ጋቦን ነሐሴ 21 ቀን 2008 ዓ.ም. ያካሄደችውን የፕሬዚዳንት ምርጫ ተከትሎ፣ አገሪቱን ላለፉት ሰባት ዓመታት የመሩት አሊ ቦንጎና ተቀናቃኛቸውና የቀድሞ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ዦን ፒንግ በየግላቸው ምርጫውን ማሸነፋቸውን መግለጻቸው በአገሪቱ የፖለቲካ ውዝግብ አስነስቷል፡፡
ፍራንስ 24 እንደዘገበው፣ በምርጫው ማግሥት የአገሪቱ ዋና ከተማ ሊቨርቪል ጭር ብላ የዋለች ሲሆን፣ የሁለቱ ተቀናቃኞች ደጋፊዎችም በአገሪቱ ብጥብጥ ያነሳሉ ተብሎ ተፈርቷል፡፡ ምርጫው ከመደረጉ 15 ቀናት አስቀድሞ በሁለቱም በኩል የተደረጉ የምርጫ ቅስቀሳዎችም በአገሪቷ ብጥብጥ ሊያስነሱ እንደሚችሉ ሥጋት ነበር፡፡
ከፍተኛ ደጋፊ አላቸው የተባሉት የ73 ዓመቱ ፒንግ ቦንጎን ማሸነፋቸውን የሚያሳዩ ቁጥሮች ለደጋፊዎቻቸው ያሠራጩ ሲሆን፣ ይህም የምርጫ ቦርዱ ውጤት በይፋ ሳያሳውቅ መሆኑ ደጋፊዎቻቸው የምርጫ ቦርድ ውጤትን እንዳይቀበሉ፣ በተቃራኒው ለብጥብጥ እንዲነሳሱ ያደርጋልም ተብሏል፡፡
‹‹ያለው ሁኔታ የሚያሳየው ወሳኙን የፕሬዚዳንት ምርጫ ማሸነፋችንን ነው፤›› ብለው ለደጋፊዎቻቸውና ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ፒንግ፣ የአገሪቱን የምርጫ ሕግ ባለመከተላቸው የጋቦን የአገር ውስጥ ሚኒስቴር አውግዟል፡፡ ‹‹ዕጩ ፕሬዚዳንቱ ዦን ፒንግ የምርጫውን ዴሞክራሲያዊ ሒደት መዝብሮታል፤›› ሲልም አስታውቋል፡፡
የ57 ዓመቱ ቦንጎ ለ42 ዓመታት አገሪቱን የገዙት አባታቸውን በምርጫ ተክተው እ.ኤ.አ. ከ2009 ጀምሮ ላለፉት ሰባት ዓመታት አገሪቱን የመሩ ሲሆን፣ ‹‹ይኼኛውን ምርጫ ስለማሸነፌ እርግጠኛ ነኝ?›› ብለዋል፡፡ ለተቀናቃኛቸው ፒንግ ደግሞ፣ ‹‹ምርጫ ቦርድ ውጤት ሳይገልጽ ቀድሞ የሌላውን ውጤት ባዶ የማድረግ አካሄድ ዋጋ ያስከፍላል፤›› ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
‹‹ድቡን ሳትገድል በፊት ቆዳውን መሸጥ አትችልም፤›› ያሉት ቦንጎ፣ ፒንግ የምርጫ ቦርድ ውጤት ሳይገልጽ ቀድሞ አሸንፌያለሁ ማለታቸውን ቢኮንኑም፣ እሳቸውም በምርጫው እንዳሸነፉ ተናግረዋል፡፡ ምርጫው ከተጠናቀቀ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ የቦንጎ ቃል አቀባይ አሊያን ቢሊ፣ ቦንጎ በአገሪቱ ከሚገኙ ዘጠኝ ከተሞች በአምስቱ እየመሩ መሆኑን በኋላም በአገሪቱ የመንግሥት ቴሌቪዥን ቦንጎ ለቀጣዮቹ ሰባት ዓመታት አገሪቱን በፕሬዚዳንትነት ለመምራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ምንም እንኳን የምርጫ ውጤት ባይገለጽም፣ ባገኘነው መረጃ መሠረት አሸንፈናል ብለን መናገር እንችላለን፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
ቢሊ በምርጫ ወቅት ብዙ ማጭበርበሮች መስተዋላቸውንና በተለይ የተቀናቃኞች ጠንካራ ደጋፊዎች ባሉባቸው አካባቢዎች ምርጫው ተጭበርብሯል ሲሉ፣ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴርም በአንዳንድ ምርጫ ጣቢያዎች ማጭበርበሩ እንደነበር፣ ሆኖም የምርጫ ሒደቱ አጥጋቢና አዎንታዊ መሆኑን ገልጿል፡፡
የሕዝብ ብዛቷ ከሁለት ሚሊዮን የማይበልጠው ጋቦን በነዳጅ ምርቷ ትታወቃለች፡፡ በአፍሪካ ሀብታም ከሚባሉ አገሮችም አንዷ ናት፡፡ ሆኖም የነዳጅ ምርት አቅርቦቷ ማሽቆልቆሉና የነዳጅ ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ መውደቁ በአገሪቱ የበጀት ቅነሳን አስከትሏል፡፡ ይህም ተቃዋሚዎች በቦንጎ አገዛዝ ኅብረተሰቡ ኑሮውን ለመግፋት እየተቸገረ ነው በማለት ተቀባይነት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡
ከአሥር ዕጩዎች አንዱ የሆኑት ዦን ፒንግ፣ የቦንጎ ቀኝ እጅ የነበሩና ለዓመታትም በአገሪቱ ቁልፍ ቦታዎች ሲሠሩ የቆዩ ናቸው፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበርም ነበሩ፡፡ በዚህም ታዋቂነትን አትርፈዋል፡፡
ጋቦንን ላለፉት ሰባት ዓመታት የመሩት ቦንጎ ይፋዊ ውጤት ከመገለጹ በፊት፣ ፒንግን በምርጫ ማሸነፋቸውንና ምርጫው ተጭበርብሯል ቢሉም፣ የተቀናቃኞቻቸው ደጋፊዎች ቦንጎ ጋቦኒዝ አይደለም ሲሉ ካርድ መምዘዝ ጀምረዋል፡፡ ሮይተርስ እንደዘገበው፣ ተቃዋሚዎች ቦንጎ ጋቦኒዝ ሳይሆኑ ከምሥራቅ ናይጄርያ በሕፃንነታቸው በማደጐ መጥተው አገሪቷን ላለፉት 42 ዓመታት ከገዙት አሳዳጊው ጋር የኖሩ ናቸው ሲሉ፣ ቦንጎ ግን ውሸት ነው ሲሉ አጣጥለውታል፡፡
ፒንግ ከምርጫ ውጤት ቀድመው ይፋዊ የአሸንፌያለሁ መግለጫ መስጠታቸው በደጋፊዎቻቸው ዘንድ ይሁንታን ቢያገኝም፣ በፖለቲካ ተንታኞችም ሆነ ምርጫውን በሚታዘቡ ቡድኖች ወቀሳ ገጥሟቸዋል፡፡
መቀመጫውን በጋቦን ጐረቤት ቶጐ ያደረገው መንግሥታዊ ያልሆነው የፓን አፍሪካ ዴሞክራሲ ኦብዘርቫቶሪ የፒንግን መግለጫ አጣጥሎታል፡፡ ‹‹ከሁለት አንዱ በምርጫው አሸንፌያለሁ ቢሉ አይገርመንም፣ ይህ የጨዋታው አንድ አካል ነው፤›› ሲሉም የኦብዘርቫቶሪው መሪ ጆቪ ጋሊ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
ኦማር ባይ የተባሉ የፖለቲካ ተንታኝ ፒንግ ቢያሸንፉ ለጋቦን ዋና ለውጥ ነው፣ ቦንጎም ቢሆኑ አገሪቱን ለመምራት ብቁ ናቸው ሲሉ ለአልጄዚራ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ቦንጎ በሥልጣን መቆየት ከፈለገ ሁሉም ማሽን በእጁ ነው፡፡ የአገሪቱ ምርጫ ቦርድ ሙሉ ለሙሉ ነፃ አይደለም፡፡ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የሚያየው ፍርድ ቤትም ነፃ አይደለም፣ ዳኞችም በቦንጎ የተሾሙና የቦንጎ ቀኝ እጅ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡
የ73 ዓመቱ ፒንግና የ57 ዓመቱ ቦንጎ ለዓመታት አብረው ሠርተዋል፡፡ ቦንጎ፣ ፒንግ በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር እንዲሆኑም ትልቁን ሚና ተጫውተዋል፡፡ ፒንግ አሁን የቦንጎ ተቃዋሚ ሆነው ብቅ ቢሉም፣ በቦንጎ አባት ቤተሰብ ውስጥ ተወዳጅ የነበሩና በጋብቻም የተሳሰሩ ነበሩ፡፡ ፒንግ አገሪቱን ለ42 ዓመታት የገዙት ኦማር ቦንጎን የመጀመሪያ ልጅ አግብተው ሁለት ልጅ ወልደዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2014 ወዲህ ግን ፒንግ ለኦማር ቦንጎ ቤተሰቦች ተቀናቃኝ ሆነው ቀርበዋል፡፡
ፒንግ እ.ኤ.አ. በ2014 መጋቢት ወር ለፍሬንች ዴይሊ ለሞንድ በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹ጋቦን በቤተሰብ እጅ በተያዘ ጨቋኝ አገዛዝ ውስጥ ናት፣ በአንድ ጐሣ እየተመራች ነው፤›› ብለው ነበር፡፡
በኦማር ቦንጎ አገዛዝ ዘመን በተለያዩ የሥልጣን እርከኖች ያገለገሉት ፒንግ፣ እ.ኤ.አ. በ2016 ምርጫ ተቃዋሚ ሆነው ሲመጡ ብዙ ደጋፊዎችን አግኝተዋል፡፡ ሆኖም የምርጫው ውጤት ቀድሞ ሳይገለጽ አሸንፌያለሁ ማለታቸው፣ በሌላ በኩልም ቦንጎና ደጋፊዎቻቸው ቦንጎ አሸንፏል ማለታቸው፣ አገሪቱን ብጥብጥ ውስጥ ይከታታል ተብሎ ተሰግቷል፡፡ በምርጫው ማግሥት ሕዝቡ በፍርኃት ከቤቱ ሳይወጣ የዋለውም፣ የሁለቱ ዕጩ ፕሬዚዳንት ደጋፊዎች ብጥብጥ ያስነሱ ይሆናል በሚል ሥጋት ነው፡፡
እ.ኤ.አ. በ2009 ቦንጎ የፕሬዚዳንትነት ሥልጣን በምርጫ ሲያሸንፉ ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር፡፡ በወቅቱ ብዙዎች ሲገደሉ በየሕንፃው የሚገኙ ሱቆች ተዘርፈዋል፡፡ የፈረንሣይ ቆንጽላ ጽሕፈት ቤትም ተቃጥሏል፡፡ በወቅቱ ተፈጥሮ በነበረ ብጥብጥ ነዋሪዎች ተቸግረው የነበረ ሲሆን፣ አሁን ይህ ብጥብጥ ሊከሰት ይችላል በሚል ሥጋት ቀለባቸውን ሸምተው ከቤት ሳይወጡ መቀመጥን መርጠዋል፡፡
በምርጫው ማግሥት እሑድ ቀን ይከፈቱ የነበሩ ሱቆችና መዝናኛ ሥፍራዎች ተዘግተው የዋሉ ሲሆን፣ በጋቦን የሚገኘው የፈረንሣይ ኤምባሲም ዜጐቹ በአገሪቱ የትኛውም ሥፍራ እንዳይንቀሳቀሱ፣ በአገሪቷ ስላለው ሁኔታም የሚሰጠውን መግለጫ እንዲከታተሉ አሳስቧል፡፡ በአገሪቱ እስከ ማክሰኞ ምሽት ድረስ ምንም ብጥብጥ ባይታይም፣ የሁለቱም ደጋፊዎች ግን ውጤቱ ሲመጣ የሚሆነውን እናያለን ማለታቸው ተዘግቧል፡፡
በጋቦን ቦንጎ ዳግም ከተመረጡ መፈንቅለ መንግሥት ሊካሄድ ይችላል የሚል ሥጋት አለ፡፡ የፒንግ የቅስቀሳ አቀናቦሪ ጂን ጋስፖርድ፣ ‹‹ቦንጎ ሥልጣንን በጉልበቱ ለማቆየት ይሞክር ይሆናል፤›› ሲሉ ይህ በአገሪቱ መፈንቅለ መንግሥት ወይ ብጥብጥ ሊያስከትል እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
‹‹አሊ ቦንጎ ምርጫውን ከቁብ ሳይቆጥር በሥልጣን ለመቆየት ወስኗል፡፡ ወሳኝ ምንጮች እንዳሳወቁን ቦንጎ ወታደሮችን በከተማችን ሊቨርቪልና በአገሪቱ በሁሉም ሥፍራዎች ለማስፈር ተዘጋጅቷል፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ምርጫው አልቋል፣ መፈንቅለ መንግሥቱም ተጀምሯል፤›› ሲሉም የፒንግ ድምፅ በመፈንቅለ መንግሥት እንደሚነጠቅ ተናግረዋል፡፡
በሥልጣን ላይ ያሉት ፕሬዚዳንት ዓሊ ቦንጎ ከአገራቸው አልፈው በፈረንሣይ ፖለቲካ ውስጥ ሳይቀር እጃቸውን በማስገባት ይታወቃሉ፡፡ በፈረንሣይ ፖለቲካ ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆናቸው የሚነገርላቸው ቦንጎ፣ በዚህኛው ምርጫ ኃይል ከመጠቀም ወደኋላ እንደማይሉ ይነገራል፡፡ በአባታቸው ግማሽ የቻይና ዝርያ ያለባቸው ዦን ፒንግ ደጋፊዎች ደግሞ ዓሊ ቦንጎን ለማስቆም እንጋፈጣለን እያሉ ነው፡፡