Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እነሱ እየሰፉ እኛ እየቀጨጭን መጓዝ አይቻልም

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ውስጥ የቻይናውያን ተሳትፎ ጐልቶ እየታየ ነው፡፡ ከኢንቨስትመንቱ ውጭ በተለያዩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ውስጥም የቻይና ኮንትራክተሮች ያላቸው ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሰፋፋ ነው፡፡ ይህ እንቅስቃሴያቸውም ከሌሎች አገሮች ኩባንያዎች ይልቅ የቻይና ኩባንያዎች በተለየ እንዲታዩ አድርጓቸዋል፡፡

የቻይና ኩባንያዎች በመንገድ ግንባታ፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ፣ በትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ኢንቨስትመንት፣ በቴሌኮም፣ በሕንፃ ግንባታዎች፣ በባቡርና በኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታዎችና በመሳሰሉት መስኮች ሁሉ እጃቸው ተንሰራፍቷል፡፡ ይህ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴያቸውና ተሳትፏቸው ጐልቶ እንዲታይ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ በቻይናና በኢትዮጵያ መንግሥታት መካከል ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት ያስገኘው ውጤት መሆኑም ግልጽ ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የቻይና ኩባንያዎች የአንበሳውን ድርሻ የያዙበት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታም ይጠቀሳል፡፡ ግንባታው ላይ ብቻም ሳይሆን በአንዳንዶቹ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥም አብዛኛውን የመሥሪያ ቦታ ወስደው ፋብሪካዎችን ለማንቀሳቀስ እየተዘጋጁ ነው፡፡

በቻይናውያን እንዲህ እየተስፋፋ የመጣው ተሳትፎ ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የጐላ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ይህ ተግባራቸው የሚፈለግ ነው፡፡ አወንታዊ ነው፡፡ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ተለምነው ጭምር የሚመጡት ለአገር የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ታሳቢ ተደርጐ ነው፡፡ እነሱም በዚያኑ ያህል ተጠቃሚ መሆናቸው እንደተጠበቀ ማለት ነው፡፡ ለጽድቅ አይመጡምና፡፡ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች በቻይናና በሌሎች ኩባንያዎች መያዛቸው ግን በዚያው ልክ የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን ተሳትፎ ኢምንት እያደረገው ይመስላል፡፡ ቆም ብለን እንድናስብ ሳያስገድደንም አልቀረም፡፡ ትንሹንም ትልቁንም ሥራ ለቻይናውያን አሳልፎ መስጠቱም ለአደጋ ሊጋብዝ ይችላል፡፡

አገር በቀል ኩባንያዎች ወዴት እንዳሉ ለመጠየቅ እስኪዳዳ ድረስ በኢንዱስትሪ ዘርፉ ኢንቨስት ማድረግ ያለባቸው ወይም የሚጠበቅባቸው የውጭ ኩባንያዎች ብቻ መስለው እየታዩ ነው፡፡ አገሪቱ ነገ ትደርስበታለች የተባለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወይም በኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚፈለገው ውጤት፣ አሁን እያየን ካለነው አኳያ ሲታይ በውጭ ኩባንያዎች የሚሽከረከር ይመስላል፡፡ የኢትዮጵያውያን ኩባንያዎች ተሳትፎና ሚና እየደበዘዘ መጥቷል፡፡ የአገር ውስጥ ኢኮኖሚው ድርሻ የሠራተኛ ጉልበት ማቅረብ ላይ ብቻ የተገታ ሆኖ እንዳይቀር መሥጋትም ተገቢ ነው፡፡

የአገራዊ ኩባንያዎች ተሳትፎ እየጠበበ ከሄደ፣ የውጭ ኩባንያዎች የበላይነቱን ተቆጣጥረው፣ ኢኮኖሚያችን በውጭ ኩባንያ ላይ ተንጠልጥሎ ይሄ ነው የምንለው አገር በቀል ኩባንያ ላይኖረን ይችላል የሚል ሥጋትም አለ፡፡

ሰሞኑን እንደሰማነው በአፍሪካ ቀዳሚ የሚባል የቤት ቁሳቁስና የግንባታ ግብዓት ማምረቻዎች ይሰባሰቡበታል በተባለው የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በመግባት ቀዳሚዎቹ የቻይና ኩባንያዎች ሆነዋል፡፡

የቤት ውስጥ መገልገያዎች ወይም ፈርኒቸሮች ሳይቀር የሚመረቱበት ይህ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ እንደታሰበው ሙሉ በሙሉ በቻይና ኩባንያዎች ብቻ የሚያዝ ከሆነ፣ ዛሬ ከአነስተኛ እስከ መካከለኛ ደረጃ የቤት ዕቃዎች የሚያመርቱ አምራቾች ነገ ምን ሊሆኑ ነው? ምን ሊውጣቸው ነው? ያስብላል፡፡ የአገር በቀል ኩባንያዎች ዕጣ ከወዲሁ ሥጋት አጥልቶበታል፡፡ በእርግጥም የቻይናዎቹ ኩባንያዎች በየመንደሩ ካለ በሺዎች ከሚቆጠሩ ፈርኒቸር አምራቾች በተሻለ አምርተው በአነስተኛ ዋጋ መሸጣቸው ሲታሰብ፣ የእኛዎቹ ከጨዋታ ውጭ የመሆናቸው ሚስጥር ሳይታለም የተፈታ ሆኖ ይታያል፡፡

የውጭ ኩባንያዎች የግድ የሚያስፈልጉን ከሆነም አገር በቀል ኩባንያዎች ተሳትፎ በቅድሚያ ሊታሰብበት እንደሚገባ እንዲህ ዓይነቶቹ ክስተቶች ያሳዩናል፡፡ ስለዚህ የውጭ ኩባንያዎች የሚሳተፉባቸው ሥራዎች አገር በቀሎቹን ስላለመጉዳታቸው፣ ከገበያ ስላለማስወጣታቸው ቀድሞ ሊታሰብበትና ሊጠይቅ ይገባዋል፡፡ ጊዜው የውድድር ቢሆንም ታሳቢ ሊደረጉ የሚገባቸው ጉዳዮች መዘንጋት የለባቸውም፡፡ ውድድሩ ይኑር ከተባለም አገር በቀል ኩባንያዎች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በማገዝ ጠንክረው እንዲወጡ መርዳት ከተጠናከሩና ለውድድር ብቁ ከሆኑ በኋላ በተመሳሳይ ሥራ ላይ የሚሰማሩ የውጭ ኩባንያዎች ቢጋበዙ እንኳ ሊፈጠር የሚችለውን ቀውስ ይቀንሳል፡፡

በሁሉም የኢንቨስትመንት ዘርፎች እየተበራከቱ የመጡት የቻይና ኩባንያዎች፣ በተለያዩ የግንባታ ሥራዎች ላይ አሸናፊ ሆነው እየሠሩ ያሉ የቻይና ተቋራጮች አሁን ላሉበት ደረጃ የደረሱት በመንግሥታቸው ድጋፍ ጭምር ነው፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የቻይና መንግሥት ሁለንተናዊ ድጋፍ አላቸው፡፡ እንዲያውም ጥቂት የማይባሉት የቻይና ኩባንያዎች መንግሥታዊ ናቸው፡፡ ይህ የሆነው ለጥቅም ነው፡፡ ኩባንያዎቻቸውን ደግፈውና አሳድገው አገራቸውን የማሳደግ ራዕይ ስለሰነቁ ነው፡፡ ስለዚህ ብዙ የኢንዱስትሪ መንደሮች እየተፈጠሩ ባሉበት ወቅት፣ በመንደሩ ውስጥ የሚገቡት የውጭ ኩባንያ ብቻ ከሚሆኑ ይልቅ ትላልቅ አገር በቀል ኩባንያዎችም እንዲፈጠሩ የመንግሥት እገዛ ግድ ይላል፡፡

ቢያንስ በእያንዳንዱ የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከሚገቡ የውጭ ኩባንያዎች ውስጥ የተወሰኑት ኢትዮጵያውያን ኩባንያዎች ቢሆኑ ሌሎችም ከኢትዮጵያ ኩባንያዎች ጋር የሚጣመሩ የውጭ ኩባንያ እንዲሆኑ በማድረግ በቀላል ኢንዱስትሪዎች ላይ አገር በቀል ኩባንያዎች ተሳትፎን የሚያጐላ አሠር መቅረጽ ግድ ይላል፡፡

አሁን እንደሚታየው ለአገሬውና ለውጭ ዜጐች ወይም ኩባንያዎች የተከለሉት የሥራ ዘርፎች በግልጽ ያለመታወቅ ወይም ብዥታ ያለበት ነው፡፡ በግልጽ ከሚታወቀው ከፋይናንስ ተቋማትና ቴሌኮም ዘርፎች ውጭ ሌላው የቢዝነስ ዘርፍ ድብልቅልቅ ያለ ነው፡፡ መደብር ችርቻሮ ውስጥ የውጭ ኩባንያ ከገባ ነገሩ አያስቸግርም፡፡ ለውጭና ለአገር የተለየ አሠራር አለ ቢባል እንኳን ነገሩን የበለጠ ግልጽ ለማድረግ ዘርፎቹን ድጋሚ መከለስ ያስፈልጋል ያለበለዚያ አይደለም በኢንዱስትሪ ዘርፍ ሌላውንም ሥራ ልንሰጥ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በቀላል ኢንዱስትሪዎች ላይ የኢትዮጵያውያን ተሳትፎ እንዲጐላ ለማድረግ ለኢትዮጵያውያን ብቻ የተከለሉ ቀላል ኢንዱስትሪዎች ዘርፍ ሊኖር ይገባል፡፡ ነገ የዓለም ንግድ ድርጅት ሲኮን የኢትዮጵያ ተወዳዳሪነት በአገር በቀል ኩባንያዎች ሳይሆን በሌሎች እጅ ሙሉ ለሙሉ እንዳይወድቅ ከወዲሁ ነገሩን ማሰብ ተገቢ ነው፡፡  

የእኛ አገር ባለሀብቶችም ሆኑ በግንባታው ዘርፍ ላይ ያሉ ድርጅቶች እስካሁን እየሄዱበት ካለው መንገድ መለስ ብለው ሊያስቡ ይገባል፡፡ ከችርቻሮ ወጥተው ኢንዱስትሪን አዕምሯቸው ውስጥ ያስገቡ፡፡ ፅዱ ተቋራጭ ኩባንያ ይኑረን፡፡ በግልና በጋራ ተጣምሮ መሥራት ልምድ ማዳበር ከተለመደው አሠራራቸውም በመውጣት ሥራ ይኖርባቸዋል፡፡      

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት