Friday, July 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ልማት ባንክ ለሰፋፊ እርሻዎች ብድር መስጠት የሚያስችል ዝግጅት እንዲደረግ ለሁሉም ቅርንጫፎች ትዕዛዝ ሰጠ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በሁሉም ክልሎች ለሚገኙ ቅርንጫፎቹ ባስተላለፈው የውስጥ ማስታወሻ፣ ጥሩ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ሰፋፊ የእርሻ ፕሮጀክቶች ለሚቀጥለው ምርት ዘመን ብድር ለማቅረብ ከወዲሁ ዝግጁ እንዲሆኑ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተሾመ ዓለማየሁ ከሳምንት በፊት ለሁሉም ቅርንጫፎች በጻፉት የውስጥ ማስታወሻ፣ ቅርንጫፎች የሚቀጥለው ዓመት የእርሻ ወቅት ከመድረሱ በፊት የፕሮጀክቶቹን ሥራ አፈጻጸም በመገምገም፣ የብድር ማራዘሚያና የሥራ ማስኬጃ ብድር የሚያስፈልጋቸውን በመለየት ከወዲሁ ዝግጅት እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡

አቶ ተሾመ ይህንን የውስጥ ማስታወሻ ከመጻፋቸው በፊት ባንኩ ብድር ሰጥቷቸው በመቋቋም በዝናብ ከሚለሙ የእርሻ ፕሮጀክት ባለሀብቶች ጋር፣ ኅዳር 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ውይይት ተደርጓል፡፡

በዚህ ውይይት ላይ ባለሀብቶቹ ሰባት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረጋቸውን አቶ ተሾመ በጻፉት ደብዳቤ አስታውሰዋል፡፡

ባለሀብቶቹ መስተካከል አለባቸው ካሏቸው ጉዳዮች መካከል የመጀመርያው ባንኩ በየጊዜው ክትትል እንዲያደርግ ይጠይቃል፡፡ በተለይም በዘር፣ በአረምና በምርት ስብሰባ ወቅት የፕሮጀክቶችን የሥራ አፈጻጸም ባለመገምገሙ ችግር እየተፈጠረ መሆኑን ባለሀብቶቹ አመልክተዋል፡፡ በተጨማሪ ባንኩ ፕሮጀክቶችን በቅርበት እየተመለከተ ድጋፍ ቢያደርግ ክፍያዎችን ለመፈጸም ዝግጁ እንደሚሆኑ መግለጻቸው ተመልክቷል፡፡ ባንኩ ግን ቀረብ ብሎ በትብብር መሥራት አለመቻሉ፣ ከፍተኛ ደንበኞቹንና ፕሮጀክቶቹን በዕውን አለመረዳቱ፣ የሚሠራውንና የማይሠራውን ለይቶ አለማወቁ፣ የግብርና ወቅቶችን ያገናዘበ የብድር አለቃቀቅ አለመኖር፣ ኢንሹራንስን በተመለከተ ግልጽ አሠራር አለመኖር የሚሉት ችግሮች ጎልተው መውጣታቸውም ተገልጿል፡፡

አቶ ተሾመ በጻፉት የውስጥ ማስታወሻ፣ ‹‹በየወቅቱ የተሟላ የክትትል ሥራ መሥራት፣ ደንበኞቻችን ያጋጠሟቸውን ችግሮች ገምግሞ የተለያዩ መፍትሔዎችን ለምሳሌ ብድር ማራዘሚያና ተጨማሪ ብድር መስጠትና የመሳሰሉት የመፍትሔ ዕርምጃዎች መውሰድ፣ ከሁሉም በላይ ብድሮችን መሰብሰብ የዲስትሪክቶች ዋናው ሥራ ስለሆነ መርሐ ግብር በማዘጋጀት ክትትል እየተደረገ ሪፖርት በየወሩ መቅረብ አለበት፤›› በማለት አፅንኦት ሰጥተው ዲስትሪክቶችን አሳስበዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የሚቀጥለው ዓመት የእርሻ ወቅት ከመድረሱ በፊት ደንበኞች እንደ ሥራ አፈጻጸማቸው፣ የብድር ማራዘሚያና የሥራ ማስኬጃ ብድር የሚያስፈልጋቸውን ከወዲሁ በመለየት ዝግጅት እንዲደረግ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡

በሰፋፊ እርሻ መስክ የተሰማሩ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች መንግሥት በተለይም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በቂ ድጋፍ እያደረገላቸው ስላልሆነ ምርታማ ካለመሆናቸውም በላይ፣ ፕሮጀክቶቻቸው በታማሚ ብድር ጎራ እየተሠለፉ መሆኑን በመጥቀስ መንግሥት መፍትሔ እንዲሰጣቸው ሲወተውቱ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች