የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በዘርፉ ካሉ የሙያ ማኅበራት ጋር በመተባበር ዘንድሮ ስላደረጋቸው እንቅስቃሴዎች ሪፖርት ባቀረበበት ዕለት፣ ማኅበራቱ የሚያጋጥሟቸውን ማነቆዎች አሳውቀዋል፡፡ የማኅበራቱ ተወካዮች እንደገለጹት፣ በዋነኛነት የበጀት እጥረት፣ ቢሮ ማጣት፣ የፖሊሲና አመራር ችግሮች ይፈታተኗቸዋል፡፡ ማኅበራቱ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እንዲሁም ከሌሎችም የሚመለከታቸው ተቋሞች በቂ እገዛ እያገኙ አለመሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ነሐሴ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አዳራሽ የተገኙት በባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ያሉት ማኅበራት ተወካዮች በዋነኛነት የጠቀሱት የበጀት ውስንነት፣ ለሥራቸው አስፈላጊ ግብዓቶችን ከማሟላት እንዳገዳቸው ተናግረዋል፡፡ አብዛኞቹ ማኅበራት ሥራ የሚያከናውኑበት ቢሮ የሌላቸው ከመሆኑም በላይ፣ እንቅስቃሴዎቻቸውን የሚገቱ የሕግ ማዕቀፎች እንዳሉም ጠቅሰዋል፡፡
ባለሙያዎቹ ከውጪ የሚያስገቧቸው ዕቃዎች ላይ የሚጣለው ቀረጥ ከፍተኛ እንደሆነና የአንዳንድ ዘርፎች ባለሙያዎች አገር ውስጥ ሲሠሩ መብታቸውን የሚያስጠብቁላቸው ሕግጋት አለመኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ እንደ ምሳሌ የተሰጠቀሱት የሙዚቃ መሣሪያዎች ላይ ያለው ቀረጥና የፊልም ፖሊሲ አለመጽደቅ ናቸው፡፡
የሙያ ማኅበራትን ማነቆዎች ከተናገሩት አንዱ፣ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ዳዊት ይፍሩ እንደገለጹት፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ማኅበራቸውን በአሁን ወቅት ቢደግፍም፣ ማኅበሩ ከተቋቋመበት ጊዜ አንፃር እገዛው ዘግይቷል፡፡ ፕሬዚዳንቱ፣ ማኅበሩ ለሙዚቃው የሚያደርገው አስተዋጽኦ በአጽንኦት እንዲታይም ጠይቀዋል፡፡ ሐሳባቸውን በከፊል የተጋሩት የኢትዮጵያ ፋሽን ዲዛይነሮች ማኅበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ እጅጋየሁ ኃይለጊዮርጊስ፣ በፋሽን ዘርፍ የሚገለገሉባቸው መሣሪያዎች ያለባቸውን ከፍተኛ የቀረጥ ጉዳይ አንስተዋል፡፡ የፋሽን ባለሙያዎች ሥራዎቻቸውን የሚያሳዩበት ማዕከል አለመኖርም ክፍተት እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡
በቱሪዝሙ ካሉ ማኅበራት መካከል፣ በቱሪስቶች የትራንስፖርት አቅርቦትና በመዳረሻ ቦታዎች ያለው ዋጋ ተመን ላይ ጥያቄ ያነሱ ነበሩ፡፡ የቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች የዋጋ ተመን በየጊዜው እንደሚጨምርና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አንዳች መርሕ ማውጣት እንዳለበት ተመልክቷል፡፡ በተያያዥም የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ የማድረግ ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው ተጠይቋል፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ታደለች ዳለቾ፣ የቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች የክፍያ ሥርዓትን በተመለከተ ጥናት ተሠርቶ፣ መመርያ እንደወጣና በቅርቡ እንደሚተገበር ተናግረዋል፡፡ የቱሪስት መዳረሻዎች ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ እንዲሆኑ የተደረጉ ጥረቶች እንዳሉም ገልጸዋል፡፡ ችግሩ ሙሉ በሙሉ ባይቀረፍም፣ የቱሪስት መዳረሻዎችን በብሬልና በምልክት ቋንቋ በተዘጋጁ ጽሑፎችና ፊልሞች ለማቅረብ መሞከሩን አስረድተዋል፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ኢ/ር አይሻ መሐመድ፣ የሙያ ማኅበራቱ የጠቀሷቸው ቢሮ ማጣትን የመሰሉ ችግሮች በሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ጥረት ብቻ እንደማይፈቱ ገልጸዋል፡፡ ማኅበራቱ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር ባደረጉት ስምምነት መሠረት መሥሪያ ቤቱ ሊያደርግ የሚችለውን ድጋፍ እንደሚሰጥም አክለዋል፡፡ ይህም ለስብሰባ ወይም ትርዒት ለማሳየት የሚገለገሉበት አዳራሽን ያጠቃልላል፡፡ በቢሮ ረገድ ግን የተባለ ነገር የለም፡፡
ሚኒስትሯ፣ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በተጨማሪ ሌሎች መሥሪያ ቤቶች በሚመለከታቸው ጉዳዮች ላይ ከማኅበራቱ ጋር በጥምረት መሥራት እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡ ሚኒስትሯ ለማኅበራቱ አስቸጋሪ የሆኑ የሕግ ማዕቀፎች እንዳሉ ከአስተያየት ሰጪዎቹ ጋር ተስማምተዋል፡፡ የሕግ ማዕቀፍ ላልተዘጋጀላቸው ዘርፎች ፖሊሲና መመርያ በማውጣት ረገድ እንቅስቃሴዎች ቢደረጉም በአጭር ጊዜ ለመተግበር እንደሚከብድም ገልጸዋል፡፡ የብዙ ባለሙያዎች መነጋገሪያ የሆነው ረቂቅ የፊልም ፖሊሲ ላይ የተሰነዘሩበት ጥያቄዎች ካልተመለሱ ሰነዱን ለማጽደቅ አይቻልም ብለዋል፡፡
በዕለቱ የሙያ ማኅበራቱ የሚገጥሟቸውን ችግሮች ሲገልጹ፣ በሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ በኩል በ2008 ዓ.ም. ከማኅበራቱ ጋር የተከናወኑ ሥራዎችና መሰናክሎችም ተገልጸዋል፡፡
በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ኢንዱስትሪ ልማት ትብብር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደስታ ካሳ እንደሚሉት፣ በኪነ ጥበቡ ዘርፍ ከሚሠሩ ማኅበሮች መካከል የደራስያን፣ የሙዚቀኞች፣ የፊልም ሠሪዎች፣ የሠዓሊያንና ቀራፂያን እና የቴአትር ባለሙያዎች ማኅበሮች ጋር በመተባበር ዐውደ ርዕዮችና የባለሙያዎች ዝክር ተካሂደዋል፡፡ በየዘርፉ ስላሉ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ጥናትና ምርምሮች ተሠርተዋል፡፡ በባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ያለው እንቅስቃሴ ከገጠሙት እንቅፋቶች ውስጥ የሙያ ማኅበራት አባሎቻቸውን አቀናጅተው ማንቀሳቀስ አለመቻላቸው አንድ ችግር ነው፡፡
አንዳንድ ማኅበራት ከሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ጋር አብሮ ከማቀድ ውጪ በተግባር እንዳልተሳተፉም ተገልጿል፡፡ የማኅበራት አመራሮች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡም ተጠይቋል፡፡ በተያያዥም ማኅበራቱ ከባለድርሻ አካሎች ጋር እንዲሁም ተቀራርበው ቢሠሩ ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸው እንደሚጨምር ተመልክቷል፡፡
ዘንድሮ ከባህል ዘርፍ ማኅበራት ጋር ከተሠሩት ሥራዎች ከሠዓሊያንና ቀራፂያን ማኅበር ጋር በመሆን የሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የመታሰቢያ ሐውልት መጠናቀቅና ከኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበራት ፌዴሬሽን ጋር የተሠራው አካል ጉዳተኞችን በባህልና ኪነ ጥበብ የማሳተፍ እንቅስቃሴ ተጠቅሰዋል፡፡
በቱሪዝም ዘርፍ ካሉ 15 ማኅበሮች ጋር ከተሠሩ ሥራዎች፣ የሆቴሎች ደረጃ ምደባ ይገኝበታል፡፡ ከዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በዱር እንስሳት ቆጠራና ምደባ የታቀደው መሠራቱም በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡ ዘንድሮ ታቅደው ካልተከናወኑ ሥራዎች መካከል፣ የቱሪዝም ሥነ ምግባር መመርያ ይገኝበታል፡፡ በየማኅበሩ ያሉ ባለሙያዎች የሥነ ምግባር ኮድ በማውጣት እንዲተገብሩ ለማድረግ ቢታቀድም አልተከናወነም፡፡ ባጠቃላይ በዕለቱ፣ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እና በዘርፉ ያሉ የሙያ ማኅበራት በዓመቱ አሳክተናል ያሏቸውንና መሰናክል የሆኑባቸውንም ተወያይተዋል፡፡