Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናእስከ 15 ዓመት የሚያስቀጣ የአደገኛ ቆሻሻ ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ ቀረበ

እስከ 15 ዓመት የሚያስቀጣ የአደገኛ ቆሻሻ ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ ቀረበ

ቀን:

 

 

በዮናስ ዓብይ

የአደገኛ ኬሚካልና ቆሻሻ ወደ አገር ውስጥ አገባብ፣ አጠቃቀምና አወጋገድ ለመቆጣጠር አዲስ ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ፡፡

ረቂቅ ሕጉ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል በተባለለት የቁጥጥር ዕርምጃ፣ ጥፋተኛ በሚባሉ አስገቢዎችና አምራቾች ላይ እስከ 15 ዓመት የሚደርስ እስራትና እስከ አምስት ሚሊዮን ብር የሚደርስ የገንዘብ መቀጮ በድንጋጌው ውስጥ አስፍሯል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ማብራርያ ካልሰጡ አባላቱ መደበኛ ስብሰባ እንደማይሳተፉ በመግለጻቸውን ምክንያት ለሁለት ሳምንታት ተቋርጦ የቆየው ፓርላማ፣ ሐሙስ ታኅሳስ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ መደበኛ ሥራው ሲመለስ ሁለት አዋጆችን ያፀደቀ ሲሆን፣ በሁለት አዳዲስ ረቂቅ አዋጆችም ላይ ተወያይቷል፡፡

በዕለቱ ከቀረቡ ረቂቅ አዋጆች ውስጥ የአደገኛ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ረቂቅ አዋጅ ነው፡፡ አደገኛ ቆሻሻዎች የሚያደርሱት የአካባቢ ብክለትና የኅብረተሰብ ጤና አጠባበቅን በተመለከተ ዝርዝር ድንጋጌዎችን አካቷል፡፡ ረቂቅ አዋጁ አደገኛ ቆሻሻዎችን ከምንጫቸው ለማቆጣጠር የሚያስችል ሥርዓት ለመዘርጋት ይረዳልም ተብሏል፡፡

ማንኛውም ቆሻሻ አመንጪ ያለበትን ኃላፊነት በሚደነግገው አንቀጽ፣ አመንጪው ግለሰብ ወይም ተቋም አደገኛ ቆሻሻውን የመሰብሰብ፣ የመለየት፣ የማስወገድ፣ ብሎም ፈቃድ ባለው አካል ተሰብስቦ ደግሞ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ እንዳለበት ያስገድዳል፡፡ እንዲሁም ቆሻሻው የተከማቸበትን ኮንቴይነር በአግባቡ በማሸግ በግልጽ የሚታይ መለያ በአማርኛና በእንግሊዝኛ መጻፍ አለበት፡፡

በረቂቅ አዋጁ መሠረት አደገኛ ቆሻሻዎችን የሚያጓጉዙ የጭነት ተሽከርካሪዎች የሚጠበቁባቸው መረጃዎች በዝርዝር ሰፍሯል፡፡ የአመንጪው ማንነት፣ አድራሻ፣ የአደገኛ ቆሻሻው ዓይነት፣ መጠን፣ ባህርይ፣ መደበኛ አያያዝና የአያያዝ ዘዴዎችን ማካተት እንዳለበት ተካቷል፡፡

ስለድንበር ዘለል የአደገኛ ቆሻሻ እንቅስቃሴዎች የሚደነግገው የረቂቅ አዋጁ ክፍል እንዳስቀመጠው፣ ማንኛውም በድንበር ዘለል የአደገኛ ቆሻሻ እንቅስቃሴ መሰማራት የሚፈልግ አካል እንዲቆጣጠርና ፍቃድ እንዲሰጥ ሥልጣን ከተሰጠው የአካባቢ፣ ደንና የአየር ለውጥ ሚኒስቴር ፈቃድ ማግኘት እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ በተጨማሪም በክልሎች መካከል የሚደረግ ዝውውርን በሚመለከት የፌዴራል መንግሥት አሠራሮችን የሚከተል መሆን እንዳለበት ተገልጿል፡፡ ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል የሚጓጓዝ የአደገኛ ቆሻሻ መጠን መቀነስ እንሚኖርበትም ረቂቅ አዋጁ ያስቀምጣል፡፡ እንዲሁም በአገር ውስጥ የሚደረግ ማንኛውንም ክልል ተሻጋሪ አደገኛ ቆሻሻን ማጓጓዝ የሚቻለው፣ ከመድረሻ ክልል የአካባቢ ጥበቃ ተቋም ዝውውሩ በጽሑፉ ይሁንታ ሲያገኝ ብቻ መሆኑም ተደንግጓል፡፡

ከዚህ ቀደም ወጥተው በሥራ ላይ ካሉት አካባቢን የሚመለከቱ ሕጎች ወይም አዋጆች የተለየ የተባለው የቅጣት መጠንም፣ በዚህ ረቂቅ አዋጅ ውስጥ በዝርዝር ሰፍሯል፡፡

በመጀመርያ ደረጃ ከተጠቀሱት የቅጣት ድንጋጌዎች ውስጥ ትንሹ የሚባለው ያለ ሚኒስቴሩ ፈቃድ ወደ አገር ውስጥ አደገኛ ቆሻሻ ያስገባ ማንኛውም ሰው፣ ያስገባውን ቆሻሻ በ90 ቀናት ውስጥ ወዳስመጣበት እንዲመልስ ተደንግጓል፡፡ በተጨማሪም 50 ሺሕ ብር የገንዘብ ቅጣትና ከአምስት ዓመት የማያንስ ፅኑ እስራት ይቀጣል፡፡ ያለ ፈቃድ የገባው ቆሻሻ ወደ አካባቢ ዘልቆ ብክለት ካደረሰ ግን ቅጣቱ ወደ አንድ ሚሊዮን ብርና የአሥር ዓመት ፅኑ እስራት ከፍ እንደሚልም ተመልክቷል፡፡

ከፍ ሲልም ማንኛውም ሰው በሕገወጥ መንገድ ያስገባው አደገኛ ቆሻሻ አካባቢን ከበከለና የተበከለውን አካባቢ ያላከመ ከሆነ፣ 15 ዓመት ፅኑ እስራትና ከአምስት ሚሊዮን ብር የማያንስ የገንዘብ መቀጮ እንደሚጣልበት ተደንግጓል፡፡

በረቂቅ አዋጁ የተወሰኑ ድንጋጌዎች ውስጥ ምክር ቤቱ መጠነኛ ውይይት ካደረገ በኋላ ለዝርዝር ዕይታ፣ ለአካባቢና ተፈጥሮ ሀብት ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምፅ መርቶታል፡፡

በተመሳሳይ ቀን ምክር ቤቱ የተወያየበት ሌላኛው አጀንዳ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የሠራተኞች አስተዳዳርን የሚመለከት ረቂቅ ደንብ ነው፡፡ ምክር ቤቱ በዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የቀረበውን እንዲሁ ለሰው ኃይል አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምፅ መርቶታል፡፡

በዕለቱ ከቀረቡት አጀንዳዎች ውስጥ የዕፅዋት አዳቃዮች መብት ረቂቅ አዋጅና በአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ቦታ ማዘዋወሪያና ማዘመኛ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ፣ በኢትዮጵያ መንግሥትና በፈረንሣይ የልማት ድርጅት ተደርጎ የነበረውን ስምምነት ምክር ቤቱ አፅድቋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...