– በዓመት እስከ 700 ሺሕ ሕገወጥ ‹‹ዲሾች›› እየገቡ ነው ተብሏል
በአገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፉ በመምጣታቸው ሳቢያ ጉዳት አድርሰውብኛል ያላቸውን ተመሳስለው የተሠሩ ምርቶች እንዲያዙለት የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ኩባንያ የሆነው ዩሮስታር ግሩፕ ለፖሊስ ባመለከተው መሠረት 3,000 የሳተላይት መቀበያ ዲሾች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ታወቀ፡፡
ጀኔይድ ካህን የዩሮ ስታር የውጭ አገሮች የሽያጭ ኃላፊ ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ ሐሙስ ነሐሴ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. በመርካቶ አካባቢ በተደረገው ድንገተኛ አሰሳ ሁለት መጋዘኖች ውስጥ ታጭቀው የነበሩ ከ15 እስከ 20 ሺሕ በሐሰት ተመሳስለው የተሠሩ ዲሾች ተገኝተዋል፡፡ ፖሊስ 3,000ውን በኤግዚቢትነት መያዙንም ካህን ተናግረዋል፡፡
ከተያዙት ዲሾች ባሻገር አንድ ዋና አስመጪና ሁለት አከፋፋዮች በቁጥጥር ሥር ውለው በኩባንያው ክስ እንደተመሠረተባቸውም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ዩሮ ስታር ግሩፕ እ.ኤ.አ. ከ2009 ጀምሮ በኢትዮጵያ የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ የተሰጠው፣ የንግድ ምልክትነቱ የተከበረለት መሆኑን ያስታወቁት ካህን፣ በየጊዜው እየጨመረ በመጣው የተመሳሳይ ምርቶች ጫና ምክንያት የገበያ ድርሻውን እያጣ መምጣቱን አስታውቀዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ዩሮስታር በኢትዮጵያ የነበረው የገበያ ድርሻ 90 ከመቶ እንደነበር የተናገሩት ካህን፣ በዚህ ዓመት ወደ 30 ከመቶ ዝቅ እንዲል ያስገደዱት የተመሳሳይ ምርቶች በገፍ ወደ አገር ውስጥ መግባት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
በመርካቶ አካባቢ የተደረገው ድንገተኛ ፍተሻ ብቻም ሳይሆን እ.ኤ.አ. ከ2013 እስከ 2016 ባለው ሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ያለውን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መረጃ ዋቢ በማድረግ ኃላፊው እንዳብራሩት ከሆነ፣ በየዓመቱ ከ700 ሺሕ በላይ ተመሳስለው የተሠሩ የሳተላይ መቀበያ ዲሾችና ሪሲቨሮች ለገበያ ውለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ኩባንያው የገበያ ድርሻው በማጣት ለጉዳት ሲዳረግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
በመርካቶ ለተካሄደው ድንገተኛ ዘመቻ፣ የፖሊስ ኃይል፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንና ኩባንያው የተካተቱበት ሲሆን፣ ገበያው ላይ የታዩት ምርቶችም መጠነኛ የፊደላት ለውጥ በማድረግና ከዩሮስታር ዲሽ ጋር አምሳያ እንዲኖራቸው ሆነ ተብሎ በማዘጋጀት ለገበያ ሲቀርቡ የነበሩ ምርቶች ተይዘዋል፡፡
ላለፉት 20 ዓመታት በኤሌክትሮኒክስ ውጤቶችና በተለያዩ የስልክና የቴሌቪዥን ምርቶች መስክ ሲንቀሳቀስ የቆየው ዩሮስታር ግሩፕ፣ በምግብና በሌሎች ሸቀጦች ንግድ፣ በሪል ስቴትና በመሳሰሉት ዘርፎች በ50 አገሮች ውስጥ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ኩባንያ ነው፡፡