በጎንደር ከተማና አካባቢው ካለፈው ወር ጀምሮ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ከዚህ በኋላ እንደማይቀጥል መንግሥት ቢያስታውቅም፣ ተቃውሞው በአማራ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች እየተስፋፋ ተጨማሪ ቦታዎችን እያዳረሰ መሆኑን ምንጮች ገለጹ፡፡
ተቃውሞው በርከት ያሉ ወረዳዎችን እያዳረሰ መምጣቱንና ከባህር ዳር ደብረ ማርቆስ የሚወስደው መንገድ ከነሐሴ 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ መዘጋቱንና የትራንስፖርት አገልግሎት መስተጓጎሉን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ እስከ ማክሰኞ ነሐሴ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ምሽት ድረስ ተሽከርካሪዎች ከአዲስ አበባ እስከ ደብረ ማርቆስ ብቻ መሄድ ቢችሉም፣ ከደብረ ማርቆስ ወደ ባህር ዳር የሚወስደው መንገድ ዝግ ሆኖ መቆየቱ ተገልጿል፡፡
በምዕራብ ጎጃም በዱር ቤቴ ወረዳ ከነሐሴ 22 እስከ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. በተደረገው የተቃውሞ ሠልፍ ስምንት የሚደርሱ ግለሰቦች ከፖሊስ ጋር በተደረገው ግጭት ቆስለው ወደ ባህር ዳር ፈለገ ሕይወት ሆስፒታል መላካቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በአንፃሩ ነሐሴ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. በዚሁ ወረዳ የቀጠለው የተቃውሞ ሠልፍ ምንም ዓይነት ግጭት ሳይኖር በሰላም ማለፉን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ነሐሴ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ግጭት የተከሰተው ነዋሪዎች ወደ ሌላ ወረዳ በተሽከርካሪ ይጓዙ በነበሩ የፌዴራል ፖሊሶች ላይ መንገድ ለመዝጋት ባደረጉት ግብግብ መሆኑን የዓይን እማኞች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይም በዳንግላ ከነሐሴ 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ነሐሴ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ማምሻ ተቃውሞ መካሄዱ ተገልጿል፡፡ በሒደቱም በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የዓይን እማኞች እንደገለጹት በውል ያልታወቁ ግለሰቦችና የወረዳ አመራሮች ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፣ ስምንት ያህል መኖሪያ ቤቶች በእሳት ተቃጥለዋል፡፡
በሌላ በኩል በባህር ዳር ሁለተኛ ዙር የቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ ከነሐሴ 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ነሐሴ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. በከተማዋ የተለያዩ ሥፍራዎች የተኩስ ድምፅ መስማታቸውን በከተማዋ ነዋሪ የሆኑ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
በደብረ ማርቆስ ከነሐሴ 16 እስከ ነሐሴ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. የቆየ የቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ አድርገው ነበር፡፡ በዚህ ሳምንት ግን የተለየ የጎዳና ተቃውሞም ሆነ የቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማና ከፀጥታ ኃይሎች ጋር የሚያጋጭ ክስተት አልተስተዋለም፡፡ ነገር ግን በከተማዋ ከፍተኛ ቁጥር ያለውና ከወትሮው እጅግ የበዛ የፖሊስና የፀጥታ ኃይል መታየቱን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም ከሁለት ሳምንት በፊት የደብረ ማርቆስ ነዋሪዎች ጎዳና በመውጣት በመንግሥት ላይ ተቃውሞ ለማሰማት ቢሞክርም፣ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ግጭት ተፈጥሮ ተቃውሞው መገታቱ ይታወሳል፡፡
ፖሊስ ቁጥራቸውን በይፋ ያልተገለጸ ግለሰቦችንም በቁጥጥር ሥር ማድረጉ ተገልጾም ነበር፡፡ በቁጥጥር ሥር ውለዋል የተባሉት የደብረ ማርቆስ ነዋሪዎች የተወሰኑት እንደተለቀቁ ቢገለጽም፣ ከእስር የተፈቱት ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል እስካሁን የታወቀ ነገር የለም፡፡
እንዲሁም በተመሳሳይ ጎንደር ላይ በቀዳሚነት የተጀመረው የአደባባይ ተቃውሞና በኋላም ወደ ቤት ውስጥ የመቀመጥ የተቀየረው የተቃውሞ አድማ፣ አድማሱን በማስፋት ወደተለያዩ የክልሉ ወረዳዎች እየተዛመተ መምጣቱን መረጃዎች እያመለከቱ ይገኛል፡፡
በሞጣ፣ በደምቢያ፣ በቆላድባ፣ በጋይንት፣ በማቻከል፣ በአዲስ ዘመን፣ በቡሬ፣ በአርባያና በመሳሰሉት በርከት ባሉ ወረዳዎች የተቃውሞውን መስፋት የሚያሳዩ እንቅስቃሴዎችና ውጥረቶች የተስተዋሉ መሆናቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በየቦታው የሚስተዋሉት ተቃውሞዎች በተለይም በኦሮሚያ ከኅዳር ወር ጀምሮ፣ እንዲሁም በአማራ ክልል ባለፉት ጥቂት ወራት የተካሄዱትን ጨምሮ በመንግሥት ላይ እየተሰማ ያለው ተቃውሞ ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ ከተከሰቱት ተቃውሞዎች ከፍተኛ መሆኑ እየተነገረለት ነው፡፡