በመልካሙ ተሾመ (ጠበቃና የሕግ አማካሪ)
‹‹ነፍጠኛ ስንኞች›› የተሰኘችዋን የግጥም መድበል ሸምቼ ደጋግሜ ዘለቅኋት፡፡ ብዙ ደስ አለኝ፡፡ ብዙ ተነሸጥኩ፡፡ ጥቂት አዘንኩ፡፡ ከጥቂት ጥቂት ከፍ ያለ ተበሳጨሁ፡፡ ይህን ሁሉ ስሜቴን በተደራሲነት መብቴ ጀቡኜ እንደሚከተለው ጻፍኩት፡፡ ይህ ጽሑፍ ነፍጠኛ ስንኞችን በማሄስ ወይም በመዳሰስ ዓላማና ቅርፅ አልተሰናድቶም፡፡ እንዲሁ በነፃ ዕይታ ተጻፈ እንጂ፡፡
ገጣሚ መላኩ አላምረው (መለኛው) በፌስቡክ መንደር ‹‹መለኛ ሐሳቦች›› በሚል ገጹ ባለ ከባድ ሚዛን ቦክሰኛ ሆኖ ሲጫወት አውቀዋለሁ። ጎጃም/ሰከላ ተወልዶ አድጎ የሸገር ነዋሪ ለመሆኑም ‹የፕሮፋይል› መረጃው ያሳያል፡፡ ጎጃሜ ሁሉ ባለቅኔ ነውና ጃል!
ይህ ወጣት ገጣሚ ስለአገር ያገባኛሉን በግጥም አዋህዶና ቀምሞ ‹‹ነፍጠኛ ስንኞች›› ብሎ በሰየመው መድብሉ፣ የአገሬ ፖለቲካ የሁልጊዜ መነሻና መድረሻ ስለሆነው ነፍጠኝነት የራሱን ሙግት ይዞልን ቀርቧል።
‹‹ነፍጠኛ ስንኞች››ን እኔ እንዳነበብኩት
የመጀመርያ መጀመርያዋን ገጽ (Cover Page) እንዲህ ዓይተናታል፡፡ የመደቡ ጥቁር መሆን ጣሊያን፣ እንግሊዝ፣ ግብፅ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን ወዘተ. የቃጡብንን ቅኝ የመግዛት ሙከራና ወረራ፣ በጦቢያችን ላይ የጋረጡብንን አደጋ ያመለክታል፡፡ የአምስት ዓመት የፍዳ ዘመን፣ የአህመድ ግራኝን የጨለማ ጊዜያችንን ይጠቁማል፡፡ የዘመነ መሳፍንትን ጥቀርሻ የታሪክ ምዕራፋችንን ይገልጽልናል፡፡ በዴሞክራሲና በፍትሕ በኩል ደግሞ የሁልጊዜ የጨለማ በርኖሳችንን ይወክላል፡፡ ጥቁሩ ሙሉ ገጹ መሆኑ ከሚነግረን በስተቀር ያለመኖሩን ነው፡፡ ጨለማው የሁላችንም ነበር፣ ነው፡፡ አብሮነታችን ጨለማውን በመጋራት፣ ጥቁር ሸማችን አብሮ በመልበስም ነው፡፡
በዚህ ጥቁር መደብ ላይ በቀጫጭን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ መስመሮች የተሠራች የኢትዮጵያ ካርታ አለች፡፡ ኢትዮጵያ እልፍ ፍዳና መከራ ተከፍሎባት ከጥቁር ባህር የተበጀች እንቁ ናት ሲለን ይመስለኛል፡፡ መስመሮቹ መቅጠናቸው ስለምንድነው? ብንለው ዛሬ የኢትዮጵያ ህልውና አደጋ ላይ ስለመውደቁ ለመግለጽ፣ ለመጠቆም ነው የሚለን ይመስለኛል፡፡ መለኛው በአንድ በኩል ሙሉዋን ኢትዮጵያን በመሣል ኤርትራን እንደ ድሮዋ አንድ የኢትዮጵያ ክፍል ናት ማለት ሲቃጣው በሌላ በኩል ደግሞ ቀይ ባህርን ሌላ አገር ያደረገ የራስን ዕድል በራስ መወሰን ይሉት ፖለቲካ ኢትዮጵያን ጨርሶ እንዳይበትን የፈራ ይመስላል፡፡ ከቀደመ ፀባዩ ተነስተን አደጋው ቢያሳስበውም በኢትዮጵያ ተስፋ አልቆረጠም፡፡ ይልቁንም ኢትዮጵያ ወደ ቀደመ ክብሯ ተመልሳ ኤርትራንም ይዛ ልዕለ ኃያል ትሆናለች የሚል ሩቅ ዓላሚ ነው ማለት እንችላለን፡፡ ወዲያውም የዓባይ ልጅ ነውና እንዲህ መተለቅ ይጠበቅበታል፡፡ ኤርትራ ሌላ አገር ሆና ሳለ፣ የመመለሷም ነገር የማይታሰብ ሆኖ ሳለ፣ መለኛው ይህንን ሁሉ ዘሎ የጃንሆይ ዘመንን ኢትዮጵያ ይዞ ብቅ የማለቱን ነገረ ምክንያት ብንፈልግ የኢትዮጵያን ህልውና ከጨለማው ባህር ከጥቁር አለት ያጎነቆሉ አባታቶቻችን ልጆች ነንና የሚያቅተን፣ የማንችለው የለም የሚል ትምክህት የሚል መልስን እናገኛለን ይመስለኛል፡፡
ከላይ ወደ ታች የተነጣጠረ ረዥም አልቤን ይሁን ስናይፐር በደንብ ያልለየ ጠመንጃው የሆነው ሁሉ የሆነው በነፍጠኞች አባታቶቻችን ነው፡፡ ጦቢያን ከጥቁር አፈር አበጅተው እስትንፋሳቸውን እፍ ብለው ሰው ያደረጓት (ያውም ውብ ቆንጆ እመቤት) ነፍጠኛ አባቶቻችን ናቸው፡፡ ነፍጠኝነት የኢትዮጵያ አስገኝ ነው፡፡ ከመከራ የዳንው፣ ከፍዳ የተረፍነው፣ ከመጥፋት ያመለጥነው በነፍጠኞች አባታቶቻችን አልሞ ተኳሽነት ነው፡፡ ይህንኑ ጠመንጃ እንደ ፊደል ‹‹ነ›› መጠቀሙ መጀመርያ ቃል ነበር እንዲል አስቀድሞ ነፍጥና ነፍጠኛ ነበረ፣ ከፊደሉም በፊት ሲለን ይመስለኛል፡፡ ጦቢያችንና እኛን ከፍ ከሚያደርጉን አንዱ የራሳችን ፊደልና ቋንቋ የፈለሰሙት ጠመንጃቸውን ተንተርሰው አሰላስለው ነው፡፡ መለኛው የዛሬም የመውጫ መንገዳችን ነፍጥና ነፍጠኝነት ነው እያለን ነው፡፡ አሁንስ ተስፋችን ማን ነው? ነፍጠኝነት አይደለምን? እያለን እንደሆነ እገምታለሁ፡፡
‹‹ጠ›› ለምን ቀይ ሆነች? ነፍጠኝነት መስዋዕትነት ነው፡፡ ነፍጠኛ እንደሆነ መሞትም መግደልም አያሳስበውም፡፡ የሚሞትለት ጉዳይ ቢኖረው ጊዜ ሁላ ይሰዋል፡፡ የሚገድልበት ቁምነገር ባገኘ ጊዜ ሁላ ለመግደል አያመነታም፡፡ ነፍጠኝነትና መስዋዕትነት አይነጣጠሉም፡፡ ነፍጠኝነት ተራ ጀብደኝነት አለመሆኑን ሲያመሰጥር ይችኑ ‹‹ጠ››ን የልብ ቅርፅ ሰጣት፡፡ አንድም ነፍጠኛ ልባም ነው፣ አይሞቀው አይበርደው የራሱ ልክ ያለው ልኩንም ማንም ሳይነግረው የሚያውቅ አውቆ አደር ነው ሲለን፣ ወዲያውም የነፍጠኛ ልቡ ለፍቅር ስስ ነው እያለን ይመስላል፡፡ በተለምዶ የፍቅር መግለጫ ተደርጋ የምተወሰደዋን የልብ ቅርፅ የነፍጥ፣ የጠመንጃ አቻ አድርጎ ማቅረቡ ጦቢያችን አባቶቻችን ነፍጥ ብቻ ሳይሆን ፍቅርም የገበሩላት ናት ማለቱ ነው፡፡‹‹ነፍጠኛ›› ብሎ በመጻፍ ውስጥ ‹‹ነ›› እና ‹‹ጠ›› እኩል አበርክቶ እንዳላቸው ሁሉ፣ ጦቢያችንን በመሥራት ረገድ ነፍጠኝነትና ፍቅር ተመሳሳይ አበርክቶ ነበራቸው፡፡ ይህ አቻነታቸው ዛሬም ወደፊትም የተጠበቀ ነው ማለት ይመስለኛል፡፡
የግርጌ ማስታወሻ ይህን ሁሉ የምለው በይመስለኛል ነው፡፡ መለኛውን ስለ የሽፋን ገጹ ምን ማለትነት አልጠየቅኩትም፡፡ በእኔ በኩል አሁንም እንዲነግረኝ አልፈልግም፡፡ ይህ እኛ ተደራሲዎች የማንደራደርበት መብታችን ነው፡፡ ወዲያውም ግጥማቸውን የሚተረጉሙ ገጣሚዎችን አልወድም፡፡ ሚዛናዊ ለመሆን በማሰብ፣ ይልቁንም ከውዳሴ ይልቅ ትችት መልካም ነው ብዬ በማመን በሽፋን ገጹ ላይ አንዳች ጉድለት አግኝቼ ለማጓን ጣርኩ ደከምኩ፡፡ አልተሳካልኝም፡፡ መለኛው የሽፋን ሥዕሉን ከተቺ ዓይኖች አርቆ ሰቅሎታል፡፡ እስኪ ወደ ውስጥ እንዝለቅ፡፡ ውስጡን ስንዘልቅም በሽፋን ገጹ ልክ ተቀኝቶ፣ ተመሳጥሮና ጎምርቶ እናገኘዋለን፡፡
‹‹የነፍጠኛ ስንኞች››ን ጓዳ በወፍ በረር ስመለከተው
መላኩ ገና በመጀመርያ ግጥሙ አፍቃሪ ኢትዮጵያ፣ የአንድነት ቀናኢ ሆኖ ይጀምራል፡፡ የውስጡ የሚያውቃት፣ የተነገረችውን ኢትዮጵያ ፈልጎ እንዳጣት በመናዘዝ እንጠቁመው ዘንድ ይማፀናል፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ከሰውነት እኩል ያቆመዋል፡፡ በዚህ ግጥሙ የዘውጌ ፖለቲካ የዘረኝነት፣ የበቀልተኝነትና የጥላቻ ሽኩቻ ነው ይላል፡፡ እንዲህ የመሰለውን የአገር ሥሪት አማሮ ሰው በመሆኑ ብቻ የሚኖርባትን ኢትዮጵያ ይፈልጋል፡፡ ያችን ኢትዮጵያ ካየን እንጠቁመው ዘንድ አደራ በሰማይ አደራ በምድር እያለ ይለማመነናል፡፡
በአገሬ ምድር
ለብሔር ያልሆነች፤
በዘር ያልተያዘች፤
ከበቀል የፀዳች – ከቂም ከጥላቻ፤
ሰዎች ሚኖሩባት፣ ሰው በመሆን ብቻ፤
አንድ ‹የሰው ከተማ›፣ አንድ ‹የሰው ሥፍራ›፤
ምናልባት ካያችሁ፣ ጠቁሙኝ አደራ፤
ከሰው ተደምሬ፣ የሰው ፍሬ ላፍራ፡፡
(ገጽ 6)
ይህ ተስፋ መቁረጥ፣ ይህ ፍለጋ፣ ይህ ልመና፣ ይህ እንጉርጉሮ የገጣሚው ብቻ አይመስለኝም፡፡ ሁላችንም እንዲህ ያለችውን ኢትዮጵያ በመፈለግ ብዙ ተንከራተናል፡፡ ፈልገን ባጣናት ጊዜ አለመኖሯን ማመን/መቀበል ቢያቅተን ምናልባት ባናገኛት እንጂ ትኖራለች ብለን ተስፋ ማድረግን መርጠን ለሌሎች ፈላጊዎች አደራ ንገሩን ብለናል፡፡ መላኩ አላምረው የሚፈልጋት አገር አለመኖሯን በዓይኑ በብረቱ ቢያረጋግጥም፣ ፈልጎ ቢያጣትም የፍለጋውን ዶሴ መዝጋት አልፈቀደም፡፡ ከግጥሙ ውጭ በሆነው እሱነቱም አፍቃሪ ኢትዮጵያ መሆኑን ለሚያውቅና ይህንን እምነቱን እንደ ፖለቲካ ቆሞ ቀርነት ለሚቆጥርበት ለእንደ እኔ ያለ ጓደኛው ይህ ግጥሙ የሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ለቅሶው መሆኑን ይገነዘባል፡፡
‹‹ነፍጠኛ›› በሚል ርዕስ የከተባት ግጥሙም (ገጽ 14) ነፍጠኛ ለአንድ ብሔር ተለይቶ የተሰጠው አይደለም፣ ለአገር አንድነት ሲባል ጠላትን አሳድዶና ለይቶ ለሚመታ ሁሉ የሚሰጥ የክብር የጀግንነት ስም እንጂ ይላል፡፡ አሉላ አባነጋ፣ በላይ ዘለቀና አብዲሳ አጋም እኩል ነፍጠኞች ናቸው ሲልም ነፍጠኝነት ለአንድ ብሔር ብቻ የሰጠውን ስምምነታችን ይሞግታል፡፡ በቀዳሚ ግጥሙ ፈልጎ እንዳጣት የተናዘዘልንን አገር ነፍጠኝነትን ያህል ጀግንነት የሁላችንም ነው በሚል ሐቲት ለማግኘት ይደክማል፡፡ ግጥሙ የተጻፈው ነፍጠኛ እያለ ለሚሰድበው ለሌላው ወገን መልስ ሆኖ መሆኑ የሚነግረን ግን የሁላችንም ነፍጠኞች ነን ሙግቱ የጠፋችበትን አገሩን የማስገኘት ጉልበት እንደማይኖረው ነው፡፡
‹‹አማራ ነኝ›› ባለው ግጥሙም (ገጽ 23) የእስካሁኑን አስጠብቆ እናገኘዋለን፡፡ አማራነት ለአገር ለወገን መጨነቅ፣ ለደቡብ ሰሜን፣ ምዕራብና ምሥራቅ ሕመም መድረስ መሆኑንና ለራስ ብቻ ማለት ከንቱ ዘረኝነትና ጎጠኝነት ነው ይላል፡፡
‹‹አማራ ነኝ
ራሴን የማስከብር፣
ሌላውን ፍጹም የማልንቅ፤
ለራሴ ብቻ የማልኖር፣
ላገር ለወገን የምጨነቅ፤
‹‹በማንነቴ የምመካ፣
አዎን አማራ ነኝ እኔ፤
አንዲት አገርን የማልም፣
ሰንደቋ ማይጠፋ ካይኔ፡፡. . .››
እያለ አማራነት የቆመው ለኢትዮጵያነት በመውደቅ ስለመሆኑ ይገልጥልናል፡፡ ነፍጠኝነትም በማናቸውም መንገድና መሣሪያ ለኢትዮጵያ አንድነት መታገል ነው ይላል፡፡ ተለምዷዊውን የነፍጥ ብያኔም አፍርሶ በመሥራት ስለኢትዮጵያ አንድነት ቅኔ መዝረፍ ከጣሊያን ጋር ከመዋደቅ እኩል ነፍጠኝነት ነው ሲል ይከራከራል፡፡ ክርክሩ ሰሚ ሲያጣ ይሁን ወይም የመሸነፍ ስሜት ሲያድርበት ወይም የአማራነት ትምክህቱ ተነስቶበት እንዲህ ይፎክራል፡፡ ‹‹ከፍ በአገር፣ ዝቅ በዘር›› በሚለው ግጥሙ (ገጽ 85) ‹‹. . .
አብረን ከፍ ለማለት ብንወድም ባንወድም፣
የመስዋዕት ምድር ከሰማይ አትወርድም፡፡››
በብሔር መደራጀት፣ የዘር ፖለቲካ ዝቅ ማለት መወረድ ነው የሚለውን የቀደመ ሙግቱን ገፍቶበታል፡፡
ለአንድ ኢትዮጵያ የተሰው ነፍጠኛ አባቶቻችን ልጆች ነንና ‹‹በድኩም አዕምሮ. . .ሴራ›› ተጠልፈን ልንወድቅ አይገባም፡፡ ሴረኞች ሆይ አዕምሯችሁ ይቅር ይላል፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ከማይደረስበት ሰማይ ጋር ሲያመሳስለው ብሔርተኝነትን ደግሞ የመጨረሻው ዝቅታ አድርጎ አቅርቦታል፡፡ እንዲህ ከፍ አድርጎ የሰቀለው ኢትዮጵያዊ አንድነት ቢያስስ ቢፈልገው ሊያገኘው ባለመቻሉ ተስፋ የቆረጠው ገና ከመነሻው ቢሆንም፣ ተስፋ በመቁረጥም ውስጥ ፍለጋውን ጨርሶ አላቆመምና ወጥቶ ወርዶ ጋራ ሸንተረሩን ፈትሾ ያጣውን አንድነት በጦር በኩል ለማግኘት ያስባል፡፡ በሌላ በማናቸውም መንገድ አንድ ለመሆን አልቻልንምና ‹‹ወራሪ ላክልን›› እያለ እግዜሩን ይለምናል፡፡ በመደበኛ የጡመራ ባህሪው የሰላም ሰባኪ የሆነው መላኩ ጦርነት እስኪመኝ ድረስ የማይቻል የሆነበትን አንድነት ለመልቀቅ አለመድፈሩ ነፍጠኝነቱን እንድንጠራጠረው ያደርጋል፡፡
በመጨረሻም ገጽ 98 ላይ ባኖራት ‹‹ነፍጠኛ ስንኞች›› ግጥሙ (የመድበሉ መጠሪያ) ይህን ሁሉ የሚደክመው የነፍጠኛ አባቶቹን አደራ ላለመብላት እንደሆነ ይነግረናል፡፡
በተለይ ምን ወደድኩለት?
ሀ) የያዘው ጭብጥ ምንም ይሁን ምን ለነገሩ ለኖረው ግድ አክብሮቴ ከፍ ያለ ነው፡፡ ቅኔ ከመዝረፍ ወጥቶ የፖለቲካ እንጉርጉሮ ማሰማት አንዳች ዓይነት መረዳት ይፈልጋል፡፡ ዶክተር ዶናልድ ሌቪን (ጋሽ ሊበን) ‹ኢንዲቪዡዋሊስት› ነው የሚለው የጎጃም ሰው እንዲህ ያሉ የነገረ መንግሥት ግጥሞችን መዘመር መጀመሩን እንደ ትልቅ ለውጥ እመለከተዋለሁ፡፡ የመላኩ አላምረው ግጥምም በዚህ ረገድ የሚኖረው ምን ማለትነት ቀላል አይደለም፡፡ በአገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን ዘንድ ‹‹የፍቅር ደብዳቤ ከመጻፍ የሚዘል ቁምነገር የለውም፡፡ ቅኔ ከመዝረፍ የሚተርፍ የፖለቲካ ነፍስ የለውም፤› የሚባለው የጎጃም ወጣትም ‹ስታተስኮውን› የሚንድ ስለመሆኑ ፍንጭ አድርጌ እወስደዋለሁ፡፡ በተለይም የመላኩን ለዘብተኝነት በፌስቡክ ጽሑፎቹ የማውቀው ነውና ከእሱ አንፃር ግዙፍ ለውጥ ሆኖ ይታየኛል፡፡ በዚህም በጣሙን ደስተኛ ነኝ፡፡
ለ) በግጥሙ የተቀነቀኑት መሠረተ ሐሳቦች ብዙ መንታ ሙግቶች የሚበቅልባቸው፣ በሐሳቦቹ ላይ የሚኖረን አረዳድም ሆነ አፈታት የነጋችን ሁለነገር የሚወስን ርዕሰ ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡ ግጥም የቃላት ድርደራ ሳይሆን የሐሳብ መርቀቅ፣ መግዘፍ፣ መገለጥ ነው ብሎ ለሚያምን ለእንደ እኔ ዓይነቱ አንባቢና በተራ የቃላት ጨዋታ ባለቅኔ በሚኮንበት አገር የሚገኝ የግጥም ወዳጅ ነፍጠኛ ስንኞች ግሩም መድብል ይሆንለታል፡፡
ሐ) የነፍጠኛ ስንኞች ግጥሞች የግብር ይውጣ ወይም እኔ ምን አገባኝ ግጥም አይደለም፡፡ የነፍጠኝነት ብያኔና እሱን ተከትሎ የሚመዘዘው የፖለቲካ ገመድ የኢትዮጵያ አንድነትና የመውጫ በሩ ገጣሚው እንደ አንድ ማናቸውም ገጣሚ በእግረ መንገድ ተናግሮት የሚያልፍ አይደለም፡፡ ሙያዬ ሥራዬ ብሎ ያለመታከት የሚሟገትለት ዋና ነገሩ ነው፡፡ ዋና የመድበሉ ጨመቅ እስኪሆን ድረስና የመሰልቸት አደጋን ሁሉ እስኪታገስ ድረስ ዋጋ ከፍሎበት የጻፈው ነውና ወድጄዋለሁ፡፡
መ) በእነ ፀጋዬ ገብረ መድኅን አገር፣ በእነ በዕውቀቱ ሥዩም መንደር፣ በእነ በረከት በላይነህ ከተማ፣ በእነ ኤፍሬም ሥዩም ቀዬ፣ በእነ ገብረ ክርስቶስ ደስታ ባድማ . . . በቅኔ ባበደች አገር፣ በቅኔ ጥርሱን በነቀለ ሕዝብ መሀል ግጥም ይዞ መምጣት ከፍ ያለ በራስ መተማመንን ይጠይቃል፡፡ ከዚህ አንፃር ለመላኩ ያለኝ አድናቆት ከፍ ያለ ነው፡፡
ምን ቅር አለኝ?
ሀ) የማመሥገኛውና የመግቢያው (መግቢያውን መተኮሻ ብሎታል) ገጾች የመድበሉ ግጥሞችን ሐሳብ በሚመጥን ከፍታ አልተጻፉም፡፡ ምሥጋናም ሆነ መግቢያ፣ መውጫም ሆነ የሽፋን ገጽ በጠቅላላው ግጥሙ/መድበሉ ላይ ተፅዕኖ አላቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ መግቢያም ሆነ ምሥጋና ወደ ዋናው ተራራ የመውጫ የመስፈንጠሪያ ሜዳዎች ናቸው እላለሁ፡፡ ወዲያውም ገጣሚ የቃላት ጌታ ነውና የአንባቢውን ስሜት ወደ ግጥሙ መንፈስ ለመሳብ፣ ለመክተትና ለመጎተት እነዚህ ማስጀመርያዎች ከዋናው ግጥሞቹ እንደ አንዱ ሆነው ወይም በልጠው ሊጻፉ ይገባ ነበር፡፡
ለ) ነፍጠኛ ስንኞች ይዞት የመጣ አዲስ ሙግት አይደለም፡፡ ቀለሙ አዲስ ቢሆንም መሠረተ ሐሳቡ የቆየ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አንድነት አቀንቃኝ ሆኖ በመቅረቡ ደስተኛ አይደለሁም፡፡ በፊት ለፊት ውይይትም እንደሆነው በመድበሉም ኢትዮጵያ ወይም ሞት ማለቱን አልወደድኩለትም፡፡
የግርጌ ማስታወሻ
‹‹ነፍጠኛ ስንኞች›› የግጥም መድበል ጥሩ እየተነበበና እየተወደደ እንደሆነ መጽሐፍ ሻጮችም ግጥም ወዳጆችም መስክረዋል፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ሳትለቅ በወቅታዊው የአማራ ፖለቲካ ላይ የምትለኮስ ክብሪት ናት መድበሏ፡፡ ገጣሚው አማራ ነኝ ቢልም ቅሉ፣ ያው ኢትዮጵያ ናት ውሉ፡፡ በዚህም የሁልጊዜም የነፍጠኞች ምኞት የተከበረችና የታፈረች ኢትዮጵያን ከማየት ከፍም ዝቅም እንደማይል አይቼባታለሁ፡፡ አገራዊ ጉዳይ ግድ ብሎት በጥበባዊ ገለጻ አስውቦ ለተደራስያን በማቅረቡ መለኛውን አመስግኘዋለሁ፡፡ መልካም ንባብ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡