርዶ ማሰብ ይሆናል፡፡ ከዚህም አልፎ ይህንን ኢሃይማኖታዊና ኢሰብዓዊ ተግባር በምሬት እየተቃወመ ላለው ለአብዛኛው የአማራ ሕዝብም ተገቢ ክብርና ዕውቅና መንፈግም ይሆናል፡፡ እዚህ ላይ ለማሳየት የተፈለገው ዋናው ነገር አካባቢን ከሌላ ብሔር የማፅዳት ፕሮጀክት በአገር ደረጃ ተግባራዊ ከተደረገ፣ ቆመንለታል ለሚሉት የአማራ ሕዝብ አይጠቅምም ብቻ ሳይሆን ከማንም በላይ ተጎጂ የሚሆነው እሱ ነው፡፡

በተጨማሪም የእኛ ያልሆነ ለቆ ይውጣልን የሚለው አመለካከት ልዩነትን አለመቀበል ስለሆነ ሌላ ጣጣም አለበት፡፡ ልዩነት ያለመቀበል ሲመጣ ማቆሚያ የለውም፡፡ የአማራ ሕዝብ አንድ የሆነውን ያህል ልዩነትም አለው፡፡ የሃይማኖት ልዩነት አለው፣ የፖለቲካ አመለካከት፣ የኢኮኖሚ አቅም ልዩነት አለው፡፡ ሌሎች የልዩነት መሠረቶችም አሉት፡፡ በመሆኑም ተሳክቶለት የሌላውን ብሔር ጠራርጎ ክልሉን ካፀዳ በኋላም ቢሆን ትግሉ አያበቃም፡፡ ወደ ውስጡ ተመልሶ የሃይማኖትም ሆነ ሌሎች ልዩነቶችን በማሳደድ መተራመሱ አይቀርለትም፡፡ ልዩነትን መቀበል እንጂ ማስወገድ አይቻልም፡፡ ስለዚህ ይህ አካሄድ በሌላ ክልል ውስጥ ለሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ብቻ ሳይሆን፣ በክልላቸው ውስጥ ለሚኖሩትም ቢሆን ዘላቂ ሰላምና እርጋታ የሚሰጥ አይሆንም፡፡ በመጨረሻም በተለያዩ ክልሎች በብዛትና በስፋት የሚኖር ሕዝብ፣ በውስጡም የሃይማኖትና ሌሎች ልዩነቶችን ይዞ የሚኖር ሕዝብ ሆኖ እያለ ክልሉን ከሌላ ብሔር ለማፅዳት መነሳትና መሞከር በመስተዋት ቤት እየኖሩ ሌላው ላይ ድንጋይ የመወርወር ያህል እንዳይሆን፣ አርቆ አሳቢ ወገኖች ቢገቡበት ይበጃል ባይ ነኝ፡፡ ሳይቃጠል በቅጠል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...