Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርኢሕአዴግ ይፍረስ ወይስ ይታደስ?

ኢሕአዴግ ይፍረስ ወይስ ይታደስ?

ቀን:

በሊሕ ላማ

ጊዜው ጊዜ የሚሰጥ አይደለም፡፡ የሚገመትም አይደለም፡፡ በፍጹም ስለነገው ማወቅ አይቻልም፡፡ እናም ኢሕአዴግ ከፊት ለፊቱ ሁለት ወፍራም አማራጮች ተጥደውበታል፣ መፍረስ ወይም መታደስ፡፡ 17 ዓመታትን በበረሃ ከርሞ ሦስት አሠርታት ለሚጠጋ ጊዜ የቤተ መንግሥትን ጥቅም ያወቀ ድርጅት መፍረስን ይመርጣል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ ምርጫው መታደስ የሚለው ይሆናል ማለት ነው፡፡ በእርግጥ መታደስም ቀላል አይደለም፡፡ የግንባሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴና ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ ይህንን ሊያደርግ እንደሚችል በገደምዳሜ ተናግሯል፡፡ ‹‹ያለፉትን አሥራ አምስት ዓመታት (ከ1993 ዓ.ም. ተሃድሶ ወዲህ ያለውን ጊዜ ማለቱ ነው) ውጤትና ውድቀት በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል›› ማለት፣ በሌላ ቋንቋ ሌላ ተሃድሶ ሊያደርግ ነው የሚል ትርጉም እንዳለው የሚጠቁም ነው፡፡

ጥያቄዎቹ ‹‹በእርግጥ የአሁኑ ኢሕአዴግ ግልብጥብጥ ያለ ተሃድሶ ለማድረግ ወኔው አለው ወይ? ተሃድሶ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮችስ ምን ምን ናቸው? ይህንን ለማድረግ የሚያስችልና ተሃድሶውን የሚቀበል ግለሰብ ወይም ቡድን አለ ወይ?›› የሚሉ ይሆናሉ፡፡ ድርጅቱ ‹‹እኔ የራሴን ከራሴ እጀምራለሁ፣ ሥራ አስፈጻሚው ውስጥ በሥልጣን መባለግ አለ ይህንን አፀዳለሁ፣ ሥልጣንን የግል ጥቅም ማበልፀጊያ ያደረጉ ሰዎች በዝተውብኛል፣ እናም ሕዝብ ከጎኔ ይቁም፣ እኔም ራሴን አርማለሁ…›› ሲል በአደባባይ ንስሀ ገብቷል፡፡ እንደተባለው ግንባሩ መፍረስን የማይመርጥና ለመታደስ ከተዘጋጀ ቀላል የማይባሉ ወጥመዶች አሉበት፡፡ ወጥመዶቹ ወይ ይይዙታል ወይ እሱ ራሱ አስቀድሞ ይይዛቸዋል፡፡

ኢሕአዴግ ምን ዓይነት ተሃድሶ ያድርግ?

ፖለቲካዊ ተሃድሶ

በዚህ ወር ሁለተኛ አጋማሽ ላይ የወጣው የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ መግለጫ ስለፖለቲካዊ ተሃድሶ፣ ስለፖሊሲ ለውጥና ተያያዥ ጉዳዮች አያወራም፡፡ ይልቁንም ከ1993 ዓ.ም. ወዲህ ስኬታማ ፖሊሲዎቹ ያጎናፀፉትን ድል ይተርካል፡፡ ይኼ ምናልባት ለፖለቲካዊ ለውጥ አለመዘጋጀቱን የሚጠቁም ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ይህንን ዓይነት ተሃድሶ ያላደረገ ኢሕአዴግ ከሞቱት በላይ ከቆሙት በታች መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ በግልጽ ቋንቋ ፖለቲካዊ ተሃድሶ ያስፈልጋል፡፡ ፖለቲካዊ ተሃድሶ ሲባል ከስሙ ይጀምራል፡፡ ኢሕአዴግ የሚለው ሶሻሊስታዊ ስያሜ፣ ካፒታሊስት ነኝ ለሚል ድርጅት አይሆንም፡፡ ይህ ድርጅት እስካሁን አለመዋሀዱም ሆነ ፓርቲ አለመሆኑ ይዞት የመጣው ጣጣ ቀላል አይደለም፡፡ በ1980ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት ሕወሓትና ኢሕዴን ጥምረት የመሠረቱት ሥልታዊ በሆነ ምክንያት ነበር፡፡ ደርግን በጋራ ለመጣል!! ይህ ሥልት ግን ከሥልትም አልፎ ወደ ስትራቴጂካዊነትም አድጎ ዛሬም ድረስ አለ፡፡

ቀድሞ ነገር ፓርቲዎች ጥምረት የሚመሠርቱት የተለያየ ግን ለመታረቅ የማያስቸግር ርዕዮተ ዓለም ሲኖራቸው፣ በነጠላ ሥልጣን ለመያዝ የሚያስችል መተማመኛ ድምፅ ሲያጡ፣ ወዘተ. ነው፡፡ ኢሕአዴግ በተባለ ጃንጥላ ሥር ያሉ አራት ድርጅቶች ግን ቅንጣት ያህል የመርህ፣ የፖሊሲ፣ የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ሳይኖራቸው ዛሬም በጥምረት ግንባር ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ የሕወሓትን ፖለቲካዊ ፍልስፍና ከብአዴን፣ የኦሕዴድን ከደኢሕዴን በአጠቃላይ አንዱ ከሌላው ያለውን ኅልዮት ለይቶ ማብራራት በማይቻልበት ሁናቴ ዛሬም በጥምረት ውስጥ ሆኖ ኢሕአዴግ መባሉ አስገራሚ ነው፡፡ እናም ግንባሩን አፍርሶ ከጥምረት ወደ ውህደት ማምጣት ድርጅቱን ከተጋረጡበት ፈተናዎች ሁሉ ለማዳን የሚያስችል የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና ነው፡፡ ከዚያም ኢሕአዴግ የግንባር ባርኔጣውን አውልቆ ፓርቲ ሆኖ ሲመጣ በሽታው ቀለል ይለዋል፡፡

በእርግጥ ይኼኛውን ነገር ኢሕአዴግን ሆኖ ለሚያስብ ሰው አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ዋናው ችግር የሕወሓትን ግርማ ሞገስ የሚያኮሰምን ነው የሚለው አስተሳሰብ ነው፡፡ በእርግጥ የድርጅቱ አስኳል የሆነው ሕወሓት ለግንባሩ መመሥረት ሚናው ቀላል አይደለም፡፡ ግንባሩ በአንድ ወቅት ውጤታማ ሆኖ ደርግን ጥሏል፡፡ አሁን ግን ጊዜው አይደለም፡፡ ይህንን ሕወሓት ሊያምንና ወቅታዊ መሆኑን ሊቀበል ይገባዋል፡፡ ኢሕዴንን ወደ ብአዴንነት (ከኅብረ ብሔራዊነት ወደ ብሔራዊነት) ያሳነሰ ግንባር፣ ሕወሓትንና ሌሎቹን ወንድሞቹን ወደ ኅብረ ብሔራዊነት ማሳደግ ሊከብደው አይገባም፡፡ የግንባሩ መፍረስ ዛሬም ድረስ ነፃ አውጭ ለሆነው ሕወሓትም (ስሙ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጭ የሚል መሆኑን ልብ ይሏል) ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡ በአንድ በኩል ሌሎቹ የግንባሩ አባላት ለስማቸው መጠሪያ እንኳ ዴሞክራሲ የሚል ቃል ሲያስገቡ፣ ሕወሓት የለውም፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ ዛሬም እንደ 1977 ዓ.ም. ይህ ድርጅት ነፃ አውጭ ነኝ እያለ በአማፂ ቡድን ስያሜ ይጠራል፡፡ የቀድሞ ወዳጁ ሻዕቢያ እንኳ ለአፉ ያህል ዴሞክራሲያዊ የምትል ቃል ሰንቅሮ (ሕግዴፍ-ሕዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲና ለፍትሕ) ስሙን ሲቀይር ሕወሓት ዛሬም በቆላ ስሙ ላይ የሙጥኝ ብሎ ቀርቷል፡፡

ድርጅቱ ስም የመቀያየር ችግር የለበትም፡፡ በረሃ ሲገባ ማገብት (ማኅበረ ገስግስቲ ብሔረ ትግራይ) ነበር፡፡ ብዙም ሳይቆይ ተሕሓት (ተጋዳሊ ሕዝቢ ሓርነት ትግራይ) ሲል ራሱን ሰየመ፡፡ በኋላም ሕወሓት (ሕዝበ ወያኔ ሓርነት ትግራይ) ሆኖ አዲስ አበባ ገብቷል፡፡ በየወቅቱ ስሙን የቀያየረበት ምክንያት አሳማኝ እንደሆነ አመራሮቹም ሆኑ አባላቱ ይናገራሉ፡፡ ስለዚህ አሁንም ቢሆን ይህ ድርጅት ስሙን አድሶ ለመምጣት ብዙ ሺሕ ምክንያቶች አሉለት፡፡ የአሁኑ ስም ቅያሬ በእርሱ ፊታውራሪነት የተመሠረተውን ግንባር ንዶ ለዘመኑ የሚመጥን መሆን ይገባዋል፡፡ ይህንን ማድረጉ ጥቅሙ ለራሱም ጭምር መሆኑን የነፃ አውጭው ድርጅት አመራሮች ሊያውቁት ይገባል፡፡ ሉዓላዊ ሥልጣን ባላቸው ክልሎች ላይ ጣልቃ ይገባል፣ ቁልፍ የሥልጣን ቦታዎችን ማጣት አይሻም፣ ከሚለው ወቀሳ ለመዳን፣ ‹‹ይህንን ግንባር ማፍረስ›› የሚለውን ምክረ ሐሳብ ሊቀበለው ይገባል፡፡ የወቀሳው ውሸትነትና ኢ-ምክንያታዊነት የሚረጋገጠውም ይህንን ግንባር ለማፍረስ ሕወሓት ቁርጠኛ ሲሆን ነው፡፡ እንደ ደቡብ አፍሪካ ያሉ ብዙ ባህልና ቋንቋ ያለባቸው አገሮች፣ እንደ ህንድ በስብጥረ ጎሣ የተሞሉ አገሮች የሚመሩት በአንድ ፖርቲ (ANC & BJP) ነው፡፡ እናም ግንባሩ ራሱን ለማደስ የእነዚህን አገሮች ልምድ ማየት አለበት፡፡ ከዚያ መቐለ ላይ ያለው ኢሕአዴግ ሐዋሳ ላይ ካለው ኢሕአዴግ የማይለይ፣ አንድ የሲዳማና አንድ የሽሬ ሰው እኩል የሚያጣጥሙት ይሆናል፡፡

የግንባሩ ሌላኛው ግዙፍ ችግር አግላይ መሆኑ ነው፡፡ ኢሕአዴግ አምስት ክልሎችንና ሁለት የከተማ መስተዳድሮችን አግልሏል፡፡ ኢሕአዴግ ማለት የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ማለት ነው፡፡ ግን ግንባሩ አራት ክልሎችን ብቻ የሚያስተዳድሩ ድርጅቶች ያዋቀሩት ነው፡፡ ‹‹ሌሎቹ ክልሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች አይደሉም ለማለት ነው?›› ወይስ ‹‹እነዚህኞቹ ዴሞክራሲም አብዮትም አያስፈልጋቸውም›› ለማለት ነው አምስቱን ክልሎች ትቶ ሁለት ከተማ መስተዳድሮችን ረስቶ ግንባር ነኝ ማለት?! በምርጫ ሰሞን እየገጠመ ያለው ጉዳይም በቀላሉ እየታለፈ ነው፡፡ አዲስ አበባና ድሬዳዋ ላይ ለመወዳደር ኢሕአዴግ ማሠለፍ ያለበት ግንባሩን ከመሠረቱት አባል ድርጅቶች ብቻ ነው መሆን ያለበት፡፡ ኢሕአዴግ ራሱ ፓርቲ ሆኖ መምጣት አይችልም፡፡ እርሱ ግን እንዲያ እያደረገ ነው፡፡ ጎንደር ላይ ብአዴንን ሆኖ ይሠለፍና አዲስ አበባ ላይ ኢሕአዴግ ሆኖ ነፍስ ይዘራል፡፡ ወለጋ ላይ ኦሕዴድ ሆኖ ይቀርብና ድሬዳዋ ሲደርስ መለያውን አውልቆ በኢሕአዴግነቱ ይሠለፋል፡፡ ስለዚህ በሁለቱ ከተሞች ላይ ኢሕአዴግ የሚባል ግንባርም ፓርቲም እስከሌለ ድረስ ይህንን ጥምረት ወደ ውሕደት ማምጣት መከራከሪያ ሊቀርብበት የማይገባ እውነት ነው፡፡ እናም ወቅታዊው ተሃድሶ ይህንንም ማጤን ይገባዋል!!! የግንባሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መግለጫ ግን ያለበትን ችግር ከሙስና ጋር ብቻ አያይዞ ማቅረቡ፣ ለዚህ ጉዳይ ትኩረት እንዳልተሰጠው የሚያመለክት ነው፡፡

የርዕዮተ ዓለም ጉዳይ

የኢሕአዴግ የፖለቲካ ማጠንጠኛ ከአልባኒያ ሶሻሊዝም እስከ ነጭ ካፒታሊዝም ይደርሳል፡፡ ብዙ የርዕዮተ ዓለም ጃኬቶችን አውልቆ ለብሷል፡፡ አሁን ግን ምን ዓይነት መለያ እንደለበሰ ግልጽ አይደለም፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ልማታዊ ዴሞክራሲ የተባሉ ጃኬቶችን ደራርቦ እንደለበሰ ግን እሙን ነው፡፡ ቢያንስ የግንባሩ ስም ላይ ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› የሚሉ ቃላት ስላሉ ድርጅቱ ይህንን ርዕዮት ያቀነቅናል ማለት ነው፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ ልማታዊ ዴሞክራሲ የግንባሩ ኅልዮት መሆኑን ከ1993 ዓ.ም. ወዲህ የታተሙ የድርጅቱ ሰነዶች ያስነብባሉ፡፡ እነዚህ እርስ በራሳቸው የሚጣረሱ ጽንሰ ሐሳቦች ናቸው፡፡ ልማታዊ ዴሞክራሲ ፖለቲካዊ አስተምህሮ በአጭሩ ልማትንና ዴሞክራሲን አብሮ ማስኬድ፣ ሁለቱንም ወደ ውጤት ማምጣት የሚል ትርጉም እንዳለው ግንባሩ ደጋግሞ ጽፏል፣ ተናግሯል፡፡ ስለአብዮታዊ ዴሞክራሲ ግን ከጥቂት ነባር አመራሮች በስተቀር በግልጽና በዝርዝር የሚያብራራ ሰው አልታየም፡፡ ከጅምረ ነገሩ ይኼ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚባለው ርዕዮተ ዓለም ኢሕአዴግ ቆሜለታለሁ ከሚለው መርህ ጋር ይጋጫል፡፡

አብዮታዊ ዴሞክራሲ የማርክሳዊ ኅልዮት ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ በ1978 ዓ.ም. በአማርኛ ተተርጉሞ የታተመው የማርክሲዝም ሌኒንዝም መዝገበ ቃል ይህንን የፖለቲካ ፍልስፍና እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፡፡ ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ ከፊል ካፒታሊስትና በአብዛኛው በቅድመ ካፒታሊስት የዕድገት ደረጃ ላይ በሚገኙ አገሮች ሥልጣን ለመጨበጥ ፀረ-ፊውዳል፣ ፀረ-ኤምፔሪያሊስት፣ ፀረ-ካፒታሊስት የሆነውን ትግል በማርክሳዊ ሌኒናዊ ድርጅት ግንባር ቀደም መሪነት የሚያራምድ ኃይል ነው፡፡›› በዚህ ድሐፍና በግልጽ እንደተቀመጠው ካፒታሊዝምም ሆነ የዚህ ፍልስፍና ወንድም ነፃ ገበያ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጠላቶች ናቸው፡፡ ኢሕአዴግ በአንፃሩ የነፃ ገበያ ፍልስፍናም ሆነ፣ ነጭ ካፒታሊዝም የምሞትላቸው መርሆዎች ናቸው ብሏል፡፡ ይህ እርስ በርሱ የሚጣረስ ነው፡፡ ጠላት ለሆኑት ፍልስፍናዎቹ እሞታለሁ ማለት የሚቃረን ነው፡፡

በነገራችን ላይ ይህ ፍልስፍና በ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በምሥራቅ አውሮፓ፣ በጀርመን (በከፊል) እና በመሰል ሶሻሊስታዊ አገሮች ይተገበር የነበረ አስተሳሰብ ነበር፡፡ ከሶሻሊዝም መንኮታኮት በኋላም ይህ ኅልዮት አብቅቶለታል፡፡ አላበቃለትም ቢባል እንኳ በካፒታሊዝምና በነፃ ገበያ አራማጅ አገሮች ይህ ፖለቲካል ኢኮኖሚ በፍፁም ተቀባይነት የለውም፡፡ በአንድም ካፒታሊስታዊ አገር ውስጥ ይህ ፍልስፍና ገቢራዊ ሆኖ አይገኝም፡፡ ምክንያቱም ፍልስፍናው የወገነው ነፃ ገበያን ከመሳሰሉ የዴሞክራሲ ጽንሰ ሐሳቦች በተቃራኒ ነው፡፡ ይህንን መርህ እከተላለሁ የሚለው የኢትዮጵያ ገዥ ግንባር ግን በቢላዋው ሁለቱም ወገን (በደንደሱና በስለቱ) እየበላ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ርዕዮተ ዓለማዊ መደበላለቅ ካላጠራ፣ አማራጭ የላችሁም ከሚላቸው ተቃዋሚዎቹ የባሰ ብዥታ ውስጥ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ የአንድ ፖለቲካ ቡድን መመዘኛ የሚከተለው ፍልስፍና እንጂ ያሰባሰባቸው ሰዎች አይደሉም፡፡ ኤኤንሲ 106 ዓመቱ ነው፡፡ ይህንን ፓርቲ ከመሠረቱ ሰዎች አንድም በሕይወት የለም፡፡ ሥርዓቱና ርዕዮተ ዓለሙ ግን አብሮት አለ፡፡ ስለዚህ ኢሕአዴግም የሚከተለውን የፖለቲካ ፍልስፍና ማጥራት ወቅታዊ ግዳጁ ሆኖ ተቃርቧል፡፡

የፖሊሲ ተሃድሶ

የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው መግለጫ በ1993 ዓ.ም. ተሃድሶ ማግሥት የተተገበሩ ፖሊሲዎች ውጤታማ ስለመሆናቸውና በአፈጻጸም በኩል ስለገጠማቸው ችግር  የሚተርክ ነው፡፡ በአጭር ቋንቋ ‹‹ፖሊሲዎቹ ውጤታማ ናቸው›› ተብሏል፡፡ ስለዚህ ኢሕአዴግ የፖሊሲ ተሃድሶ ለማድረግ ቁርጠኛ አይደለም ማለት ነው፡፡ ግን በጣም ብዙ ጉዳዮች ፈጣን ለውጥ ይሻሉ፡፡ ዋነኛው ግን የግብርና ፖሊሲ ነው፡፡ ታዋቂው ደራሲ ግርሃም ሃንኩክ “Ethiopia; The Challenge of Hunger” የሚል መጽሐፍ አለው፡፡ በዚህ መጽሐፉ ላይ እንደሚተርከው፣ ይቺን አገር ድርቅ የተባለ መዓት የሚቀጣት ከ13ኛው ክፍለ ዘመን አንስቶ ነው፡፡ ለዘጠኝ ክፍለ ዘመናት የተጣባንን ድርቅና ረሃብ የኢትዮጵያ ግብርና ዛሬም ሊቋቋመው አልቻለም፡፡ ደርግ የተባለው ቡድን ወደ ሥልጣን የመጣው ንጉሡን፣ ውሻቸውንና ቅምጥል ኑሯቸውን ከወሎ ረሃብተኞች ጋር አነፃፅሮ የሚያሳይ ቪዲዮ ለሕዝብ ቀድሞ በማድረስ ነበር፡፡ ሕዝቡ በጃንሆይ ላይ እንደተቆጣ ካረጋገጠ በኋላ ከዙፋን አውርዶ አሠራቸው፡፡ ሥርወ መንግሥቱም ላይመለስ ተገረሰሰ፡፡

ከዓመታት በኋላ በ1977 ሌላ ረሃብ፣ ሌላ ድርቅ ከደርግ መንግሥት ጋር ተፋጠጠ፡፡ ስሙንም ‘የተፈጥሮ መዛባት’ ሲል ጠራው፡፡ የወሎና የትግራይ ጉዳተኞች ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ግን ኮተቤን እንዳያልፉ ትዕዛዝ የሰጠው ይኼው ጁንታ ነበር፡፡ በዚያው ሰሞን በረሃ ላይ ከነበሩት አማፅያን አንዱ ሕወሓት ነውና አቶ መለስ ዜናዊ ለቢቢሲ እንዲህ አሉ፡፡ ‹‹እየተዋጋሁለት ያለሁት ሕዝብ በምግብ እጦት እየሞተ ነው፡፡ ይህ ሕዝብ ጠንካራ ሠራተኛ ነው፡፡ ግን በድጋፍ ማጣትና ሳይንሳዊ ግብርናን ባለመተግበሩ ሕዝቡ እየሞተ ነው፡፡ ስህተቱ ግን ከእነሱ አይደለም፡፡›› በወቅቱ የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ አባል የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ የተናገሩት ለረሃቡ ተጠያቂው ሕዝብ ሳይሆን መንግሥት ነው፣ ገበሬ ሳይሆን ፖሊሲ ነው የሚል ይዘት ያለው ነው፡፡ ግን የአቶ መለስ ድርጅት ወደ ሥልጣን መጥቶም አገሪቱ ጠኔ አልተለያትም፡፡ በተደጋጋሚ የተከሰተው ድርቅ ብዙ ሕዝብ ፈትኗል፡፡ በእርግጥ በረሃብ የሞተ ሰው ስለመኖሩ የወጣ ዘገባ የለም፡፡ በዚህም መንግሥት ድርቅን ተቋቁሜያለሁ የሚል መግለጫ በየዓመቱ እንዲያወጣ ሆኗል፡፡ ይህ ሁኔታም ደርግ ጃንሆይን፣ ኢሕአዴግ ደግሞ ደርግን እንደከሰሰበት ሁሉ ተቃዋሚዎቹ በዚህ በኩል ኢሕአዴግን ሲከስሱት አይደመጡም፡፡ 10.2 ሚሊዮን ሕዝብ አፋጣኝ ምግብ ያስፈልገዋል ሲባል እንኳ ተቃዋሚዎቹ፣ ‹‹መንግሥት ድርቁን አልተቋቋመውም›› ብለው ሲናገሩ አልተሰሙም፡፡ ግንባሩ ከነችግሮቹ ድርቁን በጊዜያዊነት መክቶታል፡፡ ድርቅን መቋቋም የተቻለው ግን አገሪቱ ከድሮው የተሻለ የውጭ ግንኙነት መርህ ያላት በመሆኑ (ርዕዮተ ዓለም ላይ ያልተመሠረተ) እና ለጋሽ አካላት እጃቸው ስላላጠረ እንጂ፣ ውጤታማ የሆነ የግብርናና የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ስላለን አይደለም፡፡ ይህንን ማመን ለኢሕአዴግ ፈታኝ ቢሆንም ሊያጤነው ግን ይገባል፡፡

አቶ በረከት ስምዖን የሁለት ምርጫዎች ወግ በተሰኘው መጽሐፋቸው፣ የኢትዮጵያ ገበሬ ድህነት ሰበቡ ስንፍናና ለሥራ የሚሰጠው ጊዜ ማነስ መሆኑን እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ክረምቱን ብዙ ለፍቶ በበጋ ሠርግና ተዝካር ሲያሳልፍ ጊዜውን የሚያባክነው የኢትዮጵያ አርሶ አደር በዓመት ከመቶ ሃምሳ ቀናት በላይ አይሠራም፡፡ ሃምሳ ሁለት ቅዳሜና እሑዶች በድምሩ መቶ አራት ቀናት ይነጥቁታል፡፡ በክርስትናም ሆነ በእስልምና ሃይማኖቶች ቅዱሳን መጻሕፍቱ ያልከለከሏቸውን ቀናት በዓላት አድርጎ እያከበረ የሚያባክናቸው በርካታ የሥራ ቀናትም አሉት፡፡ በዚህ ላይ ለሠርግና ተዝካር የሚያውለው የሥራ ጊዜ አለ፡፡ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል አፍላ የሥራ ወቅት ከሆነው ወርኃ ግንቦት ሁለት ተከታታይ ሳምንታት የጰራቅሊጦስን በዓል ለማክበር ሲባል ሥራ ይፈታበታል፡፡ እነዚህ ሁሉ ተዳምረው በዓመት ሦስት መቶ ቀናት መሥራት የነበረበት አርሶ አደር ቢያንስ ከሁለት መቶ ቀናት በላይ ያርፋል፡፡››

ይህ ጉዳይ እንደ አንድ ምክንያት ሊጠቀስ የሚችል እንጂ መሠረታዊ ሰበብ አይደለም፡፡ ነገርየው በቀጥታ ከፖሊሲ ጋር የሚገናኝ መሆኑን ታውቆ የኢትዮጵያን ገበሬ ከድህነት፣ ከረሃብና ከኋላ ቀርነት ማላቀቅ ወቅታዊ ነው፡፡ በየትም ዓለም በግብርና መር ኢኮኖሚ ያደገ አገር የለም፡፡ ኢሕአዴግ ምሳሌዎቼ ናቸው የሚላቸው እነ ደቡብ ኮሪያ እንኳን ፈጥነው ያደጉት በኢንዱስትሪ መር ፖሊሲ ነው፡፡ በቻይና ከሦስት አሥርታት በፊት 75 በመቶ የሚጠጋ ሕዝብ ገበሬ ነበር፡፡ አሁን ከ50 በመቶ የላቀ ቻይናዊ ኑሮው ከኢንዱስትሪ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በኢንዱስትሪ ላይ የተመሠረተ ምጣኔ ሀብት ለውጭ ንግድም ሆነ ለዘላቂነት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራም ሆነ ዝናብ ላይ ላልተመሠረተ አስተማማኝ ዕድገት ወሳኝ መሆኑ በተግባር ተረጋግጧል፡፡ ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ 85 በመቶ የሚሆነው ኢትዮጵያዊ ገበሬ ነበር፡፡ ለዚያውም ኋላቀር በሆነ እርሻ ላይ የተመሠረተ፡፡ ከ26 ዓመታት በኋላ ይኼ አኃዝ ዝቅ ያለው በሁለት በመቶ ብቻ ነው፡፡

ስለዚህ ዛሬም ግብርና ትልቁ ቀጣሪ፣ ትልቁ የውጭ ምንዛሬ ምንጭና ዋነኛው ኋላቀር ሴክተር ነው ማለት ነው፡፡ በአጭር አገላለጽ ዛሬም ለኢንዱስትሪ ሊሆን የሚገባው መሬትና ወደ ከተሜነት ሊያድግ የሚገባው ሕዝብ ብዙ ነው፡፡ እናም የገጠር ዕደ ጥበባትን በማሳደግ፣ ትናንሽ ከተሞችን የመለስተኛ ማቀነባበሪያዎችና የኢንዱስትሪ ማዕከላት በማድረግ፣ ወዘተ. በዚህ በእርሻ ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረውን ሕዝብ መቀነስ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የመሬት ፖሊሲውን በድጋሜ ማጤን ግድ ይሆናል፡፡ ‹‹መሬት መሸጥ መለወጥ የሚቻለው በኢሕአዴግ መቃብር ላይ ነው›› የሚለውን ደረቅ መከራከሪያ ግንባሩ ሊከልሰው ያስፈልጋል፡፡ ቢያንስ እንደ ወዳጁ ቻይና በከፊል መሬት የሚሸጥበትንና የሚለወጥበትን መንገድ ማመቻቸት፣ ለዚህ የሚሆን ጠንከር ያለ የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ፖሊሲ ቢሻሻል ሊኖረው የሚችለው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ብዙ መሆኑ ሊታመንበት ይገባል፡፡ ኢሕአዴግ ለሚቀጥሉት ዓመታት የሚተገበር ተሃድሶ አደርጋለሁ ሲልም፣ ለዚህ አገሪቱን ለተጣባው ድህነት የሚሆን መሠረታዊ ለውጥ በማምጣት ሊሆን ይገባዋል፡፡

የሕገ መንግሥት ማሻሻያ

የ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት ወደ 22ኛ ዓመቱ እየተንደረደረ ነው፡፡ ይህ ርዕሰ ሕግ ሲፀድቅ የአገሪቱ ሕዝብ 57 ሚሊዮን ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ ደግሞ በወቅቱ ከ15 ዓመት በላይ የነበረው ሕዝብ 51 በመቶ ያህሉ ነው፡፡ ከዚህ መካከል በሕገ መንግሥቱ ረቂቅ ላይ የተወያየው 16 ሚሊዮን ብቻ መሆኑን መንግሥት በተደጋጋሚ ገልጿል፡፡ ይህ ማለት 41 ሚሊዮን ሕዝብ የአሁኑ ሕገ መንግሥት ሲፀድቅ ተሳታፊ አልነበረም ማለት ነው፡፡ ከ1987 ዓ.ም. ወዲህም የሕዝብ ቁጥሩ ጨምሮ 100 ሚሊዮን መድረሱ እየተገለጸ ነው፡፡ በዚህ አኃዝ መሠረት ሰማኒያ አምስት ሚሊዮን የሚጠጋ ኢትዮጵያዊ ባልተወያየበት፣ ባልወሰነበትና ባልተሳተፈበት ሕገ መንግሥት እየተመራ ነው ማለት ነው፡፡ በዚህ አመክንዮ ብቻ አዲሱ ትውልድ ይህንን ሕገ መንግሥት እንደገና እንዲመክርበትና እንዲያሻሽለው፣ የራሴ ብሎም እንዲቀበለው ማድረግ የኢሕአዴግ ወቅታዊ ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡

ከዚህ ከተጠቀሰው ምክንያት ውጪ በራሱ ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻል የሚያስገድዱ ምክንያቶች ብዙ ናቸው ብለው ምሁራንና ፖለቲከኞች ይሞግታሉ፡፡ በተለይ ሙሉ በሙሉ ሕገ መንግሥቱ ከኢሕአዴግ ማኒፌስቶ የተቀዳ መሆኑ ከፖለቲካ ድርጅትም በላይ የሆነ ሰነድ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ ከዚህም ባሻገር ስለተጋነነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት መብት፣ ገደብ ስላልተደረገለት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን ዕድሜ፣ እስካሁን ድረስ እያጨቃጨቀ ስላለው ብሔር ተኮር ፌዴራሊዝም፣ የመገንጠልና ራስን በራስ የማስተዳደር መብት፣ የመሬት አጠቃቀም ግዴታዎች፣ ወዘተ. አንኳር የውይይት አጀንዳዎች ሆነው ሕገ መንግሥቱ ላይ ድጋሜ ትኩረት (Reconsideration) ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ለዚህም ሕዝቡም ሆነ የፖለቲካ ድርጅቶች በግልጽ ውይይትና ክርክር ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ ይህንን ለማድረግ ግን ግንባሩ ቅድሚያ ፈቃደኝነቱን ለአደባባይ አውጥቶ ሊያሳይ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ሀብት (Resource)፣ መዋቅርና ተቋማት ደግሞ ከ1987 ዓ.ም. በላቀ ሁናቴ አሉ፡፡ በመሆኑም ቢያንስ 50 በመቶውን ሕዝብ ማወያየት ይቻላል ማለት ነው፡፡

በአጠቃላይ ኢሕአዴግ አንዳንድ ከፍተኛ አመራሮቹን በእስር፣ በጡረታ፣ በዝቅተኛ ሹመት፣ ከኃላፊነት በማንሳት፣ ወዘተ. ገለል አድርጎ ሳያበቃ ፖለቲካዊና ሥር ነቀል ለውጥ (Fundamental POlitical Reformation) አድርጎ ከላይ በተጠቀሱት ሐሳቦችም ላይ ሆነ በሌሎች መርሆዎች ላይ ግብልጥልጥ ያለ መልክ ይዞ ሊመጣ ይገባዋል፡፡

ማነው ተሃድሶ የሚያደርገው?

በአንድ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያቶች ተሃድሶ ወይም ለውጥ ይደረጋል፡፡ በአበዳሪዎች፣ በለጋሾች፣ በወዳጅ አገሮች፣ በውጭ ጠላቶች፣ ወዘተ. ግፊት የሚካሄደው ተፅዕኖው ውጫዊ ነው፡፡ በሕዝብ ፍላጎት፣ በፖለቲካ ድርጅቱ ፖሊሲዎች ማርጀት፣ በአመራሮች ድክመትና ግለኝነት፣ በአመራሮች አለመግባባት ወዘተ. ጊዜ የሚካሄደው ተሃድሶ ደግሞ ውስጣዊ ምክንያቶች የሚወልዱት ነው፡፡ ኢሕአዴግ ለተሃድሶ እጁን እንዲሰጥ ያደረገውም ይኼው ሁለተኛው ምክንያት ነው፡፡ በፖለቲካ ተሃድሶ ወቅት አስጊው ነገር ቀውስ ነው፡፡ በተለይ ፖለቲከኞቹ አመለካከታቸውን ወደ ደኅንነት ተቋማቱና ጦር ሠራዊቱ ካወረዱት ሊከፋፍሉትና ለአገርም አደጋ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ፕሮፌሰር አሌክስ ዲ ዎል “Upperhand” የሚለው አንድ ተደማጭ ግለሰብ ወይም ቡድን ሊኖር ግድ ነው፡፡ ልክ እንደ ቻይናው ዴንግ ዓይነት፡፡

የ1993 ዓ.ም. ተሃድሶ ያመጣው ለውጥ ምንም ይሁን ምንም አገሪቱን ወደ ቀውስ አለመውሰዱ ግን በብዙ ሃያሲያን ተወድሷል፡፡ ለዚያ ለውጥ የአቶ መለስ ክንድ ጠንካራ ስለመሆኑ አያከራክርም፡፡ ጥያቄው እንዲህ ያለውን ተሃድሶ ኮሽ ሳይል ማፍረጥረጥ የሚችል አካል አለ ወይ የሚለው ነው፡፡ የአቶ ኃይለ ማርያም መንግሥት እንዲህ ያለውን ዕርምጃ በራሱ ላይ እንዳይወስድ የሚያደርጉት ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ አንደኛው ለ1993 ዓ.ም. የተሃድሶ ፖሊሲዎች አብዝቶ ታማኝ መሆኑና ይህንንም የመለስ ራዕይ (Legacy) አድርጎ መቀበሉ ነው፡፡ ሁለተኛው ልምድ ማነስ ነው፡፡ አቶ መለስ በተሃድሶ ረገድ ተግባራዊ ልምድ ነበራቸው፡፡ በ1969 ዓ.ም. ሕንፍሽፍሽ ድርጅቱን ሊበትነው ሲል በቦታው ነበሩ፡፡ በ1977 ዓ.ም. ድል ባደረጉበት መድረክ መሪ ተዋናይ ሆነው አጠናቅቀዋል፡፡ ከዚያም ባሻገር በደኅንነት መሥሪያ ቤቱም ሆነ በጦሩ፣ በድርጅቱ አባላትም ሆነ በግንባሩ ውስጥ ስማቸው እየጎላ በመጣ ወቅት በ1993 ዓ.ም. የተካሄደው ተሃድሶ በእሳቸው የበላይነት እንዲያበቃ ግድ ሆነ፡፡

እንዲህ በሚለው አኳኋን አቶ ኃይለ ማርያምም ሆኑ ካቢኔዎቻቸው በአብዛኛው ከ1993 ዓ.ም. ተሃድሶ በኋላ የመጡ ፖለቲከኞች በመሆናቸው ጉዳዩ ሊወሳሰብባቸው ብሎም ሊከብዳቸው ይችላል፡፡ የሀቀኛ ፖለቲካ (Genuine Politics) አቀንቃኝ ለሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ የሴራ ፖለቲካን (Political Intrigue) አብዝቶ የሚፈልገው የተሃድሶ ትወራ ሊከብዳቸው ይችላል፡፡ ሌላኛው አጠራጣሪ ጉዳይ ተሃድሶው የሚያመጣውን በጎም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ሙሉ በሙሉ መቀበል የሚችል የኢሕአዴግ አባል፣ አመራር፣ የመንግሥት ባለሥልጣንና ተቋም የመኖሩ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ አቶ ኃይለ ማርያም ልምድ ያላቸውን ጡረተኛ ባለሥልጣናትና አማካሪዎቻቸውን እንዲጠቀሙ የሚገደዱበት ምክንያት ብዙ ሊሆን ይችላል!!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው yayeshime02@gmail ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...