Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጃፓን ለመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለአፍሪካ ልማት መመደቧን ይፋ አደረገች

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ከሦስት ዓመት በፊት ከሰጠችው 32 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ 67 ከመቶውን መልቀቋን አስታወቀች

በኬንያ በተካሄደው ስድስተኛው ቶኪዮ ኢንተርናሽናል ኮንፈረንስ ለአፍሪካ ልማት (ቲካድ) ጉባዔ ወቅት፣ ጃፓን በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥ ለአፍሪካ ልማት የሚያግዝ 33 ቢሊዮን ዶላር መመደቧን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ይፋ አደረጉ፡፡ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ መንግሥታቸው ከአሥር ቢሊዮን ዶላር በላይ ሲያቀርብ፣ የጃፓን ኩባንያዎች ቀሪውን ገንዘብ በኢንቨስትመንት መስክ እንደሚያዋጡ አስታውቀዋል፡፡

በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት በጃፓንና በአፍሪካ መንግሥታት መካከል በአፍሪካ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት፣ በአይበገሬ የጤና ሥርዓት ግንባታ እንዲሁም በማኅበራዊ መስክ በተለይም በሰው ኃይል ልማት፣ በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና፣ በአደጋ ሥጋት ቅነሳ፣ በምግብ ዋስትናና በመሳሰሉት መስኮች ላይ በማተኮር በአንድ ድምፅ የተስማሙበትን የናይሮቢ ውሳኔ (ዲክላሬሽን) የተባለው ስምምት አጽድቀዋል፡፡

በዚህም መሠረት በእነዚህ መስኮች ኢንቨስት ይደረጋል የተባለው 33 ቢሊዮን ዶላር፣ ከጃፓን ተለቆ በአፍሪካ ተግባር ላይ ከሚውልባቸው መካከል ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ጥራት ያለው የመሠረተ ልማት ግንባታ ነው፡፡ እስካሁን ከታወቁ የገንዘብ መጠኖች መካከል ከአሥር ቢሊዮን ዶላር በላይ ለዚህ ዘርፍ መመደቡን ለመረዳት ተችሏል፡፡ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለንግድ እንቅስቃሴና ማስፋፊያ፣ 1.8 ቢሊዮን ዶላር ለአየር ንብረት ለውጥ፣ ለተፈጥሮ አደጋዎች መከላከያ፣ 500 ሚሊዮን ዶላር ለምግብ ዋስትና፣ ለፀጥታና መረጋጋት 500 ሚሊዮን ዶላር፣ 330 ሚሊዮን ዶላር ለአስተኛና መካከለኛ ዘርፍ ድጋፍ የሚውል ገንዘብ በሦስት ዓመት ውስጥ ለአፍሪካ እንደሚለቀቅ ይጠበቃል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አቤ በንግግራቸው ይፋ እንዳደረጉት የሚቀጥለው ቲካድ ጉባዔ ወይም ቲካድ ሰባት በጃፓን እስከሚካሄድበት ጊዜ ድረስ አፍሪካ 33 ቢሊዮን ዶላር ያህል ከጃፓን በብድር፣ በዕርዳታና በቴክኒካል ድጋፍ መልክ እንድታገኝ ይደረጋል፡፡

33 ቢሊዮን ዶላሩ ከላይ ከተጠቀሱት ዋና ዋና ሥራዎች መካከል 2,000 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለመገንባት ይውላል፡፡ ከዚህም ባሻገር ሦስት ሚሊዮን አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የጂኦተርማል ኃይል ማመንጫዎች እ.ኤ.አ. እስከ 2022 ተግባራዊ እንደሚደረጉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቤ አስታውቀዋል፡፡ እስካሁን የነፃ ትምህርት ዕድል ያገኙትን ከ500 በላይ ተማሪዎች ጨምሮ በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት 1,500 በ‹‹አፍሪካ ቢዝነስ ኤዱኬሽን – አቤ ኢኒሼቲቭ›› ተጠቃሚ እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡

ከአፍሪካ አገሮች ውስጥ በጃፓን ድጋፍ ለውጥ እያሳዩ ካሉ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ በካይዘን አማካይነት ስሟ ተጠቅሷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ በስም ጠቅሰው ያስተዋወቁት ፒኮክ ጫማ ፋብሪካ፣ 17 ጊዜ የካይዘን ሥልጠና አግኝቷል፡፡ ፋብሪካው ቀድሞ በቀን 500 ጥንድ ጫማ ያመርት ነበር ያሉት አቤ፣ ከካይዘን በኋላ በቀን 800 ጥንድ ጫማ በማምረት የ60 ከመቶ ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል፡፡ በጠቅላላው በአፍሪካ የ30 ከመቶ የምርት ጭማሪ በካይዘን የማኔጅመንት ፍልስፍና አማካይነት እንዲመጣ የማድረግ ዓላማ እንደተወጠነ ይፋ አድርገዋል፡፡

ሁለት ሚሊዮን ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋን ፕሮግራሞችን በአፍሪካ መተግበርም የቲካድ ስድስት የሦስት ዓመታት ተልዕኮዎች ከሰነቋቸው መካከል እንደሚመደቡ ጠቅላይ ሚኒስትር አቤ አስታውቀዋል፡፡ 

ከጥቂት ሳምታት ቀድሞ በጃፓን ኢ ሺማ የተካሄደው የቡድን ሰባት አገሮች በርካታ ነጥቦች ላይ ትኩረት ማድረጉን፣ በዚህም ከ200 ቢሊዮን ዶላር ለዓለም ታዳጊ አገሮች ጃፓን መመደቧን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ የአፍሪካ ድርሻ 33 ቢሊዮን ዶላር ሆኗል፡፡

በጃፓን ዮኮሃማ ከተማ የተካሄደው አምስተኛው የቲካድ ጉባዔ ወቅት ጃፓን ለአፍሪካ ልማት 32 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብታ እንደነበር ይታወሳል፡፡ አምስት ዓመታት ሊሞላው ሁለት ዓመታት የሚቀሩት የአምስተኛው ቲካድ ጉባዔ አፈጻጸምን በማስመልከት የጠቅላይ ሚኒስትር አቤ ቃለ አቀባይ፣ በጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥም የፕሬስ ኃላፊ በመሆን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዘርፉን የሚመሩት ያሱሂሳ ካማሙራ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ከ32 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ 14 ቢሊዮን ዶላሩ የኦፊሴል ዕርዳታ ስም የሚለቀቅ መሆኑንም ካማሙራ ጠቅሰዋል፡፡

በመሆኑም በአምስተኛው ጉባዔ ወቅት ቃል ከተገባው 32 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ እስካለፈው ዓመት 67 ከመቶው ወይም 21.5 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነው ገንዘብ መለቀቁን አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ አምስተኛው የቲካድ ጉባዔ ለአምስት ዓመታት ሲካሄዱ ከቆዩትና ላለፉት 20 ዓመታት በጃፓን ሲካሄዱ ከቆዩት የመጨረሻው ነው፡፡ ከዮኮሃማ ጉባዔ በኋላ ግን በየሦስት ዓመቱ እንዲካሄድ፣ በየተራ አንድ ጊዜ በጃፓን ሌላ ጊዜ በአፍሪካ እንዲካሄድ የአፍሪካ አገሮች በጠየቁት መሠረት በኬንያ የተካሄደው የመጀመሪያው ነው፡፡

እ.ኤ.አ. በ1993 በጃፓን መካሄድ የጀመረው የቲካድ ጉባዔ ሲጠነሰስ ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ ዓለም ፊቱን ከአፍሪካ በማዞሩ ምክንያት ጃፓን ይህንን ለመቀየር ማካሄድ የጀመረችው እንደሆነ ጃፓናውያኑ ይናገራሉ፡፡ ‹‹አፍሮ-ፔሲሚዝም›› እየተባለ የሚታወቀውና በአፍሪካውያን ላይ ተስፋ የቆረጠውን ዓለም ዳግም ወደ አፍሪካ እንዲመልስ ለማድረግ የተጠነሰሰው ቲካድ ቀስ በቀስ ዓላማውን ከመምታት አልፎ ከሌሎች እንደ ቻይና፣ ህንድና አሜሪካ ካሉ አገሮች ውድድር እየገጠመው እንደመጣ ጃፓኖች ይናገራሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች