Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እንዲህ ይነገረን እንጂ!

እነሆ መንገድ። ቅደም ተከተል በጠፋው የተወለጋገደ አረማመድና ሠልፍ ለሻሞ ጉርሻ እንደሚራከብ የአራዊት መንጋ፣ መንገዱን ሥርዓት አላውቀው ብሏል። “እናንተ ‘ነውር ነው’ ማለት ቀርቶ ነውር የሚሉት ቃል ራሱ ተረሳ እኮ፤” ትላለች ከሾፌሩ ጀርባ ነጠላዋን የምትጨምቅ ሴት። “ኧረ ምንድነው? የእኔ ታክሲ ሳፋ ነው እንዴ? ደግሞ ብለው ብለው ልብስ ይጨምቁ ጀመር? እርስዎ ሴትዮ ግን ለምንድነው የማይተውኝ?” ወያላው ያለቃቅሳል። “ዝም በል። ‘ሲሉ ሰምታ…’ አለ ያገሬ ሰው። ደግሞ በገዛ ታክሲዬ ስትል ነው የሰማውህ? ነውረኛ…” ብላ ስታበቃ፣ “ናማ ልጅ አጫምቀኝ፤” እያለች አጠገቧ ወደተሰየመ ወጣት ዞረች። “እ?” ወጣቱ ደንግጦ ያያታል። “ይኼውልህ ዛሬ ዮሴፍ ቀብሬያት መጣሁ። አብሮ አደጌ ቀድማኝ ሞተች። ታዲያ ዝናቡ እንዲችው እላዬ ላይ አያልቅ መሰለህ?” ስትለው ወጣቱ “ታዲያ አይጠለሉም ነበር?” አለ የግዱን ሊያጫምቅ በእጁ የያዘውን ቦርሳ ቦታ እየሰጠ።

ወያላው በተቀመጠበት በግልምጫ ሲያፈጥበት እኛ ታዝበን እንስቃለን። ‘ጨማቂው ሳይሆን አጫማቂው ባሰኝ’ አለ ወያላው ሲል አንድ ተሳፋሪ ይተርታል። “ምነው ታዲያ መጠለያ አልነበረም?” አጫማቂው ወጣት ሴትዮዋን ማስወራቱን ቀጠለ። “አይ ልጄ እኛ እንደ እናንተ መሰልናችሁ? የዘመኑ ልጆች ለዝናብ ትሮጣላችሁ። ለመብረቅ ትሮጣላችሁ። ለንፋስ ትሮጣላችሁ። ምነው ግን ለሜዳልያ፣ ለሞገስ፣ ለሥርዓት፣ ለክብር መሮጥ ሰነፋችሁ?”  ብላ ስታፈጥበት፣ “እኔ የማውቀው ስለራሴ ብቻ ነው፤” አለ ደንግጦ። “ጎሽ። በላ ስለራስህ የምታውቀውን ንገረን፤” በሚያጉረመርም ድምጿ ስታንባርቅበት፣ “ለጊዜው ግምገማ ላይ ነኝ። ግምገማውን ስጨርስ መግለጫ ብሰጥ አይሻልም?ሰ” ብሎ ወጣቱ ፈገግ አለ። ‘‘ምን ያስቅሃል?” ብላ መልሳ ደግሞ፣ “ሟቿ ወዳጄም ልክ እንደ አንተ ግምገማ ላይ ውላ ግምገማ ላይ እንዳደረች ነበር። ግን ምን ዋጋ አለው ሞት ቀደማት፤›› ስትለው ልጁ ደንግጦ ‘አውርዱኝ’ ማለት ነበር የቀረው። ሳይቀደሙ የሚቀድሙ ብፁአን ወይስ ብልሆች የሚባሉት?

ጉዟችን ተጀምሯል። በቀዳዳ ጫማው ከወይዘሮዋ ነጠላ የተጨመቀው የዝናብ ውኃ ሰርስሮ ገብቶ ቢከረስሰው፣ “እምዬ ሉሲ ድረሽ፤” ብሎ ወያላው ዘሎ ፈረጠ። “ኧረ አረጋጋው። ጉንዳን ቆነጠጠኝ ብለህ ሦስት ሺህ ዘመን ያንቀላፋችውን የጠራህ ጥይት ቢመታህ ማንን ልትጠራ ነው?” አለው መሀል መቀመጫ ላይ አጠገቤ የተሰየመ ጎልማሳ። “ጥይት ሌላ ጉንዳን ሌላ። ብሎ የጫማውን ሚስጥር ደበቀን። ልክ የከተማችን መስታወት ዓይን ሕንፃዎች ጉራንጉሩን ሠፈራችንን እየደበቁ እንደሚያወዛግቡን። “ውይ! የሉሲን ነገር አታንሱብን እባካችሁ። እኔ መች አውቄ። ገና ዛሬ እኮ ነው የምሰማው። እኔ ክልትው ልበል…፤” እያለ መጨረሻ ወንበር የተሰየመ አላጋጭ ሙሾ ማውረድ ጀመረ። “ምን ተባለ ደግሞ?” ብላ ጠየቀችው አጠገቡ የተሰየመች ቀዘባ።

“አልሰማሽም እንዴ? እምዬ ሉሲ ከዛፍ ላይ ወድቃ መሞቷ በጥናት ተረጋገጠ እኮ። ያው ዘገባው አሟሟቷን አውርቶ ለቅሶውን ‘ላሽ’ አለው፤” ሲል ተሳፋሪው በሳቅ አውካካ። ተሳቀልኝ ብሎ ወጣቱ ቀጠለ። “በነገራችን ላይ በጥናት ባይረጋገጥም ሉሲ ልክ እንደወደቀች ወዲያውኑ ሕይወቷ አላለፈም። እኔን እኔን እያለች ለራሷ ስታለቅስ ባለቤቷ ደርሶ ነበር። ሲያያት እሪ አለ። ድረሱልኝ  ቢል የከበበው ዛፍ ነው። እነሆ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው አሉ በዚህች ምድር እሪታ የማይደመጠው። ከከበቡት ዛፎች አንዱም እሷን የጣለው ነው፡፡ ቁልቀል እያየው ይወዛወዛል። ‘ምን አገኘሽ?’ አላት። ‘ዛፍ’ አለችው። ‘በል እኔ መሄዴ ነው። አደራዬን ተቀበል። ዛፍ የሚባል እፅዋት ከዚህች ምድር አጥፋ፤’ አለችው። እነሆ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በዚህች ታላቅ ምድር ትልቅ ሰውና ትልቅ ዛፍ አልበረክት አለ እላችኋለሁ፤” ሲል ለፈጠራ ክህሎቱ ተጨበጨበለት። ለቆረጣና ለጭብጨባ የምንቸኩለውን ያህል ነገር ለማጣራት የምንዘገየው ግን ለምን ይሆን?!

ጉዟችን ቀጥሏል። መጨረሻ ወንበር የተሰየመውን ወጣት ሚቲዎሮሎጂ በጥሞና ስታዳምጥ የቆየቸው ቀዘባ ጭቤጨባው ጋብ እንዳለ፣ ‹‹ታዲያ ይኼ ዛሬ ከምሠራው ሥራ ጋር አይጋጭም? ማለቴ ሉሲ ከዛፍ ወድቃ ሞተች። ዛፍም ከምድሪቷ ላይ ተመናመነ። ሉሲም ሆነ ዛፎች ከምድሪቷ ላይ ለረጅም ጊዜ ተረስተው ኖሩ። ዛሬ ሉሲ ተገኘች። ዓለም አወቃት። ልክ ችግኝ ተከላ ላይ መረባረብ በጀመርንበት ዘመን ላይ ደግሞ ሉሲን የገደላት ዛፍ መሆኑ ታወቀ። ይኼ እንዴት ነው እርስ በርሱ አይጋጭም?›› ስትል አጠገቤ የተሰየመው ጎልማሳ፣ ‹‹ኧረ በፈጠረሽ ንቂ። ሙሉውን ታሪክ ቀጥታ ነው እንዴ የወሰድሽው? እኛ እኮ ምፀት ላይ ነን፤›› ሲላት ለቀስተኛዋ ቀበል አድርጋ፣›› እናንተዬ ግራ ገባን እኮ? የማንን ሌጋሲ እንደምናስቀጥል አላውቅ ብለን ያደገውን ስንቆርጥ የማያድገውን ስንኮተኩት መሀል ላይ ቀረን። ወይ ዘንድሮ?›› ብላ ከንፈር መጠጠች። ‹‹ቀና ብዬ ባየው ዛፍ ይተነፍሳል፣ ትንፋሼ ሲቆረጥ የሚኖር መስሎታል’ አለች አሉ ሉሲ። እናም አንዳንድ ሰዎች አሉ ሕዝብ በሚያዋጣላቸው ካርቦን ዳይኦክሳይድ እንደሚኖሩ ረስተው በመወዛወዛቸው የሚቀጥሉ። አይገርሙም?›› ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመች ስታሸሙር፣ ‹‹15 ዓመታት ወደኋላ ሄደው መጡ። ከዚህ በላይ ምን ያድርጉ ነው የምትይው?›› አላት ከአጠገቧ። ‹‹እሱን እኮ ነው የምልህ? በመወዛወዝና ፀንቶ በመቆም መሀል ያለው ልዩነት አልገባቸው ያሉ በዝተዋል። ቃል የእምነት ዕዳ ዘፈን ሆኖ ቀረ…›› ብላው ቆዘመች። እንዴት ነው ግን እንዲህ ሰው ሁሉ በየመንገዱ እየቆዘመ ዓመት የሚያረጀው ያስብላል?

ወያላችን አሥር ጊዜ እግሩን ከጫማው ብቅጥልቅ እያደረገ ሒሳብ ለመሰብሰብ እንደተራበ ዘንዶ ይጥመለመላል። ይኼኔ ወደ ቀኝ አስቦ ወደ ግራ ሲዞር አንድ እጁ ተስፈንጥሮ ጋቢና የተሰየሙትን አዛውንት አናት ዳበሳቸው። ‹‹ዘራፍ!›› ብለው ሲዞሩ እጅ ነው። ‹‹ምን አደረግኩህ አንተ? በዚህ ሰው በላ በሆነ ወር የምታስደነግጠኝ? ዘመን ሳልሻገር እንድቀር ነው?›› አሉት። ወያላው ደንግጦ እየደጋገመ ይቅርታ ሲላቸው፣ ‹‹በቃ! በቃ! ይቅርታ አንዴ ነው። ምሕረት ነው ለዘለዓለም። የዘመኑ ልጆች በአፋችሁ ይቅርታውንም ምሕረቱንም አረከሳችሁት፤›› ሲሉ ነጠላዋን ገመድ ዘርግታ እላያችን ላይ ማስጣት የቀራት ቴአትረኛ ሴትዮ፣ ‹‹አይ አባቴ ልፉ ቢልዎ እኮ ነው። ምኑን አውቀውት ደግሞ የዘንድሮ ልጆች። ሳያነቡ ይጽፋሉ፣ ሳያዳምጡ ይመልሳሉ፤›› አለቻቸው። ‹‹እህ እሱንማ ታዲያ መች እነሱ ብቻ ሆኑ እንደፋሽን የያዙት። እኛ ትልልቆቹ አልባስንም? ማንን አይተው ማንን ሰምተው አድገው ይመስልሻል አገሩ እንዲህ የእብድ የመሰለው?›› አሏት።

የምትለው አታጣም ቀጠለች። ‹‹ከዚህ በላይ እንዴት እንሁን እኛ? ወልደን አሳደግን። ያውስ ያልወለዱ የታደሉ በሚባልበት ዘመን፡፡ ሕግና ሕገ መንግሥት እንዲህ እንዳሁኑ ቢያንስ በመጽሐፍ ታትሞ በማይቀነቀንበት ዘመን አምጠን ወልደን አሳደግን? ዛሬ እነሱ ናቸው ከአባቶቻችን እንሻላለን የሚሉት። በምን አይሉኝም? እኛ ድሮ መንደር ለመንደር ቡና ላይ ነበር ወሬ የምናነፈንፈው። እነሱ ግን ዛሬ አንድ ሥፍራ ቁጭ ብለው ምንድነው ሚሉት በዚህ በጎልጉልና በፌስቡክ ውኃ የማይቋጥር ሠልፍ በመጠራራታቸው፣ የወሬና የስድብ እቁብና እድር በመመሥረታቸው እንጂ ሌላማ ሙያ አላየንም፤›› ብላ አንድ በአንድ ስትገላምጠን ወጣቶቹ አውራ ጣታቸውን እያሳዩ ‘ላይክ’ አስቆጠሯት። ዘንድሮ በ‘ላይክ’ ብዛት በትረ ሥልጣን የሚጨበጥ ቢሆን ኖሮ መቼም ጉድ እናይ ነበር!

ጉዟችን ወደ መገባደዱ ነው። አዛውንቱ ለሾፌራችን አንድ ታሪክ እያጫወቱት ነው። መጨረሻ ወንበር የተሰየሙ ቅብጥብጥ ወጣቶች ‘የእንጀራ ልጅ ስሜት ተሰማን’ ባሉት መሠረት ጮክ ብለው ታሪኩን እያጫወቱን ነው። በጥንታዊት የኩሽ ኢትዮጵያ ዘመን ሰብታህ የተባለ ንጉሠ ነገሥት ጽሑፍ ማጻፍ ይጀምራል። ጽሑፉን የዛፍ ቅርፊት ልጥ ላይ ነበር የሚያጽፈው። እንደ ዛሬ ዘመን ጋዜጣ መሆኑ  ነው። የጠፋን፣ የሞተን፣ የሸፈተን ሰው ማሳወቂያ፣ እንዲሁም ንጉሡ አዋጅ ሲያወጣ ለሕዝቡ ማብሰሪያ እንዲሆን ብሎ ነው። ታዲያ አንድ ቡርኔ የሚባል ሰው እንዴት ዛፍ የሰው ቋንቋ ሊናገር ይችላል ብሎ አመፀበት። የለም ይህ ወደ ሥልጣኔ የሚመራ ሥልት ነው። ገንዘብ ማካበትና መኩራት ብቻ የሰው ልጅ ባህሪ አይደለም። እየተሻሻልን ለመሄድ እንዲህ በሥነ ጽሑፍ ሥልጣኔ መበርታት አለብን ቢለው አሻፈረኝ ብሎ ሸፈተበት። ቆይቶ ዘመን አልፎ የዛፍ እንጨት ልጥ ላይ ከመጦመር የበሬና የበግ ቆዳ ላይ መጦመር ሲጀመር ቦርኔ የሚባለው የንጉሡ ተቃዋሚ ባሰበት። ምን ቢል ጥሩ ነው?›› ሲሉ አፉን ከፍቶ ይሰማቸው የነበረው ተሳፋሪ በአንድ ድምፅ፣ ‹‹ምን አለ?›› አላቸው።

‹‹ያለውማ በግ ባ ማለት እንጂ ሌላ የሰው ቋንቋ በምን አውቃ ትናገራለች? ይህ የጽሑፍ ነገር ካልቆመ ሽፍትነቴን አልተውም አለ። ታሪኩ መቼም ብዙ ነው። ኋላ አሶራውያን ይኼን የኩሽ የሥነ ጽሑፍ ግኝት ወስደው አስፋፍተውት ይኼው ዛሬ ዓለም ሥነ ጽሑፍ የጀመረው እዚያ ነው ብሎ ተስማምቷል። ዛሬም ሲታየኝ አንዳንዱ አካሄዳችን ልክ እንደ ቦርኔ ይመስለኛል። ቦርኔ ያስብ የነበረው ሥልጣኔን እንጨትና በግ ያስተምራሉ እንዴት ትሉኛላችሁ ነው። አያችሁ ያሰበው እሱ ቀጥታ ነው። መስሚያ ጆሮ፣ መመልከቻ ዓይን፣ ማመዛዘኛ ልቦና ይስጥህ ያለው ንጉሡ ያኔ ለእሱ ብቻ ይመስላችኋል?›› ብለው አበቁ። ወያላችንም ‘መጨረሻ’ ብሎ ሸኘን። እንዲህ ይነገረን እንጂ! መልካም ጉዞ!   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት