Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናመድረክ በአገሪቱ ለተከሰተው ችግር ኢሕአዴግ ኃላፊነቱን እንዲወስድ ጠየቀ

መድረክ በአገሪቱ ለተከሰተው ችግር ኢሕአዴግ ኃላፊነቱን እንዲወስድ ጠየቀ

ቀን:

  • ሕዝቡ ያነሳቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ አላገኙም ብሏል

ኢሕአዴግ በአገሪቱ ለተከሰተው ችግር ኃላፊነቱን እንዲወስድና ለጥፋቶቹ ሌላ ማመካኛ መፈለጉን እንዲያቆም፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ መድረክ (መድረክ) ጠየቀ፡፡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ምክር ቤት የሰጧቸው መግለጫዎች ሕዝቡ የሚያነሳቸውን መሠረታዊ ጥያቄዎች የሚመልሱ አይደሉም ብሏል መድረክ፡፡

መድረክ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ነሐሴ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው፣ ኢሕአዴግ የሕዝቡን ጥያቄዎች በአግባቡ አልተረዳም፡፡

‹‹ሕዝቡ ባካሄዳቸው ተቃውሞ ሠልፎች መጀመሪያ ላይ የአዲስ አበባን ክልል የማስፋፋቱ ዕቅድ እንዲሰረዝ፣ የወልቃይትና የቅማንት ሕዝቦች የማንነት ጉዳይ በአፋጣኝ እንዲወሰን፣ ወዘተ. የሚሉ ቀላል ጥያቄዎች ይነሱ ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ደግሞ በመንግሥትና በገዥው ፓርቲ ባለሥልጣናት እየተፈጸሙ ያሉት የመሬትና የንብረት ዝርፊያዎች እንዲቆሙና ብልሹ አስተዳደር እንዲወገድ የሚሉ ጥያቄዎች ቀረቡ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ጥያቄዎቹ ጥልቀት እያገኙ በመሄድ፣ በሠልፈኞቹ እየተነሱ ያሉት ባልመረጥናቸው አስተዳዳሪዎች አንገዛም፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻችን ይከበሩ፣ ነፃነታችን ታፍኗል፣ ፍትሕ እንፈልጋለን የሚሉ የመሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ጥያቄዎች ሆነዋል፤›› በማለት የተቃውሞዎቹን የለውጥ ሒደት የገለጸው የመድረክ መግለጫ፣ ኢሕአዴግ ምላሽ በማለት ያስቀመጠው መፍትሔ ከጥያቄዎቹ ክብደት አንፃር የማይመጥን እንደሆነና ከልምድም እንደታየው መፍትሔ የሚያስገኝ አይደለም ብሏል፡፡

መድረክ ከኢሕአዴግ መግለጫዎች ኃላፊነት ለመውሰድ መቸገሩን እንደተረዳ ገልጿል፡፡ በአንድ በኩል አባላቱ የመንግሥትን ሥልጣን በመጠቀም ለመክበር በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሕዝቡን በማስመረር ለፈጠሩት ችግር ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸውና በአዲሱ ዓመት ተጨባጭ ዕርምጃዎችን እንደሚወስድ ገልጾ፣ በሌላ በኩል ግን ለጥፋቶቹ ሌላ ማመሃኛ በመፈለግ በሕዝቡ እንቅስቃሴ ‹‹የጥፋት ኃይሎች›› የሚላቸው እጅ እንዳለበት መክሰሱን እንደ አብነት ጠቅሷል፡፡

ዕርምጃዎችን ለመውሰድ ግምገማን እንደ ቁልፍ መሣሪያ መጠቀሙም አዋጭ እንዳልሆነ መድረክ አመልክቷል፡፡ ‹‹የካድሬ ሹመኞቹ ግምገማና አስመሳይ ብወዛ የተለየ ዕርምጃ እንደማይሆን ይታወቃል፤›› ብሏል፡፡

መድረክ ከኢሕአዴግ መግለጫዎች ሕዝቡ አምባገነናዊ ሥርዓቱን ለመቃወም መነሳቱን ኢሕአዴግ እንዳልተገነዘበ መረዳቱንም ጠቁሟል፡፡ መድረክ ሕዝቡ በከፍተኛ መስዋዕትነት እየታጀበ እያካሄደ ያለውን የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ‹‹ልማት ያስከተለው ነው›› በማለት ኢሕአዴግ መግለጹ እንዳስገረመውም ገልጿል፡፡

‹‹ይህን እንቅስቃሴ ለማክሸፍ መንግሥት በሚወስዳቸው የኃይል ዕርምጃዎች በዓመቱ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ተገድለዋል፣ ሺዎችም ከሕግ አግባብ ውጪ ታስረዋል፣ እጅግ በርካታ ንብረት ወድሟል፣ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ተስተጓጉለዋል፣ በኢንቨስትመንትና በቱሪዝም እንቅስቃሴዎችም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል፤›› በማለት የደረሰውን ጉዳት የዘረዘረው መድረክ ኢሕአዴግ ለችግሮቹ ብቻዬን መፍትሔ አገኛለሁ ማለቱ ሌላ ጉዳት የሚያስከትል አካሄድ እንደሆነም ኮንኗል፡፡

‹‹የተነሱት የሕዝብ ጥያቄዎችም የችግሮቹ ፈጣሪ በሆነው ኢሕአዴግ መፍትሔ ያገኛሉ ብሎ መድረክ በጭራሽ አያምንም፤›› በማለትም መግለጫው ያትታል፡፡ በሕዝቡ እንቅስቃሴ የተፈጠረውን ያለመረጋጋት በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ሲረጋገጥ፣ ነፃ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ ምርጫ ሲካሄድ፣ መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ሲከበሩ፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ሲኖርና  በአገሪቱ ያሉ ባለድርሻ አካላት ሁሉ በሒደቱ ተሳትፎ ሲኖራቸው እንደሆነም መድረክ በመግለጫው አስረድቷል፡፡

መድረክ በአሁኑ ጊዜ ሕዝቡ በራሱ ተነሳሽነት በነቂስ በመውጣት እያቀረባቸው ያሉ ጥያቄዎች ላለፉት በርካታ ዓመታት መድረክን ጨምሮ በተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በሲቪል ማኅበረሰቡ፣ በሚዲያ ሰዎች፣ በምሁራንና በበርካታ ዜጎች ሲቀርቡ የነበሩ እንደሆኑም አስታውሷል፡፡ ይሁንና ምላሽ ስላላገኙ አሁን በሚቀርቡበት መልክ ለመምጣት አስገዳጅ ሁኔታዎች እንደተፈጠሩ ገልጿል፡፡

እነዚህ መሠረታዊ ጥያቄዎች ሕዝባዊ መሠረት እንዳላቸው እየታወቀ ‹‹ትምክህተኞች፣ ጠባቦች፣ ሻዕቢያዎች፣ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች፣ በአጠቃላይ የጥፋት ኃይሎች እየፈጠሯቸው ያሉ ችግሮች ናቸው፤›› በማለት መግለጹ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሠልፈኞችና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው የራሳቸው ግንዛቤ እንደሌላቸውና በሌሎች እንደሚታለሉ አድርጎ ስለሚቆጥር በሕዝቡ ላይ ያለውን ንቀት የሚያንፀባርቅ እንደሆነም መድረክ አስረድቷል፡፡

በመጨረሻም መድረክ በሺዎች የሚቆጠሩ የታሰሩ ዜጎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱና ሕዝቡም ላይ እየደረሰ ያለው ወከባ በአስቸኳይ ቁሞ፣ ሕዝቡ በሰላማዊ ሠልፍ ኢሕአዴግ ላይ ያለውን ተቃውሞ የማሰማት ሕገ መንግሥታዊ መብቱ እንዲከበር ጠይቋል፡፡ በተጨማሪም ለተፈጠረው የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ተጠያቂ በመሆኑ መንግሥት ካሳ እንዲከፍልና ሕዝቡ ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን የሚያጠራ ገለልተኛ ዓለም አቀፋዊ አካል እንዲቋቋም ጠይቋል፡፡ በአገሪቱ ያሉትን የዴሞክራሲ፣ የሰላምና መረጋጋት ጉዳዮችን በዘላቂነት ለመፍታት ኢሕአዴግ ከመድረክና ከሌሎች ሀቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በአስቸኳይ ድርድር ውስጥ እንዲገባም መድረክ አበክሮ ጠይቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመገረም እየተመለከቱ አገኟቸው]

ምንድነው እንዲህ ቀልብሽን የሳበው? ስለሰላም ኖቤል ሽልማት ዜና እየተመለከትኩ ነበር። እና...

የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መመሥረትና የአማራ ክልል ጥያቄ

አማራ የኢሕአዴግ አንዱ መሥራችና አጋር ከሆነው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ...

የሽንኩርት ዋጋ ሰማይ የነካበት ምክንያት ምንድነው?

ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት የሸማቾችን ኪስ ካስደነገጡ መሠረታዊ ከሚባሉ...

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ኤግዚቢሽን ማዕከልን እንዲያስተዳድር የተሰጠው ኮንትራት ለምን ተቋረጠ?

በአዲስ አበባ ከተማ ለንግድ ትርዒት ዝግጅት ብቸኛ በመሆን የሚጠቀሰው...