Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊ ልጓም ያልተገኘለት የአገር ልጅ ስደት

 ልጓም ያልተገኘለት የአገር ልጅ ስደት

ቀን:

የጥቁርና የነጭ ሕዝቦችን ልዩነት ከቀለም በዘለለ እንደ ጌታና ሎሌ የገዘፈ ተቃርኖ እንዲኖራቸው አድርጎ የነበረው የባሪያ ንግድ በሁለቱ ዘሮች መካከል የገዥና ተገዢ ስሜት ፈጥሮ አልፏል፡፡ በባሪያ ንግድ ከከበሩ አገሮች መካከል አፍሪካውያንን ለ200 ዓመታት ያህል እንደ ሸቀጥ ስትሸጥ የነበረችው ፖርተቹጋል በግምባር ቀደምነት ትጠቀሳለች፡፡ በእነዚህ ሁለት ምዕት ዓመታት 4.5 ሚሊዮን አፍሪካውያን በባርነት ከአገራቸው እንዲወጡ ማድረጓ በታሪክ ሰፍሯል፡፡

 ጥቁር ሆነው በመፈጠራቸው ብቻ የነጮች የግል ንብረት ወይም ባለዕዳ ተደርገው ይቆጠሩ የነበሩ አፍሪካውያን ባርነት ተፈጥሯዊ ግዴታቸው እስኪመስል እንደ ሰው ሳይሆን እንደ ማሽን ይሠሩ፣ እንደ እንስሳም ይቆጠሩ ነበር፡፡ አንዱን ከአንዱ ለመለየት በጋለ ብረት ምልክት ያስቀምጡባቸው፣ መልዕክት ለማስተላለፍ ብቻ ከታንኳ ወደ ባህር ውስጥ ገፍትረው ይጥሏቸው እንደነበርም ተተርኳል፡፡

በባርነት የሚኖሩ ጥቁሮችን በጩቤ ወግቶ መግደልም በስፓርታውያን ዘንድ የወንድነት መለኪያ  ተደርጎ ይታሰብ ነበር፡፡ በጉዞ ላይ እያሉ በሚያጋጥማቸው አደጋ ሕይወታቸውን የሚያጡም ብዙ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1526 እስከ 1,867 ወደ አሜሪካ ከተጓዙ 12.5 ሚሊዮን ጥቁሮች መካከል አሜሪካ መድረስ የቻሉት 10.7 ሚሊዮኑ ብቻ ሲሆኑ፣ የተቀሩት በጉዞ ወቅት ሕይወታቸውን በግፍ ያጡ ናቸው፡፡

- Advertisement -

የነጮችን አንገት የሚያስደፋውን ታሪካዊ ክስተት ለማከም ሁሉም እኩል ነው በሚል መርህ ዓለምን ለመምራት ጥረት ቢደረግም የባሪያ ንግዱ ዳግም መፈጠሩ ከሰሞኑ ተሰምቷል፡፡ የዚህኛውን ለየት የሚያደርገው ይህንን ሰብዓዊነት የጎደለው ድርጊት የሚፈጽሙት አፍሪካውያንም ጭምር መሆናቸው ነው፡፡

በሕገወጥ መንገድ ወደ አውሮፓ የሚገቡ አፍሪካዊ ሕገወጥ ስደተኞች በአማፂያን መመራት ከጀመረች ዓመታት ያስቆጠረችውን ሰሜን አፍሪካዊቷን ሊቢያ ያቋርጣሉ፡፡ ነገ ያልፍልናል በሚል ተስፋ ወደ ሊቢያ ድንበር የሚገቡ ስደተኞች አውሮፓ ሳይደርሱ ባህር ውስጥ ሰጥመው ይሞታሉ፡፡ በረሃ ላይ በውኃ ጥም ሊሞቱ አልያም በአውሬ ሊበሉ ይችላሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ እንደ ዕቃ ለባርነት በጨረታ ይሸጣሉ፡፡ በሊቢያ የአንድ አፍሪካዊ ዋጋ እስከ 400 ዶላር ይደርሳል፡፡ ከሌሎቹ የተሻለ አቋም ላይ የሚገኝ አንድ አፍሪካዊም የሚሸጥበት ዋጋ አንፃራዊ ልዩነት አለው፡፡ በጊዜ ማሽን ተመልሰው በአህጉሪቱ የነበረውን የባሪያ ንግድ የሚታዘቡ ያህል በሊቢያ የሚከናወነውን የባሪያ ጨረታ መጧጧፉን ሲኤንኤን በመስኮቱ ያስቃኘው በቅርቡ ነው፡፡

በሕገወጥ መንገድ ወደ አውሮፓ በተለይም ወደ ጣሊያን ለመግባት የሞት ሽረት ትግል ከሚገጥሙ አፍሪካዊ ስደተኞች መካከል ኢትዮጵያውያን ይገኙበታል፡፡ የሚደርስባቸውን ኢሰብዓዊ ድርጊት ተቋቁመው ወደ አውሮፓ የሚገቡት ከቁጥር አይገቡም፡፡ አብዛኞቹ በጉዞ ላይ እንዳሉ ሕይወታቸውን ያጣሉ፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ባህር ውስጥ ሰጥመው የሞቱ ዜጎች ሁነኛ ማሳያ ናቸው፡፡ በሊቢያ በአይኤስ አንገታቸው ተቀልቶ በግፍ የሞቱት ኢትዮጵያውያን፤ ሊቢያን ማቋረጥ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ አሳይቷል፡፡  

መና ሆነው የሚቀሩት፣ የዓሳ ነባሪ እራት የሚሆኑት በምዕራብ፣ በደቡብና በምሥራቅ የመውጫ በሮች በመጠቀም ነው፡፡ ወደ አውሮፓ ለመግባት የሚያደርጉት ጉዞ የሚጀምረው የምዕራብ መውጫ በር በሆነው መተማና ሑመራ ነው፡፡ ከዚያም በሱዳን በኩል አድርገው ወደ ሊቢያ፣ ግብፅ ይገባሉ፡፡ መዳረሻቸው ወደ ሆነው አውሮፓ ለመግባት በመርከብና በጀልባ ባህር ማቋረጥ ይኖርባቸዋል፡፡

ከበረሃው፣ ከባርነቱ፣ ከግድያው፣ ከአስገድዶ መደፈሩና ሌሎችም በጎዞ ሒደት ላይ ከሚያጋጥሟቸው አደጋዎች የተረፉ በዚህ ከባድ ጉዞ ባህር ውስጥ ሰጥመው ሊያልቁ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡

ግፍ የሚውሉባቸው ገና ከአገር ከመውጣታቸው ጀምሮ ሲሆን፣ ሴት ኢትዮጵያውት በጎረቤት አገሮች በተለይም በሱዳን ከፈቃዳቸው ውጪ በወሲብ ንግድ ለመሰማራት ይገደዳሉ፡፡ አደገኛ በሚባለው በግብፅ በኩል በሚደረገው ጉዞ ስደተኞች ተገደው የአካል ክፍላቸው እንደ ዳቦ ተቆርጦ ሊወሰድ ይችላል፡፡

ብርቱ ሆኖ የተገኘ በሚያሸንፍበት በዚህ የጉዞ ሒደት በርካቶች ከንቱ ሆነው ይቀራሉ፡፡ ያሰቡበት ቦታ የሚደርሱት ጥቂት ብርቱዎች አልያም ዕድለኞች ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2016 እስከ መስከረም 30 ጣልያን መድረስ የቻሉ ኢትዮጵያውያን 3,109 ናቸው፡፡

እ.ኤ.አ. በ2015 የጣልያንን ድንበር ተሻግረው ከገቡ 182,436 ሕገወጥ ስደተኞች መካከል 22 በመቶ የሚሆኑት ከአፍሪካ ቀንድ የተነሱ ናቸው፡፡ ከዚህ ውስጥ 20,718 ኤርትራውያን፣ 3,447 ኢትዮጵያውያን እንደነበሩ የዓለም አቀፍ የስደት ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡ የፖለቲካ ጥገኝነት የሚጠይቁ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ኤርትራዊ ነን ብለው የሚያስመዘግቡበት አጋጣሚ እንዳለም ተሰምቷል፡፡

በደቡባዊ መስመር የሚደረገው ጉዞ ደግሞ በሞያሌ በኩል ወደ ኬንያ የሚገባበት ነው፡፡ የዚህ መስመር መዳረሻ ደቡብ አፍሪካ ስትሆን፣ እዚያ ለመድረስ የታንዛኒያ፣ የማላዊና የሞዛምቢክን ድንበሮች ማቋረጥ ግድ ይላል፡፡ ከ17,000 እስከ 20,000 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንና ሶማሊያውያን ዜጎች በየዓመቱ ይህንን መስመር ተጠቅመው ወደ ደቡብ አፍሪካ ይገባሉ፡፡ በዚህ የጉዞ ሒደት ከ500 እስከ 600 የአሜሪካ ዶላር እንዲከፍሉ ይጠየቃሉ፡፡ ደቡብ አፍሪካ ከደረሱ በኋላ ያለሙትን ሕይወት መኖር የሚችሉ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ዕድል ጀርባዋን ያዞረችባቸው ከፍተኛ የሆነ የጉልበት ብዝበዛ ይደርስባቸዋል፡፡ ከዚህ ሲያልፍም የግዳጅ ሥራዎችን ያለምንም ክፍያ እንዲሠሩ ይደረጋል፡፡

በምሥራቃዊ መውጫ በሮች ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የሚደረገው ጉዞም እንዲሁ በፈተናዎች የታጠረ ነው፡፡ ከኦቦክ ወደ ጅቡቲ ከዚያም ቦሳስ አጠገብ የሚገኙ የባህር ዳርቻ ላይ የሚገኙ ከተሞችን በማቋረጥ፣ ፑንት ላንድ፣ የመን በመጨረሻም ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ የሚያስገባ መስመር ነው፡፡ በዚህ ጉዞ ስደተኞች ለሕገወጥ የድንበር አሻጋሪዎች ከ350 እስከ 550 የአሜሪካ ዶላር እንዲከፍሉ ይደረጋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2016 በመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት ብቻ 85,000 ኢትዮጵያውያን ይህንን መስመር ተከትለው የመን መድረሳቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን ይፋ ያደረገው ሪፖርት ያሳያል፡፡ በሪፖርቱ መሠረት እ.ኤ.አ. ከ2012 እስከ 2015 ድረስ ብቻ 290,000 ኢትዮጵያውያን ሕገወጥ ስደተኞች የመን ደርሰዋል፡፡

የሰሜን መውጫ በሮችን በመጠቀም በሕገወጥ መንገድ ወደ እስራኤል የሚገቡ ስደተኞች ቁጥርም ቀላል አይባልም፡፡ እ.ኤ.አ. በ2011፣ ከአፍሪካ ቀንድ የተነሱ 17,000  ስደተኞች የእስራኤልን ድንበር አቋርጠዋል፡፡ እስራኤል ሕገወጥ ስደተኞች ወደ ግዛቷ እንዳይገቡ ድንበሯን በግንብ ከዘጋች በኋላ እ.ኤ.አ. በ2016 ወደ እስራኤል መግባት የቻሉ ሕገወጥ ስደተኞች 11 ብቻ ነበሩ፡፡

በፌዴራል ጠቅላይ አቃቢ ሕግ የሕግ ጥናት ማርቀቅና ማስረጽ ዳይሬክቶሬት አቃቢ ሕጉ አቶ አወል ሱልጣን እንደሚሉት፣ በዚህ መስመር የሚያልፉ ወንድ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እዚሁ ጎረቤት አገር ጅቡቲ በግዴታ ሥራ እንዲሰማሩ ይደረጋሉ፡፡ ከዚህ ሲያልፍም በቤት ሠራተኝነት፣ በተላላኪነት እንዲሁም በሌብነትና በልመና እንዲሰማሩ ይገደዳሉ፡፡

ያልፍልኛል በሚል ባልተጨበጠ ህልም አገራቸውን ለቀው የሚወጡ ሕገወጥ ስደተኞች የመደፈር አደጋ ያጋጥማቸዋል፡፡ እንደ ምግብ፣ አልባሳት፣ መጠለያ ያሉ መሠረታዊ ፍላጎታቸው ላይሟላላቸው፣ እንደ ዕቃ በዕዳ መያዣነት ለሌላ ሦስተኛ ሰው ተላልፈው ሊሰጡም ይችላሉ፡፡ በአጠቃላይ ስደት በርካቶች እንደ ሊቢያው በቀጥታ ጨረታ ለባርነት የሚሸጡበት ወይም በሥውር ለሞትና ለከፋ ብዝበዛ የሚዳረጉበት የሕገወጦች መድረክ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ከቀናት በፊት ለጋዜጠኞች ባዘጋጀው የሁለት ቀናት ሥልጠና ላይ በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ውይይት ተካሂዶ ነበር፡፡ በወቅቱ ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኙት ባለሙያ ሕገወጥ ስደትን አስመልክቶ ያለውን ችግርና የሕግ ማዕቀፍ በስፋት አብራርተዋል፡፡ ‹‹ገንዘብ ስጠኝ የሆነ ነገር መሥራት እፈልጋለሁ ብሎ ልጅ ሲጠይቅ የለኝም አርፈህ ቁጭ በል የሚል ወላጅ ለስደት ሲሆን ቤት ንብረቱን ሸጦ ገንዘብ ይሰጣል፤›› የሚሉት ባለሙያው፣ ለሕገወጥ ስደተኞች ቁጥር መብዛት ማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው በስደት ያልፍልኛል የሚል ሥር የሰደደ አመለካከቱ የፈጠረው ችግር መሆኑን ይናገራሉ፡፡

የሕዝብ ቁጥር መብዛት፣ ድህነት፣ ሥራ አጥነት፣ የመሬት እጥረት፣ የአመለካከት ችግር፣ የአቻና የቤተሰብ ግፊት ለሕገወጥ ስደት ቀዳሚ ምክንያቶች ናቸው፡፡ በአይኦኤም ኢትዮጵያ የብሔራዊ ፕሮግራም ኦፊሰሯ ወ/ሮ ልዩነት ደምስስ በአፍሪካ 70 በመቶ የሚሆኑ ወጣቶች ሥራ አጥና ዝቅተኛ ክፍያ በሚያስገኙ ሥራዎች የተሰማሩ መሆናቸውን ይህም ስደትን እንደ አማራጭ አድርገው እንዲያስቡ እንደሚያደርጋቸው ይናገራሉ፡፡ ለእነዚህ ሥራ አጥና ኑሯቸውን የሚደግፉበት በቂ ገንዘብ ለማያገኙ ወጣቶች ተገቢው ትኩረት ተደርጎ መሥራት ካልተቻለ የችግሩ ጥልቀትና አሳሳቢነት ከዚህ የበለጠ የሚሆንበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡ እንደ ኦፊሰሯ ገለጻ፣ እ.ኤ.አ. በ2045 በአህጉሪቱ የሚገኙ ወጣቶች ቁጥር በሁለት እጥፍ አድጎ 400 ሚሊዮን ሲደርስ ምላሽ ለመስጠት ነገሮች ከባድና ውስብስብ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ስደተኞቹ ከአገር ውስጥ በሚወጡባቸው መውጫ በሮች አካባቢ የሚፈጸመው የወንጀል ድርጊትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ይገኛል፡፡ በተለይም ከአፍሪካ ቀንድ ደቡባዊ መውጫ በሮችን ተጠቅመው ስደተኞችን ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚያስገቡ ደላሎች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ በዚህ መስመር ለሚደረገው ጉዞ ስደተኞቹ እንዲከፍሉ የሚጠየቀው ዋጋም እ.ኤ.አ. ከ2009 እስከ 2016 ባሉት ዓመታት ውስጥ የ69 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ወ/ሮ ልዩነት በሪፖርታቸው አሳይተዋል፡፡ ዝቅተኛ የነበረው የሴት ስደተኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚገኝ ሲሆን፣ ከጠቅላላው ስደተኞች መካከል የሴት ድርሻ ወደ በዓለም 48 በመቶ ከፍ ማለቱን ይናገራሉ፡፡

ዜጎች ሕገወጥ ስደትን ብቸኛው አማራጫቸው አድርገው እንዲያስቡ ከሚያደርገው የቤተሰብና የአቻ ግፊት በተጨማሪ ደላሎችና ሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህ ሕገወጥ የጉዞ ሰንሰለት ውስጥ ዋና ተዋናይ በመሆን በዜጎች ላይ ወንጀል እንዲፈጸምባቸው የሚያደርጉሕገወጦች የሚጠየቁበት፣ የዜጎች ሕጋዊ እንቅስቃሴ የሚገዙበት ሁለት አዋጆች አሉ፡፡

አንደኛው የኢትዮጵያ የውጭ አገር ሥራ ሥምሪት አዋጅ ቁጥር 923/2008 ነው፡፡ ይህ አዋጅ የአሠራርና የአደረጃጀት ክፍተት ያለበትን የቀድሞውን አዋጅ 623/2001 የተካ ነው፡፡ ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኙት ባለሙያ እንደሚገልጹት በሥራ ላይ ያለው አዋጅ የውጭ አገር ሥራ ሥምሪት ተቋማዊ አመራር፣ ኤጀንሲዎች፣ አሠሪዎች፣ ሠራተኞች፣ ወኪሎች አጥፍተው ሲገኙ ስለሚወሰዱባቸው ዕርምጃዎች በዝርዝር የያዘ ጭምር ነው፡፡

በኢትዮጵያ መንግሥትና በተቀባይ አገሮች መካከል የሁለትዮሽ የሥራ ሥምሪት ስምምነት መሠረት ዜጎች ሕጋዊ ሒደቶችን ጠብቀው እንዲሄዱ የሚያደርግ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ጆርዳን፣ ኩዌት፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ካታር ከኢትዮጵያ ጋር የሁለትዮሽ የሥራ ሥምሪት ስምምነት ኖሯቸው በጋራ በመሥራት ላይ የሚገኙ አገሮች ናቸው፡፡ እንደ ባለሙያው ገለጻ፣ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶችና ከኢራን ጋር በቀጣይ ስምምነቱን ለመፈረም እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደተኞችን በሕገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን የተመለከተው አዋጅ ቁጥር 909/2007 በሰባት ክፍሎች የተከፋፈለና 50 አንቀጾችን የያዘ ነው፡፡ ከተከለከሉ ዕጾች ዝውውር ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ እየተስፋፋ የመጣውን የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀልን መከላከልና ጥፋተኞች እንዲቀጡ ማድረግ ዓላማው ነው፡፡ እንደ አቶ አወል፣ የወንጀሉ ፈጻሚዎች አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ መምጣት፣ የሚፈጸምበት ዘዴ፣ ኢንቨስት የሚደረግበት ገንዘብ ከፍተኛ መሆንና ወንጀሉ የሚፈጸመው በተደራጁ የወንጀል ቡድኖች መሆኑ ወንጀሉን ውስብስብና በቀላሉ የማይፈታ አድርጎታል፡፡

 በዚህ ወንጀል የሚሳተፉ ወንጀለኞችን በሕግ እንዲጠየቁ የማድረግ ሥራም በስፋት እየተሥራ ይገኛል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2013 እስከ 2016 ባሉት ጊዜያት ከ2,000 በላይ የሚሆኑ ግለሰቦች ተከሰዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል 403 የሚሆኑ ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ክስ ቀርቦባቸው 266ቱ ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2015 ብቻ 366 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው 54ቱ ጥፋተኛ ተብለው መታሰራቸውን ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኙት ባለሙያ አብራርተዋል፡፡

በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ያለፍላጎታቸው ለወሲብና ለጉልበት ብዝበዛ በሚዳረጉበት በዚህ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር በርካቶች ለሞት ይዳረጋሉ፡፡ ኩላሊታቸው ተወስዶ በጥቁር ገበያ ሊሸጥ ይችላል፡፡ መቀጣጫ እንዲሆኑ ተብሎ በግፍ የሚገደሉም አሉ፡፡ በሕይወት እንዳሉ ውሻ እንዲበላቸው የሚደረጉም ያጋጥማሉ፡፡ በሰውነታቸው ላይ ሰዋዊ መብታቸው ተገፎ እንደ ዕቃ በጨረታ የሚሸጡበት የባሪያ ንግድ እንዲመለስ ያደረገው ይህ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርና ድንበር የማሻገር ወንጀል የሰው ልጅ ገንዘብ ለማግኘት ሲል ምን ያህል ርቀት ሊሄድ እንደሚችል የሚያሳይ ነው፡፡

በከፍተኛ ደረጃ በመስፋፋት ላይ በሚገኘው በዚህ ወንጀል ተከሰው ጥፋተኛ የሚባሉ ወንጀለኞች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2008፣ 5,212 ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ተከሰው 2,983ቱ ጥፋተኛ ተብለው ተቀጥተዋል፡፡ በዚሁ ዓመት 30,961 ዜጎች ተጠቂ ተብለው ተለይተዋል፡፡ ይህ ቁጥር እ.ኤ.አ. በ2011 ወደ 7,909 ተከሳሾች፣ 3,969 ጥፋተኞችና ወደ 42,291 ተጠቂዎች  አድጓል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2015 ደግሞ 18,930 ሕገወጦች ሲከሰሱ፣ 6,609 የሚሆኑት ጥፋተኛ ተብለው ቅጣት ተጥሎባቸዋል፡፡ 72,823 ተጎጂዎችም ተለይተዋል፡፡

በርካቶችን ለስቃይ እየዳረገ የሚገኘው ሕገወጥ ስደት በሕጋዊ መንገድ ሲደረግ በአንፃሩ የተሻለ የኢኮኖሚ አማራጭ ይሆናል፡፡ እንደ ህንድና ፊሊፒን ያሉ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በሕጋዊ ስደት መጠቀም ችለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ሦስት ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ከአገራቸው ውጪ ይኖራሉ፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ወደ አገር ውስጥ የሚልኩት የውጭ ምንዛሪም ከአገሪቱን ጠቅላላ ምርት የሰባት በመቶ ድርሻ አለው፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...