Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርጠቅላይ ሚኒስትር ሆይ እጅዎን ከንፁኃን ደም እንዲሰበስቡ እለምንዎታለሁ

ጠቅላይ ሚኒስትር ሆይ እጅዎን ከንፁኃን ደም እንዲሰበስቡ እለምንዎታለሁ

ቀን:

ይህን ደብዳቤ የምጽፍልዎት ሰው ያሬድ ጥላሁን እባላለሁ። የወንጌል አገልጋይ ነኝ። ከጌታ ምኅረትን ተቀብዬ ላለፉት 27 ዓመታት ዘር፣ ጎሣ፣ ቀለም፣ ጾታ፣ እምነትና የፖለቲካ አመለካከት ሳልለይ ለትንሽ ለትልቁ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ስሰብክ የኖርኩ ነኝ። ዛሬ ይህንን ደብዳቤ የምጽፍልዎት በልብ ጭንቀትና በብዙ ዕንባ ነው። ከሰሞኑ በእርሶ አንደበት የተነገረውንና የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል በዜጎች ላይ የኃይል ዕርምጃ እንዲወስድ የሚፈቅደውን ንግግር አድምጫለሁ። ከተቀመጡበት ወንበር ግዝፈትና በዙሪያዎ ከከበብዎት ውጥረት አንፃር የገቡበትን አስጨናቂ ሁኔታ ለመረዳት እሞክራለሁ። የሚወስኑትም ውሳኔ በግል የእርሶ ብቻ እንዳልሆነና አንዳንድ ጉዳዮችም ከአቅምዎ በላይ ሊሆኑ እንደሚችሉ እገምታለሁ።

ሆኖም በአንደበትዎ የተነገረውና በታሪክ መዝገብ ተቀርጾ የሚኖረው ይህ ውሳኔዎ በእግዚአብሔር፣ በሰውና በኅሊናዎ ዘንድ ከፍተኛ ተጠያቂነት እንደሚያመጣብዎ ሳስብ ከልብ አዝናለሁ። እርሶ በእግዚአብሔር ምኅረት የተፈጠሩ፣ በምኅረቱ ያደጉና አሁን ለደረሱበት ከፍተኛ የኃላፊነት ሥፍራ የበቁ መሆንዎን በሚገባ ያውቃሉ። ይህን ለእርስዎ የተሰጥዎትን የመኖር መብት ለሌሎች ይነፍጋሉ ብዬ አላስብም። ሆኖም አሁን በእርስዎ መሪነት፣ በገዛ አንደበትዎ የተነገረውና የተላለፈው ይህ ውሳኔ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምትክ የማይኖራቸው ኢትዮጵያውያን ሕይወት ላይ ሞትን የሚያጠላ ነው።

ሕዝብ ጥያቄ አለኝ ብሎ አደባባይ ሲወጣ፣ አጥጋቢ ምላሽ አላገኘሁም፣ እንዳልናገር ታፍኛለሁ ብሎ እምቢተኝነት ሲያሳይ፣ የተለያዩ ፖለቲካዊ መፍትሔዎችን በማፈላለግ ሕዝብን ማረጋጋት የመንግሥት ባሕሪይ ነው። ዛሬ ድምፁን ለማሰማት በየሥፍራው እንደ አሸን የፈላው ሕዝብ፣ ላለፉት 25 ዓመታት ለኢሕአዴግ አመራር ፀጥ ለጥ ብሎ የተገዛ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባረፉ ጊዜ ዕንባውን የረጨ፣ ደረቱን የደቃ ሕዝብ ነው። የፍትሕ ዕጦትና የመድልዎ ብዛት አንገሽግሾት የሚሰማኝ መንግሥት አለ በማለት አደባባይ ቢወጣ እንደ እባብ ተቀጥቅጧል፣ ተዋክቧል፣ ታስሯል፣ ተሰዷል፣ ተገድሏል። ለዚህ እውነታ ማስረጃ ማቅረብ የሚገባኝ አይመስለኝም፡፡ እርሶም አጥርተው እንደሚያውቁት አልጠራጠርም። “በቁስል ላይ ዕፀጽ” እንዲሉ አሁን በኢሕአዴግ ጉባዔ የተወሰነውና በእርስዎ ትዕዛዝ የተንቀሳቀሰው ኃይል ጉዳዩን ወደ ከፋ ደረጃ እንደሚያሸጋግረውና በብሔሮች መካከል የማይሽር ጠባሳ እንደሚያሳድር እርስዎንም በእግዚአብሔርና በሰው፣ በታሪክና በሕሊናዎ ተወቃሽ እንደሚያደርግዎ በብዙ ትህትና መግለጽ እወዳለሁ።

አሁንም ጊዜው ሳይመሽ ፖለቲካዊ መፍትሔዎች ላይ እንዲተኮር፣ የኃይል ዕርምጃው እንዲቆም፣ ተዓማኒ ዕርምጃዎች እንዲወሰዱና ሌሎችንም ያሳተፈ አገራዊ መግባባት ላይ እንዲደረስ አቅምዎ እስከሚፈቅድ የበኩልዎትን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ፤ ይህንንም ማድረግ ካልቻሉ ከሚፈሰው የንፁኃን ደም እጅዎን እንዲያነጹ ሰውን በመልኩና በምሳሌው በፈጠረ በሕያው እግዚአብሔር ስም እማጸንዎታለሁ።

                                                                   (ፓስተር ያሬድ ጥላሁን)
 

 

* * *

መንግሥትና ሕግ ባለበት አገር በባለሥልጣናት እንድንዘረፍ ተደርገናል

ከታች ስሜ የተጠቀሰው አመልካች፣ በሲዳማ ዞን በደሌ ወረዳ ሶያማ ቀበሌ ውስጥ ከሚገኝ 31 ሔክታር ክፍት መሬት ውስጥ አምስት ሔክታር መሬት ለዘመናዊ የከብት እርባታ ሥራ እንዲሰጠኝ ከቀበሌ እስከ ክልል አስተዳደር ካቢኔ ባለው ርከን መሠረት በአግባቡ ጠይቄያለሁ፡፡

ጥያቄዬ አጥጋቢ ሆኖ በመገኘቱ ተወስኖና ፀድቆ በኅዳር 16 ቀን 2006 ዓ.ም. ሕጋዊ የኢንቨስትመንት ሰርቲፊኬት፣ የይዞታ ማረጋገጫና ለ25 ዓመታት የፀና ውል ተቀብዬ ለኢንቨስትመንት የሚያስፈልጉኝን ማቴሪያሎችና ግብዓቶች በከፍተኛ ወጪ ገዝቼ ወደ ሥራ ልገባ ስል ግን ከጀርባ ሆነው በሚያስተባብሯቸው በጥቂት የዞንና የወረዳ አመራሮች በመታዝ 13 የቀበሌ ነዋሪ ግለሰቦች ሁከት ፈጠሩብኝ፡፡

የኢንቨስትመንት ልማቱ እንዳይደናቀፍና ሁከቱም እንዲቆም የዞኑንና የወረዳውን ቁልፍ አመራሮች በማመልከቻ ብጠይቅም ሊያቆሙልኝ ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ የኋላ ድጋፍ ያገኙት እዚህ ግለሰቦች፣ በታኅሳስ 22 ቀን 2006 ዓ.ም. ዘራፊዎችን በማስተባበር ዝርፊያ አካሂደዋል፡፡ ይኼንኑ ለፍርድ ቤት አቅርቤ ከወረዳ እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዲሁም እስከ ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ በሁለት ዓመት ጽኑ እሥስራትና በሦስት ዓመት ገደብ በማስቀመጥ መጠነኛ የገንዘብ መቀጫ ጥሎባቸው እንዲታረሙ መክሮ ለቋቸዋል፡፡ ይሁንና በዚህ ሳይታረሙ የፍርዱ ቤት ውሳኔን ንቀውና የአመራሮችን ግፊት ተማምነው ደግመው በሚያዝያ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. በአምስቱ ሔክታር መሬት ላይ የሚገኝ የሣር ንብረት በኃይልና በጉልበት ገብተው ዘርፈዋል፡፡ በዚህም ወቅት አመልክቼ ወንጀሉን የሚከላከልልኝ በመጥፋቱ፣ ለሲዳማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎትና የፍትሐ ብሔር ችሎት ጉዳዩን አቀረብኩ፡፡

 በዚሁ መሠረት በየካቲት 9 ቀን 2008 ዓ.ም. የዋለው የሲዳማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፍትሐ ብሔር ችሎት፣ 13 ግለሰቦች ዘረፋውን በማስተባበር ወደ ባለሀብቱ ሕጋዊ ይዞታ በኃይል ገብተው ለፈጸሙት የሁለት ዓመታት ዝርፊያ በሙያተኛ በተገመተው መሠረት እንዲከፍሉ ይፈርድባቸዋል፡፡ አሁንም ግን ከኋላ አይዟችሁ በሚሏቸው አካል የተማመኑ በመሆናቸው በሕጋዊ መንገድ ይግባኝ ከመጠየቅና ይልቅ ዳኛው ላይ ዝተው እኔንም ‹‹ንብረትህን በሙሉ እንዘርፋለን፣ እናወድማለን፣ አንተንም እንገልሃለን፤›› በማለት ከችሎት ግቢ ሳይወጡ አስፈራርተውኛል፡፡ ከግቢው እንደወጡ ወዲያውኑ ዘርፈው፣ ቀስቅሰውና አስተባብረው በእኔና በ16 ሌሎች ተጎጅ አመልካቾች ንብረት ላይ ዝርፊያ፣ ውድመትና የእርሻ ጭፍጨፋ አካሂደዋል፡፡

ይህ መጠነ ሰፊ ዝርፊያ ሲካሄድ የዳሌ ወረዳ የቀድሞ ፖሊስ አዛዥ ድርጊቱን በመቃወም ከነፖሊሶቹ፣ የወረዳው ፀጥታና አስተዳደር ኃላፊ እንዲሁም የወቅቱ አስተዳደር የነበሩት ግለሰብ በቦታው ነበሩ፡፡

እኔ ከፍርድ ውሳኔው በኋላ እነዚሁ ተፈረደባቸውም ለዝርፊያና ንብረትን ለማውደም ዝተው በመሄዳቸው ለዞኑ ፖሊስ አዛዥ፣ ለዞኑ ፀጥታና ለአስተዳደር ኃላፊው ስለጉዳዩ ባመለክትም፣ ለወረዳው ፖሊስ ውክልና ከማለት ውጪ ያደረጉት አንዳችም መከላከል የለም፡፡ ይህም በመሆኑ በዕለቱ ወዲያውኑ ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አመልክቼ ደውለው ሲጠይቋቸው፣ ንብረቴ እንዳልተነካ አስመስለው በመንገር አቤቱታዬን አቀዝቅዘውና የክልል ዕርዳታ እንዳላገኝ አድርገው ለሦስት ተከታታይ ቀናት የተካሄደውን ዝርፊያ ደግፈዋል፡፡

ለዚሁም ማስረጃ የሚሆነው ከየካቲት 9 ቀን እስከ የካቲት 11 ቀን 2008 ዓ.ም. እኩለ ቀን ድርስ ዝርፊያው ከተካሄደ በኋላ የዞኑ ፀጥታና አስተዳደር ኃላፊ እንዲሁም የዞኑ ፖሊስ አዛዥ ከዳሌ ወረዳ የወቅቱ አስተዳደርና ፖሊስ አዛዥ ጋር በመሄድ ዘራፊውን ሰብስበውና አበረታተው፣ ኢንቨስትመንቱን እንሰርዛለን፣ ብለው እነሱ ያነሳሷቸው ሰዎች በእኔ ላይ በቂ ዝርፊያና ቅጣት የፈጸሙ መሆኑን ተናግረው ሞራል ሰጥተዋቸው ተመልሰዋል፡፡ የእነዚህ የወረዳና የዞን አካላት እጅ ያለበት በመሆኑም  እስካሁን ስድስት ወር እስኪያልፈው ድረስ ዘራፊዎች ቃላቸውን ቀርበው እንዳይሰጡና ለፍርድ እንዳይቀርቡ እየተደረገ ያለው፡፡

በዞኑና በወረዳ አመራሮች እገዛ የተፈጸመብን ዝርፊያ ስለሆነ በክልሉ ፖሊስና ዓቃቤ ሕግ እንዲጠራልኝና/እንዲጠራልን ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቤቱታ አቅርቤ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ድርጊቱ ከባድ ውንብድና መሆኑን በጥናት ሪፖርት ያቀረበውንና ይህም በወረዳ ፖሊስ ተጣርቶ በአጣዳፊ ሁኔታ ለሕግ እንዲቀርብ የተደረገውን ሁሉ በማን አለብኝነት አልተገበሩትም፡፡ ቀጥሎም በኢፌዴሪ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሐዋሳ ቅርንጫፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የፍትሕ መዛባት መፈጸሙን ገልጾ ጉዳዩ ወደ ሕግ እንዲቀርብ የተላለፈላቸው ሪፖርትን መነሻ በማድረግ ለመፈጸም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው፣ እኛ ተጐጂዎች የሰውና የሰነድ ማስረጃ አቅርበንም ቢሆን እስከ ዛሬ ስድስት ወራት ድረስ ለዘራፊዎቹ በአመራሩ ሽፋን እየተሰጠ ወደ ሕግ እንዳይቀርቡ ቃላቸውም እንዳይወጡ ተደርጐ ይገኛል፡፡

በዚሁ ዝርፊያ በግምት ከ20 እስከ 25 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት የወደመ ሲሆን፣ የእኔ ንብረት የሆኑ አራት ቤቶቼን አፍርሰው ሸጠዋል፡፡ ሁለት የወንድሜ ልጆችን ሣር ቤቶች አፍርሰው ልጆቻቸውና እንዲበነተኑ፣ በተለያየ ቀበሌ ዘመድ ጋ ተሰደው እየኖሩ ይገኛሉ፡፡ ከብቶቻቸው ታርደው ተበልተዋል፡፡ የሌሎችም አርሶ አደሮች ቤቶች በሙሉና በከፊል ፈርሰዋል፡፡ ንብረቶቻቸው ተወስደዋል፡፡

ይህ የንብረት ድምሰሳ፣ ውድመት፣ ዘረፋና ጭፍጨፋ ከተከናወነ በኋላ አመራሩ በድርጊቱ በማዘን፣ ወንጀለኞችን ተከታትሎ ወደ ሕግ ከማቅረብ ይልቅ ለዘራፊዎች በማገዝ ለዘረፋው ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት በመሞከር ላይ ያለ ከመሆኑም በላይ ለውድመቱ መነሻ የሆነውን የኢንቨስትመንት ውልና ቦታ ሰርዞታል፡፡ ይህም የሚያመለክተው ለዝርፊያው ያላቸውን ድጋፍ ነው፡፡

 ሕግና መንግሥት ባለበት አገር በሐዋሳና ይርጋለም ከተማ መካከል በኢንተርናሽናል አስፋልት መንገድ ላይ የተደረገ ዝርፊያ ዘራፊዎች ለስድስት ወራት ለሕግ እንዳይቀርቡ መንግሥት ከፍተኛ አደራና ሹመት የሰጣቸው አካላት መደገፋቸው የሚገርም ጉዳይ ነው፡፡ ይባስ ብለው ቀደም ሲል በወንጀልና በፍትሐ ብሔር የቅጣት ፍርድ የተላለፈባቸውን የቀበሌ አፈ ጉባዔ፣ ሊቀመንበርና ፀጥታና አስተዳደር አድርገው ሾመዋቸው ይገኛሉ፡፡ በእነዚሁም አማካይነት ወደ ቀዬአችንና ይዞታችን እንዳንደርስ ተደርገን እንገኛለን፡፡ ይህንን ለክልሉ አመራር አካላት አቤቱታ ብናቀርብም ሊሰማን አልቻለም፡፡ ስለዚህ በሪፖርተር ጋዜጣ አማካይነት የመላው የሲዳማ ሕዝብ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለጥቃት የዞኑና የወረዳ ባለሥልጣናት የተደረገብንን ግፍና በደል ሰምቶ እንዲፈርድ ለሚዲያ አቅርበናል፡፡

ስለዚህ እነዚህ ጥቂት ወረዳውን የዞኑ ኃይሎች በተጠላለፈ ኔትወርክ የተያያዙ ስለሆነ የክልል ግብረ ኃይል ሪፖርት፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት፣ የክልል ኮሚሽን መጻፎችን እንዲሁም እኛ ተጐጂዎች ያቀርብናቸውን አቤቱታዎች መስማት የማይፈልጉና ይልቁንም በሕይወታችን ላይ አደጋ ለማድረስ የሚዝቱና የሚያስፈራሩ ናቸው፡፡ በስውርም የሚተጉት አካሄድ አላቸው፡፡ የሕግ የበላይነትን ሊያከብሩና ሊያስከብሩ የሚፈልጉ አይደሉም፡፡

ስለሆነም ጉዳያችን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ጣልቃ ገብቶ ከክልሉ ፖሊስና ከክልሉ ዓቃቤ ሕግ ጋር እንዲያጣራልን እስከዚያው ግን፡

  1. ፍርድ ቤቶች ነፃ ሆነው የእኔንና የአርሶ አደሮችን ጉዳይ እንዳይመለከቱ በእነዚህ አካላት የሚደረግ ከፍተኛ ጫና እንዲቆምልን፣
  2. በቀበሌያችንና በቀዬያችን የመኖር መብት እንዳይኖረን፣ የተፈረደባቸውን ወንጀለኞች በመሾም የተጋረጠብን አደጋ ለእኛና ለ120 ቤተሰቦቻችን የመኖርና ሠርቶ የመኖር መብት የሚጋፋ ስለሆነ ሕጋዊ ጥበቃ እንዲደረግልን፣
  3. ከተጣራ በኋላ በኢቨስትመንት መሬት ምክንያት ለጠፋው ንብረት ተገቢ ካሳ እንዲከፈለን፣
  4. የፍርድ ውሳኔ ያረፈበት ሁከት ይወገድ እየተባለ ያለውን የኢንቨስትመንት መሬት መሠረዝ የዳኝነት አካሉን ውሳኔ መሠረዝ ስለሆነ ወደነበረበት እንዲመለስልንና በታላቅ አክብሮት እንጠይቃን፡፡

(ጴጥሮስ ደብሶ ከ16 አርሶ አደሮች ጋር)     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...