Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እንዳላየን አልፈን ነገር ብናበርድስ?

ሰላም! ሰላም! ባሻዬ ሬዲዮናቸውን ይዘው ጋቢያቸውን አጣፍተው ይለፈልፋሉ። ብርዱ ነው ግብሩ እንዳትሉኝ። ምን የማያስለፈልፈን ነገር አለ ዘንድሮን ሁሉም ለፍላፊ ሆነና አዳማጭ ጠፋ እንጂ። እና ጠጋ ብዬ ሳዳምጣቸው፣ “አንድ ቋንቋ አላግባባን ብሎ እየተደነቋቆርን ጭራሽ አዲስ ቋንቋ?” ይላሉ። ‘ለግዕዝ ቋንቋ ትኩረት አልተሰጠም’ የሚል ፕሮግራም ሥራዬ ብለው እያዳመጡ። ቋንቋው ቀርቶ ዜጋው ትኩረት የተሰጠው ይመስል፣ አሁን እስኪ በዚህ ሰዓት ይኼ ይወራል? ማለቴ ሰሚ ያለ ይመስል ለማለት ነው። እና ጠጋ ብዬ፣ “ባሻዬ ምናለበት ቢተውት? ይልቅ ገና ሳምንት ቀርቶታል። ምን አስበዋል?” ብዬ ወሬ ጀመርኩ። እሳቸው ግን የሰሙኝ አይመስሉም። “ሰማህ? ስማ! ስማ! ጀርመን እስከ ማስተርስ ድረስ የግዕዝ ቋንቋን እንደምታስተምር ታውቅ ነበር? ስማ! ስማ! ሰማህ? ለካ ጀርመኖች የደረሱበት የሕክምና ጥበብ በሙሉ የተገለበጠው በግዕዝ የተጻፉ ድርሳናትን መርምረው ነው? ስማ! ስማ!” እያሉ ልቤን ሲያወልቁት ቆዩና ድንገት ዕንባ በዓይናቸው ግጥም ብሎ ግድግዳውን ተደግፈው ዓይናቸውን ጨፈኑ።

ደንግጬ፣ “አመመዎ እንዴ? ሰው ልጥራ?” እያልኩ ስወራጭ፣ “ማንን ትጠራለህ ልጅ አንበርብር? ሰው ያለ ይመስል ሰው ልጥራ የምትለኝ። ሰው ቢኖርማ ሕመም በጅምላ ይታደለን ነበር? ቁጭት በደቦ እንሰፍር ነበር? ሰው ልጥራ? ሰው ያለ ይመስል፤” እያሉ ተደግፈውኝ ተነስተው ወደ መኝታ ክፍላቸው ገቡ። እኔም የመጣሁበትን የዶሮ ቅርጫ ሐሳብ በይደር ከድኜ ወደ ሥራዬ ከነፍኩ። በሽለላና በቀረርቶ ብቻ ሕዝብ ከእኔ በላይ፣ ባህል ከእኔ በላይ፣ ሥልጣኔ ከእኔ በላይ የሚልን  በዕንባና ከንፈር በመምጠጥ ይገሩታል እስኪ? እና ይኼ አሁን ባሻዬ ሳይገባቸው ቀርቶ ነው ወይስ እኔ ሐሞቴ ፈሷል? ያልፈሰሰበት ያለ ይመስል ምን ትጠይቀናለህ አትሉኝም?!

‘የሐሞትን ነገር ሐሞት ያነሳዋል’ እንበልና እንቀጥል እስኪ። የዘንድሮ ወኔ መቼም ከአፍ አያልፍም። “ሁሉም ወኔ ወኔ ይላል . . .” አለኝ በቀደም ዕለት የባሻዬ ልጅ። “ወይኔ! ወይኔ! ለማለት ፈልጎ ይሆናላ!” አለው እንደ እኔው ደላላ ወዳጄ እየቀለደ። ድሮም ሐሳብ ጠፍቶበት በስሜት ልጥ በአጀብ ለታሰረ ሰው ከዘራፍ ሌላ ምን መላ ይታየዋል ብላችሁ ነው? ናደው፣ ደርምሰው፣ ገንጥለው፣ እጨደው . . . ይላሉ። ዞሮ በራሳቸው የማይደረስ የሚመስላቸው ቀልደኞች ሁላ። ይኼን የምላችሁ ምክንያት ስላለኝ ነው። በቀደም  አንዱ መጣና ያውም ቤቴ ድረስ፣ “እኔ የምለው በቃ ለምን ዓባይን ለጊዜው አናቆመውም? በዚህ የኑሮው ውድነት ሜጋ ፕሮጀክቶቻችን ከቀጠሉ መጨረሻችን ምን እንደሚሆን አስበኸዋል?” አለኝ ብላችሁ ታምኑኛላችሁ? ይኼው እኔ ልሙት!

ቆይ ግን ደላላው አንበርብር ምንተስኖት እንኳን በዓባይ ግድብ፣ እንኳን በስኳሩ ስለጓዳዬ ስለቤቴ ብቻዬን እወስናለሁ እንዴ? ዘመኑ የእኩልነት ነው። ጠንካራ ሆነ አልሆነ የብዙ ሰዎች ሐሳብ ጥቂቶችን የሚያሸንፍበት ነው። በአጭሩ የዴሞክራሲ ነው። ካልጠፋ ሰው አምቶ ሊያሳማኝ ካልሆነ በቀር ቤቴ ድረስ መጥቶ የልማቱን ግስጋሴ ለጊዜው ካላቆምን በረሃብ እናልቃለን’ የሚለኝ በጤናው ይመስላችኋል? እኔ ስላልመሰለኝ፣ “በኋላ እንወያይበታለን አሁን ወደ ሥራ እየሄድኩ ነው፤” ብዬ ገፍቼ አስወጣሁት። እስኪ አስቡት። ጤነኛ ሰው ሥራ ይቁም፣ ራዕይ ይቁም ብሎ ቤታችሁ ድረስ ይመጣል? እኔ በአገሬ ቀልቡ ያልራቀው ሰው ሲል የማውቀው፣ “የስኳሩ ገንዘብ የት ደረሰ? አታመጡትም ወይ? ማን በላው? ተጨማሪ የህዳሴ ግድብ የሚገድብ ገንዘብ በሙሰኞች የሆድ፣ የግብዝነት፣ አደራ በማይከብደው የእኔ ብቻ ስልቻ ተሰልቅጦ ተበላ ብላችሁ ነግራችሁን እርማችሁን አውጡ ሳትሉን የት ጠፋችሁ?” ሲል ነው። አንዱ ደግሞ፣ “አንበርብር ወኔ የለውም፤” ብሎኝ አረፈው አሉ። ስሜት ብቻ አልሰለቻችሁም? ወይስ እኔ ብቻ ነኝ?

ሳላስበው አየር በአየር አንድ ሙሉ ኮንቴይነር መወልወያ አሻሻጥኩ። በዚህ አጋጣሚ ስገረም ወድቆ የተነሳ አንድ ሲኖትራክ ጆሮውን ተባለ። አለ እኮ እሱ። የኑሮን ነገር ለሚያውቀው መቼም የፈጣሪን ቸርነትና ረድኤት አይረሳውም። አንዱ፣ ‹‹የልማቱን ነገር ተውት። ሆድ ይፍጀው። እኛ ልማት ሲባል አገር ማልመት መስሎን እንጂ፣ ሰው እያመነመኑ አንዳንዶች ብቻ የሚለሙበት ልማት መሆኑን ቀደም ተብሎ ቢነገረን እኮ ወራጅ እንል ነበር በሰላም። እኛ ካልወረድን እነሱ አይወርዱማ። እና ኪሴ አበጥ ሲል ወደ ባንክ ሄድኩ። ላስገባ ነዋ። እህ ስል ሠልፍ። ምንድነው ስል ሲስተም የለም። እናንተ እንጂ እኛ ከጥንትም ሲስተም ነበረን። ስልቻ ውስጥ ጎተራ ውስጥ መሬት ቆፍረን እየቀበርን ብዙ ሺሕ ዓመታት ኖረናል። ይብላኝላችሁ ለእናንተ . . .›› ሲል እኔ ድግሞ ወደ ባሻዬ ሄድኩ።

እንዲህ ዓይነት አጋጣሚ ላይ ባሻዬ ናቸው ተቀብለው የሚያስቀምጡልኝ። አባት አያሳጣችሁ መቼም። ማለቴ ሲስተም ከሌለው አባት ምንም ማድረግ የማይችል ደግ አሳቢ ሰው ለማለት ነው። ኧረ ተውኝ ዘንድሮ። እና ባሻዬ ዘንድ ስደርስ ባሻዬ፣ ‹‹ምን ጉድ ነው ዘንድሮ?›› እያሉ ከሞባይላቸው ጋር ይታገላሉ። ‹‹ምነው ተበላሸች?›› ስላቸው፣ አድርጎት ነው። እኔ እኮ እንደ ድሮዬ በፖስታ ብጻጻፍ ይሻለኛል። ዝም ብላችሁ ነው እናንተ ልጆች ዕዳ የምታስገቡኝ፤›› ብለው ወቀሳ ጀመሩ። ‹‹ምን ሆኑ?›› ብዬ ስልካቸውን ሳየው የጽሑፍ መልዕክት ነው። ‘ይኼን ቁጥር በመላክ ስኬታማ ትዳር እንዲኖርዎት ያድርጉ። ስለመልካም ትዳር ወሳኝ እውነታዎችን እንነግርዎታለን . . .’ ይላል። ነገሩ ገባኝ። ባሻዬ ዘመኑ በፍጥነትና በቴክኖሎጂ ስም እያሳበበ አንዳንድ ነገሮችን ያለቦታቸው ሲያስቀምጣቸው አይመቻቸውም። ግን ችግሩ ባሻዬ ተመቻቸውም አልተመቻቸውም ዘመኑ ገንዘብ ማሳደጃ ነው። አይደለም እንዴ?

እና ለማረሳሳት የባጥ የቆጡን ስቀባጥር፣ ‹‹ወይ ትዳር? ትዳር እንዲህ በጽሑፍ መልዕክትና ጥቅስ ስምር ሲል። ኧረ ለመሆኑ ስኬትና ትዳር ምንድነው የሚያገናኛቸው? ቋንቋውን ከየት ነው የሚያመጡት?›› እያሉ ቆይተው አንድ ነገር አጫወቱኝ። ምናሉኝ፣ በአንድ ቀዬ ትዳራቸው የሚያስቀና አካላቸው ቢያረጅም ከሚስታቸው ጋር ያላቸው ፍቅር እያደር የወጣት የሆነ አዛውንት ነበሩ አሉ። ‹‹መቼም አበባ ካለ ንብ ያንዣብባል። ስኬታችሁና ደስታችሁ እያደር ምቀኛ ሲያፈራ ስታዩ ጽጌሬዳ ጉያ እሾህ ጠፍቶ እንደማያውቅ አስታውሱ። ምነው ስንት መርሳት የሚገባንን ነገር አንረሳም እያል በጎሳ እያበርን? የማይገነባ ነገር ከማስታወስ በሜዳ ሳር ጤዛ መመሰጥ ለኑሮ የሚበጅ ሚስጥር ያካፍላል ይባላል።

እና አንድ ቅናተኛ የአዛውንቱን ጎጆ ማፍረሻ መላ ሲፈልግ (መቼም ኑሮ ያልተወደደበት መሆን አለበት የቻፓ መላ ትቶ ፍቅር ማፍረሻ መላ ሲፈልግ ጊዜ የሚያጠፋው) ሰነባብቶ ማምለጫውንም አዘጋጅቶ (የቀናተኛም ብሩህ አለው ማለት ነው? ይታያችሁ እንግዲህ) ጠጋ ብሎ “አንቱ! ኧረ ይህች ሚስትዎ ትሄዳለች። ምን ሆና ነው?” ይላቸዋል። “አይተሃታል?” ይላሉ በቸልታ። “በዓይኔ በብረቱ . . .” ይመልሳል። ሰውዬው ሚስታቸውን ወዲያው ጠርተው፣ “ሰማሽ ስምሽን? ሂያጅ ነች ይሉሻል። ይኼው ወሬኛው ፊት ጠየቅኩሽ . . .” ሲሏቸው ሚስታቸውን ወሬኛው ጣልቃ ገብቶ፣ “አንቱ! እንዴት ያሉ ሰው ነዎት ግን? ትሄዳለች ስልዎ በሐሳብ ትነሆልላች ማለቴ እንጂ ትወሰልታለች መቼ ወጣኝ?” ብሎ ሲቆጣ፣ “በል ተወው ወንድሜ። ያለ ዛሬም ሐሳብ ሲዎሸም አልሰማሁ” ብለው አባረሩት። ላልደረሰበት የቃላት ጨዋታ አይመስልም አሁን ይኼ ታሪክ? እንዲያው እኮ!

በሉ እንሰነባበት። ከትናንት ወዲያ የጠፋ መብራት ዛሬ ገና መምጣቱ ነው። ትናንት የሄደችው ውኃችን ነገ ወይ ከነገ ወዲያ ትመጣለች ተብሎ ይጠበቃል። ለዝርዝሩ መብራትና ውኃ ልማትን አነጋግሩ አልላችሁም መቼስ? መልስ በሌለበት አገር ጥያቄ ማብዛት ራስን ማስጠቆር ብቻ እንደሆነ ላለፉት ሃያ ምናምን ዓመታት ዓይተነዋል። ዓይተነው ዓይተነው ዓይናችን አለመጥፋቱ፣ ሰምተነው ሰምተነው ጆሯችን አለመደንቆሩ በራሱ ተዓምር ነው። “ሰማይ ያለባላ መቆሙ ምን ያስደንቅሃል? እኛ አለን እኮ ያለምግብና ውኃ፣ ያለ በቂ ትራንስፖርት አቅርቦትና የዜጋ አክብሮት ወጥተን እየገባን ሠርተን እየገበርን የምንዘረፍ። ተዘርፈን የማንጠይቅ። ጠይቀን የማይሳካልን። መልሰን ራሳችን ራሳችንን የምንዘርፍ፤” አለኝ በቀደም ምሁሩ የባሻዬ ልጅ። እንግዲህ አስቡት ይኼን የሚያነፃፅርልኝ ካለባላ የቆመው ሰማይ ጋር ነው። ‘አንዳንድ ነገሮች ብዙ ያስገርሙኛል’ ነበር ድሮ ዘፈኑ። አሁን መገረማችሁ አስገርሟችሁ ዘፈን ካላደረጋችሁት በቀር፣ አንዳንድ ነገሮች ዛሬም የሚያስገርሟችሁ ከሆነ እናንተ ገና አዲስ ዳያስፖራ ናችሁ ማለት ነው። አብራራው ስትሉ ሰማሁ መሰለኝ። ‘ይቅርታ ሲስተም የለም፣ ትንሽ ይጠብቁኝ አደራ፣ አንድ ሳምንት ብቻ . . . ‘ እንዳልል አቅሙ የለኝም፡፡ ማን ነበር ‘የበረቱትማ እያዩሽ አለፉ . . .’ ያለው? እንዳላየን አልፈን ነገር ብናበርድስ? መልካም ሰንበት!

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት