Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹የክረምት ትራፊኮች››

‹‹የክረምት ትራፊኮች››

ቀን:

መስቀልያ መንገዱ ላይ ዩኒፎርም ለብሰው ከቆሙት አራት ወጣቶች መካከል አንደኛው እጁን ከወዲያና ወዲህ እያወናጨፈ በአካባቢው ያለውን የትራፊክ ፍሰት ይቆጣጠራል፡፡ ቀልጣፋነቱን ለተመለከተ በሥራው ዓመታት የቆየ እንጂ ገና ጀማሪ አይመስልም፡፡ ተሽከርካሪዎችና እግረኞች ደንቡን ጠብቀው እንዲተላለፉ አስችሏቸዋል፡፡ ሌሎቹ ግን አልፎ አልፎ ተሽከርካሪዎችን በማስቆም እግረኞች እንዲተላለፉ ከማድረግ ባለፈ ብዙም የሚያደርጉት አልነበረም፡፡ በተለይም በአሥራዎቹ አጋማሽ ላይ የሚገኙት ሁለቱ በጎ ፈቃድ ትራፊኮች ትከሻ ለትከሻ ተቃቅፈው አላፊ አግዳሚውን እያዩ ነበር፡፡

ትምህርት ቤቶች በሚዘጉበት ወቅት ተማሪዎች የዕረፍት ጊዜያቸውን በተለያዩ ሁነቶች ያሳልፋሉ፡፡ አንዳንዱ ቤተዘመድ ለመጠየቅ ከከተማው ርቆ ሲቆይ፣ ሌሎቹ የተለያዩ የክረምት ትምህርቶችን ይማራሉ፣ እንደዚሁም ደግሞ በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ተግባራት ላይ በመሰማራት ማኅበረሰቡን ለመርዳት የሚንቀሳቀሱም አሉ፡፡ ተማሪዎቹ በበጎ ፈቃደኛነት ከሚሳተፉባቸው የሥራ መስኮች መካከል ትራፊክ አገልግሎት ይጠቀሳል፡፡

የዘጠነኛ ክፍል ተማሪው ወጣት ተስፋዬ አስማረ፣ በዚህ ክረምት በጎ ፈቃደኛ ትራፊክ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡ የተለያዩ የበጎ ፈቃደኛ ፕሮግራሞች ላይ ተሳትፎ በማድረግ የበኩሉን መወጣት የህሊና ዕረፍት እንደሚሰጠው ይናገራል፡፡ ነፃ አገልግሎት ሲሰጥም ይህ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የበጎ ፈቃደኝነት ተግባራት በተለይም በበጎ ፈቃደኛ ትራፊክነት ተሰማርቶ እንደሚያውቅ ይናገራል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹በዚህኛው ዓመት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተን ነው እየሠራን ያለነው፡፡ ከዚህ በፊት ግን ፍላጎቱ ያላቸው ወጣቶች ዝም ብለን ተደራጅተን እንሠራ ነበር›› ይላል፡፡ ስለ መሠረታዊ የትራፊክ ሕጎች ሥልጠና ወስዶ መሥራት ከጀመረ ሁለት ወራትን አስቆጥሯል፡፡ ቦሌ፣ መስቀል አደባባይና በሌሎች በከተማዋ በሚገኙ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ በሚስተዋልባቸው ቦታዎች እየተዘዋወረ ይሠራል፡፡ በሥራው ለእግረኛ ቅድሚያ የማይሰጡ አሽከርካሪዎች፣ ትዕዛዝ የማይቀበሉ እግረኞች ያጋጥሙታል፡፡ ተመሳሳይ ድርጊት የሚፈጽሙን በሕጉ መሠረት እንዲታረሙ በሚያደርግበት ጊዜም ምናገባህ የሚሉት፣ የሚሰድቡት፣ እንዳሉ ይናገራል፡፡ እሱና መሰሎቹ የሚሰጡትን አገልግሎት በማድነቅ የሚያመሰግኗቸውም አሉ፡፡

ደቡብ ክልል ተወልዶ ያደገው ወዳጆ ወንድሙ፣ እንደ ተስፋዬ ሁሉ በጎ ፈቃደኛ ትራፊክ ሆኖ መሥራት ከጀመረ ሁለት ወራትን አስቆጥሯል፡፡ 25 ዓመቱ ሲሆን የአሥረኛ ክፍል ትምህርት አጠናቆ ወደ ሙያ ትምህርት ለመግባት በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡የህግ ባለሙያ የመሆን ህልም አንዳለው የሚናገረው ወጣቱ ሕግ ከማስከበር ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሙያዎች በተለየ እንደሚስቡት ይናገራል፡፡ ለዚህም ነው ክረምቱን በጎ ፈቃደኛ ትራፊክ ሆኖ ለማሳለፍ የወደደው፡፡

‹‹የደኅንነት ጉዳይ መሆኑን እያወቁ ሕግ ጥሰው አለቦታቸው የሚቆሙ ተሽከርካሪዎች ብዙ ናቸው፡፡ እንደዚህ የሚያደርጉትን ልናስረዳቸው እንሞክራለን፡፡ እምቢ ሲሉ ግን እንዲቀጡ የሰሌዳ ቁጥራቸውን ለበላይ አካላት እናስተላልፋለን›› የሚለው ወዳጆ፣ እስካሁን ትዕዛዝ የተላለፉ ከአሥር የሚበልጡ አሽከርካሪዎች እንዲቀጡ ማድረጉን ተናግሯል፡፡

አደባባይ መዞር ሲኖርባቸው ነገር ግን ይህንን ሳያደርጉ ድንገት ወደ አንዱ አቅጣጫ መሪያቸውን በመጠምዘዝ የሚበሩ አሽከርካሪዎችም በተደጋጋሚ ጊዜ እንደሚያግጥሙት ይገልፃል፡፡ ከእግረኞችም በኩል የተለያዩ ችግሮች እንዳሉ ይናገራል፡፡  በፍጥነት መንገድ ላይ  ራሳቸውን ለአደጋ የሚያጋልጡ፣ ስልክ እያናገሩ መንገድ የሚያቋርጡ እግረኞች እንዳሉም ገልጿል፡፡

ፕሮግራሙ በርካቶች አልባሌ ቦታ እንዳይውሉ አድርጓል፡፡ አርአያነት ያለው ተግባር በመሆኑም አንዱ አንዱን እያየ ወደ ሥራው እየገባ ይገኛል፡፡ የ15 ዓመቷ ጽዮን ዮሐንስ በጎ ፈቃደኛ ትራፊክ ሆና ለመሥራት የወሰነችው፣ በበጎ ፈቃኛ ትራፊክነት የተመዘገቡ ጓደኞቿን ተመልክታ ነው፡፡ በምሥራቅ ድል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የ7ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ታዳጊዋ፣ ክረምቱን ለዚህ ተግባር ማሳለፏ ደስተኛ እንዳደረጋት ትናገራለች፡፡ ይህንን ነፃ አገልግሎት በቀን በሁለት ፈረቃ ይሰጣሉ፡፡ ከጠዋት አንድ ሰዓት እስከ ረፋዱ አራት ሰዓት፣ እንዲሁም ከሰዓት በኋላ ከዘጠኝ እስከ 12 ሰዓት በከተማዋ በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች በመገኘት የትራፊክ ፍሰቱን ለማሳለጥ እገዛ ያደርጋሉ፡፡

በጎ ፈቃደኛ ወጣት ትራፊኮች የሚል ጽሑፍ የሠፈረበት አንፀባራቂ ዩኒፎርም ደርበው የትራፊክ ፍሰት በሚበዛባቸው መንገዶች ላይ ቆመው ሕግ ለማስከበር በሚያደርጉት ጥረት የተለያዩ ነገሮች እንደሚያጋጥማቸው ጽዮን ትናገራለች፡፡ ‹‹አንዳንዶች ትራፊክ መሆናችንን ሳያውቁ ጥሰውን ያልፉንና ተመልሰው መጥተው ይቅርታ ይጠይቁናል፡፡ እያወቁ የሚያጠፉም አሉ፡፡ ሲያጠፉ ታርጋ ጽፈን ለማስተላለፍ ስንልም ምንም እንደማናመጣ የሚናገሩን ብዙ ናቸው›› ትላለች፡፡ በሥራ ላይ እያሉ የሚላከፉ እግረኞችና አሽከርካሪዎችም ጥቂት አይደሉም፡፡

የ15 ዓመቷ ሠራዊት መርክንም ጽዮን የጠቀሰቻቸው ሁኔታዎች የየዕለት ገጠመኟ መሆኑን ትናገራለች፡፡ ሠራዊት ከዚህ ቀደም በማንኛውም ዓይነት የበጎ ፈቃድ ተግባር ተሳትፋ አታውቅም፡፡ ይህ የመጀመሪያዋ ነው፡፡ ሥራው ቤተሰቦቿን በሥራ የማገዝ ኃላፊነቷን እንዳያስተጓጉልባትም ጎህ ሲቀድ ከእንቅልፏ በመነሳት ምግብ ማብሰል ቤት ማዘገጃጀት ትጀምራለች፡፡ የቤት ውስጥ ሥራዋን እንዳጠናቀቀችም ዩኒፎርሟን አጥልቃ በበጎ ፈቃድ ወደተሰማራችበት የትራፊክነት ሥራ ትሄዳለች፡፡ የዕረፍት ጊዜዋን ቤት ውስጥ ሆና ከማሳለፍ የተሻለ መሆኑን የምትናገረው ታዳጊዋ፣ ትርፍ ጊዜዋን ትርጉም ያለው ነገር ላይ በማዋሏ ደስተኛ መሆኗን ገልጻለች፡፡

የበጎ ፈቃደኛ ወጣት ትራፊክ አገልግሎት ፕሮግራም ከተጀመረ 14 ዓመት  ቢሆነውም በተደራጀ መልኩ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አራት ዓመቱ ነው፡፡ በአሁኑ ፕሮግራም 3000 ወጣቶች ተመልምለው ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ባሉባቸው 25 አደባባዮችና 30 የመንገደኛ ማቋረጫዎች ተሰማርተው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

‹‹ወጣቶቹ ወደ ሥራ የገቡት ሥልጠና ተሰጥቷቸው ነው፡፡ በሥልጠናው  ለእግረኛ ቅድሚያ እንዲሰጥ፣ እግረኞች ግራ ይዘው እንዲሄዱ፣ የማቋረጫ መስመሮችን እንዲጠቀሙ ማድረግና የመሳሰሉትን እንዴት ማስፈጸም እንዳለባቸው አውቀዋል›› ያሉት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ኮማንደር ፋሲካ ፈንታ ፕሮግራሙ በክረምት ብቻ የተወሰነ መሆን አይገባውም ብለዋል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ የመጣው የትራፊክ አደጋን ለመከላከል ተመሳሳይ ፕሮግራሞች ወሳኝ ናቸው ያሉት ኮማንደሩ፣ ፕሮግራሙ ሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ እንደተጀመረ፣ ወጣቶቹም በከተማው በሚገኙ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ በሚኖርባቸው 10 ክፍላተ ከተሞች ተሰማርተው ከሰኞ እስከ ዓርብ እያገለገሉ እንደሚገኙ፣ ሕግ የሚተላለፉ አሽከርካሪዎች ሲያጋጥሟቸው ዕርምጃ የመውሰድ ሥልጣን እንደተሰጣቸው አብራርተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...