Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ዋና ዋና የጃፓን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት አሳይተዋል

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በኬንያው ጉባዔ እንደሚገኙ አስታውቀው ሳይታሰቡ ቀርተዋል

  በኬንያው ትልቁ የአፍሪካና የጃፓን ጉባዔ (ቶኪዮ ኢንተርናሽናል ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ለአፍሪካ ልማት ቲካድ) ላይ ከታደሙ ከ100 በላይ ትልልቅ የጃፓን ኩባንያዎች መካከል ስድስት ያህሉ በኢትዮጵያ ማከናወን ስለሚፈልጓቸው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች የመንግሥት ኃላፊዎችን አነጋግረዋል፡፡

  አሥር ሺሕ ተሳታፊዎች በታደሙበት፣ ከአራት ሺሕ በላይ የጃፓን መንግሥት ኃላፊዎች፣ የጃፓን ሴኔት አባላትና የትልልቅ ኩባንያ ባለቤቶችና ከፍተኛ ኃላፊዎች በተገኙበት የናይሮቢው ስድስተኛው የቲካድ ስብሰባ ላይ ትልልቅ የጃፓን ኩባንያዎች ማለትም፣ ቶዮታ ቱሾ ኮርፖሬሽን፣ ቶሺባ ኮርፖሬሽን፣ ማሩቤኒ ኮርፖሬሽን፣ ሱሚቶሞ ኮርፖሬሽን፣ ኮዮ ሆልዲንግና ሌሎችም ትልልቅ የጃፓን ኩባንያዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምን አግኝተው ለማነጋገር ቀጠሮ አስይዘው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በስብሰባው እንደሚገኙ አስታውቀው ሲጠበቁ በነበረበት ወቅት ድንገት ሳይታሰብ መቅረታቸው ተሰምቷል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የመሩት የኢትዮጵያ ልዑክም በስብሰባው ታድሞ የተወሰኑ ኩባንያዎችን አነጋግሮና የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሞ ተመልሷል፡፡

  በአንፃሩ ብዙ በተባለለትና ከ30 በላይ የአፍሪካ መሪዎች በተገኙበት ጉባዔ ወቅት የኢትዮጵያ ሚናና የጃፓን ግዙፍ ኩባንያዎች አንድ ላይ በተገኙበት ወቅት አግባብቶና አነጋግሮ ለማምጣት የነበራቸው ዕድልም ከሌሎች አገሮች አኳያ ሲታይ የተሳካ አይመስልም፡፡ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትሩ አቶ አብዱላዚዝ አህመድ፣ የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አብዲሳ ያደታን ጨምሮ አሥር የሚደርሱ የኢትዮጵያ መንግሥት ልዑካን በናይሮቢው የቲካድ ጉባዔ ታድመው መመለሳቸው ታውቋል፡፡  

  በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት ካሳዩት መካከል የቶዮታ ግሩፕ አካል የሆነው ቶዮታ ቱሾ ኮርፖሬሽን በጂኦተርማልና በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ መስክ ሁለት የመግባቢያ ስምምነቶችን በናይሮቢ ከመንግሥት ጋር ተፈራርሟል፡፡ ማሩቤኒ ኮርፖሬሽን እንደ ቶዮታ ቱሾ ሁሉ (ቶዮታ ቱሾ ቀድሞው ከሞኤንኮ የሚሠራና መኪኖችን በማቅረብ ላይ የሚገኝ መሆኑ ይታወቃል)፣ በኢትዮጵያ የቡና ኤክስፖርት ንግድና በሌሎችም ንግድ ነክ መስኮች ላይ ተሳትፎ ሲያደረግ የቆየ ነው፡፡

  ከሌሎቹ ኩባንያዎች ሁሉ እስካሁን በገንዘብ ረገድ በመጀመሪያው ምዕራፍ ምን ያህል ኢንቨስት እንደሚያደርግ ያደረገው ሱሚቶሞ ኮርፖሬሽን ነው፡፡ ሱሚቶሞ ኩባንያ በኢትዮጵያ በሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት ለማድረግ የሚችልበትን ዕቅድ ማዘጋጀቱን፣ ይህንን ለመንግሥት ይፋ ማድረጉን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፍጹም አረጋ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ አቶ ፍጹም ለሪፖርተር እንዳብራሩት ከሆነ፣ ኩባንያው በብረታ ብረት ኢንዱስትሪ መስክ የመሠማራት ፍላጎት አለው፡፡

  ከኩባንያው የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ሱሚቶሞ ኮርፖሬሽን በብረታ ብረት መስክ የብረት ቱቡላሬ ምርቶችን፣ ቆርቆሮዎችንና ፌሮ ነክ ያልሆኑ ልዩ ልዩ ብረታ ብረቶችን የሚያመርት ክፍል አለው፡፡ በትራንስፖርትና ኮንስትራክሽን መስክ ከሚታወቅባቸው ሥራዎች መካከል በመርከብ፣ በኤሮስፔስ ዕቃዎች፣ በባቡር መኪኖች ወይም ፉርጎዎች፣ በአውቶሞቢሎች፣ በግንባታ መሣሪያዎችና በሊዝ ንግድ ሥራ ይታወቃል፡፡

  ከእነዚህ ኩባንያዎች ባሻገር በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ መስክ ትልቅ ቦታ ያለው ቶሺባ ኮርፖሬሽን በኢነርጂ ዘርፍም ትልቅ ቦታ እያገኘ የመጣና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ማሽነሪዎችን በማምረት ለገበያ በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡

  ዮሱኪ ያማማቶ የቶሺባ ዓለም አቀፍ የጂኦተርማልና የተርማል ኃይል ሽያጭ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ ኩባንያው በኢትዮጵያ የጂኦተርማል ኃይል ውስጥ ለመግባት የጃፓን መንግሥት የሚለቀውን ፈንድ እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡ በተለይ በአልቶ ላንጋኖ ፕሮጀክት የጃፓን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) አስጠንቶ ማስተግበር የጀመረው የጂኦተርማል ኤሌክትሪክ ኃይል ልማት ፕሮጀክት ሒደት ላይ፣ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችሉ ተርባዮችን ለማቅረብ ተዘጋጅቷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የሙከራ ቁፋሮ ተጠናቆ ሁለት ከጉድጓዶች አምስት ሜጋ ዋት ኃይል ማምረት እንደተጀመረ ያማማቶ ጠቅሰዋል፡፡ ይሁንና በአልቶ ላንጋኖ እስከ 70 ሜጋ ዋት ኃይል ለማመንጨት እንዲቻል ቢያንስ 20 ጉድጓዶች መቆፈር ይኖርባቸዋል፡፡

  በጂኦተርማል ኢነርጂ መስክ ቶዮታ ቱሾ ኮርፖሬሽን ለመግባት ስምምነት ፈርሟል፡፡ በመሆኑም ቶዮታ ቱሾን የሚቀናቀነው ቶሺባ ኮርፖሬሽን በዚህ መስክ ለመሰማራትና የጂኦተርማል ተርባይኖችን ለማቅረብ ላይ ታች እያለ ሲሆን፣ በመስከረም ወር ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል፡፡

  በኬንያው የቲካድ ስድስት ጉባዔ፣ አሥር ሺሕ ታዳሚዎች መገኘታቸውን የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አስታውቀዋል፡፡ በሁሉ መልኩ ስኬታማ ሆኖ የተጠናቀቀው ይህ ጉባዔ፣ ከ73 ያላነሱ የመግባቢያ ስምምነቶች በአፍሪካውያንና በጃፓናውያን መካከል የተፈረሙበት፣ 2,000 የጃፓን ኩባንያ ወኪሎች፣ 100 የኩባንያ ኃላፊና ባለቤቶች የተገኙበት ከ30 በላይ የአፍሪካ መሪዎች የተሳተፉበት ትልቁና በአፍሪካ ሲካሄድም የመጀመሪያው ጉባዔ ነው፡፡ የመግባቢያ ስምምነቶቹ ከተፈረሙ በኋላ በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ወቅት የጃፓንና የኬንያ መሪዎችና የ20 አፍሪካ አገሮች መሪዎች፣ 22 የጃፓን ኩባንያዎች እንዲሁም ስድስት የአፍሪካና ዓለም አቀፍ ተቋማት ተገኝተዋል፡፡ ኢትዮጵያን በመወከል ኮሚሽነር ፍጹም አረጋ ተገኝተዋል፡፡

   

   

   

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች