Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅየአራት ኪሎው ‹‹ምርኮኛ›› ወንበር

የአራት ኪሎው ‹‹ምርኮኛ›› ወንበር

ቀን:

ቢጫማ መልክ ያለው ይህ ወንበር፣ የዛሬን አያድርገውና በመጨረሻው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት (1923-1967) የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት (ፓርላማ) የእንደራሴ መቀመጫ ነበረ፡፡ በወንበሩ መደገፊያ ላይ የንጉሣዊው ሥርዓት ምልክት ዘውድና የቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ስም በምሕፃር ‹‹ቀኃሥ›› ተጽፎበት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ወታደራዊው ደርግ ፓርላማውን በ1967 ዓ.ም. በተቆጣጠረ በአምስት ዓመቱ፣ ኢሠፓአኮን (የኢትዮጵያ ሠርቶ አደሮች ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን) ሲያቋቁም ጽሕፈት ቤቱን ያደረገው በፓርላማው ሲሆን፣ ለአመራሮቹና ለአባላቱ መቀመጫ የሚሆን አዳዲስ ወንበር ለመግዛት አላስፈለገውም፡፡ ዘውዳዊውን ወንበር በሶሻሊስታዊ ኮሚኒስታዊ ወንበር ለመለወጥ የዘየደው፣ በዘውዳዊው ምልክት ላይ የኮሚኒስት ምልክትን መዶሻና ማጭድ መቀባት ነበር፡፡ እንዳሰበውም ተሳክቶለት እስከ ግብዓተ ሥልጣኑ ዘለቀ፡፡ 1983 ዓ.ም. የ17 ዓመቱ ሥርዓት ሲያከትምና ኢሕአዴግ መንበሩን ሲቆናጠጥ ወንበሮቹን ከፓርላማው ሲያስወግዳቸው፣ አንዳንዶቹ ወንበሮች ታላቁን ቤተ መንግሥት (ዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት) ደጃፍ ላይ ለሚጠብቁት በማረፊያነት እያገለገሉ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ከፊል እግራቸው በመሰበሩ ለቆራሌው መዳፍ ተዳርገው አንዱ ለሊስትሮ ተላልፏል፡፡ አራት ኪሎ ወወክማ አካባቢ የተገኘው ይህ በፎቶው ላይ የሚታየው ባለሦስት እግር ወንበር እርጅናው ሰበብ ሆኖ የመዶሻና ማጭድ ምስሉ ቀለሙ መልቀቁ ዎርጂናሌው ዘውዳዊ ምልክቱ እንዲታይ አድርጎታል፡፡

  • ሔኖክ መደብር

 ******

 አይ አንበሳ!

ያ ግርማ ውበቱ

ሰውነቱ፣

ያ ጎፈር አንገቱ

ግዙፍነቱ፣

ያ ቁጣ ድንፋቱ

ኃያልነቱ፣

. . . በነበረ ሲቀር

ሲታገት ጉልበቱ፤

በዕድሜ ሲሸበብ

ሲታቀብ ስሜቱ፤

ዧ! ይላል ከአውላላው፤

ለጥ! ይላል ከሜዳው፡፡

. . . ቢወረርም በዝናብ

በከበብም በንብ

‹‹ዝምምም . . .›› ነው፤

ዝም!

አጣጥሮ አያገሳ፤

ኃያል ክንዱን አያነሰ፤

አይ አንበሳ!

                  ******

ከጨረቃ ድል በኋላ

ሦስቱ የአሜሪካን ጠፈርተኞች ከጨረቃ ደርሰው፤ የጨረቃውን አፈር ዘግነው፤ ድንጋይ ለቅመው፤ እስከተመለሱ ድረስ፤ ውኃ እንደምትጠጣ ዶሮ ወደላይ አንጋጥጠን ሰማይ ሰማዩን ስንመለከት ከርመን ነበር፡፡ የአንዳንዶቹ አንገት በቅጭት ሕመም አልተያዘም ብለን በጨረቃ አንምልም፡፡ አጎንብሰው ይቅር ብለን በማለት እግዚኦ ሲሉ የከረሙም አሉ፡፡

ያም ሆነ ይህ ሰው እግሩን ጨረቃ ላይ አሳርፏል፡፡ አፈር ዘግኖ ጠጠር ለቅሞ ተመልሷል፡፡ ሰው ከአካባቢው መጥቆ የዓለምን አየር ቀዶ ጨረቃ ላይ በማረፍ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የንግድ መንኮራኩሮች፣ የዕረፍታቸውን ጊዜ ጨረቃ ለማሳለፍ የሚፈልጉትን ሰዎች ወይም ወሬ የቸገራቸውን ጋዜጠኞች የሚያመላልሱበት ጊዜ ይመጣ ይሆናል፡፡ (ለዚህ ጉዞ ተጓዥ ጋዜጠኞችን እያሠለጠንን ነን!)

ከመሄዱ በፊት ግን ወደ አዲስ ከተማ በሴይቸንቶ ተጉዞ፤ አንዳንድ ሰዎች፤ ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ጨረቃ ላይ በማረፉ የተሰማቸውን እንዲጽፍልን ጠይቀነው ነበር፡፡

ጥያቄ፡- ‹‹እሜቴ፤ ሰው ጨረቃ ላይ መውጣቱን ሰምተዋል?››

መልስ፡- ‹‹ጆሮ የማያሰማው ነገር የለም፡፡ ሰምቻለሁ፡፡››

ጥያቄ፡- ‹‹ሲሰሙ ምን ተሰማዎት ታዲያ?››

መልስ፡- ‹‹ምን ይሰማኛል? አበስኩ ገበርኩ ማለት ነው››

ጥያቄ፡- ‹‹እርስዎስ አባቴ?››

መልስ፡- ‹‹መስማቱን ሰምቻለሁ፡፡ ልጄ፤ ሰው ብርሃን ላይ ያርፋል ብለህ አንተስ እንዴት ታምናለህ››

ተጓዥ ጋዜጠኛችን፡- ‹‹አባቴ፤ ጨረቃ’ኮ ልክ እንደ መሬት ናት፡፡ ብርሃን አይደለችም፡፡ ጠፈርተኞቹ አፈር ይዘው መመለሳቸውን አልሰሙም እንዴ!››

መልስ፡- ‹‹አዬ ልጄ፤ እኔ ለእንደዚህ ያለው ቀልድ ጊዜ የለኝም፤ የፍርድ ቤት ቀጠሮ አለብኝ›› ብለውት፤ በመገረም ራሳቸውን እያወዛወዙ መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡ ተጓዥ ጋዜጠኞችንም እየተገረመ፤ የሚጠይቀው ጥያቄ ሌላ ጥያቄ ቢያስከትል ምን መልስ እንደሚሰጥ እያሰላሰለ ሲሄድ፤ አንድ ሸምገል ያሉ ሰው አገኘና፤ ሰው ጨረቃ ላይ አርፎ በመመለሱ የተሰማቸውን እንዲገልጹለት ጠየቃቸው፡፡

መልስ፡- ‹‹እግዚኦ ማለት ብቻ ነው፡፡ መጽሐፈ ዕዝራን አላንበብክም? ሰው ጨረቃ ላይ ከወጣ ምን ቀረ ብለህ ነው? ስምንተኛው ሺሕ ደርሷል፡፡ አትጠራጠር፡፡ ሰው የሚያጠፋውና ያው ራሱ ሰው ነው የሚሠራው፡፡ እግዜር ምድርን ሰጥቻችኋለሁ፤ ብዙ ተባዙባት፤ ምድርን ሙሏት ነው ያለን፡፡ ጨረቃ ላይ መውጣት ከትዕዛዙ ውጭ መሆን ነው፡፡ እግዚኦ ማለት ነው፡፡››

የዘመናችንን የቴክኖሎጂ ዕርምጃ በማድነቅ፤ እጹብ ነው፤ ድንቅ ነው ሲል የተለየን ተጓዥ ጋዜጠኛችን፤ አበስኩ ገበርኩ፤ እግዚኦ እያለ ተመለሰ፡፡

  • መነን መጽሔት (1961)

*****

 

የእንግሊዙ ልዑል ሃሪና የቀድሞው የአሜሪካ

ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ወግ

የእንግሊዙ ልዑል ሃሪና ባራክ ኦባማ በካናዳ የተገናኙት በመስከረም 2010 ዓ.ም. ነበር፡፡ ልዑል ሃሪ በቶሮንቶ ጀግኖችን፣ የታመሙና ጉዳት የደረሰባቸውን የመከላከያ አባላት ለማሰብ ባዘጋጁት ስፖርታዊ ጨዋታ ላይ ኦባማ ሲገኙ፣ ልዑሉ እንዲሁ በጨዋታ ብቻ አልሸኟቸውም፡፡ ይልቁንም የፕሬዚዳንትነት ሥልጣናቸውን ለዶናድ ትራምፕ ካስረከቡ በኋላ የመጀመርያ ነው የተባለውን ቃለ መጠይቅ አድርገውላቸዋል፡፡ የዚህኑ ቃለ መጠይቀ አርትኦት ለመሥራት ደግሞ የቢቢሲው ‹‹ሬዲዮ 4›› ቱዴይ ፕሮግራም ጋር የተቀመጡት ታኅሣሥ 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ነው፡፡ ቢቢሲም ኦባማ ከልዑሉ ጋር የነበራቸውን ወግ እንዲህ አቅርቦታል፡፡

‹‹የትራፊክ መጨናነቅ ገጥሞኝ አያውቅም ነበር፣ የትራፊክ መጨናነቅ ስፈጥር ነበር የቆየሁት፤›› የሚሉት ኦባማ፣ ባለቤታቸው ሚሼል ኦባማ ለፖለቲካው ዝንባሌ ባይኖራቸውም፣ ውሳኔያቸውን ይደግፉላቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

‹‹ጋብቻችን ጠንካራ ነው፣ አሁንም እርስ በርስ ጓደኛሞችም ነን፡፡ ልጆቻችን በሚገርም ሁኔታ ጉብል ሆነዋል፡፡ በጋራ መሥራታችንም ቤተሰቡን አንድ አድርጎታል፤›› ሲሉ ከሚሼል ጋር ያላቸው ግንኙነት በጠንካራ የጋብቻና ቤተሰባዊ ፍቅር ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የፕሬዚዳንት ትራምፕን ስም ባያነሱም፣ ዋይታውስን ከተሰናበቱ በኋላ አንዳንድ ችግሮች ማስተዋላቸውን፣ አገራቸው እንዴት ወደፊት እንደምትጓዝ እንደሚያሳስባቸው፣ በአጠቃላይ ሲታይ ግን ከሚጠብቁት በላይ የመንፈስ እርካታ ማግኘታቸውንም ተናግረዋል፡፡

 

የእንግሊዙ ልዑል ሃሪና የቀድሞው የአሜሪካ  ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ወግ

ራስን ከፕሬዚዳንትነት ውጪ ካለው ኑሮ ጋር ማጣጣም

ኦባማ ከፕሬዚዳንትነት መላቀቅን ‹‹እንግዳና ዕድል፤›› ይሉታል፡፡ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ጊዜ ሕይወታቸው በሙሉ በሩጫ የተሞላ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ላይ በዝግታ መብረር ጀምረዋል፡፡ ጉዳዮች ወዲያው መፈጸም የነበረባቸው ጊዜ አልፎ፣ አንድ ውሳኔ ባለማስተላለፋቸው የሰው ሕይወት ሊጠፋ ይችላል ከሚለው ጭንቀታቸው ዕፎይ ብለው መረጋጋትም ጀምረዋል፡፡ ‹‹አሁን ከሚሼል ጋር ተጨማሪ 45 ደቂቃ ማውራት ካለብኝ አወራለሁ፣ ቁርሴንም ተረጋግቼ እበላለሁ፤›› ይላሉ፡፡ ከመምራት ይልቅም ቀጣዩ ትውልድ እንዲመራ ማሠልጠን ላይ መጓጓታቸውን ያክላሉ፡፡

የማኅበራዊ ሚዲያው ተፅዕኖ

ልዑል ሃሪ፣ በሶሻል ሚዲያው ስለሚተላለፍ የውሸት ዜናዎች፣ ፅንፈኝነትና የሰዎችን ሰብእና የሚያቆሽሹ መረጃዎችን ለማስቆም እርሶ ቢሆኑ ምን ያደርጋሉ? ብሎ ጠይቆ ነበር፡፡

‹‹ቴክኖሎጂው የተለያዩ አመለካከቶችን ለማንሸራሸር አመቺ ነው፡፡ ማኅበረሰባችንን ለማጠልሸት መዋል የለበትም፡፡ የጋራ እሴት እንዲኖረን የሚያግዘን መሆን አለበት፡፡ መንግሥታት ይህንን በሕግ ስለማስገዛታቸው እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ሆኖም በመምራት ላይ ያለን ሰዎች የኢንተርኔት አጠቃቀም ምኅዳር ላይ አንድ የሚያደርገን አሠራር እንዲኖረን መሥራት እንዳለብን አምናለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ኦባማ በልዑል ሃሪ ሠርግ ተጋብዘዋል?

ኦባማና ልዑል ሃሪ ሲያወጉ የልብ ወዳጅ ይመስሉ ነበር፡፡ ሆኖም ልዑሉ በግንቦት 2010 ዓ.ም. ለሚፈጸመው የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ ኦባማን ይጋብዝ አይጋብዝ የተነፈሰው ነገር የለም፡፡ ሆኖም በእንግሊዝ ያሉ ሚዲያዎች ልዑሉ በሠርጉ ላይ ኦባማን ቢጋብዝ ትራምፕና እንግሊዝ ያላቸውን ግንኙነት ሊያሻክር ይችላል የሚል ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...