Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክየመንግሥትና የግል አጋርነት ረቂቅ አዋጅ ላይ ትኩረት የሚጠይቁ ጉዳዮች

የመንግሥትና የግል አጋርነት ረቂቅ አዋጅ ላይ ትኩረት የሚጠይቁ ጉዳዮች

ቀን:

በውብሸት ሙላት

ፓርላማው የ2009 ዓ.ም. መደበኛ የሥራ ዘመኑን ከማጠናቀቁ በፊት ከሚኒስትሮች ምክር ቤት በመቀበል ወደ ቋሚ ኮሚቴዎች ከመራቸው ረቀቂ አዋጆች መካከል አንዱ የመንግሥትና የግል አጋርነትን የሚመለከተው ነው፡፡ ፓርላማው በቅርቡም የሕዝብ ውይይት እንዲደረግበት በመገናኛ ብዙኃን ጥሪ አቅርቦ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህንን ረቂቅ አዋጅ በሚመለከት ባለፈው ሳምንት (ታኅሳስ 15ቀን 2010 ዓ.ም.) ታትሞ የወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ የአዋጁን አጠቃላይ ገጽታዎች ቀርቧል፡፡ ይህ ጽሑፍ ከባለፈው ሳምንት የቀጠለ ሲሆን፣ ዓበይት ትኩረቶቹ ረቂቅ አዋጆቹ ላይ የተካተቱ ነገር ግን ፍተሻም አጽንኦትም የሚያስፈልጋቸው ነጥቦች ላይ ነው፡፡ 

የፕሮጀክት ኩባንያ

ረቂቅ አዋጁ በተለይም በምዕራፍ አሥር ሥር በመንግሥትና በግል አጋርነት ስምምነትን አተገባበርና ይዘት አንፃር ብዙም ያልተዘወተሩ ጽንሰ ሐሳቦችን አካቷል፡፡ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ለመተግበር የሚደረጉ ስምምነቶች ይዘታቸው ምን መምሰል እንዳለበትና እንደሚተገበር ዘርዘር ያለ ሥርዓት አስተዋውቋል፡፡ ጨረታውን በማሸነፍ ተዋዋይ የሚሆነው አካል  ፕሮጀክቱን  የሚተገብር አዲስ ድርጅት በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት ማቋቋም እንዳለበት ይጠይቃል፡፡ እንዲህ ዓይነት ኩባንያ (የንግድ ድርጅት) በአገራችን በግል ድርጅት ማቋቋም አልተለመደም፡፡

የመንግሥትና የግል አጋርነት በሚጠቀሙ አገሮች ዘንድ እንደተለመደው ለተለየ ዓላማ፣ ለአንድ ፕሮጀክት ትግበራ ብቻ የሚሆን ድርጅት ይቋቋማል፡፡ ድርጅቱ የሚቋቋመው ከመንግሥት የተረከበውን ፕሮጀክት ለመፈጸምና የውል ዘመኑ ሲያልቅ ለማስረከብ ነው፡፡ በእዚህ መንገድ የመቋቋሙ ዓቢይ ምክንያት የፕሮጀክቱ ኪሳራና ኃላፊነት የተዋዋይ ባለሀብቱ ሌላ ዕዳ ወደ ፕሮጀክቱ ላይ ወደሚኖሩት ሀብት እንዳይተላለፍ ለመገደብ ነው፡፡

ጨረታ አሸናፊው ድርጅት የመንግሥትና የግል አጋርነትን ፕሮጀክት ስምምነቱን ብቻ ለመተግበር እንዲሁም ፕሮጀክቱ እየተተገበረ ባለበት ወቅት ድርጅቱ በተለያዩ ምክንያቶች ቢፈርስ፣ የመክሰር (Bankruptcy) ውሳኔ ቢተላለፍ የፕሮጀክቱ ህልውናም አብሮ እንዳያከትምም ያግዛል፡፡ የባለሀብቱ በሌሎች ሥራዎችና ተግባራት ምክንያት ዕዳ ቢኖርበት ከፕሮጀክቱ እስካልመነጨ ድረስ በመንግሥትና የግል አጋርነትን  ስምምነት ውስጥ የሚገኘውን ንብረት በማቻቻያነት እንዳይውል ለማድረግ ይጠቅማል፡፡ በመሆኑም ከመክስር ውሳኔ ሩቅ ነው ማለት ይቻላል፡፡

በአገራችን ከእዚህ ጋር የሚቀራረቡ የንግድ አሠራርና ድርጅቶች አሉ ከተባለም በባለበጀት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚቋቋሙ የንግድ ድርጅቶች ናቸው፡፡ በምሳሌ ለማስረዳት በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ‹ኢንተርፕራይዞችን› ማቋቋማቸው ይታወቃል፡፡ በእነዚህ ኢንተርፕራይዞች አማካይነት የንግድ ሥራዎችን ያከናውናሉ፡፡ የኢንተርፕራይዞቹ ሰው ኃይል አስተዳደር፣ የፋይናንስ ሥርዓትና የተጨማሪ እሴት ታክስ አሰባሰብ ወዘተ. ከዩኒቨርሲተው መደበኛ አሠራር የተለየ ነው፡፡ የሰው ኃይል አስተዳደሩ በሲቪል ሰርቪስ ሳይሆን በአሠሪና ሠራተኛ፣ የፋይናንስ ሥርዓቱ ደግሞ ሌሎች የግል ድርጅቶች በሚከተሉት መንገድ በንግድ ሕግ ነው፡፡ በመሆኑም የኢንተርፕራይዞቹ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ወዘተ. ወደ ዩኒቨርሲቲው አይተላለፍም፡፡ እዚያው ራሱን ችሎ የቆመ ይሆናል፡፡

የፕሮጀክት ኩባንያም ከላይ ከቀረበው ምሳሌ ጋር ተመሳሳይ ዓላማና አሠራርን ለመከተል ሲባል የሚቋቋም ኩባንያ ነው ማለት ይቻላል፡፡  ይሁን እንጂ፣ የግል ድርጅቶች እንዲህ ዓይነት ኩባንያዎችን እንዴት ማቋቋም እንደሚችሉ ተጨማሪ ሕግ ማስፈለጉ አያጠያይቅም፡፡ የፕሮጀክት ኩባንያ የሚመሠረተው በጨረታው አሸናፊ ድርጅት ነው፡፡ በአሸናፊ ድርጅት በአክሲዮን የሚቋቋም መሆኑን ረቂቅ አዋጁ ይጠቁማል፡፡ በንግድ ሕጉ ስድስት ዓይነት ያላቸው የንግድ ድርጅቶች ዕውቅና አላቸው፡፡ በግለሰብም ንግድ ፈቃድ አውጥቶ መነገድ እንደተጠበቀ ማለት ነው፡፡ ከስድስቱ ውስጥ ተራ የሽርክና ማኅበር አትራፊ የንግድ ሥራ ውስጥ ስለማይሠማራ ከእሱ ውጭ ያሉት ግን በጨረታ ተካፋይ እንዳይሆኑ እስካልተከለከሉ ድረስ ዕጩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ በሽርክና ማኅበርም የፕሮጀክት ኩባንያ መመሥረቱ ብዙም ሚዛን አይደፋም፡፡ የሽርክና ማኅበር በባህሪያቸው ኃላፊነታቸው የተወሰነ ስላልሆነ፡፡ በመሆኑም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ወይም በአክሲዮን ማኅበር መልክ ብቻ ነው ሊቋቋሙ የሚችሉት፡፡

ከእነዚህ ከሁለት ዓይነት ማኅበሮች ውስጥ በየትኛው እንደሚቋቋም፣ እንዲሁም አዲስ ባለአክሲዮን የሚሆኑ ሰዎች ሳያስፈልግ አሸናፊው ድርጅት ብቻ ባለአክሲዮን የሚሆንበት ስለመሆን አለመሆኑ ወዘተ. ተጨማሪ ሕግ ያስፈልጋል፡፡ ሁሉንም አክሲዮኖች ባለቤት የሚሆነው አንድ ድርጅት (ሰው) የሚሆን ከሆነም ረቂቅ የንግድ ሕጉ እስካልፀደቀ ድረስ አሁን ባለው የንግድ ሕግ የሚተዳደር አይሆንም፡፡ ባለአንድ ሰው የአክሲዮን ማኅበር በንግዱ ሕጉ ዕውቅና ስለሌለው፡፡ በተጨማሪም አሸናፊው ባለሀብት የውጭ ድርጅት ከሆነ በውጭ ባለሀብቶች የማይቋቋሙ ድርጅቶች በርካታ ስለሆኑ በምን ሁኔታ እንደሚቋቋሙ አይዘረዝርም፡፡

ለብድር ዋስትና  የሚሰጥ ንብረትና የአበዳሪው መብት

የመንግሥትና የግል አጋርነትን  ስምምነቶችን ዕውን ለማድረግ የግል ድርጅቶቹ የፋይናንስ ምንጭ እንዲገኙ ማመቻቸት የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ ብድር እንዲያገኙ፣ ለብድር ዋስትና የሚሆኑ ንብረቶችን ማገዝም ይጠበቅበታል፡፡ ረቂቅ አዋጁም በተለያዩ አንቀጾች ላይ ይኼንኑ የሚገዙ አንቀጾች አሉት፡፡

በሕግ ተለይቶ በዋስትና እንዳይሰጥ ካልተከለከለ በስተቀር ማንኛውንም ዓይነት ንብረቶች በማስያዝ ብድር ሊያገኙ እንደሚችሉ ይገልጻል፡፡ ራሱ የሚሠራውን መሠረተ ልማት ጨምሮ የግል ድርጅቱ ያሉትን መብቶች በሙሉ በመያዣነት ሊጠቀምባቸው ይችላል፡፡ ችግሩ የሚመነጨው የግል ድርጅቱ የተበደረውን ሳይከፍል በሚቀርበት ጊዜ አበዳሪው አካል በምን መልኩ ዕዳውን ማስመለስ እንዳለበት አልተመለከተም፡፡ ፕሮጀክቶቹ የሚፈጸሙት ለሕዝብ ጥቅም ተብለው ስለሚሆን አበዳሪውም አካል ብድሩን ለማስመለስ መያዣዎቹን የሚሸጣቸውና ለሌላ አገልግሎት የሚውሉ ከሆነ የመንግሥትና የግል አጋርነትን  ስምምነቱ ዓላማውን መሳቱ አይቀሬ ይሆናል፡፡ ስለሆነም አበዳሪው አካል በመያዣው ንብረት፣ በተለይም በማይንቀሳቀሰው ላይ፣ የሚኖረውን መብት በሕግ ለይቶ ማስቀመጥ ተገቢ ነው፡፡

ለውል የተተወው ጉዳይ መብዛት

ረቂቅ አዋጁ ለመንግሥትና የግል አጋርነትን  ስምምነቶች ምንነት ለይቶ አስቀምጧል፡፡  ‹‹የመንግሥትና የግል አጋርነቱን የውል ቃሎችና ሁኔታዎች ለመወሰን በተዋዋይ ባለሥልጣንና በግል ባለሀብቱ መካከል የሚደረግ ውል›› መሆኑን አንቀጽ 2(13) ላይ ትርጓሜ ተሰጥቶታል፡፡ በስምምነት የሚገዙና የሚሸፈኑት ጉዳዮችና ሁኔታዎች ደግሞ በርካታ ናቸው፡፡ የተወሰኑትን ብቻ ለመዘርዘር ያህል የፕሮጀክቱ ስምምነት የሚቆይበት ጊዜ፣ ባለሀብቱ ክፍያ የሚገኝበት ሥርዓት፣ ፕሮጀክቱ በሚፈጸምበት ቦታ ላይ ከሚገኙት ንብረቶች ውስጥ የግልና የመንግሥት የሚሆኑትን መለየት፣ ፕሮጀክቱ በሚቋረጥበት ጊዜ የሚከፈል ካሳና ምክንያቶች፣ የፕሮጀክት ኩባንያን የሚመለከት በርካታ ጉዳዮች በውል መሸፈን ካለባቸው ሁኔታዎች ውስጥ በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ እነዚህን የሚመስሉ ሌሎች ሁኔታዎችም አሉ፡፡

የውል ጉዳዮችን በሚመለከት በዋናነት ሁለት ነጥቦች መታወስ አለባቸው፡፡ አንደኛው ረቂቅ አዋጁ በርካታ ሁኔታዎች በውል እንዲሸፈኑ ከተወ፣ ስምምነቱ (ውሉ) ማካተት ያለበትን ዝቅተኛ ነጥቦች መወሰን ወይም ማስቀመጥ የነበረበት መሆኑ ነው፡፡ የስምምነቶቹን/የውሎቹን ቃሎችና ሁኔታዎች እንዲወስኑ ሥልጣን የተሰጣቸው ለተዋዋይ ወገኖች ነው፡፡ መንግሥትን ወክለው የሚዋዋሉት አካላትን የሚኖራቸውን ሥልጣን በተወሰነ መልኩ ገደብ ካልተበጀለት ለሙስናም ለኪራይ ሰብሳቢነትም አመቺ ይሆናል፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት በዚህ አገባብ ባለሥልጣናት በሕግ የተፈቀደላቸውን ሥልጣን መሠረት አድርገው ከሕዝብ ይልቅ ባለሀብቱንና ራሱን የሚጠቅምበት ሁኔታን የሚመለከት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ሥልጣንን ያለአግባብ ለመጠቀም የተመቸ ይሆናል ለማለት ነው፡፡

ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ አዋጁ ለማሳካት የሚፈልጋቸውን የግልጽነት እሴት ስለሚቃረን ነው፡፡ ከዚያ ባለፈም ተመሳሳይ ለሆኑ ፕሮጀክቶች የተለያዩ የውል ሁኔታዎችን መተግበርንም ያስከትላል፡፡ በመሆኑም ውሉ ከአዋጁ መንፈስ ውጭ  የፍትሐዊነትን መርሕ እንዲፃረር በር መክፈቻ ይሆናል፡፡ የሌሎች የበርካታ አገሮች ተሞክሮ ግን ከኢትዮጵያው በተቃራኒ ነው፡፡ የመንግሥትና የግል አጋርነትን  ስምምነት ሲደረግ ውሉ መያዝ  ያለበትን ጉዳዮች ያስቀምጣል፡፡ ረቂቁ ግን በውል ሊገለጹ የሚችሉ ሁኔታዎች አንዳንዴ በመፍቀድ ብቻ አልፎታል፡፡ አንዳንዴ በአስገዳጅነት አስቀምጧል፡፡ በመፍቀድ ብቻ ካለፈው ደግሞ ማካተትም አለማካተትም በተዋዋዮቹ ፍላጎት ይወሰናል፡፡

በውሉ ካልተካተቱ ተመልሶ ወደ ፍትሐ ብሔር ሕጉ ወይም ሌላ ሕግ መመለስ ግድ ይሆናል፡፡ እንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች ሲከሰቱ ደግሞ መንግሥትን (ሕዝብን) የሚጎዱ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በአጠቃላይ በውል እንዲወሰኑ የተተውት ጉዳዮች በርካታ ከመሆናቸው አንፃር ረቂቅ አዋጁ ወይም ደግሞ እሱን ተክትሎ በሚወጡ ደንብና መመርያዎች ላይ እንዲሸፈኑ ማድረግ ይገባል፡፡

የግል ባለሀብቶቹ

ከመንግሥት ጋር ውል በመፈጸም እንደ ግል ባለሀብት በመሆን አገልግሎቱን የሚያቀርቡት የተለያዩ አካላት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በመንግሥት ባለቤትነት ሥር ሆነው ነገር ግን እንደማንኛውም የግል ባለሀብት የሚወዳደሩ አሉ፡፡ በፌዴራል ሥርዓት ደግሞ የክልልና የፌዴራል መንግሥት የሚያቋቁሟቸው ድርጅቶች አሉ፡፡ የፌዴራሎቹ በክልል፣ የክልሎቹ በፌዴራል ፕሮጀክቶች ውስጥ መሳተፍ ይችላሉ ወይ? ሌላው በጥያቄነትም የሚነሳው የመንግሥት የሆነ የንግድ ተቋም ከግል ባለሀብቱ ጋር መወዳደር ይችላል ወይ? የውጭ ባለሀብቶች እንደ አገር ውስጥ ባለሀብት መሳተፍ ይችላሉን? አንዳንድ አገሮች ከውጭ ይልቅ ለአገር ውስጥ ባለሀብት ትኩረት የሚሰጡ አሉ፡፡ ለአብነት ብራዚልን መውሰድ ይቻላል፡፡ ረቂቅ አዋጁ እንዲህ ዓይነቱን ሁኔታ ለመወሰን ብዙም ፋይዳ የለውም፡፡

የቦርዱ አባላት ሁኔታ

የመንግሥትና የግል አጋርነት በማስተዳደር ረገድ መንግሥትን የሚወክሉ በዋናነት አራት ተቋማት አሉ፡፡ የመንግሥትና የግል አጋርነት ቦርድ፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር፣ ለዚሁ ተግባር ሲባል በሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ሥር ሆኖ የሚቋቋም ዳይሬክቶሬት ጀኔራልና ከግል ባለሀብቱ ጋር ውል የሚያደርገው መሥሪያ ቤት ናቸው፡፡ ቦርዱና ዳይሬክቶሬት ጀኔራሉ እንደ አዲስ የሚደራጁ ተቋማት ናቸው፡፡ ሥልጣን፣ ተግባርና ኃላፊነታቸውም በረቂቁ ላይ ተዘርዝሯል፡፡ ረቂቅ አዋጁ ፕሮጀክቶችን በአጋርነት በመተግበር  ለማሳካት ካሰባቸው ዓላማዎች  አንፃር የቦርዱ ጥንቅር፣ የአባላት አመራረጥ ሁኔታዎችን እንመልከት፡፡ አስቀድመን ግን ኃላፊነቱን በአጭሩ መግለጽ ተገቢ ነው፡፡

ቦርዱ በርካታ ኃላፊነቶች አሉበት፡፡ በአጋርነት የሚሠሩ ፕሮጀክቶችን አዋጭነት ጥናት ይገመግማል፣ የፕሮጀክቶችን አወቃቀር መርምሮ ያፀድቃል፣ የጨረታ ውጤቱን ያፀድቃል፣ የሥጋት ድልድሎችን ጨምሮ የፕሮጀክት ማሻሻያዎችን የማፅደቅ ሥልጣንም አለው፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው የግብርና ሌሎች ማበረታቻዎችን በመለየት ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ለውሳኔ ያቀርባል፡፡ የተለያዩ የዋስትና ጥያቄዎች ላይ የውሳኔ ሐሳብ ያቀርባል፡፡ ለገንዘብ ተመጣጣኝ ዋጋ የማያስገኙና በዳይሬክቶሬት ጀኔራሉ የሚወጡ ዝቅተኛ መሥፈርቶችን የማያሟሉ ውሎችን እንዳይፈረሙ ተዋዋይ የመንግሥት ባለሥልጣንን ወይም የልማት ድርጅትን መከልከል ይችላል፡፡ ከሞላ ጎደል ሥልጣንና ኃላፊነቱ እነዚህ ሲሆኑ አሥር አባላት የሚኖሩት የቦርዱ ጥንቅር ደግሞ  እንደሚከተለው ነው፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ፣ የትራንስፖርት፣ የውኃ መስኖና ኤሌክትሪክ እንዲሁም የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትሮች፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ፣ የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ የዳይሬክቶሬት ጀኔራሉ ዳይሬክተር፣ የተዋዋይ መሥሪያ ቤቱ የበላይ ኃላፊና በገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትሩ ከግሉ ዘርፍ የሚመረጡ ሁለት አባላት ናቸው፡፡

በአጋርነት የሚሠሩ ፕሮጀክቶችን በማስተዳደር ረገድ ከፍተኛው ተቋም ቦርዱ ሆኖ ሳለ፣ እንዲሁም ረቂቅ አዋጁ  ለማሳካት ካሰበው አንፃር የአባላቱ ጥንቅርና ከግሉ ዘርፍ ለሚመረጡት ሁለት ሰዎች ምንም ዓይነት መሥፈርት አለመቀመጡ ተግዳሮት መሆናቸው አይቀርም፡፡ በመንግሥትና የግል አጋርነትን  ስምምነት እንደሚሠሩ ረቂቁ ያስቀመጣቸው በዋናነት ከኮንስትራክሽን ዘርፉ ጋር የሚገናኙ ናቸው፡፡ በመገንባት፣ በማሻሻል ወይም በመጠገንና በማስተዳደር ወዘተ. ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲህ ዓይነት ፕሮጀክቶችን ከሚመሩ ተቋማትና የዕለት ተዕለት ሥራቸው የሆኑ ሁለት ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች ግን የቦርዱ አባላት ውስጥ አልተካተቱም፡፡ አንደኛው የኮንስትራክሽን ሲሆን፣ ሁለተኛው የቤቶችና ከተማ ልማት ሚኒስትሮች ናቸው፡፡ የተለያዩ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶችም በራሳቸው የሚያስተዳድሯቸው መሠረተ ልማቶች ቢኖሩም እነዚህ ሁለቱ ግን ዓብይ ተግባራቸው ነው፡፡ ከግንባታ ጋር በተያያዘ ወቅታዊ የሆኑ ችግሮችን፣ ፈተናዎችንና መልካም አጋጣሚዎችን፣ የዋጋ ሁኔታን እንደሚያውቁ የሚጠበቁት እነዚህ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች ናቸው፡፡

ከመሠረተ ልማት ጋር ተያይዞ ቦርዱ ውስጥ ከተጠቀሱት ሙያዊና ቴክኒካዊ ጉዳዮችን የሚያስተዳድሩ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች የትራንስፖርትና የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ናቸው፡፡ የገንዘብና ኢኮኖሚ፣ የብሔራዊ ባንክና ፕላን ኮሚሽን ከፋይናንስ፣ ማክሮ ኢኮኖሚ፣ ጨረታን ከማስተዳደርና ከሌሎች መሥፈርቶች ቢለኩ ተገቢነታቸው አያጠራጥርም፡፡ ከሚሠራው ሥራ ጋር በተገናኘና ቴክኒካዊ ከሆነው ጉዳይ አንፃር ግን ሁለቱ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች ተገቢነታቸው አያጠያይቅም፡፡

በተጨማሪ የመንግሥትና የግል አጋርነትን  ስምምነቶች ከሕግ ይልቅ ወይም ባልተናነሰ የሚተዳደሩት በውል ነው፡፡ ይህ ቦርድ ውሎችን በመመርመር የማፅደቅና እንዳይፈረምም የማዘዝ ሥልጣን አለው፡፡ ውሎቹን ተዋዋይ የመንግሥት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤትና በዳይሬክቶሬት ጀኔራሉ ውስጥ የሚገኙ የሕግ ባለሙያዎች እንደሚያዘጋጇቸውና እንደሚመረምሯቸው ግልጽ ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ የመጨረሻ አፅዳቂው አካልም ከሕግ አንፃርም መፈተሽ ያስችለው ዘንድ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ መሥሪያ ቤት መካተት አለበት፡፡

በእንዲህ ዓይነት ስምምነቶች ለሚከናወኑ ተግባራት አስተዳደርና ውጤታማነት ሲባል ቦርድም ይሁን ሌላ ቡድን ሲቋቋም በዋናነት ከሦስት የሙያ ዘርፎች የሚገኙ ሰዎች መካተት ተገቢነት አለው፡፡ ረቂቅ አዋጁ ራሱም ለዚሁ ምስክር ነው ማለት ይቻላል፡፡ የፋይናንስ፣ የቴክኒክና የሕግ ሙያዎች ናቸው፡፡ ተዋዋይ ባለሥልጣንም ከእነዚህ ሙያዎች የተውጣጣ የፕሮጀክት አስተዳደር ቡድን ማቋቋም እንደሚገባው አንቀጽ 14(1) ላይ ተገልጿል፡፡  በመሆኑም ረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 8 ላይ የቦርዱን አባላት ጥንቅር ሲዘረዝር ለቴክኒካዊ ጉዳዮች ግምገማና አስተዳደር ትኩረት በመስጠት አባላት መጨመር ያለበት ሲሆን፣ ብዙ ነገሩ በውል እንደሚገዛ ስለሚታወቅ ደግሞ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሊወከል ይገባል፡፡ የሌሎች አገሮች ልምድም ቢሆን ከእዚሁ ጋር የተስማማ እንጂ እንደ ረቂቅ አዋጁ አይደለም፡፡

ከቦርድ አባላት ጋር በተገናኘ ሁለተኛው እንከን ከግሉ ሴክተር የሚወከሉትን ሁለት አባላት የሚመለከት ነው፡፡ ረቂቅ አዋጁ፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትሩ የፈለገውን አባላት በፈለገው መሥፈርት፣ በፈለገው ዘዴ እንዲመርጥ የሚያስችል ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚያገለግሉ እንዲሁም በምን በምን ምክንያቶች ከቦርድ አባልነት እንደሚነሱ ምንም ፍንጭ አይተውም፡፡ በአማራጭም በደንብ ወይም መመርያ እንደሚወሰንም ረቂቁ አያመለክትም፡፡ በደፈናው ሚኒስትሩ እንዲመርጥ ሥልጣን በመስጠት ዘሎታል፡፡ የሌሎች አገሮች ልምድ የሚመሰክረው ግን አንድም የሙያ ማኅበራትን በመጥቀስ፣ ካልሆነም በደንብና መመርያ ይወሰናል እንጂ እንዲሁ ለአንዱ ሚኒስትር በዝርው አልተውትም፡፡  አገሮች ከኮንስትራክሽን፣ ዲዛይንና አርክቴክቸር እንዲሁም ኢኮኖሚክስ የሙያ ማኅበራት ወይም ተቋማት  አለበለዚያም በእነዚህ ዘርፍ ውስጥ የሚገኙ ባለሙያዎች የግል ዘርፉን እንዲወክሉ ማድረግ የተለመደ ነው፡፡ 

የግጭት አፈታት ዘዴና ሕግ

ረቂቅ አዋጁ ከመንግሥትና የግል አጋርነትን  ስምምነት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ግጭቶች ላይ ተፈጻሚ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕግ እንደሆነ ደንግጓል፡፡ ግጭቶቹን ለመፍታት የሚፈልጉበትን ሥልት በስምምነት መምረጥ እንዲችሉ ለተዋዋዮቹ ተትቷል፡፡ በሌሎች ሕጎች (ለምሳሌ አስተዳደር ውሎች) የተደነገገ ቢኖር እንኳን እነዚህን ድንጋጌዎች በመሻር ለስምምነት/ለውል የበላይነት ሰጥቷል፡፡

ረቂቁ ላይ መካተት የነበረበት አንድ ጉዳይ አለ፡፡ የግል ድርጅቱ ከመንግሥት ጋር ውል ገብቶ ለሕዝብ የሚያቀርበውን አገልግሎት በተመለከተ ከሕዝብ በኩል ቅሬታ ሊነሳ ይችላል፡፡ ይህ ቅሬታ ወደ ግጭት በሚያድግበት ጊዜ ክስ ወይም በሌላ መንገድ እንዲፈታ አቤቱታ አቅራቢ መሆን የሚችለውን ወገን ማንነት የሚመለከት ነው፡፡ ቅሬታው ሲፈታ ውጤቱ የሚፈጸመው ሁሉም ተጠቃሚ ላይ የሚሆንበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ክርክርና ሙግቱ የሕዝብ ጥቅምን የሚመለከት ይሆናል፡፡ ለነገሩ፣ በመንግሥትና የግል አጋርነትን  ስምምነት የሚሠሩትም የሕዝብ አግልግሎትን የማይሰጥና የሚጎዳ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ሕዝቡን በመወከል ማንም ያገባኛል የሚል፣ የግል ጥቅም እንዳለውም እንደተጣሰበትም ማሳየት ሳይጠበቅበት ክርክር ሊቀርብ የሚቻልበትን ሥርዓት (Public Interest Litigation) ዕውቅና መስጠትን ይጠይቃል፡፡

ይህ ዓይነቱ ክርክር በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ ላይ ስላልተካተተ ልክ እንደየአካባቢ ብክለት ክርክር ሁሉ በአዋጁ ማካተት አግባብነት ይኖረዋል፡፡ ሕዝቡ ላይ ለሚደርስ ጉዳት ፍትሕ የሚያገኝበት ዘዴ አዋጁ አሠራር መዘርጋት አለበት፡፡ ሌሎች አገሮች በዚህ ዓይነት አዋጅም ባይሆን በሌላ ሕግ ጥቅም ላይ ስላዋሉት እንደ አዲስ ማካተት አላስፈለጋቸው ይሆናል፡፡ ለአብነት ተጠቃሚው ላይ የሚጣለው ታሪፍ ከፍ ቢል አንድ ወይም ሁለት ሰው ክስ የማቅረቡ ሁኔታ የሚታሰብ ስላልሆነ እንዲህ ዓይነቱን አሠራር ትኩረት ቢሰጠው መልካም ነው፡፡

የይችላል አንቀጾች. . .

ረቂቅ አዋጁ  በተወሰኑ አንቀጾች በተለይም ደግሞ በመጨረሻው ምዕራፍ ሥር በሚገኙት ውስጥ ከሕግ አርቅቆትና ከሕጉ መንፈስም ግብም አኳያ ሲታዩ መሠረታዊ ስህተት ያለባቸው ድንጋጌዎችን ይዟል፡፡ አንዳንዶቹ አንቀጾች በስምምነቱ ውስጥ ከተፈለገ የሚካተቱ ካልሆነ የሚቀሩ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ተዋዋዩ የመንግሥት ባለሥልጣን ከፈለገ የሚያደርጋቸው ካልፈለገ የሚተዋቸው በሚመስልና ባልተለመደ መልኩ የተቀረፁ ናቸው፡፡ በምሳሌነት የሚከተሉትን እንጥቀስ፡፡

አንቀፅ 58 ‹‹በዚህ አዋጅ መሠረት የሚወጣው መመርያ የፕሮጀክት ስምምነት ሊቋረጥ የሚችልባቸውን ምክንያቶች ሊዘረዝር ይችላል፤›› የፕሮጀክት ውሎች የሚቋረጥባቸው ምክንያቶች በአዋጁ ውስጥ አልተጠቀሱም፡፡ በመመርያውም ላይ እንዲወጡም አያስገድድም፡፡ በውል ካልተካተቱ፣ መመርያና ደንቡም ላይ ካልወጡ በወደ ፍትሐ ብሔር ሕጉ በመመለስ ማንኛውም ውል የሚቋረጥበትን ሁኔታ መጠቀም ግድ ይሆናል፡፡  አንቀጽ 64ም እንዲሁ ተመሳሳይ ችግር አለበት፡፡ አንቀጽ 62 ላይ ደግሞ የግል ባለሀብቱ ላይ ከኅብረተሰቡ ቅሬታዎች በሚነሱበት ጊዜ የሚፈቱበትን ‹‹ቀላልና ውጤታማ የሆነ የቅሬታ ማስተናገጃ ዘዴ እንዲተገበር ሊጠይቅ ይችላል፤›› ይላል፡፡  ላይጠይቅም ይችላል፡፡ ጠይቆ የግል ባለሀብቱ ባይተገብረው ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል የተቀመጠ ነገር የለም፡፡ እንደዚህ ዓይነት በርካታ አንቀጾችን ረቂቁ ይዟል፡፡ እነዚህ አንቀጾች ካልተስተካከሉ ጉዳቱ ዞሮ ዞሮ የሕዝብ ነው፡፡

ረቂቅ አዋጁን በእዚህ መልኩ መፈተሻችንን ብንቀጥል በርካታ እንከኖችን እናገኛለን፡፡ ቁም ነገሩ፣ ከመፅደቁ በፊት የተቻለውን ያህል ትኩረት እንዲደረግበትና በተቻለ መጠን የሕዝብን ጥቅም ማስከበር እንዲችል ጥረት ይደረግ ዘንድ ለማሳየት ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...