Sunday, September 24, 2023

የኢሕአዴግ ምክር ቤት ውሳኔዎችና ያቀረባቸው ጥሪዎች አንድምታ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚኖርባቸው የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች በርካታ አካባቢዎች የተነሱትን ሕዝባዊ አመፆችና ተቃውሞዎች አስመልክቶ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ በነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ ባካሄደው ስብሰባ፣ የተቃውሞው ዋነኛ መነሻ ከመልካም አስተዳደር ጋር የተያያዘ በዋናነትም የመንግሥትን ሥልጣን ለግል ጥቅም ማዋል የፈጠረው ቁጣ መሆኑን ገልጿል፡፡

ከዚህ በኋላ የኢሕአዴግ ምክር ቤት በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ለቀናት ያካሄደውን ስብሰባ አጠናቆ ነሐሴ 22 ቀን 2008 ዓ.ም. መግለጫ አውጥቷል፡፡ በዚህ መግለጫ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ያሳለፈው ውሳኔ በድጋሚ ተንፀባርቋል፡፡ በተጨማሪነትም በአማራ ክልልና በትግራይ ክልል አዋሳኝ ድንበሮች የተቀሰቀሱት የድንበር ጥያቄዎችን፣ የሁለቱ ክልል መንግሥታት በመነጋገር እንዲፈቷቸው ውሳኔ ማሳለፉን የምክር ቤቱ መግለጫ ያስረዳል፡፡

‹‹በአማራ ክልል በሰሜን ጐንደርና በአጐራባች የትግራይ ወረዳ መካከል ከወሰን ማካለል ጋር ተያይዞ በተነሳው ጉዳይ በሕወሓትና በብአዴን አመራሮች በኩል መፍትሔ ከመስጠት አኳያ የተከሰተው መዘግየት ተገቢ እንዳልሆነ በመገምገም፣ ሁለቱ ድርጅቶች ከዚህ ድክመት ተላቀው ፈጣንና ሕዝብን ማዕከል ያደረገ መፍትሔ እንዲሰጡ፤›› ሲል ወስኗል፡፡

በማከልም ‹‹በትግራይ ክልል ከወልቃይት ጋር ተያይዞ የተነሳው ጥያቄ በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ተከትሎ እንዲታይ፣ እነዚህና ለግጭት መንስዔ የሆኑ ወቅታዊ ጉዳዮችም ከሕዝብ ጋር በመመካከርና በመግባባት፣ እንዲሁም የሕግ የበላይነት በተከበረበት አኳኋን እንዲፈታ መደረግ አለበት፤›› ሲል በውሳኔው ገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ምክር ቤቱ ለመላ አገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሰላም ጥሪውን ያቀረበ ሲሆን፣ የፀጥታ ኃይሉም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን እንዲጠብቅ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

‹‹በቅርቡ በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረውን ግጭት ለማስወገድ የከፈላችሁትን የሕይወትና የአካል መስዋዕትነት ምክር ቤቱ በአድናቆት ይመለከተዋል፡፡ አሁንም በጥረታችሁና በከፈላችሁት መስዋዕትነት የተገኘውን ሰላም ለማደፍረስ የሚጥሩት ኃይሎች የተለመደው ሕዝባዊ ባህሪያችሁ ሳይለያችሁ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ዘብ እንድትሆኑ ምክር ቤቱ ጥሪውን ያቀርብላችኋል፤›› የሚል ጥሪውን የኢሕአዴግ ምክር ቤት አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) የምክር ቤቱ ውሳኔ ሕዝብ ካነሳው ጥያቄ ጋር ፈጽሞ እንደማይጣጣም፣ ለመፍትሔውም አጋዥ አለመሆኑን ለሪፖርተር በላከው መግለጫ ገልጿል፡፡

ሕዝቡ ባካሄዳቸው ተቃውሞ ሠልፎች መጀመሪያ ላይ የአዲስ አበባን ክልል የማስፋፋቱ ዕቅድ እንዲሰረዝ፣ የወልቃይትና የቅማንት ሕዝቦች የማንነት ጉዳዮች በአፋጣኝ እንዲወስን፣ ወዘተ. የሚሉ ቀላል ጥያቄዎች ይነሱ እንደነበር መድረክ በመግለጫው አስታውሷል፡፡ ቀስ በቀስም በመንግሥትና በገዥው ፓርቲ ባለሥልጣናት እየተፈጸሙ ያሉት የመሬትና የንብረት ዝርፊያዎች እንዲቆሙና ብልሹ አስተዳደር እንዲወገድ የሚሉ ጥያቄዎች ማቅረቡን፣ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ጥያቄዎቹ ጥልቀት እያገኙ መሄዳቸውን ጠቁሟል፡፡

ባልመረጥናቸው አስተዳዳሪዎች አንገዛም፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻችን ይከበሩ፣ ነፃነታችን ታፍኗል፣ ፍትሕ እንፈልጋለን የሚሉ መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች የሕዝብ ጥያቄዎች መሆናቸውን ገልጿል፡፡ በመፍትሔነትም ኢሕአዴግ አሁን በያዘው መልኩ ብቻውን መፍትሔ ሊያመጣ የማይችል በመሆኑ፣ ከመድረክና ከሌሎች ሀቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በወቅቱ የሕዝብ ጥያቄዎች መፍትሔ በመሻቱ ቁም ነገሮች ላይ በአስቸኳይ ድርድር ውስጥ እንዲገባ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

የኢሕአዴግ ምክር ቤት የወልቃይት ሕዝብ የአማራ ብሔርተኝነትን አስመልክቶ የትግራይ ክልል በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ውስጥ ሆኖ እንዲፈታ መወሰኑን ገልጿል፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያ የወልቃይት ሕዝብ ጥያቄ ለዓመታት ተድበስብሶ ዛሬ ላይ የገነፈለ መሆኑን አስታውሰው፣ ሕዝቡ ያነሳው ጥያቄ የተመለሰበት አግባብ አገርን እየመራ ካለ ፓርቲ የሚጠበቅ አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡

የወልቃይት ሕዝብ ለትግራይ ክልል ጥያቄውን ለማቅረብ በተፈጠረበት ጫና ባለመቻሉ ጉዳዩን ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት በተወካዮቹ አማካይነት እንዳቀረበ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ጥያቄው ሕጋዊ ተዋረዱን ጠብቆ ያልመጣ በመሆኑ ወደ ትግራይ ክልል በመጀመሪያ መቅረብ እንዳለበት በመግለጽ ተወካዮቹን እንደመለሳቸው አስታውሰዋል፡፡

የወልቃይት ሕዝብ በተወካዮቹ አማካይነት ያቀረበው ጥያቄ ምንም ይሁን ምን በፓርቲ ደረጃ በጥልቀት ተወያይቶ ውሳኔ ሊያገኝ ይገባል እንጂ፣ ጉዳዩን ወደ ትግራይ ክልል ለማቅረብ ምንም ዓይነት ጥረት እንዳልተደረገ በማስመሰል በድጋሚ መምራቱ ተገቢ አይደለም ይላሉ፡፡

የወልቃይት ሕዝብ ጥያቄ የማንነት አለመሆኑ በግልጽ እንደሚታይ፣ በመሆኑም የኢሕአዴግ ምክር ቤት እስከ መጨረሻው ድረስ ዘልቆ መወያየት ሲገባው ውይይቱን በማይገባ አቅጣጫ መርቶታል የሚል ግምት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ራሱ በቀጥታ በስም ዕውቅና የሰጣቸው የብሔረሰብ ማንነቶች በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47(1) ላይ መዘርዘራቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ እነርሱም ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሞ፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ ናቸው፡፡

ከላይ ከተገለጹት የብሔር ማኅበረሰቦች ውስጥ ያልወደቀ የብሔር ማኅበረሰብ ሕገ መንግሥታዊ መሥፈርቶቹን ሲያሟላ የብሔር ማኅበረሰብነት ዕውቅና እንደሚያገኝ አስረድተዋል፡፡ የሥልጤና የወልቃይት ሕዝቦች ጥያቄ የተመለሰውም በዚሁ አግባብ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ መረዳት የሚቻለው የብሔር ማኅበረሰብ የማንነት ጥያቄ ልዩ መሆንን ይጠይቃል ብለዋል፡፡

በመሆኑም የወልቃይት ተወካዮች የአማራ ብሔርተኝነት ጥያቄን ሊያቀርቡ እንደማይችሉ፣ ምክንያቱ ደግሞ የአማራ ብሔርተኝነት በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና ያገኘ በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡

ዕውነቱ ግን የወልቃይት ሕዝብ ጥያቄ ተዛብቶ ቀረበ እንጂ የጥያቄው መንፈስ የወሰን ጥያቄ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት የተነሳው ተቃውሞ መላው አማራን በሚያስብል ደረጃ ያነሳሳበት ምክንያትም የአማራ ክልል የወሰን ጥያቄን የሚመለከት በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

‹‹ስለዚህ የኢሕአዴግ ምክር ቤት የወልቃይት ጥያቄን በተሳሳተ ትርጓሜው ሊረዳው አይገባም፡፡ ምክር ቤቱ የፖለቲከኞች ስብሰባ እንደመሆኑና የተፈጠረው ቀውስም አገርን ሊበትን የሚችል በመሆኑ የጥያቄውን መንፈስና ይዘት ጠልቆ ማየትና አንጥሮ መመርመር ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

በዚህ መንገድ የሚታይ ከሆነ የወልቃይትን ጉዳይ የአማራ ክልልና የትግራይ ክልሎች ተነጋግረው እንዲፈቱት፣ የክልል ወሰን ለውጥ ጥያቄ የሚያስነሳም ከሆነ በሕገ መንግሥታዊ አካሄዱ መሠረት እንዲፈቱት የፖለቲካ ነፃነትንና ዴሞክራሲያዊነትን መፍቀድ ነበረበት ይላሉ፡፡

በዚህ መንገድ መሄዱ ሕዝብ አመኔታ እንዲኖረው ያደርጋል የሚሉት የሕግ ባለሙያው፣ ለትግራይ ክልል መመራቱ ውጤቱ ግልጽ በመሆኑ ግጭቱን ሊያቀጣጥለው ይችላል ብለዋል፡፡

የወልቃይት ሕዝብ አጠቃላይ ፍላጐትን መሠረት በማድረግ በየትኛው ክልል መተዳደር እንደሚፈልግ ማጣራትና በዚያው አግባብ መሠረት መወሰን ትክክለኛው መስመር መሆኑን፣ ሕገ መንግሥቱ በኢትዮጵያ እንዲሰፍን የሚፈልገውም ይኸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

‹‹ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ የወልቃይት ጉዳይ ወደ ትግራይ ክልል መመራቱ የአማራ ክልል በጉዳዩ ላይ ጥያቄ እንደሌለው ያስመስላል፡፡ ጥያቄውንም እንዳያነሳ ገደብ የሚጥል ያስመስለዋል፤›› ብለዋል፡፡

ፓርቲው ለፀጥታ ኃይሉ ያቀረበው ጥሪ ሕጋዊነት

ምክር ቤቱ ነሐሴ 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ‹‹በጥረታችሁና በከፈላችሁት መስዋዕትነት የተገኘውን ሰላም ለማደፍረስ የሚጥሩትን ኃይሎች የተለመደው ሕዝባዊ ባህሪያችሁ ሳይለያችሁ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ዘብ እንድትሆኑ፤›› ሲል ጥሪውን አቅርቧል፡፡

አስተያየታቸውን ለሪፖርተር የሰጡት የሕግ ባለሙያው አቶ ውብሸት ሙላት፣ የፀጥታ ኃይሉ ራሱን የቻለ ክልላዊና ፌዴራላዊ አወቃቀር እንዳለው ይገልጻሉ፡፡

የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት የክልሎችን ሥልጣን በሚዘረዝረው አንቀጽ 51 (6) እና 52 (2)(ሰ) ላይ እንደደነገገው የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት የየራሳቸውን የፖሊስ ተቋማት እንደሚያደራጁና ክልሎችም ይህንኑ ሥልጣናቸውን እንዳረጋገጡ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የፌዴራል ፖሊስ በክልል ውስጥ ወንጀልን ለመከላከል፣ ፀጥታ ለማስፈን የሕዝብን ደኅንነት ለማስጠበቅ በስፋት የሚገባባቸው ጊዜያት መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህንን በተመለከተም ከሕገ መንግሥቱ በተጨማሪ የፌዴራል መንግሥት በክልሎች ጣልቃ የሚገባበትን ሁኔታ ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 359/1995 መደንገጉን ይገልጻሉ፡፡

ክልሉ በራሱ አቅም ሊቋቋመው የማይችለው ወይም በክልሉ ሕግ አስከባሪ ተቋማት መቆጣጠር የማይችል የፀጥታ ችግር ሲያጋጥመውና ራሱ ክልሉ በጠየቀ ጊዜ፣ የፌዴራል ፖሊስ ወይም የመከላከያ ሠራዊቱ ሁኔታውን እንዲያረጋጋ ሊገባ እንደሚችል በሕግ መደንገጉን ገልጸዋል፡፡ ሌላኛው ደግሞ በክልሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተከናወነ መሆኑን የፌዴራል ፓርላማው ሲያረጋግጥ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን በመጥራትና የጋራ ስብሰባ በማካሄድ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ሊደረግ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

ሦስተኛው ሕጋዊ አሠራር ደግሞ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ ላይ ሲወድቅ ማለትም በክልል መንግሥታት ተሳትፎ ወይም ዕውቅና በትጥቅ የተደገፈ አመፅ አልያም ከሌላ ክልል ወይም ብሔር ጋር ችግር ሲፈጠር፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፌዴራል መንግሥቱን ጣልቃ እንዲገባ ሊያግዝ እንደሚችል በዚህም ወቅት የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊቱ ሊገቡ እንደሚችሉ ያስረዳሉ፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች ባልተሟሉበትና አሠራሮቹ በሌሉበት የፖሊስና የፀጥታ ኃይሉን ችግሮች በታዩባቸው አካባቢዎች ማሰማራት፣ ገለልተኛ እንደሆነ የሚቆጠረውን ወይም የሚፈለገውን የፀጥታ ኃይል በፖለቲካ እንዲፈረጅ ያደርጋል ሲሉ ወቅሰዋል፡፡

በተገለጹት ሕጋዊ አሠራሮች የመከላከያና የፌዴራል ፖሊስ አባላት እንዲሰማሩ የሚደረጉት በመንግሥት ውሳኔ እንጂ፣ በፓርቲ ጥሪ አለመሆኑን ባለሙያዎች ተችተዋል፡፡

የኢሕአዴግ ምክር ቤት በቅርቡ ባወጣው መግለጫ ለፀጥታ ኃይሉ ያቀረበው ጥሪም ተቀባይነት የሌለው፣ የፀጥታ ኃይሉ በፓርቲ እንደሚታዘዝ ለሕዝብ ትርጉም የሚሰጥና የሚሰማራው ኃይልም እንዲፈረጅ የሚያደርግ ነው ሲሉ ሌሎች ባለሙያዎችም ተችተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -