Thursday, February 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

የሉሲ ከዛፍ ላይ አወዳደቅ መላምት በምስል

ትኩስ ፅሁፎች

የሉሲ ከዛፍ ላይ አወዳደቅ መላምት በምስል

ከ41 ዓመት በፊት በሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ አፋር ሀዳር ውስጥ የተገኘችው ሉሲ፣ አሟሟቷ እንዴት እንደነበረ የሚያሳይ አዲስ ግኝት ነሐሴ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. በመላው ዓለም ይፋ ሆኗል፡፡ የአዲስ አበባ እና የቴክሳስ ዩኒቨርሲቲዎች ተመራማሪዎች ባጠኑት መሠረት የሉሲ አሟሟት፣ ከ12 ሜትር በላይ ከሚረዝም ዛፍ ላይ መውደቋ ነው፡፡ ተመራማሪዎቹ
እንደገለጹት የተዘጋጀው ምስል ይህንኑ ያሳያል፡፡

ባማራት!

ላዲስ እጮኛዬ

ፍጹም ለወደድኳት

ነፍሷ ያሳሻትን

ጥሬ ላቀርብላት

ይዞኝ አዲስ – ፍቅር

ስለወዘወዘኝ

ላሞላላት ሳለግም

ልቧ ሲፈቅድልኝ

ምን አማረሽ ፍቅሬ

የኔ ውዷ ክብሬ

ብዬ ብጠይቃት

ኖሮ ያዋለላት

. . . አለች . . .

‹‹ጥቁር – ወተት›› እንድፈተንበት

ከልዬ አጥናፍ ካጥናፍ

ፍቅርዬ ላማራት

እንጂ ነጭ ወተት

ላም ጥቁር የት አላት?

ባሰምር ደክሜ

ብትቀይርልኝ

ከፋፍታ አፎቿን – አለች

‹‹ነጭ-ኑግ›› አርግልኝ

ገባኝ’ና ግራ

እንዲህ ለጦፍኩላት

በምድር ስላጣሁ

ፍል-ገቷን ለመሙላት

ጀርባ – በጀርባ ሆን

ፍቅርዬ – ባማራት!

  • ማሙሽ ላቀው ‹‹ብቸኝነት›› (2005)

* * *

ቡርኪና ፋሶ የሴቶች መቀመጫ ውድድርን አገደች

በቡርኪና በየዓመቱ ይካሄድ የነበረውን ትልቅ መቀመጫ ያላቸው ሴቶችን ውድድር መንግሥት ማገዱን ሮይተርስ ዘገበ፡፡ የውድድሩ አዘጋጅ የነበረው አቶ ሀማዶ ዱአምባሂ ውድድሩ የሴቶችን ገጽታ ለመገንባት የፋሽን ዲዛይነሮችም የአፍሪካውያን ሴቶችን ውበትና አለባበስ በዓለም አቀፍ መድረክ እንዲጠቀሙበት ለማድረግ እንደሚረዳ ይገልጻሉ፡፡ እሳቸው ይህን ቢሉም የአገሪቱ የሴቶች ጉዳይ ሚኒስትር ላውሪ ዘንጐ የሴቶችን ገጽታ የሚያጐድፍን ነገር ሁሉ የማስወገድ ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸው አስተያየቱ መጀመሪያ የተላከላቸው በማኅበራዊ ድረ ገጽ እንደሆነ ከዚያም ወደ ዕርምጃ መግባታቸውን አስረድተዋል፡፡ ተመሳሳይ የቁንጅና ውድድሮች በሌሉት የምዕራብ አፍሪካ አገሮችም የሚካሄድ ሲሆን የሴቶች መብት ተከራካሪ ቡድኖች ስለጉዳዩ ያላቸው ስሜት የተደበላለቀ ነው፡፡

* * *

ጣሊያን ሱፐር ማርኬቶች ያልተሸጡ ምግቦችን ለተቸገሩ እንዲሰጡ ልታደርግ ነው

የጣሊያን መንግሥት ምግብ በመሸጥ ላይ የተሰማሩ ትልልቅ ኩባንያዎች ያልተሸጡላቸውን ምግቦች ቆሻሻ አድርገው በማስወገድ ከሚያባክኑት እንዲለግሱት የሚያስችል መንገድ ቀይሻለሁ ብሏል፡፡ መንግሥት ይህን ሊያደርግ ያሰበው ሱፐር ማርኬቶች ያልተሸጡላቸውን ምግቦች ለበጐ አድራጐት ድርጅቶች መስጠት የሚያስችላቸውን ሕግ በማውጣት ነው፡፡ ከወራት በፊት ሱፐር ማርኬቶች ያልተሸጠላቸውን ምግብ እንዳይጥሉ የሚያግድ ሕግ ካወጣችው ከፈረንሳይ ቀጥሎ የዚህ ዓይነት ሕግ በማውጣት ጣሊያን ሁለተኛዋ የአውሮፓ አገር ነች፡፡ ረቂቅ ሕጉ እስካሁን ትልቅ ድጋፍ ያገኘ ሲሆን በቀጣዩ ሳምንት ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ፈረንሳይ ያልተሸጡ ምግቦችን የሚጥሉ ሱፐር ማርኬቶችን ስትቀጣ ጣሊያን ደግሞ ያልተሸጡ ምግቦችን ለለጋሽ ድርጅቶች ለሚሰጡ ኩባንያዎች ማበረታቻ ታደርጋለች፡፡ በአሁኑ ወቅት ጣሊያን በየዓመቱ ቆሻሻ ለማስወገድ የምታወጣው 12 ቢሊዮን ዩሮ ሲሆን ይህ ረቂቅ ሕግ ይህን ወጪ በመቀነስ ረገድ ጠቀሜታው የጐላ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡  

* * *

ከ300 የሚበልጡ አጋዘኖች በመብረቅ አደጋ አለቁ

በኖርዌይ ብሔራዊ ፓርክ በደረሰ የመብረቅ አደጋ በፓርኩ የሚገኙ 323 አጋዘኖች መሞታቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡ አንድ የድርጅቱ ሠራተኛ በቦታው ሲደርስ አምስት የሚሆኑ አጋዘኖች በሕይወት እንደነበሩ ነገር ግን ብዙም ሳይቆዩ መሞታቸውን ገልጿል፡፡ የበርካታ አጋዘኖች መገናኛ እንደሆነ በሚነገርለት በዚህ ፓርክ የደረሰው አደጋ ዓርብ ዕለት ከጣለው ከባድ ዝናብ ጋር የተያያዘ መሆኑን የድርጅቱ ቃል አቀባይ ካርታን ኩስቲን ገልጿል፡፡

አንዳንዴ በሚፈጠር የመብረቅ አደጋ የዱር እንስሳቱ የሚሞቱበት አጋጣሚዎች መኖራቸውን የሚናገረው ቃል አቀባዩ ‹‹ይህንን ያህል ቁጥር ያላቸው እንስሳት ሲሞቱ ይህ የመጀመሪያ ነው፡፡ ዝናቡን ሸሽተው አንድ ቦታ ተሰብስበው ሳሉ አንድ ላይ አግኝቶ ነው የፈጃቸው›› ሲል በአንዴ በርካታ አጋዘኖች ሊሞቱ የቻሉበትን አጋጣሚ ተናግሯል፡፡ ድርጅቱ ከሞቱት አጋዘኖች ላይ የደም ናሙና በመውሰድ ምርመራ እያደረገ ይገኛል፡፡   

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች