Sunday, September 24, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ቅድሚያ ለአገር ህልውና!

 የአገር ጉዳይ ሲነሳ በቅድሚያ የሚታሰበው ህልውና ነው፡፡ ዕድሜ ጠገቡ ብሂል የሚለውም፣ ‹‹አባት ቢሞት በአገር ይለቀሳል፣ እናት ብትሞት በአገር ይለቀሳል. . . አገር የሞተ ዕለት ወዴት ይደረሳል?›› ነው፡፡ ከዚህ ጥልቀትና ስፋት ያለው አባባል መረዳት የሚቻው በአገር ህልውና መደራደር እንደማይቻል ነው፡፡ የአንድ አገር ዜጎች በተለያዩ ጉዳዮች ግላዊም ሆነ ቡድናዊ አቋሞች ሊኖሩዋቸው ይችላሉ፡፡ በአገር ጉዳይ ላይ ግን ተለያይተው መቆም አይችሉም፡፡ የቀደሙት ኢትዮጵያዊያን ከትውልድ ወደ ትውልድ እያስተላለፉ ካቆዩዋቸው አኩሪ የጋራ እሴቶች መካከል አንዱና ዋናው የአገር ፍቅር ስሜት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ጉዳይ አይደራደሩም የሚባለው፡፡ የአገር ህልውና የሁሉም ነገር የማዕዘን ድንጋይ ነው የሚባለው ከአገር የበለጠ ምንም ነገር ስለሌለ ነው፡፡ ይህንን መሠረታዊ ሐሳብ ለመቀበል የሚተናነቃቸው ግን አገርን ከራሳቸውና እንወክለዋለን ብለው ከሚያስቡት ቡድን በታች ያደርጋሉ፡፡ ይህ በፍፁም ኢትዮጵያዊነትን አይወክልም፡፡ የኢትዮጵያውያንን የዘመናት አገርን ከወራሪዎች የመከላከል ተጋድሎና የእርስ በርስ መስተጋብር አይገልጽም፡፡ ኢትዮጵያውያን በበጎም ሆነ በክፉ ጊዜያት የሚታወቁት ለአገራቸው በፅናት በአንድነት በመቆም ነው፡፡ ከአገራቸው በላይ ምንም የላቸውምና፡፡

በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያውያንን የሚያስጨንቁ ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡ የኑሮ ውድነት እንደ እሳት ይጋረፋል፡፡ ልጆችን አብልቶ፣ አጠጥቶና አልብሶ ወደ ትምህርት ቤት መላክ እጅግ ከባድ ነው፡፡ በመኖሪያ ቤት እጥረት ምክንያት ከአቅም በላይ የሆነ ወርኃዊ የቤት ኪራይ የብዙዎችን ጀርባ እያጎበጠ ነው፡፡ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ወርኃዊ ገቢ የተለያዩ ወጪዎችን ሸፍኖ መኖር ለብዙዎች የአስማት ያህል ይቆጠራል፡፡ በዚህ ላይ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጭምር የተመረቁ ወጣቶች ሥራ አጥ ሆነው ለቤተሰብ ሸክም ሲሆኑ ሰቆቃው ከባድ ነው፡፡ በአገር ደረጃ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ የንግድ እንቅስቃሴ ሲዳከም፣ በጥሬ ዕቃ አቅርቦት መስተጓጎል ምክንያት ምርት ሲቀንስ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ዋጋቸውን ሲንርና በዚህም የተነሳ የሥራ ዋስትና አደጋ ውስጥ ሲወድቅ ትልቅ ሥጋት ይፈጠራል፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እየተባባሰ ሲሄድ ደግሞ ለአገሪቱ የሚያስፈልጉ ነዳጅን የመሳሰሉ ስትራቴጂካዊ አቅርቦቶች ሳንካ ያጋጥማቸዋል፡፡ በተለያዩ መስኮች ሌሎች በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ነገር ግን አሁን ዋናው ጉዳይ ‹‹መጀመርያ የመቀመጫዬን›› እንዳለችው እንስሳ፣ ለኢትዮጵያውያን በጣም አሳሳቢ የሚሆንባቸው የአገራቸው ህልውና ጉዳይ ነው፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ ሥፍራዎች በተከሰቱ ነውጦች ምክንያት በርካታ ወገኖቻችን ለሕልፈት ተዳርገዋል፡፡ ብዙዎች የአካል ጉዳት አጋጥሞአቸዋል፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ከቀዬአቸው  ተፈናቅለዋል፡፡ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ የደሃ አገር ሀብት ወድሟል፡፡ ካሁን በፊት በዚህች ታሪካዊት አገር አጋጥመው የማያውቁ ብሔር ተኮር ግጭቶች ተቀስቅሰው እጅግ በጣም ዘግናኝ የሆኑ ነውረኛ ድርጊቶች ተፈጽመዋል፡፡ ሕዝብን ከሕዝብ በማጋጨት ሕይወትን ከማጥፋት በተጨማሪ፣ ለማመን የሚከብድ ጥቃት ወገን በወገኑ ላይ እንዲፈጽም ተደርጓል፡፡ በተዓምር ሕይወታቸው ተርፎ የደረሰባቸውን ሰቆቃ የሚናገሩ ወገኖች በአካላቸው ላይ የሚታየው ጉዳት የድርጊቱን አፀያፊነት ያጋልጣል፡፡ በቅርቡ የጅምላ መቃብሮች ተገኝተዋል በመባሉ ደግሞ እንደ አገርና እንደ ሕዝብ ወዴት እየሄድን ነው ያሰኛል፡፡ በዚህ ዓይነቱ ድርጊት የተሳተፉ ሰዎች ምን ዓይነት ህሊና ነው ያላቸው ያስብላል፡፡ አሰቃቂ ድርጊት ከተፈጸመባቸው ሰዎች በተጨማሪ፣ እየተፈጸመ ያለው አሳዛኝ ድርጊት የአገር ትልቅ ሕመም መሆኑን ማመን ይኖርብናል፡፡ በዚህች ታሪካዊት አገርና በዚህ ጨዋ ሕዝብ ውስጥ ነውረኛ ድርጊቶችን ማየት ያሳምማል፡፡ በዚህ አሳዛኝ ጊዜ የአገር ህልውና እጅግ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ እንዳለ መተማመን ተገቢ ነው፡፡

በአገር ህልውና ላይ አደጋ የደቀኑ እኩይ ድርጊቶችን በቶሎ ለማስወገድ አንድ ላይ መቆም ያስፈልጋል፡፡ የትናንቱ ቁስል የሚሽረው በይቅርታና በፍቅር ብቻ መሆኑን መተማመን ይገባል፡፡ ጥላቻ አዕምሮን የሚያዝግ የበቀል መሣሪያ ነው፡፡ በጠላትነት ስሜት የተመረዘ አስተሳሰብ የአገር ፍቅር ስሜትን ይበርዛል፡፡ የማኅበረሰቦችን መስተጋብር እያፈራረሰ ጭካኔ ውስጥ ለመክተት የዕልቂት ነጋሪት ይጎስማል፡፡ በፍቅርና በመተሳሰብ ይኖሩ የነበሩትን ሳይቀር በብሔርና በመሳሰሉት በመከፋፈል እርስ በርስ ያባላል፡፡ ለአገር ዕድገትና ለዴሞክራሲያዊ ግንባታ መዋል የነበረበትን የዜጎች አንድነት በመናድ አገርን መና ያስቀራል፡፡ ኩሩዎቹና አስተዋዮቹ ኢትዮጵያውያን ግን ይህንን የተረገመ መንገድ አይፈልጉም፣ በታሪካቸውም አያውቁትም፡፡ ነገር ግን በዚህ ዘመን ይህንን ጉዞ የመረጡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የአገር ጠላት እየሆኑ ነው፡፡ እያንዳንዱን ችግር እያነፈነፉ ከብሔር ጋር በማያያዝ ፀንቶ የኖረውን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ለመደርመስ እየተጠቀሙበት ነው፡፡ የንፁኃንን ሕይወት ለአደጋ በማጋለጥ ሰላምና መረጋጋት እንዲጠፋ አሉታዊ ድርጊቶችን እየፈጸሙ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የአገር ህልውና ለአደጋ ተጋልጧል፡፡

ማንኛውም ዜጋ ከምንም ነገር በላይ ታማኝ መሆን ያለበት ለአገሩ ነው፡፡ በፖለቲካ አቋምም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች ልዩነት መኖሩ ችግር የለውም፡፡ ዋናው ቁም ነገር ልዩነትን በአግባቡ መያዝ ላይ ነው፡፡ አስተዋዮቹ ኢትዮጵያውያን  ለዘመናት ልዩነቶችን ተቀብለው፣ ነገር ግን ከልዩነቶቹ በላይ የሚያስተሳስሯቸው የጋራ ጉዳዮች ይበልጡባቸው ስለነበር በፍቅርና በመተሳሰብ ኖረዋል፡፡ ብሔር፣ ቋንቋ፣ እምነትና የመሳሰሉት ልዩነቶች ሳይገድቧቸው ተጋብተውና ተዋልደው ዘመናትን ተሻግረዋል፡፡ የጋራ እሴቶቻቸው ስለሚበልጡባቸው ልዩነቶች መኖራቸው እስኪረሳ ድረስ ተደጋግፈው በጎና ክፉ ጊዜያትን አብረው አሳልፈዋል፡፡ ይህንን የመሰለ የአገር አኩሪ ፀጋ ተይዞ ስንትና ስንት ዓይነት ገድል መፈጸም ሲቻል፣ በገዛ ወገን ላይ በጭካኔ መነሳት ምን ይሉታል? ታሪካዊ ጠላቶች ወዳዘጋጁት ወጥመድ በቀላሉ ሰተት ብሎ በመግባት የአገርን ህልውና ለማፍረስ መዳከርስ ምን የሚሉት አባዜ ነው? ከዚህ በፊት ተሰምቶ የማይታወቅ አንድን ሕዝብ ከሌላው ለመለያየት የሚነዛው ፕሮፓጋንዳ ጠቀሜታው ምንድነው? ይህንን ጨዋና አስተዋይ ሕዝብ ይዞ አገርን ወደ ታላቅነት መመለስ? ወይስ ታሪካዊ ጠላቶች እንደሚፈልጉት ማሽመድመድ? ይህ ለመላ ኢትዮጵያውያን የሚቀርብ ጥያቄ ነው፡፡ የዘመኑ ትውልድ በግልጽ ምላሽ ሊሰጥበት ይገባል፡፡

የአገር ህልውና የሚያሳስባቸው ወገኖች በሙሉ ከዚህ ዓይነቱ አረንቋ ውስጥ እንዴት ሊወጣ እንደሚቻል መፍትሔ የማፍለቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በተለያዩ የሥራ መስኮች የተሰማሩ ከወጣት እስከ አዛውንት ድረስ የአገር ህልውና ጉዳይ ሊያሳስባቸው ይገባል፡፡ የኢትዮጵያን ሰፊ ሕዝብ የሚለያዩና የእርስ በርስ ጦርነት ለማስነሳት የሚያሴሩ ኃይሎችን ማስቆም ተገቢ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መጀመርያ መንግሥት ከማንም በላይ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህ ኃላፊነት የሚገለጸው ደግሞ የእያንዳንዱን ዜጋ ደኅንነት በማስጠበቅ ነው፡፡ ለዚህም ከምንም ነገር በላይ የሕግ የበላይነት መስፈኑን ማረጋገጥ ግዴታ ነው፡፡ ሁሉም ነገር መከናወን ያለበት በሕጉ መሠረት ብቻ መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግሥትን የሚመራው ገዥው ፓርቲ ለሕግ የበላይነት ራሱን ያስገዛ፡፡ በሕገ መንግሥቱ የሠፈሩ መሠረታዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ ይከበሩ፡፡ ራሳቸውን ከሕግ በላይ ያደረጉ አካላትና ግለሰቦች ሳይቀሩ ተጠያቂ ይሁኑ፡፡ ሕጉ በዚህ መንገድ ሲሠራበት በርካታ ችግሮች ይቃለላሉ፡፡ በመቀጠል የተዘጋጋው የፖለቲካ ምኅዳር በፍጥነት ተከፍቶ ለነፃና ፍትሐዊ ምርጫ መደላድሉ ይመቻች፡፡ የፀጥታ ኃይሎች ተጠሪነታቸው ለአገርና ለሕዝብ ብቻ ይሁን፡፡ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕግ አክብረው ይንቀሳቀሱ፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት መርህ ይደረጉ፡፡ የመንግሥትና የሕዝብ ንብረት የሚዘርፉ ሌቦች በሕግ ይዳኙ፡፡ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይከበሩ፡፡ ከሕግ በላይ መሆን የሚያምራቸው በሕግ አደብ ይግዙ፡፡ ለሕገወጥነት የሚመቹ ብልሹ አሠራሮች በሙሉ ከሥር ከመሠረታቸው ይናዱ፡፡ ዜጎች በሙሉ በሕግ ፊት እኩል መሆናቸው በተግባር ይረጋገጥ፡፡ እነዚህና ሌሎች መሠረታዊ ጉዳዮች ሲሟሉ አገር ሰላም ትሆናለች፡፡ ሕገወጥ ድርጊቶች ይከስማሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር በፍቅርና በመተሳሰብ አብረው ይኖራሉ፡፡ አገራቸውን ዴሞክራሲያዊትና የበለፀገች ማድረግም ይችላሉ፡፡ በመሆኑም ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ ለአገር ህልውና እንበል!  

 

 

 

 

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በቀይ ባህር ፖለቲካ ላይ በመከረው የመጀመሪያ ጉባዔ ለዲፕሎማቲክና ለትብብር አማራጮች ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለመጀመርያ ጊዜ በቀይ ባህር ቀጣና የፀጥታ...

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...

የመጀመርያ ምዕራፉ የተጠናቀቀው አዲስ አበባ ስታዲየም የሳር ተከላው እንደገና ሊከናወን መሆኑ ተሰማ

እስካሁን የሳር ተከላውን ጨምሮ 43 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ዕድሳቱ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...