የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ከፀደቀ በኋላ 42 የፌዴራል ፀረ ሙስናና ሥነ ምግባር ኮሚሽን ዓቃቢያነ ሕግ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሲመደቡ፣ ሃያ ስምንቱ ሳይመደቡ መቅረታቸውን ምንጮች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡
እንደ ምንጮች ገለጻ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተመድበው ከነበሩት ሁለቱ እንደገና ወደ ፌዴራል ፀረ ሙስናና ሥነ ምግባር ኮሚሽን ተመልሰዋል፡፡
በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት የፀረ ሙስና የዓቃቤ ሕግ ሥራ ኮሚሽን ሥነ ምግባር ላይ እንዲያተኩርና ወደ ፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እንዲሄድ ተደርጓል፡፡ ፀረ ሙስና ኮሚሽንም ከመጪው አዲስ ዓመት ጀምሮ የረዥምና የአጭር ጊዜ ዕቅድና አሠራሮቹን መከለሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የተመደቡት ዓቃቢያነ ሕግ ምናልባትም ሌሎች የሕግ ባለሙያዎች በሚሠሩባቸው ዘርፎች ተመድበው በኮሚሽኑ እንዲቀሩ ሊደረግ እንደሚችል የሚገልጹት ምንጮች፣ ዓቃቤያኑ ሕጉ ያለመመደባቸው ምክንያቱ አለመታወቁን ይጠቁማሉ፡፡
ፍትሕ ሚኒስቴርን የሚያፈርሰውና በምትኩ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እንዲቋቋም የሚያስችለው ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ የቀረበው መጋቢት 13 ቀን 2008 ዓ.ም. ነበር፡፡ የረቂቅ አዋጁ አባሪ የሕግ ማስከበር ተግባር በዓቃቤ ሕግ የሚከናወን መሆኑን፣ ይህ የዓቃቤ ሕግነት ሥራ ግን ተበታትኖ በተለያዩ ተቋማት እየተሠራ እንደሚገኝ ይገልጻል፡፡ ከተቋማቱም ፍትሕ ሚኒስቴር፣ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ እንዲሁም የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን እንደሚጠቀሱ፣ ይህ ደግሞ ወጥነት እንደሚጎለው ይጠቁማል፡፡
ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በሕግ ጉዳዮች የፌዴራል መንግሥት ዋና አማካሪና ተወካይ ሆኖ እንደሚሠራ የሚገልጸው ረቂቅ የማቋቋሚያ አዋጁን የሕግ፣ የፍትሕና የአስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ ከሰማ በኋላ ሚያዝያ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. ፓርላማው አፅድቆቷል፡፡