Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ፖሊሲና አቅጣጫ ባልነበረበት የተጀመረው ሥራ ዛሬ ላይ ውጤት አስገኝቷል››

ወ/ሮ ገነት መንግሥቱ፣ የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ

የቤተሰብ ዕቅድ ጽንሰ ሐሳብና አገልግሎት ወደ ኢትዮጵያ በይፋ የገባው የዛሬ 50 ዓመት የከፍተኛ ትምህርታቸውን ለመከታተል ዕድል አግኝተው ወደ ህንድ አገር በሄዱ ጥቂት ወጣት ምሁራን ነበር፡፡ ወቅቱ በግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በ1958 ዓ.ም. ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛትም 22 ሚሊዮን አካባቢ ነበር፡፡ ፊደል ከቆጠሩና ባህር አቋርጠው ከተመለሱ ጥቂት ኢትዮጵያውያን በስተቀር ሕዝቡ ለዓመታት የተገነባ ልጅን እንደ ሀብት ብቻ የመቁጠር አንድ ዓይነት አመለካከትም ነበረው፡፡ ይሁንና በአገሪቱ የነበረው ከፍተኛ የእናቶችና የጨቅላ ሕፃናት ሞትና በወቅቱ ይታይ የነበረው ፈጣን የሕዝብ ዕድገት ያሳሰባቸው በጐ ፈቃደኞች የተደራጀ ተቋም ለመመሥረት እንቅስቃሴ ጀመሩ፡፡ በመጨረሻም ሐሳባቸው ሰምሮ በወቅቱ ፓዝ ፋይንደር ፈንድ ተብሎ ይጠራ በነበረው የአሁኑ ኢንተርናሽናል ፓዝ ፋይንደር በተለገሰ የገንዘብ ድጋፍ በአንዲት በጎ ፈቃደኛ ነርስ ብቻ የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡ ወ/ሮ ገነት መንግሥቱ የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ታደሰ ገብረማርያም በማኅበሩ እንቅስቃሴ ዙሪያ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ከተመሠረተ በኋላ ከነበረው የቤተሰብ ዕቅድ አመለካከት አንፃር እክል አልገጠመውም?

ወ/ሮ ገነት፡- ከምሥረታው በኋላ በነበሩት የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር፣ ምቹ የቤተሰብ ዕቅድ የሕግ ማዕቀፍ በሌለበት ሥራውን ሲያከናውን ነበር፡፡ የ1957 ዓ.ም. ወንጀለኛ መቅጫ ሕግም የቤተሰብ ዕቅድን ማስተዋወቅና ማሠራጨት ክልክል መሆኑን አስቀምጦ ነበር፡፡ ከዚህም ሌላ አንዳንድ ባሎች ‘ለሚስቶቻችን ይህን አገልግሎት ለምን ሰጣችሁ’ በሚልም ሽጉጥ መማዘዝ ደረጃ ደርሰው ነበር፡፡ ማኅበሩ ዛሬ ያለበት ደረጃ ለመድረስ በርካታ ሀይማኖታዊ፣ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ጋሬጣዎችን ተጋፍጧል፡፡ በዚህም የቤተሰብ ዕቅድ መረጃና የሥነ ተዋልዶ ምክርና የክሊኒክ አገልግሎት ለተጠቃሚዎች በመስጠት ፋና ወጊ ሆኗል፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ስትራቴጂዎችን እየቀየሰና አዳዲስ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎቶችን እያከለ፣ መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም አሠራሩን ያስፋፉበት ሁኔታ አለ፡፡ የተገኘውን ውጤት ቢያብራሩልን?

ወ/ሮ ገነት፡- በርካታ ስትራቴጂዎች ተቀርጸው ነበር፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱና ዋነኛው በመላ አገሪቱ በሚገኙ 700 የገጠር ቀበሌዎች፣ ማኅበረሰብ አቀፍ ፕሮግራም በሚል፣ የቤተሰብ ዕቅድ ዘዴዎች እዚያው ባሉት ማኅበረሰቦች እንዲሠራጭ የተደረገው ይገኝበታል፡፡ ይህም ተግባራዊ የሆነው ማኅበረሰቡ የመረጣቸውና እስከ አራተኛና አምስተኛ ክፍል ድረስ የተማሩትን፣ እንዲሁም ማንበብና መጻፍ የቻሉትን በማሠልጠን እንደ ኮንዶምና ፒልስ (በአፍ የሚወሰድ እንክብል) ለማኅበረሰቡ እንዲያዳርሱ፣ ከዚህ ውጭ ያሉትን አገልግሎቶች ክሊኒክ ሪፈር እንዲያደርጉ በማድረግ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ከፍ አድርገዋል፡፡ መንግሥትም ይህንን ተግባር ወደ ጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ከፍ እንዲል ሲያደርግ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም በዚህ ዓይነት ፕሮግራም ውስጥ ገብተዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር የጀመረውን አገልግሎት የመስጠት ሥራ ትቶ ወጣ፡፡ ሌላው ስትራቴጂ ደግሞ የወጣቶች ማዕከላትንና ቤተ መጻሕፍትን የማቋቋም ጉዳይ ነበር፡፡ ማዕከላቱ ወጣቶቹ በሙዚቃና በሥነ ጽሑፍ የራሳቸውን ክህሎት የሚያሳድጉበትን ቤተ መጻሕፍቱ ደግሞ ከተዋልዶ ጤና ጋር በተገናኘ ትምህርትና መረጃ የሚያገኙበትን በማመቻቸት ረገድ የጎላ ሚና ተጫውተዋል፡፡ በተለይ ማዕከላቱ ታዋቂ አርቲስቶችን፣ ጋዜጠኞችንና ትላልቅ ደረጃ ላይ የደረሱ ባለሥልጣናትን ሁሉ ያፈሩ ናቸው፡፡   

ሪፖርተር፡- የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ቅድመ ምርመራና ሕክምናን አስመልክቶ ማኅበሩ የሚሠራውን ቢገልጹልን?

ወ/ሮ ገነት፡- የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር የቅድመ ምርመራ አገልግሎት መስጠት የጀመረው በ1988 ዓ.ም. ነው፡፡ ከተለያዩ ሆስፒታሎች በሪፈራል የሚመጡ ታካሚዎችም በርካታ ናቸው፡፡ ከአራት ዓመታት በፊት አዲስ ቴክኖሎጂ አምጥተን ሥራ ላይ ውሏል፡፡ ቴክኖሎጂው፣ ተገልጋዮች እንደመጡ ምርመራ የሚያገኙበትንና ሕክምና የሚሰጥበትን ሁኔታ አመቻችቷል፡፡ ከእኛ አቅም በላይ የሆነውን ወደ ሆስፒታል ሪፈር የምናደርግበት አካሄድም አለን፡፡ የጡት፣ የማህፀን በር ጫፍንና የፕሮስቴት ካንሰርን አስመልክቶ በቅርቡ በተካሄደው የአፍሪካ ቀዳማዊት እመቤቶች ጉባኤ ላይ ወደ አምስት ሺሕ የሚጠጉ ሴቶችን መመርመር ተችሏል፡፡ ይህም ምርመራ የተካሄደው በአዲስ አበባና ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉት ክሊኒኮቹ ነው፡፡ በአገልግሎቱም ታዋቂ ነው፡፡ አሁን ላይ ማኅበሩ ከ50 በላይ ክሊኒኮች አሉት፡፡ በእነዚህም ክሊኒኮች የአገልግሎት አድማሱን እያሰፋ መጥቷል፡፡ ከክሊኒኮቹም መካከል አሥሩ ለሴተኛ አዳሪዎች ብቻ አገልግሎት የሚሰጡ ሚስጥራዊ ክሊኒኮች ናቸው፡፡ የተቋቋሙትም ከአፋር ጀምሮ እስከ ጋምቤላ ድረስ በተለይ ሴተኛ አዳሪዎች በብዛት በሚገኙባቸው አካባቢዎች ላይ ነው፡፡ ኤችአይቪ እና አባላዛር በሽታዎች ላይ ተከታታይ ምርመራ ያደርጋሉ፡፡ በተለይ በኤችአይቪ ላይ እስከ ሕክምና ድረስ እየተሰጠ ያለበት ሁኔታ አለ፡፡  

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ለትርፍ ያልቆመ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሆኖ የተመሠረተውና ፍላጎት ላላቸውና በሕግ የተወሰነውን የዕድሜ ክልል ለሚያሟሉ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት መስጠት የተጀመረው መቼ ነው?

ወ/ሮ ገነት፡- ማኅበሩ ለትርፍ ያልቆመ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሆኖ በይፋ የተመዘገበው በ1967 ዓ.ም. ነው፡፡ ከዚህም ሌላ በ1974 ዓ.ም. የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ፍላጎት ላላቸውና በሕግ የተወሰነውን የዕድሜ ገደብ (ማለትም ከ18 ዓመትና ከዚያም በላይ) ለሚያሟሉ መስጠቱን እንዲቀጥል የሚፈቅድ መመሪያ ወጣ፡፡ የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ እንዲወጣ ማኅበሩ ያደረገው ከፍተኛ ግፊትና የፖሊሲው መጽደቅም ማኅበሩ እራሱን እንዲያጠናክርና እንዲያስፋፋ አድርጎታል፡፡  

ሪፖርተር፡- መንግሥት የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ዘርግቷል፡፡ ከዚህ አኳያ ማኅበሩ ከገጠሩ ማኅበረሰቦች ጋር ያለው ቅንጅት በምን መልኩ ይገለጻል?

ወ/ሮ ገነት፡- ከተለያዩ የወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤቶች ጋር ስምምነት እየተፈራረምን ነው፡፡ በስምምነቱም መሠረት ክፍተት ባለባቸው ቦታዎች ላይ እየተንቀሳቀስን ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ ጽሕፈት ቤቶቹ በማይደርስባቸው ጤና ኬላዎች፣ በተለይም በአፋር ክልል ባለሙያዎቻችን በደርሶ መልስ ፕሮግራም ሙያዊ እገዛ ያደርጋሉ፡፡ በተጠቀሰው ክልል የሚካሄደው ፕሮግራም በ200 ጣቢያዎች ላይ ነው፡፡ በጤና ኬላዎች የማይሰጡትን ወደ እኛ ክሊኒክ ሪፈር ይደረጋል፡፡ በመላ አገሪቱ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ሲጀመር ሥልጠና በመስጠት እገዛ ካደረጉት መካከል አንዱና ዋነኛው የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር ነው፡፡ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በተገኘ ድጋፍ በሶማሌ ክልል በ20 ወረዳዎች፣ በቤንች ማጂ ዞን በአምስት ወረዳዎች ለሚገኙ አርብቶ አደሮች የተዋልዶ ጤና አገልግሎትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እንሰጣለን፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር አሁን በደረሰበት ደረጃ ላይ ምን እየሠራ ነው?

ወ/ሮ ገነት፡- በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል በ1986 ዓ.ም. ካይሮ ላይ የተካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ያሳለፈውን ውሳኔ ሥራ ላይ ማዋል ይገኝበታል፡፡ ጉባኤው ያሳለፈው ውሳኔ ቁንጽል አገልግሎት ከመስጠት ይልቅ ከመራቢያ አካላትና ከተዋልዶ ጤና ሒደት ጋር የተገናኙ ነገሮችን በአንድነት እንደ ተዋልዶ ጤና ታይቶ ይሰጥ የሚል ነበር፡፡ ይህም ማለት አገልግሎቱ ከቤተሰብ ዕቅድ ወደ ተዋልዶ ጤና ይምጣ የሚል ነው፡፡ ውሳኔው ተቀባይነትን አግኝቶ የተቀናጀ የተዋልዶ ጤና አገልገሎት መስጠት ተጀምሯል፡፡ በዚህም ከተካተቱት አገልግሎቶች መካከል የእናቶችና የሕፃናት ጤና አጠባበቅ፣ ኤችአይቪ/ኤድስና የአባላዘር በሽታ የመመርመርና የማከም፤ የቤተሰብ ዕቀድ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የእናቶችና የሕፃናት ጤና አጠባበቅ በእርግዝና ጊዜ ክትትል ማድረግና ማዋለድ ሲሆን፣ ይህንንም የሚያደርጉ ስድስት ከፍተኛ ክሊኒኮች አሉን፡፡ ከዚህም ሌላ የጽንስና ማህጸን ስፔሻል ክሊኒክም በማኅበሩ ዋና መሥሪያ ቤት ቅጥር ግቢ አለ፡፡ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትም እንሰጣለን፡፡ የአጭር ጊዜ የወሊድ መቆጣጠሪያ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች ስለሚሰጡ እኛ ግን የበለጠ ትኩረት አድርገን የምንሰጠው ዘላቂና የረጅም ጊዜ የወሊድ መቆጣጠሪያ ነው፡፡ ይህም ከሦስት ዓመት በላይ የሚቆይ በክንድና በማህጸን የሚገባ ሉፕ ነው፡፡ በቋሚነት መውለድ አንፈልግም ለሚሉ ሴቶችና ወንዶች በሕክምና መውለድን የማቆም አገልግሎት ይሰጣል፡፡ የወጣቶች ተዋልዶ ጤና አገልግሎትም እንሰጣለን፡፡ ለዓይነ ሥውራንና መስማት ለተሳናቸው የሥነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ተደራሽ እናደርጋለን፡፡ ሕጉን በጠበቀ መልኩ የጽንስ ማቋረጥ ሥራ እናከናውናለን፡፡ ይህ ዓይነቱ ሥራ ከተከናወነላቸው ሴቶች መካከል 95 ከመቶ በላይ ለሚሆኑት ያልታቀደ እርግዝና እንዳይመጣባቸው የቤተሰብ ዕቅድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- በቤተሰብ ዕቅድ አጠቃቀም ላይ ኅብረተሰቡ ያለውን ግንዛቤ እንዴት ይገመግሙታል?

ወ/ሮ ገነት፡- ኅብረተሰቡ አገልግሎቶቹን በተመለከተ አሁን የተሻለ ግንዛቤ አለው፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ከተካሄዱ ጥናቶች ለመረዳት እንደተቻለው በቤተሰብ ዕቅድ ድሮ የተጠቃሚው ቁጥር በጣም ትንሽ ነበር፡፡ በ1982 ዓ.ም. የተካሄደው ጥናት እንዳመለከተው፣ በመውለድ ዕድሜ ክልል ውስጥ ካሉ ሴቶች መካከል የቤተሰብ ዕቅድ ተጠቃሚዎች ወደ አራት በመቶ ብቻ ነበሩ፡፡ በ2006 ዓ.ም. በተካሄደው ጥናት ደግሞ የተጠቃሚው ቁጥር ወደ 41 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ አገር አቀፍ ጥናት እየተጠናቀቀ ሲሆን፣ የቤተሰብ ዕቅድ ተጠቃሚውም ወደ 44 በመቶ ይደርሳል ለማለት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ጥናቱ ገና አልታወቀም፡፡ ከዚህ አኳያ የተጠቃሚዎች ቁጥር 44 በመቶ ደርሷል ለማለት የሚቻለው ከምን መነሻ ነው?

ወ/ሮ ገነት፡- መንግሥት በጤና ኤክስቴንሽን የሠራው ሥራ ቀላል አይደለም፡፡ የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ደግሞ በዚህ ላይ ድጋፍ እያደረጉ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ተደማምሮ ውጤቱን ከፍ ሊያደርገው ይችላል ከሚል እምነት በመነሳት ነው፡፡ በቤተሰብ ዕቅድ ላይ ሕጉ መሻሻሉ፤ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ከታክስ ነፃ እንዲገባ መደረጉ ለተጠቀሰው ቁጥር ከፍ ማለት የየራሳቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- ሥልጠና ላይ የሰጣችሁት ትኩረት ምን ይመስላል?

ወ/ሮ ገነት፡- የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር ከ170 በላይ የዓለም አገሮችን በአባልነት ባቀፈው የዓለም አቀፍ የቤተሰብ ዕቅድ ፌዴሬሽን ሙሉ አባል ነው፡፡ የፌዴሬሽኑ የአፍሪካ ሪጅን ማኅበራችን ከተዋልዶ ጤና አገልግሎት ሙያ ለአገር ውስጥና ለኢንተርናሽናል ሠልጣኞች የሥልጠና ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል በ2005 ዓ.ም. መርጦታል፡፡ በዚህም መሠረት ቀድሞ የነበረውን የማሠልጠኛ ክፍል በማጠናከር ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ በሺዎች ለሚቆጠሩ የአገር ውስጥና የውጭ ሠልጣኞች የሙያ ሥልጠና ወይም በቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ላይ ያተኮረ ሥልጠና ሰጥተናል፡፡ የማኅበሩ ጽሕፈት ቤት ሕንፃ አራተኛው ወለል የማሠልጠኛ ማዕከል ሆኗል፡፡ ስምንቱም ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶቻችን የማሠልጠን ሥራ ያከናውናሉ፡፡ ለዚህም የተሟላ ፋሲሊቲ ያላቸው ማሠልጠኛዎች አሏቸው፡፡   

ሪፖርተር፡- የማኅበሩን አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ከግሉ ዘርፍ ጋር ያላችሁን ግንኙነት ቢያብራሩልን?

ወ/ሮ ገነት፡- በአሁኑ ጊዜ ወደ 320 የሚጠጉ የግል ክሊኒኮች አብረውን እየሠሩ ነው፡፡ ለእነዚህም የግል ክሊኒኮች ‹‹ጥምረት ለቤተሰብ ጤና›› የሚል ስያሜ አውጥተንላቸዋል፡፡ በዚህ ዓይነቱ ጥምረት እየተሰጠ ያለው የቤተሰበ ዕቅድ አገልግሎት ቀላል አይደለም፡፡ የግል ክሊኒኮቹ ሕክምና ብቻ ይሰጡ ነበር፡፡ በዚህ ሥራቸው ላይ በተጨማሪ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትን እንዲጨምሩ በማድረግ፣ አገልግሎቱን በትናንሽ ከተሞችና ከገጠር ለሚመጡት ሁሉ ተደራሽ ማድረግ ችለናል፡፡  

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር ከዕድሜው አኳያ ሲታይ ግቡን መትቷል ለማለት ይቻላል?

ወ/ሮ ገነት፡- አዎ፡፡ ምክንያቱም ምንም ሕግ፣ ፖሊሲና አቅጣጫ ባልነበረበት የተጀመረውን ሥራ ዛሬ ላይ ቆመን ስናይ ትልቅ ውጤት ተገኝቷል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ15 ዓመት በፊት የማኅበሩን ሥልጠና ያልወሰደ አንድም የጤና ባለሙያ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ አሁን ግን መንግሥትም የራሱን አቅም ገንብቷል፡፡ ያሠለጥናል፡፡ ሌሎችም ያሠለጥናሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ዕድሎች ተፈጥረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር ማየት የፈለገውም ይህንኑ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ስትራቴጂና ፖሊሲ አለን፡፡ ሕጐችም ተሻሽለዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በመንግሥት በኩል የሚደረግላችሁ ድጋፍ አለ?

ወ/ሮ ገነት፡- መንግሥት በጣም ይረዳናል፡፡ አርብቶ አደር ላይ ለቀረጽነው የሦስት ዓመት ፕሮጀክት እውን መሆን መንግሥት ትልቅ ገንዘብ ሰጥቶናል፡፡ የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴዎችን ከመንግሥት እናገኛለን፡፡ የተለያዩ መድሃኒቶችንም ይረዳናል፡፡ ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር ፈንድ (በጀት) ከውጭ የሚያገኝበት ሁኔታ አለ?

ወ/ሮ ገነት፡- አዎ፡፡ በአብዛኛው ትልቅ ሥራ መሠራት ያለበት በዚሁ ፈንድ ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም ማኅበሩ በ50 ዓመት ዕድሜው የኔ ነው የሚለው የለውም፡፡ በውጭ ለጋሾች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ዓለም አቀፉ የቤተሰብ ፌዴሬሽን ይረዳናል፡፡ ከተለያዩ የረድኤት ድርጅቶች የሚመጣም ገንዘብ አለ፡፡ ከድርጅቶቹም መካከል የኔዘርላንድ ኤምባሲ፣ ዓለም አቀፉ የሥነ ሕዝብ ድርጅት (ዩኤንኤፍፒኤ)፣ ከጃፓን ኤምባሲ፣ ከፓካርድ ፋውንዴሽነ፣ አይሪሽ ፈንድ፣ ሲዲሲ ይገኙበታል፡፡ አሁን ላይ ሆነን ስናየው ግን በዓለም ላይ ከተከሰተው የተለያዩ የኢኮኖሚ ችግሮች አኳያ ዕርዳታዎች እየቀነሱ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ማኅበሩ አገልግሎቱን በአብዛኛው በነፃ መስጠት ይጠበቅበታል ወይ? የሚል ጥያቄ አስነስቷል፡፡ ስለዚህ አገልግሎቱን ለማግኘት የመክፈል አቅም ያላቸው ተገልጋዮች በወጪ መጋራት የሚተባበሩበትንና የገቢ ማስገኛዎች የሚፈጠሩበትን ሁኔታዎች ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት እያስጠናን ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ዕርዳታዎች በመቀነሳቸው ሳቢያ የተዘጉ አገልግሎት መስጪያዎች አሉ?

ወ/ሮ ገነት፡- መዝጋት ሳይሆን በአካባቢው ላሉትና ለማስተዳደር ለሚችሉ ድርጅቶች አስረክበን እንወጣለን፡፡ እኛ ከውጭ ሆነን እንረዳለን፡፡ ይህንንም የምናካሂደው ከበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ ጋር በመቀናጀት ነው፡፡ በዚህ መልኩ ካስረከብናቸው ተቋማት መካከል አዲስ አበባ፣ አላባ፣ ከሚሴ፣ ወልቂጤና ወላይታ ከተሞች የሚገኙ የወጣት ማዕከላት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ 

ሪፖርተር፡- የማኅበሩ ጽሕፈት ቤት እየተገለገለበት ያለው አዲስ ባለ አራት ፎቅ ሕንፃ መቼ ነው የተሠራው? ለምንስ አገልግሎት እየዋለ ነው?

ወ/ሮ ገነት፡- አልሠራነውም፡፡ ቀደም ሲል በሌላ አካል የተሠራውን ገዝተን ነው፡፡ ግዥውም የተከናወነው በብድር በተገኘ ገንዘብ ሲሆን፣ ያበደረንም ፖካርድ ፋውንዴሽን ነው፡፡ ብድሩንም ከፍለን ጨርሰናል፡፡ ሕንፃው የተገዛው ሪፈራል ክሊኒክ እና የሥልጠና ማዕከል ለማቋቋም እንዲሁም ለቢሮ እንዲውልም ጭምር ነው፡፡ ስለሆነም የጽንስና የማህጸን ስፔሻሊቲ ልዩ ክሊኒክ ፈቃድ አውጥተን እየሠራን ነው፡፡  

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ከዕውቀት እስከ ሕይወት ክህሎት

ዋርካ አካዴሚ ከትምህርት አመራርና ፔዳጎጂ፣ ከሳይኮሎጂ፣ ከዓለም አቀፍ ኪነ ጥበብ፣ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ከባንኪንግና ዓለም አቀፍ ፋይናንስ አመራር ሙያዎች በተውጣጡ ባለሙያዎች የተቋቋመ የትምህርት ተቋም ነው፡፡...

ኤስ ኦ ኤስ እና ወርቅ ኢዮቤልዩ

ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ የቤተሰብ እንክብካቤ ላጡ ሕፃናት ቤተሰባዊ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የዓለም አቀፉ ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች ፌደሬሽን አካል ነው፡፡...

የግንባታ ኢንዱስትሪዎች የሚገናኙበት መድረክ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኢንቨስትመንት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ ልማትና በኤክስፖርት የሚመራ ዕድገትን እንዲያስመዘግብ ታልሞ የተነደፈና በአብዛኛው በማደግ ላይ ባለው የግንባታው ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ዘርፍም ወደ...