Friday, December 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቶዮታ አካል የሆነው ቶዮታ ቱሾ በጂኦተርማል ኃይልና በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ መስክ የመግባቢያ ስምምነቶች ፈረመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በብርሃኑ ፈቃደ፣ ናይሮቢ ኬንያ

የቶዮታ ግሩፕ ኩባንያ አካል የሆነውና የንግድ ዘርፉን የሚመራው ቶዮታ ቱሾ ኩባንያ፣ በኢትዮጵያ የጂኦተርማል መስክ ለመሰማራት እንዲሁም ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ የሚውሉ ማሽነሪዎች ማምረቻ የማቋቋም ፍላጎት አሳየ፡፡ በመንግሥትና በኩባንያው መካከል የመግባቢያ ስምምነት በኬንያ ተፈርሟል፡፡

ከ23 ዓመታት ቆይታው በኋላ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በናይሮቢ ከተማ ሲካሄድ በነበረውና ለሦስት ቀናት በቆየው፣ ስድስተኛው የቶኪዮ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ለአፍሪካ ልማት (ቲካድ) ጉባዔ፣ ከተገኙት አራት ሺሕ ያህል የጃፓን ልዑካን እንዲሁም ከ100 በላይ ኩባንያዎች መካከል ቶዮታ ቱሾ አንዱ ነው፡፡ ኩባንያው ቀደም ብሎም በኢትዮጵያ የቶዮታ መኪኖችን በማቅረብ የሚንቀሳቀስ ሲሆን፣ ሂሮኪ የተባለውና በ300 ሺሕ ዶላር ወጪ የተቀላቀለው የቆዳ ውጤቶች ፋብሪካ ከሚጠቀሱት መካከል ይገኙበታል፡፡

የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነሩ አቶ ፍጹም አረጋ ከቶዮታ ቱሾ ኩባንያ ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር በናይሮቢ ሁለት የመግባቢያ ስምምነቶችን ፈርመዋል፡፡ አንደኛው በጂኦተርማል መስክ ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት መስክ ለመሠማራት ቶዮታ ቱሾ ያለውን ፍላጎት ያሳየበት ነው፡፡

በአገሪቱ የጂኦተርማል ኃይል ማመንጨት ተግባር ላይ ሌሎች ኩባንያዎችን በመቅጠር እንደሚሠራ ለሪፖርተር የገለጹት የኩባንያው የመሠረተ ልማት ክፍለ የአፍሪካ ምድብ ኃላፊ ታካዩኪ ሚሃራ ናቸው፡፡ ኩባንያው በንግድና ኢንቨስትመንት መስክ የሚሠራ ሲሆን፣ ሐሳቡም በቁፋሮና በፍለጋ ሥራ የተሰማሩ ኩባንያዎችን በመቅጠር ፕሮጀክቶች ላይ መሰማራት ነው፡፡ በአገሪቱ በተለይ በጂኦተርማል መስክ እስከ 5000 ሜጋ ዋት ኃይል ለማመንጨት የሚያስችል አቅም አለ፡፡ ይህንን ያህል የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችሉ አካባቢዎችን ማጥናት የመጀመሪያ ተግባር መሆኑን ሚሃራ አስታውቀዋል፡፡ የቁፋሮ ሥራዎቹ በአብዛኛው በአገሪቱ የስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች ላይ በማተኮር እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡ በጂኦተርማል ወይም በእንፋሎት ኃይል መስክ ኢትዮጵያ ያላት አቅም ከኬንያ ቀጥሎ በአፍሪካ ትልቁ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ኬንያዎች ከ7,000 በላይ የጂኦተርማል ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም አላቸው፡፡

እስካሁን ኢትዮጵያ በመሬት የላይኛው ክፍል ላይ ያተኮረ ወይም የሰርፌስ ጥናት ደረጃ ላይ ትገኛለች ያሉት ሚሃራ፣ ምናልባትም ሌሎች አዳዲስ የጂኦተርማል ኃይል ማመንጫ ጉድጓዶችን ለማጎልበት የሙከራ ቁፋሮ ሥራዎች ከዚህ በኋላ በብዛት ሊጀመሩ እንደሚችሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡ በመጠናቸው ትልቅነት ወይም አነስተኛነት ገና እርግጠኛ መሆን ያልተቻለባቸው የጂኦተርማል ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች እንደሚቋቋሙም እምነት አላቸው፡፡

እስካሁን አልቶ ላንጋኖ በተባለው አካባቢ የጃፓን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) ከዚህ በፊት ባስጠናው መሠረት ከአልቶ ላንጋኖ የ70 ሜጋ ዋት ጂኦተርማል ኃይል ማመንጨት የሚያስችል አቅም እንዳለ ተረጋግጧል፡፡

ይህ በመሆኑም እስካሁን ሁለት የሙከራ ጉድጓዶች ተቆፍረው አምስት ሜጋ ዋት ኃይል እየመነጨ ይገኛል፡፡ ይሁንና ለዚህ ፕሮጀክት የሚያስፈልጉ ማሽነሪዎችንና ሌሎችም ግብዓቶችን ለማቅረብ ቶዮታ ቱሾ ኩባንያ ፍላጎት እንዳለው ሚሃራ አስታውቀዋል፡፡ ይህም ቢሆን ገና በሒደት ላይ ያለ ነው፡፡ ይሁንና በአዳዲስ የጂኦተርማል ቁፋሮ ጣቢያዎች ላይ ለመሥራት ቶዮታ ቱሾ መዘጋጀቱን፣ ይሁንና ግን የትኞቹ ሳይቶች የተሻለ ዕምቅ አቅም እንዳላቸው ገና የሚታወቅ ነገር እንደሌለ ሚሃራ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ስፌት ኢንዱስትሪ መስክም ልዩ ልዩ ማሽነሪዎችን ለመገጣጠም፣ ለማደስና መለዋወጫዎችን ለማቅረብ የሚያስችል ተቋም፣ ቶዮታ ቱሾ እንደሚመሠርት ኮሚሽነሩ አቶ ፍጹም አረጋ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በመጋቢት ወር ገደማ የኩባንያው ልዑካን ወደ አዲስ አበባ ተልከው የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪውን ገምግመዋል፡፡ በወቅቱ በተደረገው ጉብኝትም ዘርፉ ተጠንቶ አገሪቱ ለገበያ ልታውለው የምትችለው አቅም መታየቱን ሚሃራ አስታውሰዋል፡፡ በተደረገው ግምገማም ከፍተኛ ጥራት ያለው ነገር ግን አዋጪ የጨርቃ ጨርቅ እንዲሁም የቆዳ ኢንዱስትሪ መኖሩ በመረጋገጡ ኩባንያው ለእነዚህ ዘርፎች የሚውሉ ማሽነሪዎችንና ፋብሪካዎች ሲተከሉም ሙሉ ለሙሉ ተሳትፎ ለማድረግ እንደሚፈልግ አስታውቋል፡፡ ከዚህ በሻገር በጥጥ መስክም ጥራት ያላቸውን ዝርያዎችን በማቅረብ ለመሥራት ተዘጋጅቷል፡፡ ይሁንና በመንግሥት እጅ የነበሩ ኩባንያዎች እየተሸጡ በመሆናቸው ኩባንያው ከየትኞቹ ጋር መሥራት እንዳለበትም መወሰን ይጠበቅበታል ያሉት ሚሃራ፣ ይህም ቢባል ግን ዘርፉ በአፍሪካ ቀዳሚ እንዲሆን ቶዮታ ቱሾ በማገዝ እንደሚሠራ ጠቅሰዋል፡፡

አቶ ፍጹም እንዳብራሩት ከሆነ፣ ቶዮታ ቱሾ የዋናው የቶዮታ ግሩፕ ኩባንያ አካል የሆነና ራሱን ችሎ የንግድና የኢንቨስትመንት መስኩን የሚመራ ነው፡፡ ኩባንያው በዓመት ከ72 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሽያጭ ገቢ የሚያስመዘግብ ግዙፍ ኩባንያ ነው፡፡

ኩባንያው ለዘርፉ የመደበው ካፒታል፣ ጥናቱን ለማጠናቀቅ የሚፈጅበት ጊዜ፣ ለጥናቱ የሚያውለው ገንዘብ፣ ምን ያህል ሜጋ ዋት ለማመንጨት ፍላጎት እንዳለውና የመሳሰሉት ነጥቦች ላይ ገና ውይይት እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ እስከ 5,000 ሜጋ ዋት ኃይል የጂኦተርማል ኃይል የማመንጨት ዕምቅ አቅም እንዳላት ቢታወቅም፣ በተጨባጭ ምን ያህሉ ሊለማ እንደሚችልም ገና ሰፊ ጥናት እንደሚጠይቅ የቶዮታ ቱሾ ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡

በአፍሪካ ከሚንቀሳቀስባቸው አገሮች መካከል ጎረቤት ኬንያ ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ የቆየ ግንኙነት አለው፡፡ ቶዮታ፣ ኒሳን እንዲሁም ሌሎችም ትልልቅ የጃፓን ኩባንያዎች ማምረቻ ፋብሪካ ገንብተው ሲንቀሳቀሱ ዓመታት አስቆጥረዋል፡፡ በኬንያ ለቆየው የቶዮታ ኩባንያ እንቅስቃሴ አስተዋጽኦ ካደረጉት መካከል አገሪቱ ያላት ወደብ ዋናው እንደሆነ የቶዮታ ቱሾ ኩባንያ የሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ረዳት ኃላፊዋ ሂሮኮ ማጋሪያማ ለሪፖርተር አብራርታለች፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች