Saturday, September 30, 2023

የፓርላማው አዳዲስ ጅምሮችና አንድምታዎች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በሥራ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ፓርላማ አባላት ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ በሚከተለው የዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የዲሲፕሊን (ሥነ ሥርዓት) መመርያ ምክንያት፣ ከሥራ አስፈጻሚው የመንግሥት አካል ጋር የፖሊሲ ክርክር ውስጥ እንዲገቡ አይፈቀድላቸውም፡፡ በመሆኑም የሕዝብ ተወካዮች የሆኑት የፓርላማ አባላት የኃላፊነት ድርሻ የመንግሥትን የሥራ አፈጻጸም፣ የሕጎች አተገባበርና የበጀት አጠቃቀም ጉድለቶችን በመለየት ሥራ አስፈጻሚውን መከታተልና መቆጣጠር ላይ ብቻ ያተኮረ ነው፡፡ ይህንንም ኃላፊነት በዕውቀት ተደግፈው መወጣትና ተፅዕኖ የመፍጠር ብቃትና ቁርጠኝነት እንደሌላቸው ይተቻሉ፡፡

በዚህም የተነሳ የአገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን በኢትዮጵያ ፓርላማው በሕገ መንግሥት እንደተደነገገው የአገሪቱ ከፍተኛ የሥልጣን አካል መሆን እንዳልቻለ፣ ከዚህ ይልቅ ሥልጣኑን ከእርሱ በታች ወይም ለፓርላማው ተጠሪ ለሆነው የሥራ አስፈጻሚው አካል አሳልፎ ሰጥቶ በእሱ የሚታዘዝና በፓርቲ አመራሮች ተዕኖ ሥር የወደቀ በመሆኑ፣ ሕይወት የሌለው አካል አድርገው በተለያዩ መድረኮች ሲተቹ ይደመጣሉ፡፡

‹‹አንድ ሚኒስትር ፓርላማ ቀርቦ ካልተሰደበ ወይም እንዲወጠርና እንዲጨነቅ ሆኖ ካልታየ ፓርላማው ኃላፊነቱን እየተወጣ አይደለም ብሎ መደምደም ተገቢ አይደለም፡፡ ፍፁም ስህተት ነው፤›› ሲሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ በፓርላማው ላይ የሚቀርበውን ትችት ይከላከላሉ፡፡

አቶ አስመላሽ ከወታደራዊ የደርግ መንግሥት ውድቀት በኋላ በተመሠረተው መንግሥት በ26 ዓመታት ጉዞ ውስጥ ከሞላ ጎደል ያሳለፉት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነት፣ በተለይም የምክር ቤቱ የሕግ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ ላለፉት ሦስት ዓመታት ደግሞ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር በመሆን ነው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና በኢትዮጵያ የተቋቋሙ የዴሞክራሲ ተቋማት የ15 ዓመታት ጉዞ ከባለድርሻ አካላት ጋር በሚያዝያ ወር 2009 ዓ.ም. በተገመገመበት ወቅት፣ የፓርላማው ደካማነትና በመንግሥት ተፅዕኖ ሥር የወደቀ ሆኖ ስለመቆየቱ በተወያዮች መታመኑና መተቸቱን በስህተት በመፈረጅ ተከራክረዋል፡፡

የክርክራቸው ማጠንጠኛም አገሪቱ ስለምትከተለው ፓርላሜንታሪያዊ የመንግሥት አወቃቀር ሥርዓት ምሉዕ ግንዛቤ ካለመያዝ መመንጨቱን ይገልጻሉ፡፡

ኢትዮጵያ በምትከተለው ፓርላሜንታሪያዊ የመንግሥት አወቃቀር ሥርዓት በፓርላማው አብላጫ ወንበር የሚይዘው ፓርቲ ገዥ ፓርቲ እንደሚሆን፣ ሥራ አስፈጻሚውንም አካል የሚመሠርተው ይኼው አብላጫ ወንበር የያዘ ፓርቲ መሆኑ በሥርዓቱ ተከታይ አገሮች ጭምር ያለ ነባራዊ ዕውነት መሆኑን አቶ አስመላሽ ያስቀምጣሉ፡፡ በማከልም፣ ‹‹አብላጫ ወንበር በያዘውና መንግሥት በሚመሠርተው ፓርቲ መካከል የሥራ ድርሻ ልዩነት ይኖራል፡፡ ነገር ግን በርዕዮተ ዓለም ደረጃ ልዩነት የላቸውም፡፡ ታዲያ እንዴት የፖሊሲ አሠራር ሊኖር ይችላል?›› ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

አንድ በሥራቸው ሥራ ምክንያት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የፖለቲካ ተንታኝ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አቶ አስመላሽ ያቀረቡትን አመክንዮ አይስማሙበትም፡፡ አቶ አስመላሽ ያቀረቡት መከራከሪያ በሁለት ምክንያቶች ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይችል ይናገራሉ፡፡

አንድም ከኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ድንጋጌ፣ ሁለተኛ የፓርላሜንታሪያዊ ሥርዓትን ከሚከተሉ የዳበረ ልምድ ካላቸው አገሮች ተሞክሮ ያፈነገጠ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

የኢትየጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 54(4) ላይ ‹‹የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የመላው ሕዝብ ተወካዮች ናቸው፤›› የሚል ድንጋጌ ማስቀመጡን የሚጠቅሱት እኚሁ ባለሙያ፣ በዚሁ አንቀጽ ሥርም የፓርላማ አባላት ተገዥነት (ተጠያቂነት) ለሕገ መንግሥቱ፣ ለሕዝቡና ለህሊናቸው ብቻ መሆኑ በግልጽ መደንገጉን ያስታውሳሉ፡፡

በዚሁ የሕገ መንግሥት አንቀጽ 54(5) ላይም፣ ‹‹ማንኛውም የምክር ቤቱ አባል በምክር ቤቱ ውስጥ በሚሰጠው ድምፅ ወይም አስተያየት ምክንያት አይከሰስም፣ አስተዳደራዊ ዕርምጃም አይወሰድበትም፤›› ተብሎ የፓርላማ አባላት በነፃነት ያለ ፓርቲ ዲሲፕሊን ተፅዕኖ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዲችሉ መደንገጉን በመግለጽ የአቶ አስመላሽን አመክንዮ ውድቅ ያደርጋሉ፡፡

‹‹በአቶ አስመላሽ ቀረበ የተባለውን መከራከሪያ በተለያዩ የሥራ አጋጣሚዎች ከተለያዩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ የሚሰማ ይሁን እንጂ፣ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌውን የሚጣረስና ለወቅታዊው የፖለቲካ ቀውስ ዋነኛ ከሚባሉት ችግሮች እኩል ገዥው ፓርቲ የሚከተለው ዴሞክራሲዊ ማዕከላዊነት ድርሻ አለው፤›› በማለት ይከራከራሉ፡፡

በዚህ ማዕከላዊነት የታፈነ ፓርላማ እንኳን የፖሊሲ ክርክር ሊያደርግ አስፈጻሚው መንግሥት ሲባልግም መቆጣጠር ባለመቻሉ፣ አገሪቱ ቀውስ ውስጥ ልትገባ መቻሏን ይጠቅሳሉ፡፡

ፓርላሜንታሪያዊ ሥርዓትን የሚከተሉ የዓለም አገሮች ተሞክሮ የሚያሳየውም የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት እንደሚሉት አለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ይህንን የመንግሥት ሥርዓት ለዓለም ያስተዋወቀች እንግሊዝ መሆኗንና በእንግሊዙ ፓርላማ (House of Commons) አብላጫ ወንበር የያዘው ፓርቲ መንግሥት የመመሥረት ሥልጣን እንደሚኖረው፣ ነገር ግን የሚመሠረተውን መንግሥት በመከታተልና በመቆጣጠር ረገድ ፓርላማው ጠንካራ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ይህም የሆነው በእንግሊዝ ፓርላሜንታሪያዊ የመንግሥት ሥርዓት ውስጥ በመንግሥትና በፓርላማው መካከል ግልጽ የሆነ የሥልጣን ክፍፍል በመኖሩ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

በምክር ቤቱ ወንበሮች የፊት ረድፍ የሚቀመጡት የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮችና የፓርላማው አባል እንደሆኑ፣ የኋላ ረድፍ ተቀማጮች ደግሞ የሙሉ ጊዜ የፓርላማ ኃላፊነታቸውን የሚወጡ የሕዝብ ተወካዮች መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ እነዚህ ሁለት ቡድኖች የአንድ ፓርቲ አባላት ቢሆኑም፣ የሥልጣን ክፍፍላቸውን በሕግ አግባብ የሚወጡ መሆናቸውን የገለጹት እኚሁ ተንታኝ፣ መንግሥት በፓርላማው የሚፈለገውን ለማስወሰን በሚያደርገው ጥረት ከፍተኛ ክርክር እንደሚካሄድ ያስረዳሉ፡፡

የመንግሥት ወይም የፓርቲ ተጠሪ (ዊፕ) የሚባል የፓርላማ አባል የሆነ ሹመኛን ማስቀመጥ የተጀመረውም በእነዚህ ሁለት ቡድኖች መካከል ልዩነትን ለማጥበብ ወይም ሎቢ ለማድረግ ሲባል መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ፓርላሜንታሪያዊ ሥርዓትን በሚከተሉ አንዳንድ አገሮች የፓርላማ አባላት ጫማ እስከ መወራወርና ግብግብ እስከ መፍጠር እንደሚያደርሱ የሚረዱት አቶ አስመላሽ፣ ‹‹በኢትዮጵያ ፓርላማ መቼም ቢሆን ይህ እንዲፈጠር አንፈልግም፡፡ ዓላማችንም አይደለም፡፡ የተቀናጀ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ዕውን እንዲሆን ነው የምንሠራው፤›› ይላሉ፡፡

አዳዲስ ምልክቶች በኢትዮጵያ ፓርላማ

በአንድ በኩል ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ የሚከተለው ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የኢትዮጵያን ፓርላማ ሕይወት የሌለው የመንግሥት አካል አድርጎታል የሚሉ ልሂቃን አሉ፡፡ በሌላ በኩል በፓርላማውና በአስፈጻሚው መካከል የሥራ ድርሻ እንጂ የርዕዮተ ዓለም ሆነ የፕሮግራም ልዩነት ባለመኖሩ፣ የዲሲፕሊን መርሁ የፓርቲው አንድ ምሰሶ ነው የሚል ክርክርም አለ፡፡ እነዚህ ያልተፈቱ ክርክሮችና ግጭቶች ባሉበትና ተቃውሞዎች እየነገሡ በመጡበት የኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ከባቢ ውስጥ፣ ፓርላማው አዳዲስ ምልክቶችን ማሳየት ጀምሯል፡፡

እነዚህ አዳዲስ ምልክቶች መታየት የጀመሩት የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ ሥልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ ካቀረቡ በኋላ ነው፡፡

ፓርላማው ሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመኑን በመስከረም ወር 2010 ዓ.ም. ከመጀመሩ አስቀድሞ አቶ አባዱላ ከአፈ ጉባዔነት ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸው ሪፖርተር ይፋ ካደረገ በኋላ፣ አቶ አባዱላም ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸውን በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ይፋ አድርገዋል፡፡ የአቶ አባዱላ ውሳኔ ምክንያት የኦሮሞ ሕዝብና የሚወክሉት መሠረታዊ ድርጅት የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ክብር ተነክቷል የሚል ነው፡፡ ይህንኑ በይፋ ያሳወቁት አቶ አባዱላ የሚወክሉትን ሕዝብና ድርጅት ክብር ለማስመለስ እንደሚታገሉም አክለው መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡ ፓርላማው መደበኛ ሥራውን ከጀመረበት ወቅት አንስቶ የመክፈቻ ስብሰባውንና አንድ ሌላ መደበኛ የፓርላማ ስብሰባ ብቻ በአቶ አባዱላ አፈ ጉባዔነት ተመርቷል፡፡ ሌሎቹ የምክር ቤቱ ስብሰባዎች ግን በምክትል አፈ ጉባዔዋ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ እየተመሩ ነው፡፡

ታኅሳስ 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ስብሰባውን ያጠናቀቀው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አቶ አባዱላ ወደ መንግሥታዊ ሥልጠናቸው እንደሚመለሱ መወሰኑን የተለያዩ ዘገባዎች ጠቁመዋል፡፡ የሪፖርተር ምንጮች ግን ይህ ሥልጣን አፈ ጉባዔነት ሊሆንም ላይሆንም እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ሌላው የለውጥ ምልክት በፓርላማው የታየው ኅዳር 14 ቀን 2010 ዓ.ም. ሲሆን፣ በዚህ ሰብሰባ ፓርላማው ምልዓተ ጉባዔውን ለጥቂት ማሟላት ችሎ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች እንደሚነሱበት የሚታወቀውን የከተማ ፕላን አዋጅ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይሁንታ እንዲሰጥበት መርቷል፡፡  

ይህ ረቂቅ አዋጅ በ2008 ዓ.ም. በኦሮሚያ ተቀስቅሶ ለነበረው የሕዝብ ተቃውሞ ምክንያት ከሆነው የአዲስ አበባና የአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ጋር ግንኙነት ያለው በመሆኑ፣ የኦሮሞ ሕዝብንና ኦሕዴድን የወከሉ የፓርላማ አባላት ረቂቁ እንዳይፀድቅ፣ የሚፀድቅ ከሆነም የዚህ ሒደት አካል ላለመሆን በዕለቱ ስብሰባ ላለመገኘት ወስነው መቅረታቸውን የሪፖርተር ምንጮች ይገልጻሉ፡፡ በወቅቱ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ምክትል አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ ግን ይህንን አስተባብለዋል፡፡ የፓርቲው አባላት በመስክ ሥራ ላይ በመሆናቸው የተፈጠረ ክፍተት መሆኑን በወቅቱ ገልጸዋል፡፡

ኅዳር 26 ቀን 2010 ዓ.ም. የተካሄደው የምክር ቤቱ ስብሰባ የቀረበውን የደን ጥበቃና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ በ13 ድምፅ ተዓቅቦ ማፅደቁ ይታወሳል፡፡ በኢሕአዴግ የዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ከላይ የተወሰነን ውሳኔ የበታች የፓርቲው ተወካዮችና አባላት የመቀበል የፓርቲ ዲሲፕሊን የተጣለባቸው በመሆኑ፣ በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ የተቃውሞ ድምፅ ከማስመዝገብ ይልቅ ተዓቅቦን መርጠዋል፡፡ ረቂቁ የክልላችንን የተፈጥሮ ሀብት የማስተዳደር ሥልጣን የሚጋፋ ነው በሚል ነበር ተዓቅቦ ያደረጉት፡፡

ሌላው የምክር ቤቱ አባላት ያሳዩት ግዙፍ የለውጥ ምልክት በወቅታዊ የአገሪቱ የፖለቲካ ቀውስ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርላማ ቀርበው ማብራሪያ ካልሰጧቸው፣ መደበኛ ስብሰባዎችን እንደማያካሂዱ ገልጸው በውሳኔያቸው መፅናታቸው ነው፡፡  

ምልክቱ በዚህ ብቻ አላበቃም፡፡ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላትን ልዩ ጥቅም አስመልክቶ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች ታኅሳስ 13 ቀን 2010 ዓ.ም. የጠሩት ሕዝባዊ ውይይት፣ ከኦሮሚያ ክልል ተወክለው በመጡ የክልሉ አመራሮችና የፓርላማው የኦሕዴድ አባላት ከፍተኛ ተፅዕኖ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ተደርጓል፡፡ እነዚህን ተከታታይ ምልክቶችን ያጤነው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮችን ለመፍታት የጀመረውን ስብሰባ አቋርጦ፣ ሰኞ ታኅሳስ 16 ቀን 2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ሌሎች የኢሕአዴግ መሠረታዊ ድርጅቶች አመራሮች የፓርላማ አባላትን አነጋግረዋል፡፡ የፓርላማ አባላት ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማው መድረክ ተገኝተው ለጥያቄያቸው ምላሽ እንዲሰጡ ቢሆንም፣ የገዥው ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ግን የግንባሩን ሊቀመንበር ይዞ ከፓርላማ አባላቱ ጋር በፓርቲ መድረክ ተገናኝተው በዝግ ተወያይተዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ፓርላማው ታኅሳስ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡

በፓርላማው የታዩ ምልክቶች አንድምታ

ታኅሳስ 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላትን ልዩ ጥቅም ለመወሰን በተረቀቀው አዋጅ ላይ የተጠራው ሕዝባዊ ውይይት በተፅዕኖ ምክንያት ለሻይ እረፍት በተበተነበት ወቅት፣ በምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴና አቶ አባዱላ ገመዳ ከኦሮሚያ ክልል በተወከሉ አመራሮች ተከበው ሲወዛገቡ ተስተውለዋል፡፡ አቶ አስመላሽና አቶ አባዱላ ከኦሮሚያ አመራሮች ጋር የገጠሙት ክርክር የፓርላማውን የሥራ ኃላፊነት ማንም ሊያስተጓጉል አይችልም የሚል ሲሆን፣ ከኦሮሚያ የተወከሉት አመራሮች ደግሞ የፓርላማው የሥራ ሒደት ተዘሏል፣ ቋሚ ኮሚቴው በመጀመርያ የጥቅሙ ባለቤት የሆነውን የኦሮሞ ሕዝብ ሊያነጋግር ይገባል ብለው ነበር፡፡

በዚህ የሻይ ዕረፍት እሰጥ አገባ የተበሳጩ የሚመስሉት አቶ አስመላሽ፣ ‹‹ይህ ሥርዓት ወዴት እየሄደ እንደሆነ ማሳያ ነው፤›› ሲሉ በዕለቱ የተከሰተውን ውዝግብ ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡

በፓርላማው እየታዩ ያሉትን ምልክቶች አንድምታ በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ስማቸውን እንዳይገለጽ የጠየቁት የፖለቲካ ተንታኝ፣ ‹‹መነሻ ምክንያቱ ምንም ይሁን የገዥው ፓርቲ ማዕላዊነት እየተሸረሸረ መሆኑን የሚያመለክት፣ ይህም ፓርላማው ሥልጣኑን ለመወጣት እየዳኸ መሆኑን የሚያሳይ ነው፤›› ይላሉ፡፡

በፓርላማው ብቅ ያሉ ተራማጅ ኃይሎች ያሳዩት አንድ ዕርምጃ እንደሆነና ይህም ለአገሪቱ ተስፋ ብልጭ እንዳደረገ ያምናሉ፡፡ ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ሌሎች የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ሰሞኑን የፓርላማ አባላትን በፓርቲ መድረክ ማነጋገራቸው የተስፋ ብልጭታውን ሊያጠፋው ይችላል የሚል ሥጋት እንደፈጠረባቸውም ይገልጻሉ፡፡

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች ተመራማሪና የሕግ ባለሙያ አቶ ኤፍሬም ታምራት በበኩላቸው፣ በፓርላማው እየታየ ያለው ምልክት በኢሕአዴግ መሠረታዊ ድርጅቶች መካከል እየተካሄደ ያለው ትግል ወደ ፓርላማውም መዝለቁን የሚያሳይ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

በዚህ ሒደት ውስጥ እየተሸረሸረ መሆኑ ግልጽ ሆኖ የወጣው የገዥው ፓርቲ መጠርነፊያ የሆነው ማዕከላዊ ዴሞክራሲያዊነት ቢሆንም፣ ይህንኑ መሣሪያ ግን እንደ ኦሕዴድ ያሉ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ለጀመሩት ትግል እየተጠቀሙበት እንደሆነ የፓርላማው አባላት ሰሞነኛ ተግባር ማስረጃ መሆኑን በማስረገጥ ይናገራሉ፡፡

እየታዩ ያሉት ምልክቶች በገዥው ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አመራሮች ጣልቃ የመግባት ሙከራ ይጨናገፋሉ የሚል ሥጋት እንደሌላቸው የሚያወሱት አቶ ኤፍሬም፣ የሚታዩት ምልክቶች ሥር ነቀል ለውጥ በፓርላማ ውስጥ መትከል ሳይሆን ሕገ መንግሥቱ ሳይሸራረፍ እንዲተገበር የሚያደርግ ንቅናቄ እንደሚመስሉ ይገልጻሉ፡፡

‹‹ያልተለመደ ይሁን እንጂ ገዥው ፓርቲ ሊቃወመው የማይችለው ኃላፊነትን በሕጋዊ ማዕቀፍ ውስጥ የመወጣት ተግባር በመሆኑ የመቀጠል አዝማሚያው ከፍተኛ ነው፤›› ብለዋል፡፡ 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -