በአቶ ጉርሜሳ አያኖ የክስ መዝገብ የተካተቱት እነ አቶ በቀለ ገርባ (አራት ተከሳሾች) በመከላከያ ምስክርነት የቆጠሯቸው ከፍተኛ ባለሥልጣናት ለፍርድ ቤት በሰጡት ምላሽ ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት፣ ለታኅሳስ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጠ፡፡
ፍርድ ቤቱ ከታኅሳስ 17 እስከ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ እነ አቶ በቀለ በመከላከያ ምስክርነት የቆጠሯቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ አቶ ለማ መገርሳ፣ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የለገዳዲ ከንቲባ ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒና የዕድሜ ልክ ፍርደኛ አቶ አንዱዓለም አራጌን ለመስማት ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡
የመከላከያ ምስክሮቹ የበኩላቸውን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለፍርድ ቤቱ በሰጠው ምላሽ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ በከፍተኛ ሥራ ላይ በመሆናቸው ሊቀርቡ እንደማይችሉ መግለጹን ለችሎቱ አስታውቋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናትን በሚመለከት የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ለፍርድ ቤቱ በጻፈው ደብዳቤ፣ በአስቸኳይ አገራዊ ስብሰባ ምክንያት ቀርበው ለመመስከር ስለማይችሉ ፍርድ ቤቱ ችግሩን ተረድቶ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲመቻችላቸው ‹‹በአክብሮት እንጠይቃለን›› ብሏል፡፡
የዕድሜ ልክ ፍርደኛ የሆኑት የቀድሞው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ (አንድነት) ፓርቲ አመራር አቶ አንዱዓለም አራጌን በሚመለከት፣ የማረሚያ ቤቱ ጉዳይ አስፈጻሚ ለምን እንዳልቀረቡ ተጠይቀው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አቶ አንዱዓለም ከባድ ፍርደኛ በመሆናቸው ለማቅረብ እንደሚቸገር ማረሚያ ቤቱ መግለጹን አስረድተው ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን በፍርድ ቤት የተሰጠው ትዕዛዝ መጥሪያውን የማረሚያ ቤቱ ፖስተኛ እንዲያደርስ የሚል እንጂ፣ በቀጥታ ለአቶ አንዱዓለም እንዲደርሳቸው ትዕዛዝ አለመስጠቱን ጠቁሟል፡፡ በመሆኑም በሦስቱም የመከላከያ ምስክሮች ላይ ተገቢውን ትዕዛዝ ለመስጠት ለታኅሳስ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ታኅሳስ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. የግል መከላከያ ምስክራቸውን አሰምተው ያጠናቀቁት አንደኛ ተከሳሽ የኦፌኮ ወጣቶች ሊግ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አያና ጉርሜሳ ናቸው፡፡ አቶ አያና በመከላከያ ምስክርነት የቆጠሯቸው የኦፌኮ ወጣቶች ሊግ ሊቀመንበርና የሕግ ባለሙያ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ደስታ ዲንቃ ናቸው፡፡ አቶ ደስታ ከአቶ አያና ጋር በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆኑ፣ ስለአቶ አያና ለፍርድ ቤቱ የሚያስረዱት በኦፌኮ የወጣቶች ሊግ አብረው ሲሠሩ አቶ አያና የነበራቸው ባህሪ ምን ይመስል እንደነበር መሆኑን፣ ጠበቃቸው አቶ አመሐ መኮንን ጭብጥ አስይዘዋል፡፡
አቶ ደስታ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ከአቶ አያና ጋር በኦፌኮ ውስጥ የሠሩት ከየካቲት 17 ቀን 2006 ዓ.ም. እስከ ታኅሳስ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ነው፡፡ ከሥራ ውጪ አይተዋወቁም፡፡ በድርጅቱ ውስጥ እሳቸው የሊጉ ሊቀመንበር ሲሆኑ አቶ አያና ምክትል ሊቀመንበር ናቸው፡፡ በየሳምንቱ ቅዳሜ በድርጅቱ ጽሕፈት ቤት እየተገናኙ ስለፖለቲካ ፕሮግራምና ወቅታዊ ጉዳዮች ውይይት ያደርጋሉ፡፡ ሥራቸው ጥብቅና ስለሆነ፣ ሥራ በሌላቸው ጊዜ እየተገናኙ በጽሕፈት ቤቱ ወጣቱን በሚመለከት ይመካከራሉ፡፡ አቶ አያና የኦሮሞ ሕዝብ በሰላማዊ መንገድ መብቱ እንዴት መከበር እንዳለበትና የኢትዮጵያን አንድነት ማጠናከር ስለሚቻልበት ሁኔታ ውይይት እንደሚያደርጉ አስረድተዋል፡፡ ውይይት በሚያደርጉበት ጊዜ የተለያዩ የፖለቲካ ጥያቄዎችንና ሌሎች አጀንዳዎችን በመያዝ ውይይት ከማድረጋቸው ውጪ፣ ስለሽብርና ሽብርተኝነት አንስተውም ሆነ ተወያይተው እንደማያውቁ ምስክሩ ተናግረዋል፡፡ ኦፌኮም ሆነ አቶ አያና የሚያንፀባርቁት ሰላምንና አንድነትን እንጂ ስለሽብር እንዳልሆነ አክለዋል፡፡
ዓቃቤ ሕግም ለምስክሩ ባቀረበው መስቀለኛ ጥያቄ ከኦነግ ጋር በተገናኘ ስለመከሰሳቸው (ምስክሩ)፣ ስለአቶ ጉርሜሳ የዕለት ከዕለት ሥራ ስለማወቃቸው፣ በኦፌኮ ውስጥ ወጣቶች ከሽብር ተግባር ጋር በተገናኘ ስለመገምገማቸውና ሌሎች ጥያቄዎችን አቅርቦላቸው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ከኦነግ ጋር አለ ስለተባለው ግንኙነት ሲጠየቁ ጠበቃቸው ምስክሩ የመጡት ስለአቶ አያና የግል ባህሪ ለመመስከር ነው ብለው በመቃወማቸውና ፍርድ ቤቱም በመቀበሉ ምላሽ ሳይሰጡ አልፈዋል፡፡ የአቶ አያናን የዕለት ተዕለት ሥራ የሚያውቁት ባገኟቸው መጠን ብቻ መሆኑንና ሽብርን በተመለከተ ግምገማ አጋጥሟቸው እንደማያውቅ ገልጸዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በሌሎችና ታኅሳስ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. የሚሰጠውን ትዕዛዝ ጨምሮ ቀሪ የመከላከያ ምስክሮችን ለመስማት፣ ከየካቲት 5 እስከ 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡