Tuesday, May 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንግድ ምክር ቤቱ ለሕንፃ ግንባታ የመረጠው ቦታ ውሳኔ እየጠበቀ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ለሚያስገነባው ሕንፃ ያቀረበው የመሬት ጥያቄ ከአዲስ አበባ አስተዳደር ካቢኔ ውሳኔን እየተጠባበቀ ነው፡፡ ከንግድ ምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ ለሕንፃው ማረፊያ እንዲሆን የተጠየቀው ቦታ መገናኛ አካባቢ የሚገኝ ነው፡፡

3,000 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ይህ ቦታ፣ ከማንም ይዞታ ነፃ መሆኑን  በማረጋገጥ ለሕንፃ ግንባታው እንዲውል ለማድረግ ለከተማው አስተዳደር ጥያቄ በማቅረቡ የአስተዳደሩ ካቢኔ ውሳኔ እንዲሰጥበት ስለመቅረቡ የንግድ ምክር ቤቱ መረጃ ይጠቁማል፡፡

ለሕንፃው ግንባታ አመቺ ቦታ አፈላልጎ ካቀረበ የከተማ አስተዳደሩ እንደሚፈቅድለት በገባለት ቃል መሠረት ንግድ ምክር ቤቱ የግንባታ ቦታ ሲያፈላልግ ቆይቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከተጠቆመው ቦታ ቀደም ብሎ ንግድ ምክር ቤቱ በመጀመርያው ምርጫው ለሕንፃ ግንባታ ለማዋል እንዲፈቀድለት ጠይቆ የነበረው ቦታ ሜክሲኮ አደባባይ፣ ከቶታል ማደያ ጎን የሚገኝ ቦታ እንዲሰጠው ጠይቆ ነበር፡፡

ሆኖም ሜክሲኮ አካባቢ የሚገኘው ይህ ቦታ ከ20 እና ከ20 በላይ ፎቅ ካላቸው በቀር መገንባት የተከለለ በመሆኑ፣ ንግድ ምክር ቤቱ ለመገንባት ያቀደው ባለ አሥር ፎቅ በመሆኑ ቦታው ሊፈቀድለት ሳይችል ቀርቷል፡፡ ይህ ከሆነ በኋላም ሌሎች ለግንባታ ይስማሙኛል ያላቸውን ቦታዎች ሲያማርጥ ቆይቶ፣ በመጨረሻም መገናኛ አካባቢ ካለው ቦታ ላይ ፍላጎቱን በማሳረፉ እንዲፈቀድለት ጥያቄ አቅርቧል፡፡  

የቦታ ጥያቄውን የተቀበለው የከተማው አስተዳደር የመጨረሻውን ውሳኔ ከሦስት ሳምንታት በፊት ይሰጣል ተብሎ ቢጠበቅም፣ ከወቅታዊው ጉዳይ ጋር በተያያዘ ካቢኔው ባለመሰብሰቡ ውሳኔውን ሊተላለፍ እንዳልተቻለም ተጠቅሷል፡፡

ካቢኔው እንደተሰበሰበ የመገንቢያ ቦታውን እንረከባለን የሚሉት የንግድ ምክር ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሕንፃ ግንባታም በቀጣዩ በጀት ዓመት ይጀመራል የሚል ተስፋ አላቸው፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ የራሱ ሕንፃ ለመገንባት የተነሳው፣ የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤቶች የሚጠቀሙበት ነበሩ ሕንፃ ላይ የአጠቃቀምና የባለቤትነት ጉዳዮች ላይ ተፈጥሮ ከነበረው ውዝግብ በኋላ ነበር፡፡

በዚሁ መነሻነት የሕንፃ ዲዛይኑን ጨረታ በማውጣት ከመረጠም ሦስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ወደ ግንባታ ያልተገባውም የቦታ መረጣው በመዘግየቱ ነው ተብሏል፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ አሁን ከሌሎች ንግድ ምክር ቤቶች ጋር በጋራ የሚጠቀምበት ሕንፃ ሊበቃው ባለመቻሉ፣ የተለያዩ የምክር ቤቱ የሥራ ዘርፎችን በተለያዩ ሕንፃዎች ውስጥ ቢሮ በመከራየት እንዲጠቀሙ ለማድረግ መገደዱ ይገለጻል፡፡ የአዲሱ ሕንፃ ግንባታ ወደፊት ሲጠናቀቅ ግን ሁሉንም በአንድ ሕንፃ  ውስጥ በማሰባሰብና ወጪውን በመቀነስ የመሥራት ዕቅድ ተይዟል፡፡ ከሕንፃ ኪራይም ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ለማግኘት እንደሚችል ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች