Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየሠዓሊቷ ጉዞ በሦስቱ መንግሥታት

የሠዓሊቷ ጉዞ በሦስቱ መንግሥታት

ቀን:

ከወራት በፊት፣ ሠዓሊት ደስታ ሐጎስ ስቱዲዮዋ ውስጥ ጋዋን ለብሳ፣ ሸራተን አዲስ በየዓመቱ ለሚያካሂደው ‹‹አርት ኦፍ ኢትዮጵያ›› ዐውደ ርዕይ አሥረኛ ዙር የሚሆን ሥዕል እያዘጋጀች ነበር፡፡ ተንቀሳቃሽ ስልኳ ሲጠራ እጇ ላይ ያለውን ቀለም በጋዋኗ ጠርጋ አነሳች፡፡ የተደወለላት ከአምስት አሠርታት በላይ በሥነ ጥበቡ ላበረከተችው አስተዋፅኦ እውቅና እንደሚሰጣት ለመግለጽ ነበር፡፡ አንድ የሽልማት ድርጅት በሥዕልና ቅርፃ ቅርፅ ዘርፍ የዕድሜ ዘመን የሥዕል የከፍተኛ ክብር ተሸላሚ መሆኗን የሚያበስር ደብዳቤም ላከላት፡፡

‹‹በደብዳቤው፣ በሙያው እጅግ የተከበሩ መሆንዎን ስላረጋገጥን ለሽልማት ተመርጠዋል የሚለውን ሳነብ በጣም ነው የተደሰትኩት፡፡ ብዙ ሰዎች በተሰበሰቡበት ነበር የተሸለምኩት፤›› ስትል ትናገራለች፡፡ ከቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ እጅ ሽልማቱን ስትቀበል፣ ያላሰለሰ ጥረት በስተመጨረሻ እንደሚከፍል እያሰበች እንደነበር ትገልጻለች፡፡

ከዚህ ቀደም ከአገር ውስጥና ከውጭ ድርጅቶችም ተበርክቶላታል፡፡ ዓለም አቀፍ የወርቅ ሜርኩሪ ሽልማት በመላው አፍሪካ ጉባዔ፣ የዘር ኢትዮጵያ የክብር አምባሳደር፣ የአክሱም ሐውልት አስመላሽ ኮሚቴ የምስክር ወረቀትና ሌሎችም ሽልማቶች በመኖሪያ ቤቷ ሳሎን ውስጥ ይገኛሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ካዛንችስ ‹‹ሱፐር ማርኬት›› ኮከብ ሬስቶራንት የነበረበት አካባቢ ከሚገኘው አፓርታማ፣ መግቢያ አንስቶ ልዩ ልዩ አትክልት ይታያል፡፡ ‹‹ዋይልድ ብሉም››፣ ‹‹ሊሊ›› እና ሌሎችም የአበባ ዝርያዎች የሚያሳዩ ሥዕሎቿ መነሻ ለአትክልቱ ያላት ፍቅር ይመስላል፡፡ ‹‹ቪው ፍሮም ማይ ባልኮኒ›› በሚል ሥራዋ ከረዣዥም ፎቆች መካከል ግርማ ሞገሳቸው የገዘፈ ዛፎች ይታያሉ፡፡ ከመኖሪያ ቤቷ ባሻገር ያለውንና ጠዋት ማታ የምትመለከተውን ደን ያስተዋለ፣ ሥራዎቿ የሕይወቷ ነፀብራቅ መሆናቸውን ይረዳል፡፡

ተፈጥሮን ማድነቅ ደስታን ወደ ሥነ ጥበቡ ከገፋፏት ምክንያቶች አንዱ ነው፡፡ የተወለደችው ዓደዋ ከተማ ነው፡፡ አባቷ ተፈጥሮን ከመውደዳቸው ባሻገር ልጆቻቸውም ተፈጥሮን እንዲወዱ ለማድረግ ይሞክሩ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ ያደገችው አባቷ የተከሏቸውን የተለያዩ ዕፀዋት በመንከባከብ ነው፡፡ ትምህርት የጀመረችበት ንግሥተ ሳባ ትምህርት ቤትም የተፈጥሮ ሀብት የተቸረው ነው፡፡ ‹‹አባቴ የተማረም ሀብታምም ባይሆንም ብዙ የተከላቸውን አትክልት እንድንከባከብ ያደርግ ነበር፤›› ትላለች፡፡

ታዳጊዋ ደስታ ከአትክልቱ መካከል ትኩረቷን የሳበውን አበባ እየቀጠፈች ምሽት ላይ ወደ ቤት ትወስዳለች፡፡ አባቷ አበባ እንዳትቀጥፍና በምትኩ አበባ እንድትሥል ያበረታቷት ጀመር፡፡ ከአባቷ በተሰጣት ወረቀት ላይ በእርሳስ መሣል ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶም በሥነ ጥበቡ ዘለቀች፡፡

አባቷ ክራር ሲጫወቱ ማድመጥና ምሽት ላይ ጨረቃ መመልከትን የተመረኮዘው የጥበብ ሕይወቷ፣ ስመ ጥር ሠዓሊት ለመሆንና በተለያዩ አገሮች ዓውደ ርዕይ ከማሳየት አድርሷታል፡፡ ወንዶች የበዙበትን የ1960ዎቹና 70ዎቹ የሥነ ጥበብ ዓለም ሰብራ ገብታ ችሎታዋን ማስመስከር ችላለች፡፡ የሴት ሠዓሊያን የግል ዓውደ ርዕይ እምብዛም በነበረበት ዘመን፣ የግሏን ዓውደ ርዕይ በራስ ሆቴል ያሳየችው በ1962 ዓ.ም. ነበር፡፡

በ2007 ዓ.ም. 50ኛ ዓውደ ርዕይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም እስካሳየችበት ጊዜ ድረስ፣ በአሜሪካ (ካሊፎርኒያ ሉትረን ዩኒቨርሲቲ)፣ በኮርያ (13 ግሎባል ዩዝ ፌስቲቫል)፣ በካናዳ (ራይዝ ዊዝ ዘ ሰን አፍሪካን አርት ኤግዚቢት) እና በኢትዮጵያ ውስጥም በበርካታ ጋለሪዎች ሥራዋን አቅርባለች፡፡ በአስኒ ጋለሪ፣ በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴዝ፣ በሒልተን አዲስ፣ በላፍቶ ጋለሪና የቅርቡን የድንቅ ጋለሪ ዓውደ ርዕዮች መጥቀስ ይቻላል፡፡

አባቷ ታመው አስመራ የሚገኝ ሆስፒታል ከገቡ በኋላ፣ ትምህርት ከሁለተኛ ክፍል እንድትቀጥል የእናቷ እህት ልጅ ወደ አዲስ አበባ አመጧት፡፡ እቴጌ መነን አዳሪ ትምህርት ገባች፡፡ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷ ወደ ሥነ ጥበቡ ዓለም የበለጠ የቀረበችበት ነበር፡፡ በትምህርት ቤቱ የነበረውን የተደራጀ የሥነ ጥበብ ክፍል ተቀላቀለች፡፡ ዝንባሌዋን የተረዱ የሥነ ጥበብ መምሕሮቿ ሥራዎቿን አሰባስበው ለዓለም አቀፍ ውድድር ወደ ሕንድ ላኩት፡፡

‹‹በውድድሩ አንደኛ ወጥቼ ሽልማቱ በትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴር በኩል ወደ እቴጌ መነን ትምህርት ቤት መጣና ተቀበልኩ፤›› ትላለች፡፡ ዕድሜዋ እየጨመረ ሲሄድ በትምህርት ቤቱ የሥነ ጥበብ እንቅስቃሴዋ እየጎላ ሄደ፡፡ ዳይሬክተሯ ልዕልት ሒሩት ደስታ ለሠዓሊ አለ ፈለገሰላም ስለ ችሎታዋ ይነግሯቸዋል፡፡ አለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤትን እንድትቀላቀል የተደረገውም ያኔ ነበር፡፡ እድለኛ ሆና በኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ደማቅ አሻራ ያኖሩ ጥበኞች እስክንድር ቦጎስያንና ታደሰ ግዛው መምህሯ ሆኑ፡፡ በተለይም የሠዓሊና ገጣሚ ገብረክርስቶስ ደስታ አስተዋፅኦ ቀላል አልነበረም፡፡

‹‹ብሉ ኮምፖዚሽን›› እና ‹‹ኮምፖዚሽን›› የተሰኙ ሥራዎቿ የገብረክርስቶስ ተማሪ መሆኗን ከሚያመላክቱ መካከል ናቸው፡፡ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ቆይታዋ ቀላል እንደነበረ ትናገራለች፡፡ አንዲት ሴት ከወንድ ሠዓሊያን እኩል እንደምትሠራ ለመቀበል የተቸገሩ ጥቂት አልነበሩም፡፡  ‹‹የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ቃለ መጠይቅ ሲያደርጉልኝ እንዴት ወደ ሥነ ጥበብ ትገቢያለሽ? ብለው ሲጠይቁኝ ሴትና ወንድ እኩል እንደሆኑ ለማሳየት ብዬ እመልሳለሁ፤›› ትላለች፡፡ በእርግጥ ‹‹ሴት ስለሆነች ይከብዳታል›› የሚል የተዛባ አመለካከት ቢኖርም ሥራዋ ምስክር እንደሆናት ትናገራለች፡፡ ወቅቱ ከሥነ ጥበቡ በተጨማሪ በሥነ ጽሑፍና በቴአትር የታወቁ ሙያተኞች ተቀራርበው የሚሠሩበት መሆኑ የጥበብ አድማሷን እንዳሰፋው ታምናለች፡፡

የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤቱ ለሷና ለአምስት ወንድ ተማሪዎች ስቱዲዮ ሰጥቷቸው ነበር፡፡ ስቱዲዮውን ከሚያዘወትሩ ጸሐፍት መካከል መንግሥቱ ለማና ፀጋዬ ገብረመድህን ይጠቀሳሉ፡፡ ወጋየሁ ንጋቱና ደበበ እሸቱም ከስቱዲዮው አይታጡም፡፡ በነዚህ ወዳጆቿ ገፋፊነትም ከወጋየሁና ደበበ ጋር ቴአትር ሠርታለች፡፡ እሷና አምስቱ ወንድ ተማሪዎች ‹‹ዘ ያንግ አርቲስትስ ግሩፕ›› የሚል ዓውደ ርዕይ ያሳዩትም በዛው ወቅት ነበር፡፡

‹‹የመጀመሪያ ዓውደ ርዕይ ሲከፈት የትምህርትና ሥነ ጥበብ፣ የማስታወቂያ ሚኒስትርና ልዕልት ሒሩትም መጥተው ነበር፤›› በማለት ወቅቱን ትገልጻለች፡፡ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤቱ ለተማሪዎች የሚያቀርበው ግብአትና የሚያደርገው አጠቃላይ ድጋፍም አጋዥ እንደነበር ገልጻ፣ በ15 ዓመቷ የተቀላቀለችውን ትምህርት ቤት ከአምስት ዓመት በኋላ ተመርቃ መሰናበቷን ታስታውሳለች፡፡

በዲፕሎማ ከተመረቀች በኋላ በመምህርትነት ለመመደብ ከወንድ ምሩቃን ጓደኞቿ ጋር ወደ ትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴር አቀናች፡፡ ‹‹የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ላይ ‹ሴትና ወንድ እኩል ናቸው› ብለሻልና ከወንዶች ምሩቃን ጋር ተወዳድረሽ ትቀጠሪያለሽ አሉኝ፤›› ትላለች፡፡ ወቅቱ የተማሪዎች አብዮት የተፋፋመበት በመሆኑ የምትመደብበት ቦታ የማትሄድ ቢመስላቸውም፣ አስፋወሰን ኮምፕርሄንሲቭ የአሁኑ ምሥራቅ አጠቃላይ ትምህርት ቤት ስትመደብ በደስታ ተቀበለች፡፡

ወቅቱ አገሪቱ ንጉሡን በሚቃወሙ ተማሪዎች እየተነቃነቀች የነበረበት ጊዜ ቢሆንም ለጥቂት ወራት በሜካኒካል ድሮዊንግ መምህርትነት ሠራች፡፡ ‹‹ተማሪዎች ድንጋይ የሚወረውሩበት ያ ወቅቱን አስቸጋሪ ቢሆንም ተማሪዎቼ ጓደኞቼ ነበሩ፤›› ስትል ወቅቱን ትገልጻለች፡፡ ብዙም ሳትቆይ በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ሉተራን ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ዕድል አገኘች፡፡ ከትምህርት ቤቱ ከተመረቀች ከረዥም ዓመታት በኋላ ባለፈው ዓመት ካሊፎርኒያ ሄዳ ዓውደ ርዕይ አሳይታለች፡፡

ወደ ካሊፎርኒያ ለመሄድ በምትዘጋጅበት ወቅት በቤተሰቦቿ ከመጣላት ወንድ ጋር ተጫጨች፡፡ በትምህርቷ መግፋትና ከሥነ ጥበብ ጋር ተቆራኝታ የመኖር ሕልም ነበራትና ነገሩ ብዙም እንዳልተዋጠላት ታወሳለች፡፡ ሆኖም እጮኛዋም አሜሪካ ለትምህርት ይሄድ ነበርና ቀለበት አሰሩ፡፡ በካሊፎርኒያ ቆይታዋ ቅድሚያ የሰጠችው ግን ለትምህርቱ ነበር፡፡

‹‹በምንም ዓይነት መውደቅ የለብኝም ብዬ ጠንክሬ ተማርኩ፤›› በማለት ነው፡፡ የካሊፎርኒያ ቆይታዋን የምትገልጸው፡፡ ለአራት ዓመታት ከተማረች በኋላ በዲግሪ ተመረቀች፡፡ እጮኛዋን አግብታ ኢትዮጵያ ስትመለስ የጠበቃት የደርግ ዘመን ፖለቲካዊ ውጥንቅጥ ነበር፡፡ በወቅቱ የባለቤቷ ጓደኞች ሲገደሉ፣ ባለቤቷ ብቸኛ አማራጭ አድርጎ የወሰደው ወደ አሜሪካ መመለስን እንደነበር ትገልጻለች፡፡

ከባለቤቷ ጋር ከተለያየች በኋላ ልጇ ፌበንን ለብቻዋ ማሳደግ ጀመረች፡፡ ‹‹ወቅቱ ጨለማ ነበር፡፡ የደኅንነት ጉዳይም አስጊ ነበር፤›› ትላለች፡፡ አሁን የምትኖርበትን አፓርታማ ካገኘች በኋላ፣ በኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጀት እየሠራች ራሷንና ልጇን ማስተዳደሩን ተያያዘችው፡፡

ከአሥር ዓመት በኋላ በኢትዮጵያ የቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት ተቀጠረች፡፡ ከቀረጥ ነፃ ቁሳቁሶች ከሚሸጡባቸው ሱቆች በተጨማሪ ድርጅቱ በቱሪዝም ዘርፍ ጉልህ ሥራዎች ያከናውናል፡፡ የቱሪስት መዳረሻዎችን የሚያሳዩ ፖስተሮችና ባህላዊ ቁሳቁሶች ዲዛይን በማድረግ ለገበያ ያቀርባሉ፡፡

ደስታ፣ በዚህ ተቋም የሥነ ጥበበ ሥራዎች ክፍል መሥራት ቢያስደስታትም፣ ኑሮ ቀላል አልነበረም፡፡ ‹‹ያኔ በሳምንት 18 ሊትር ቤንዚን ብቻ ነበር የሚፈቀደው፡፡ ይኼ ለኔና ለልጄ መጓጓዣ አይበቃንም ነበር፤›› ስትል ከችግሮቹ አንዱን ትገልጻለች፡፡ በመንግሥት ደመወዝ እየኖሩ፣ ሥዕል እየሣሉ፣ የራሷንና የእህቷን ልጅ ማሳደግ ቢፈትንም፣ በጽናት እንደተወጣችው ታምናለች፡፡

ከልጇ ጋር በመሆን በወር ደመወዝ ምን እንደሚገዙ፣ የቱ እንደጎደለ፣ ያሰሉ ነበር፡፡ የወቅቱ ውጣ ውረድ ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን የሥነ ጥበብ ሕይወቷን የተፈታተነም ነበር፡፡ ‹‹ሳንሱር ስለነበር የምንሠራው ሥዕል አንዳች ትርጉም እየተሰጠው ችግር ውስጥ እንገባለን፤›› ትላለች፡፡ ስለዚህም ከሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌና ሌሎችም ዕውቅ ሠዓሊያን ጋር የቡድን ዓውደ ርዕይ ማሳየት ጀመረች፡፡

ዘመኑ ለሥነ ጥበብ ብቻ ሳይሆን፣ ለሥነ ጽሑፍና ለቴአትርም ነፃነት እንዳልነበረው ታወሳለች፡፡ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ በጥንቃቄ ማድረግ የግድ ስለነበር ከምትሠራቸው ሥዕሎች መካከል የምታስወግዳቸው እንደነበሩ ትናገራለች፡፡ በአንድ ወቅት ቤቷ ሲፈተሽ የተገኙ የሥዕል ቀለሞች ‹‹የኢሕአፓ መፈክር የተጻፈባቸው ናቸው፤›› መቧላን እንደ ምሳሌ ታነሳለች፡፡ ቢሆንም የከፋ ነገር ሳይደርስባት ወቅቱን አሳልፋለች፡፡

‹‹ኢትዮጵያውያን የጥበብ ሕዝቦች ነን፤›› የምትለው ደስታ ላሊበላ፣ አክሱምና ሌሎችም በርካታ የኢትዮጵያን ውጤቶችን በመጥቀስ ነው፡፡ ጠቢባን መሥራት የሚፈልጉትን እንዲያቀርቡ ግን ነፃነት እንደሚያስፈልግ ትገልጻለች፡፡ ‹‹እኛ ጥበብን ከውጭ አንማርም፡፡ ቴክኒክ ልንማር እንችል ይሆናል፤›› በማለት የአገሪቱን ጥበበኞች ተሰጥኦ ትመሰክራለች፡፡ በነፃነት መሥራት የሚለው ሐሳባኗ ወቅቱ ግን አብረው የሚሄዱ አልሆኑም፡፡ ሆኖም ሕይወት የትግል ሜዳ እንደመሆኗ እያንዳንዱን ውጣ ውረድ እንደ ትምህርት እንደምትወስደው ታስረዳለች፡፡ ደስታዋንም ሐዘኗንም በሥራዋ ማስፈርንም ትመርጣለች፡፡

‹‹በርንት ማችስ›› ከምትወዳቸው ሥራዎቿ አንዱ ነው፡፡ አንዲት ታዳጊ ሻማ ለማብራት ደጋግማ ብትሞክርም እየጠፋባት ተቸግራ ‹‹ሳበራው ሲጠፋ›› እያለች ስታነባ ያሳያል፡፡ ደስታ ይኼንን ሥዕል የሠራችው ቤቷ ወንበር ላይ ተቀምጣ ስታለቅስ ራሷን በመስታዋት ባየችበት ቅጽበት ነው፡፡

በሥዕሎቿ ፈተና የተጋረጠባቸው እንስቶች ይስተዋላሉ፡፡ ከተሞክሮዋ ተነስታ በፈተና የሚያልፉ ጠንካራ ሴቶችን ታሳያለች፡፡ ከሴቶች ይልቅ ለወንዶች በሚያዳላ ዓለም፣ ሴቶች የበለጠ መትጋት እንደሚጠበቅባቸው ታምናለች፡፡ በዚህ ረገድ ልጇም የሷን ፈለግ እንደተከተለችም ትገልጻለች፡፡

እሷ እንደምትለው፣ የመንግሥት ለውጥ ሌላውን የሥነ ጥበብ ምዕራፍ ከፈተላት፡፡ ሳንሱር መቅረቱ ያሻቸውን ሥዕል እንዲያሳዩ መንገድ መጥረጉን ትናገራለች፡፡ የመጀመሪያ የግል ዓውደ ርዕይ ስታዘጋጅ ‹‹ሺ ኢዝ ካሚንግ ባክ›› [ተመልሳ እየመጣች ነው] በሚል ዘመኑን በሚገልጽ ምሳሌያዊ ርዕስ ነበር፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ ከገባ በኋላ ብዙ ዓውደ ርዕዮች ታይተዋል፡፡ ጋለሪዎችም ተከፍተዋል፡፡ ሆኖም በቂ ግብአት የለም፤›› ትላለች የአሁኑን ወቅት ከቀደሙት ስታነጻጽር፡፡

ከአብስትራክት (ረቂቅ) ሥዕሎች በተጨማሪ ሪያሊስቲክ (እውናዊ) ሥራዎችም አሏት፡፡ ሴቶችና ተፈጥሮ ላይ ያተኮሩ ብዙ ሥራዎች ያሏት ሲሆን፣ ‹‹ሴት ስለሆንኩ የሴት ችግር ይገባኛል፤›› ትላለች፡፡ ሴትነት ማንኛውንም ዓይነት መሰናክል ከማለፍ እንደማያግድ በሥራዎቿ እንደምታሳይም ታክላለች፡፡

ብዙ ጊዜ ዓውደ ርዕይ ካሳየች በኋላ ከልጇና ከልጅ ልጇ ጋር በመሆን ከተማ የመውጣት ልማድ አላት፡፡ የማሪቱ ለገሰና የአስናቀች ወርቁ ሙዚቃዎችን ታዳምጣለች፡፡ የሙዚቃ ፍቅሯ ‹‹ትዝታ›› እና ‹‹ዘ ሚውዚሽያንስ›› ለተሰኙ ሥራዎቿ መነሻም ናቸው፡፡ ‹‹የምወደውን ነገር እያደረግኩ እየኖርኩ ነው፤›› ትላለች፡፡ ወጣት ሠዓሊያን አብራቸው ዓውደ ርዕይ እንድታሳይ ሲጋብዟት በደስታ ጥያቄያቸውን ትቀበላለች፡፡ ሙያዊ ተሞክሮዋን የምታካፍልበት መንገድ እንደሆነ ታምናለች፡፡ በርካታ ሴቶች ሥነ ጥበቡን ሲቀላቀሉ ማየት በመቻሏም ደስተኛ ናት፡፡

ሥራዎቿ በቢል ጌትስ ፋውንዴሽን፣ በሙለር ሪል ስቴት፣ በቢጂአይና ሌሎችም የአገር ውስጥና የውጭ ተቋማት ይገኛሉ፡፡ አቶ ክቡር ገናን ጨምሮ በርካታ ግለሰቦችም ሥዕሏን ገዝተዋል፡፡ ማን እንደገዛቸው ሳታውቅ የተሸጡ ሥዕሎቿ ባለቤቶች ከዓመታት በኋላ ደውለው ሥዕሏን በቤታቸው መስቀላቸውን ሲነግሯት የሚሰማትን ሐሴትም ትገልጻለች፡፡

ደስታ፣ በሥነ ጥበብ ሦስት መንግሥታትን አሳልፋለች፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ከተማረችበት አዳሪ ትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ሥነ ጥበብ ዩኒቨርሲው በንጉሡ መደገፉን ታወሳለች፡፡ ንጉሡ ትምህርት ቤቱን ከመጎብኘት፣ የኪስ ገንዘብ ለተማሪዎች ከመስጠት በተጨማሪ ለሥዕል የሚሆኑ ግብአቶችንም እንዲገዙ ያደርጋሉ፡፡ በደርግ ዘመን የነበረው ሳንሱር ሐሳብን በነፃነት ለመግለጽ ያገደ ነበር፡፡ አሁን ሳንሱር ባይኖርም ሠዓሊያን ግብአት እንደ ልብ አያገኙም ትላለች፡፡

 ‹‹ጥበብ ሰላም ይፈልጋል፡፡ ጥበብ ጥንካሬ ይፈልጋል፡፡ ጥበብ ሐቀኝነት ይፈልጋል፡፡ ብዙ ነገር ማየቴ ስላለኝ ነገር እንዳመሰግን አድርጎኛል፡፡ ሦስቱንም መንግሥታት በማየቴም ደስተኛ ነኝ፤›› ትላለች፡፡ ‹‹በሥነ ጥበብ ብቻ አይኖርም›› ከሚባልበት ጊዜ በርካታ ሠዓሊያት ያሉበት ወቅት በመድረሷም ትደሰታለች፡፡

ሁሉንም ነገር በቀና መንፈስ በማድረግ የምታምነው ሠዓሊቷ፣ ዛሬም ለረዥም ቀናት በስቱዲዮዋ ታሳልፋለች፡፡ በቅርብ ጊዜ ልዩነትም ዓውደ ርዕዮች ታዘጋጃለች፡፡ መንግሥት ለሠዓሊያን ደረጃውን የጠበቀ ግዙፍ ጋለሪ የሚከፈትበት ቦታ ቢሰጥና የኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ቢታይበት ምኞቷ ነው፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...