Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በምንዛሪ እጥረት የሚሳበቡ የገበያ ጡዘቶች ይታረሙ!

ከዶላር ምንዛሪ ለውጡ በኋላ የምርቶች ዋጋ ላይ ለውጦች ታይተዋል፡፡ በወቅቱ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉት ላይ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ተገልጾ፣ እንቅስቃሴዎችም ተጀምረው ነበር፡፡

ከአንድ ወር ተኩል በፊት ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ተደርጎባቸዋል ከተባሉት ምርቶች ውስጥ የብረታ ብረት ምርቶች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህን ምርቶች የሚያቀርቡ ሻጮች፣ የመሸጫ ዋጋቸውን አንረዋል በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ወቅት፣ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል፡፡ በዚህም መሠረት  አንዳንድ የብረት መሸጫ መጋዘኖች እንደታሸጉም ሰምተን ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ለሌሎች መቀጣጫ ይሆኖል በማለት የተወሰደው ዕርምጃ፣ የብዙዎቹን መደብሮች የናረ ዋጋ አላስለወጠም፡፡ አዳዲስ ምርቶችን አናገኝም ከሚል መነሻ ምርትን ሲሸሽጉ፣ ዋጋ እየጨመሩ የመሸጡ ነገር በብረትና በሌሎች ምርቶች ላይ እየታየ ነው፡፡  የብር ምንዛሪ ለውጡን ተከትሎ ባልተገባ ዋጋ እየሸጡ ናቸው የተባሉ ነጋዴዎች ላይ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ቢለፈፍም ለውጥ አልመጣም፡፡ የብረት ዋጋ እንደየብረት ዓይነቱ ከተገቢው በላይ የዋጋ ጭማሪ ታክሎበት እየተሸጠ ነው፡፡ የዋጋ መናር ብቻም ሳይሆን፣ ምርቱ እንደሚፈለገው መጠን በገበያው አለመገኘቱ ተጠቃሚዎችን እያማረረ ይገኛል፡፡ የዋጋ ጭማሪው በአርማታ ብረቶች ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ላሜራና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ምርቶችን በሙሉ የሚያጠቃልል እንደሆነም ይነገራል፡፡

የብረት ነክ ምርቶች ከሚገባው በላይ ዋጋ ለመጨመራቸው የተለያዩ ምክንያቶች ቢደመጡም፣ እነዚህን ምርቶች በግብዓትነት ተጠቅመው የሚካሄዱ የተለያዩ ግንባታዎችና ሌሎች አምራቾችም ላይ ጫና ተፈጥሯል፡፡

      ቀደም ያለውን የብረት ዋጋ በማስላት ውለታ የገቡ አገልግሎት ሰጪዎች፣ ልጓም አጥቷል በተባለው ዋጋ ብረት ገዝተውና የምርት ትዕዛዛቸውን አጠናቀው ለማስረከብ እየተቸገሩ ነው፡፡ በኮንስትራክሽን ዘርፍም ቢሆን፣ የግንባታ ሥራዎች ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረ ነው፡፡

ችግሩን  ከምርት እጥረት ጋር የሚያያይዙት አሉ፡፡ ከውጭ የሚገቡት ምርቶች በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ፣ ምርቱን እንደ ልብ ማስገባት ስላልቻሉ በዚህ ሰበብ እየተፈጠረ የሚገኝ ችግር ስለመሆኑም ለማመላከት የሚሞክሩ አሉ፡፡ ይሁንና ችግሩ ከምርት እጥረት ጋር ብቻ የተያያዘ ሳይሆን፣ በእጅ ያሉትንም ምርቶች በአግባቡ ካለማቅረብ ጋር ግንኙነት እንዳለው ይታመናል፡፡ እንደውም አንዳንድ ብረት አምራቾችም ሆኑ አቅራቢዎች ከነጋዴዎች ጋር ተመሳጥረው ምርቱ በበቂ ሁኔታ ለገበያ እንዳይሠራጭ እያደረጉ ነው የሚለው አስተያየት እዚህም እዚያም ይሰማል፡፡

አንዳንድ ብረት አምራቾች ከተወሰኑ ነጋዴዎች በቀር የሌሎችን የግዥ ጥያቄ የማይቀበሉ መኖራቸውም ለችግሩ መባባስ ምክንያት እየሆነ በመምጣቱ ሁኔታውን እንዳባባሰው ይነገራል፡፡ በመንግሥት በኩል በዚህ ዘርፍ ላይ ታየ የተባለውን ችግር ለመቅረፍ እወስደዋለሁ ያለውን ዕርምጃ አለመውሰዱ ገበያው ጤናማ አካሄድ እንዳይጓዝ አድርጎታል፡፡

በአዲሱ የውጭ ምንዛሪ ተመንና የሥርጭት ወይም የአቅርቦት መመርያ መሠረት፣ እነዚህን ምርቶች ለማስገባት የራሱ የሆነ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ ቢችልም በዚህን ያህል ደረጃ እጥረት ሊፈጥርና ዋጋ ሊያንር አይችልም፡፡ ስለዚህ በምንም ሰበብ የተፈጠረውን ክፍተት ለመድፈን ገበያውንም ለማረጋጋት የችግሩ ምንጮችና ሰበቦችን በመፈተሽ የማስተካከያ ዕርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ መግለጽ ግድ ነው፡፡

በእርግጥ የብረት አምራቾችም ሆኑ አቅራቢዎች እየሸጡበት ያለው ዋጋ ምክንያታዊ ስለመሆኑ ማጥናት፣ መከታተልና መቆጣጠር  አንድ ጉዳይ ሆኖ፣ በየሰበቡ ሆን ተብሎ እጥረት ለመፍጠርና ገበያውን ለመበረዝ የሚደረገውን ዓይን ያወጣ እንቅስቃሴም መቃኘት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ ብረት አምራቾች ከአገር ውስጥ ከሚሰበሰቡ ውድቅዳቂ ብረቶችን አቅልጠው የሚሠሩ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ እንዴት የምርት እጥረት ሊፈጠር ይችላል? የሚለውን ጥያቄ ስለሚያስነሳው ነው፡፡ ይህም ሲባል በቂ ውድቅዳቂ ብረት ይቀርብላቸዋል ማለትም ይቸግራል፡፡ ምክንያቱ ምንም ይሁን ግን የገበያው እንዳሻው መውጣትና መውረድ ለግንባታ ዘርፉም ሆነ የብረታ ብረት ምርቶችን በግብዓትነት የሚጠቀሙ አምራቾች ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑ መታሰብ አለበት፡፡

የውጭ ምንዛሪ እጥረቱም ቢሆን ዕውን እንደተባለው ዋጋ ሊያስጨምር የሚችል ነው ወይ? ማለት ያስፈልጋል፡፡ በነገራችን ላይ ሁላችንም እንደምንገነዘበው በብረት ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎችም ምርቶች ላይ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አለ፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ ለየባንኮቹ የሚቀርበው የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ ተደማምሮ ሲታይ ካለው አቅርቦትና ፍላጎት ጋር ፈጽሞ የማይገናኝ ነው፡፡

የሚቀርበው ጥያቄ ሁሉስ አግባብ ነው ወይ? ብለን ከጠየቅን ምላሹ ሌላ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ስለሚኖርና በተፈለገው ጊዜ ስለማይገኝ ለማንኛውም ተብሎ ሁሉም የውጭ ምንዛሪ ፈላጊ ጥያቄውን ከሚያስፈልገው በላይ ጨማምሮ ለባንኮች ያቀርባል፡፡ ይህ ደግሞ ሰው ሠራሽ ፍላጎት ስለሚሆን ለወረፋ ተብሎ የሚያዝ የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ የተምታታ ሥዕል ይሰጣል፡፡ ወረፋ ለመያዝ ብቻ የሚደረግ ጥያቄ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትን በትክክል ለማወቅ አስቸጋሪ እያደረገው መሆኑም ገበያ ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡

ይህም በመሆኑ የውጭ ምንዛሪ ዕደላን ለመተግበር የወጡ መመርያዎችን የማስፈጸም ሒደት ላይ ተፅዕኖ ስለሚኖረው፣ የውጭ ምንዛሪ የሚገኘውም ለወራት ተጠብቆ በመሆኑ (ቅድሚያ የሚሰጣቸው መስኮች መጠነኛ ዕፎይታ አላቸው፡፡ ቢያንስ ዶላሩ በተገኘ ጊዜ ሁሉ ያለወረፋ ይስተናገዳሉ) ለክፉም ለደጉ ወረፋ ልያዝ እየተባለ ያለበቂ ዝግጅት የሚቀርብ ጥያቄን ሊያስቀር የሚችል አሠራር ሊዘረጋ ይገባል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚፈጠረውን ችግር ለማቃለል ከውጭ ምንዛሪ ጥያቄና ወረፋ አያያዝ ላይ አዲስ አሠራር ቢዘረጋ፣ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሰበብ የሚፈጠሩ የዋጋ ንረቶችን በተወሰነ ደረጃ ከማቃለሉም በላይ ወረፋ ለመጠበቅ ብቻ የሚቀርቡ ማመልከቻዎችን ሊያስቀር ይችላል፡፡

ከሁሉም በላይ ግን አዲሱ የውጭ ምንዛሪ ዕደላ ለየትኛው ቅድሚያ እንደሚሰጥ የትኛው እንደሚከተል ማሳወቅም እንደ ብረትና መሰል ምርቶች ገበያ ውስጥ ዋጋቸው የሚጨመረው በዶላር እጥረት ነው የሚለውን ሰበብ ለማስቀረት ችሏል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት