Friday, February 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በኢሕአዴግ ግምገማ ምንም የሚመጣ ለውጥ የለም››

አቶ ገብሩ አሥራት፣ የቀድሞ የኢሕአዴግ አመራርና የአረና ፓርቲ ሊቀመንበር

በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ደም አፋሳሽ ግጭቶች ተከስተው በርካታ መሠረታዊ ጥያቄዎች እየቀረቡበት ባለበት ወቅት፣ ገዢው ፓርቲ ከተሃድሶ በኋላ ያለፉትን 15 ዓመታት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ማካሄድ ጀምሯል፡፡ ግጭት ባስነሱት በርካታ ትዕይንተ ሕዝቦች እየተነሱ ያሉት ጥያቄዎች አብዛኛዎቹ ሕዝብ የሚያምንባቸው ብቻ ሳይሆኑ፣ ገዢው ፓርቲ ጭምር የማያምንባቸው ናቸው፡፡ በተለይ በሙስና፣ በመልካም አስተዳደር፣ በሰብዓዊ መብቶች አከባበር፣ በነፃነትና በፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ጥያቄዎች ላይ ድምፆች ጎልተው ተሰምተዋል፡፡ ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የተለያዩ ሰነዶች ቢያዘጋጅምና ቁርጠኛ መሆኑንም በተለያዩ ጊዜያት ቢያሳውቅም፣ የታየ ለውጥ አለመምጣቱ እያስወሰቀው ነው፡፡ በወቅታዊ ሁኔት ላይ የቀድሞውን የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩትን፣ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል እየተንቀሳቀሰ የሚገኘውን አረና ፓርቲ የሚመሩትን አቶ ገብሩ አሥራት ውድነህ ዘነበ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ ከጓደኞችዎ ጋር ከመሠረቱት ሕወሓት በልዩነት ከወጡ 15 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ እነዚህ 15 ዓመታትን ወደኋላ መለስ ብለው ሲመለከቱ ምን ይታዘባሉ?

አቶ ገብሩ፡- 15 ዓመታት ቀላል አይደሉም፡፡ በእነዚህ ዓመታት ብዙ ውጣ ውረዶች አልፈዋል፡፡ እኔም እንደ ዜጋ የሚከሰቱ ጉዳዮችን እከታተላለሁ፡፡ በተለይ ከ15 ዓመት በፊት ተሃድሶ በሚል ሽፋን የተደረገው የአምባገነን አገዛዝ መቋጫ አገኘ፡፡ በእነዚህ ዓመታት በግሌም ብዙ ጫናና ወከባ ደርሶብኛል፡፡ ከዚህ በኋላ ፓርቲ አቋቁመናል [አረና]፡፡ በዚህ ፓርቲ ብዙ ጫና፣ ወከባ ተፈጥሯል፡፡ አባሎቻችን ታስረዋል፣ ተሰደዋል፣ ከሦስት በላይ ሞተዋል፡፡ በዚህ አገር ሰላም አለ ተብሎ ፓርቲ ካቋቋምን በኋላ የሚደርስብን ጫና ቀላል አይደለም፡፡ ግድያ ሲመጣ፣ እስር ሲመጣ በጣም ከባድ ነው የሚሆነው፡፡ እስካሁን 20 የሚሆኑ አባሎቻችን ታስረዋል፡፡ ገበሬዎች ሳይቀሩ ከእርሻቸው የተፈናቀሉና ታስረው የሚማቅቁ አሉ፡፡ የተሰደዱ ሁሉ አሉ፡፡ ይህ አሳዛኝ ክስተት ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ ከአገሪቱ አጠቃላይ ሁኔታ ነጥዬ አላየውም፡፡ በግሌም ሥራ እንዳይኖረኝ ተደርጓል፡፡ ክትትል ይደረግብኛል፡፡ በእኔና በቤተሰቤም ላይ ጫና እየተደረገ ነው፡፡ እነዚህን 15 ዓመታት ያሳለፍኩት በዚህ ሁኔታ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በልዩነት ከሕወሓት ወጥተዋል፡፡ ሕወሓት ውስጥ አብረዎት የታገሉ አሁን በሥልጣን ላይ ያሉ ጓደኞች ይኖሩዎታል፡፡ ከእነዚህ ጓደኞችዎ ጋር ትገናኛላችሁ? ሻይ ቡና ትላላችሁ? ስለወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ትመካከራላችሁ?

አቶ ገብሩ፡- ክፍፍሉ በተፈጠረበት ጊዜ 12 የምንሆን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ተለይተናል፡፡ ከዚያ በኋላ አሥራ ሁለታችንም በአንድ የፖለቲካ ሥርዓት ተደራጅተን አልሄድንም፡፡ ከወጣነው ውስጥ አቶ አዋሎም ወልዱ፣ ወይዘሮ አረጋሽ አዳነና እኔ ገብሩ አሥራት አረና ፓርቲ ውስጥ ነን፡፡ እኛ እንገናኛለን፡፡ ከሌሎች ጋር አንገናኝም፡፡ አልፎ አልፎ በማኅበራዊ ጉዳዮች እንገናኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- ስትገናኙ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ትመካከራላችሁ? ሰላምታችሁ የናፍቆት ነው? ይህን የምልዎት ልዩነት ቢኖርም በሌሎች ጉዳዮች ላይ መወያየትና መጠያየቅ የሠለጠነ አካሄድ በመሆኑ ነው፡፡ የእናንተ ሁኔታ ምን ሊያስተምር ይችላል?

አቶ ገብሩ፡- ልክ ነው፡፡ የኢሕአዴግ አስቸጋሪ ነገሩ ይህ ነው፡፡ እውነት ለመናገር ፖለቲካና ማኅበራዊ ጉዳዮች ተቀላቅለዋል፡፡ በፖለቲካ ከተለየህ ከማኅበራዊ ግንኙነቶችም እንድትለይ ይፈለጋል፡፡ ሁለቱን ለያይቶ የመመልከት ነገር የለም፡፡ ከሕወሓት ፖለቲካ ከተለየህ እንደ ጠላት ነው የምትቆጠረው፡፡ እንደ ጠላት ተፈርጀህ ነው ኑሮህን የምትኖረው፡፡ የዚህ ተፅዕኖ አለ፡፡ የፖለቲካ ልዩነት ይዞ በሌሎች ጉዳዮች መገናኘትና መወያየት ይቻል ነበር፡፡ በሠለጠነው ዓለም ፖለቲካ ሌላ ነው፣ ማኅበራዊ ጉዳይ ሌላ ነው፡፡ በትጥቅ ትግል ያለፈ ወገን፣ በበጎውም በክፉውም አብሮ የተንቀሳቀሰ ወገን በማኅበራዊ ጉዳዮች መገናኘት የግድ ይል ነበር፡፡ ነገር ግን ድርጅቱ በባህሪው ለፖለቲካ መሣሪያነት ነው ሁሉን ነገር የሚጠቀመው፡፡ በሕወሓት ይኼ እንደ ፖለቲካ ሥልት ነው የሚቆጠረው፡፡ በፖለቲካ ስትለያይ ነጥሎ የመምታት፣ የማዳከም አካሄድ አለ፡፡ በዚህ ጫና ተገደህ ለፓርቲው እንድታጎበድድ ለማድረግ ይሞከራል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ በልዩነት ከመለየትዎ በፊት በትጥቅ ትግሉም በመንግሥት መዋቅር ውስጥም ከፍተኛ አመራር ነበሩ፡፡ የዚያን ጊዜ የነበረው ሕወሓት/ኢሕአዴግ እና የአሁኑ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ልዩነትና አንድነቱን እንዴት ይመገግሙታል?

አቶ ገብሩ፡- ኢሕአዴግን በምናስብበት ጊዜ ባህሪውን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ድርጅቱ አሁን በችግር ውስጥ የተዘፈቀበትን መሠረታዊ ጉዳይ ማየት ያስፈልጋል፡፡ የችግሮቹ ዋና ምንጭ የሚከተለው ርዕዮተ ዓለምና ከዚህ ርዕዮተ ዓለም የሚነሱ መርሆዎች ናቸው፡፡ ኢሕአዴግ እንደሚታወቀው ማርክሳዊ ነኝ ብሎ የሚያምን ድርጅት ነበር፡፡ መርሆዎቹም ከዚህ ርዕዮቱ የሚመነጩ ነበሩ፡፡ እናም በትጥቅ ትግሉ ጊዜ ጎልቶ የወጣው ይህ ነው፡፡ ለአንድ አምባገነን መሪ ድርጀት የበላይነት ለማረጋገጥ የተነሳ ዴሞክራሲያዊ ወገናዊነት ነው፡፡ ዴሞክራሲ የሚሰጠው ለወዳጅ እንጂ ለሌላ አይደለም ብሎ የሚያምን ነው፡፡ በአጠቃላይ የአንድ ፓርቲ አምባገነንነት ለማንገስ የተነሳ ፓርቲ ነበር፡፡ ይህን ለማሳካት የተነሳ ፓርቲ ነበር፡፡ ዓለም ሲለወጥ ግን በዚህ አሠራር መቀጠል አስቸጋሪ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ውስጥ ራስዎን አውጥተው ነው እየተናገሩ ያለው?

አቶ ገብሩ፡- አለሁበት፡፡ እኔም ባለሁበት ጊዜ ያለውን ጨምሮ ነው እየነገርኩህ ያለሁት፡፡ እናም ዓለማዊ ሁኔታው ተለዋወጠ፡፡ ስለዚህ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚለው ርዕዮተ ዓለም ለአገዛዝ በሚመች መንገድ ተበጅቶ የቀደመውን አሠራር አስቀጠለ፡፡ ለምሳሌ እስካሁን ድረስ የፓርቲ የበላይነት (ሔጂሞኒ) ጥርነፋ፣ የመንግሥት አሠራር አንዱ ሌላውን ቼክ የሚያደርግበት የሌለበትና ሁሉም ነገር ለአንድ መደብ ተገዥ የሚሆንበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ የሚታወቀውን ዴሞክራሲ የማይቀበል ሆኖ ነው የቀጠለው፡፡ ስለዚህ አሁን የለውን ችግር ማየት ካስፈለገ ከዚህ መነሳት ያስፈልጋል፡፡ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መነሻነት ዴሞክራሲን የማይፈቅድ፣ ከኢኮኖሚ አንፃር የግሉን ዘርፍ የማያበረታታና መንግሥት በኢኮኖሚውና በፖለቲካው የበላይነት ይዞ እንዲሄድ የሚያደርግ ነው፡፡ የሁሉም ችግር ይኼ ነው የምለው፡፡ እምነቱ ይኼ ሆኖ እያለ ግን በውጭ አገሮች አስገዳጅነት የተነሳ ሊበራል አሠራርን እንደ ሽፋን አስቀምጧል፡፡ የሕገ ለመንግሥቱ ሲሶ የሚሆኑት መሠረታዊ የዴሞክራሲ መርሆዎች ናቸው፡፡ እነዚህ የሰብዓዊና የዴሞክራሲ መብት ድንጋጌዎች ለውጭ አገሮች ለታይታ የተቀመጡ እንጂ በተግባር ሲተገበሩ አይታይም፡፡ ገዢው ፓርቲ የሚመራው በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መርህ መነሻነት በተዘጋጁ ሰነዶች ነው፡፡ ከሰነዶቹ በሚመነጩ መመርያዎች ዜጋውን በወዳጅና በጠላት ይከፍላሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ ለወግ የተቀመጠ እንጂ የሚሠራ አይደለም፡፡ ያም ሆኖ ድርጅቱ አሁን ተለውጧል ወይ ለሚለው ጥያቄ አልተለወጠም ነው መልሱ፡፡

በ1985 ዓ.ም. የተነሳ ችግር ነበር፡፡ ታጋዩ ሙስና እየገነገነ ነው፣ እየተስፋፋ ነው የሚል ጥያቄ አንስቶ ነበር፡፡ ይህ ጥያቄ በወቅቱ ተጨፍልቋል፡፡ እንደገና ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በኋላ በ1992 እና በ1993 ዓ.ም. በድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ የነበረው የጋራ አመራር ከተባለው ርዕዮተ ዓለም ጋር የማይሄድ ስለነበር ክፍፍልን አስከተለ፡፡ ከዚያ በኋላ የአንድ አምባገነን ሰው አምባገነንነት ጎልቶ ወጣ፡፡ ያም ሆኖ ኢሕአዴግ በ1997 ዓ.ም. ከተቃዋሚዎች ከፍተኛ ተግዳሮት ገጥሞት ነበር፡፡ ክስተቱን በፀጋ ለመቀበል ዝግጁ አልነበረም፡፡ በርዕዮተ ዓለም ደረጃ ይህን ለመቀበል ዝግጁ አልነበረም፡፡ ደፍጥጦት አልፏል፡፡ ይህ ነገር ስላስደነገጠውም ተጨማሪ አፋኝ ዕርምጃዎችን ወስዷል፡፡ ነፃ ሚዲያ የሚያቀጭጭ፣ ብዙኃን ማኅበራትን የሚያፍን፣ አደገኛ ቦዘኔ በማለት አፋኝ ሕጎችን አውጥቷል፡፡ አምባገነንነት ተጠናክሮ መውጣት ችሏል፡፡ ኢሕአዴግ ከበፊቱ በአምባገነንነት ተጠናክሮ የወጣበት ጊዜ ነው፡፡ ከዚህ በኋላም የአቶ መለስ ሕልፈት ድርጅቱ ውስጥ አንድ ነገር ጥሎ አልፏል፡፡ አንድ በጣም ጠንካራ አምባገነን የነበረበት ድርጅት እሱን የሚተካ ሳያዘጋጅ አለፈ፡፡ እናም በዚህ መሠረት ኢሕአዴግ በታክቲክ ተዳክሟል፡፡ እንደ አቶ መለስ ሠራዊቱን ተቆጣጥሮ፣ መንግሥትን ተቆጣጥሮ፣ ድርጅትን ተቆጣጥሮ፣ ሁሉን ነገር በእጁ አስገብቶ የሚሄድ መሪ ክፍተት ተፈጠረ፡፡ ስለዚህ ከሥልት አንፃር ኢሕአዴግ እጅግ የተዳከመበት ጊዜ ነው፡፡ በድርጅቱ የታየው ሙስና በተጠናከረ መንገድ እንዲቀጥል በር ከፍቷል፡፡ ለብልሹ አስተዳደር የበለጠ በር ከፍቷል፡፡ አሁን በአገሪቱ የተፈጠረውን ጉዳይ ስመለከተው ድርጅቱ ከሕዝብ የተነጠለበት፣ የፖለቲካ ተቀባይነት (ሌጅትመሲ) ያጣበት፣ ይበልጥ በፀጥታ መዋቅር ለመግዛት የቆረጠበት ሁኔታ ተጥሯል፡፡ በፊት ለማስመሰል ሲባል ዴሞክራሲ አለ፣ ነፃነት አለ ይባል ነበር፡፡ በመሠረቱ እኔ ባለሁበት ጊዜም ቢሆን አገዛዙ ሁሉን ነገር ተቆጣጥሮ ለመሄድ ይሞክር ነበር፡፡ ምክንያቱም የምንከተለው ርዕዮተ ዓለምና የተከተልነው የፖለቲካ አቅጣጫ ይኼን የሚያደርግ ስለነበር አሁን የተደረሰበት ጊዜ ላይ ተደርሷል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎና ጓደኞችዎ በልዩነት ከወጣችሁ በኋላ ድርጅቱ በተለይ የአቶ መለስ ተፅዕኖ ነበረበት፡፡ ከእሳቸው ሕልፈት በኋላ የፖለቲካው የስበት ኃይል የት እንዳለ ለማወቅ የሚቸገሩ ብዙ ናቸው፡፡ እርስዎ ከኢሕአዴግ ጋር የቆዩ ሰው ስለነበሩ ይህን ጉዳይ ይረዱታልና ሐሳብዎን ቢያካፍሉን?

አቶ ገብሩ፡- እኔ ከአቶ መለስ ሕልፈት በኋላ የተገነዘብኩት ነገር ኢሕአዴግ በርዕዮተ ዓለም ያደረገው ለውጥ የለም፡፡ ከፖለቲካ አቅጣጫ ጋር የተያያዙ ለውጦችን አላደረገም፡፡ እንዲያውም የሚያስገርመኝ የሳቸውን ሌጋሲ እናስቀጥላለን የሚሉት አባባል ነው፡፡ ይኼ ለችግሩም ለውድቀቱም መነሻ ነው፡፡ የመለስ ሌጋሲ አምባገነንነት ነው፡፡ ፓርቲው ውስጥ ግን ጠንካራ ሰው ማለትም ጠንካራ አምባነገን ሊወጣ አልቻለም፡፡ በቅርቡም ሊወጣ የሚችል አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ የስበት ማዕከሉ ተበታትኗል፡፡ መከላከያ ሠራዊቱ አንድ የስበት ማዕከል ነው፡፡ ኢሕአዴግ አንድ የፖለቲካ የስበት ማዕከል ነው፡፡ ክልሎች እንደበፊቱ በጥብቅ ቁጥጥር ውስጥ አይደሉም፡፡ የራሳቸው ግዛት (ኪንግደም) ፈጥረዋል፣ የመንግሥት ተቋማትም አቶ መለስ እንደነበራቸው ተፈሪነትና ተቀባይነት በአሁኑ ወቅት ይህ ሞገስ ያለው መሪ ባለመኖሩ ራሳቸውን የስበት ማዕከል እያደረጉ ነው፡፡ ያም ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ካቤኔያቸው በሌላ መንገድ የስበት ማዕከል ናቸው፡፡ ስለዚህ በአንድም በሌላም የፖለቲካው እምብርት፣ የፖለቲካው አሽከርካሪ ይኼ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ ከውጭ አገር ዲፕሎማቶች ጋር ስንወያይ፣ ‹‹አቶ መለስ እያሉ አንድ ጉዳይ ለማስፈጸም ወደሳቸው ስንሄድ፣ ይሆናል! ወይ አይሆንም! የሚል ውሳኔ እናገኛለን፡፡ ነገር ግን  አሁን የት ሄደህ ማስፈጸም እንደምትችል አይታወቅም፤›› በማለት ይነግሩኛል፡፡ ይህን ሁኔታ ስመለከተው በአንድ አምባገነን መሪ እጅ ተከማችቶ የነበረው ፖለቲካ ወደ ሌሎች ቦታዎች ተሠራጭቷል፡፡ የስበት ማዕከሉ ተበታትኗል፡፡ ይኼ ቅራኔ ነው በኢትዮጵያ እየታየ ያለው፡፡ ኢሕአዴግ ነገሮችን ለማስፈጸም የማይችልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ የፖለቲካ የስበት ማዕከሉ የት እንዳለ የማይታወቅበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ በተደራጀ መንገድ ኢሕአዴግ የፖለቲካውን የስበት ማዕከል መቆጣጠር አልቻለም፡፡ ተሰሚነትና ክብር ያለው አመራርም የለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወጥተው ‹‹ሠልፍ እንዳታደርጉ፣ ሠልፍ ካካሄዳችሁ ትቀጣላችሁ፤›› አሉ፡፡ ነገር ግን በነጋታው በኦሮሚያም ሆነ በአማራ ክልሎች ብዙ ሠልፎች ተደርገዋል፡፡ ምክንያቱም ሕዝብ መንግሥትን ማመን አቁሟል፡፡ ንቋልም፡፡

ሪፖርተር፡- ኢሕአዴግ አራት ፓርቲዎች የፈጠሩት ግንባር ነው፡፡ መንግሥትም ይመራል፡፡ የሚወስናቸው ውሳኔዎች ግን በአጋር ድርጅቶች በሚመሩ ክልሎችም ተፈጻሚ እንዲሆኑ ይጠበቃል፡፡ ክልሎች በሚተላለፉ ትልልቅ ውሳኔዎች የራሳቸው ተሳትፎ እንዲኖራቸው በካቢኔ የሚወሰኑ ቢሆን የተሻለ አይሆንምን? እርስዎ በነበሩበት ጊዜ ይህን ለማጥራት አልተሞከረም?

አቶ ገብሩ፡- አጋር ድርጅቶች ለይስሙላ አጋር ይባላሉ እንጂ አገልጋይ ድርጅቶች ናቸው፡፡ በዚህ አገር በሚደረገው ፖለቲካዊ ውሳኔ ምንም ተሳትፎ የላቸውም፡፡ ሥልጣን ተከማችቶ የቆየው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ዘንድ ነው፡፡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ነው በዚህ አገር ያሉትን ጉዳዮች የሚወስነው፡፡ መወሰኑ ብቻ ሳይሆን መንግሥትም የተደራጀው ለይስሙላ ነው፡፡ መንግሥትና ፓርቲ አንድ የሆነበት አሠራር ነው ያለው፡፡ መሪ ድርጅት የሚለው እምነትም ይኼ ነው፡፡ ፓርቲው እያንዳንዱን እንቅስቃሴ መቆጣጠር አለበት፡፡ መንግሥትንም፣ የሙያ ማኅበራትንም የሚቆጣጠረው ፓርቲው ነው፡፡ እንዲያውም ኢሕአዴግ ሄዶ ሄዶ ማኅበራዊ እሴት የሆኑትን ዕቁብና ዕድር መቆጣጠር ጀምሯል፡፡ የኢሕአዴግ አመራር በተለይ ሥራ አስፈጻሚው ነው ዋና ተቆጣጣሪ፡፡ የኢሕአዴግ ውሳኔዎች ናቸው ገዢ፡፡ እንኳ አጋር ድርጅቶች ቀርቶ የኢሕአዴግ አባላት ራሳቸው ምንም ሥልጣን የላቸውም፡፡ ከላይ ከተወሰነ በጥርነፋ እስከ ታች ወርዶ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ ድሮ አቶ መለስ የወሰኑት እስከ ቀበሌ ድረስ ይወርዳል፡፡ አሁን ጉልበት አጣ እንጂ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ነው ሁሉን የሚወስነው፡፡ ፍርድ ቤቶች፣ ብዙኃን ማኅበራት፣ መከላከያ ሠራዊት የተለዩ ናቸው ቢባልም እውነታው ግን ይኼ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- በመተካካት መርህ በእርስዎ ደረጃ የነበሩ የቀድሞ አመራሮች በአብዛኛው ከፓርቲና ከመንግሥት መዋቅሮች ወጥተዋል፡፡ አብዛኛው በትግሉ ውስጥ ያልነበሩ አመራሮች በመተካካት በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ውስጥ ገብተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ይህ ሥራ አስፈጻሚ የሚወስነው ውሳኔ ታች ወርዶ ተፈጻሚ እየሆነ አይደለም፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ደም አፋሳሽ ግጭቶች እየታዩ ነው፡፡ በዚህ ሒደት ነባሮቹ ታጋዮች የመፍትሔ አካል የመሆን አዝማሚያ እያሳዩ ነው እየተባለ ነው፡፡ እነዚህ ክስተቶች የሚያስተላልፉት መልዕክት ምንድነው? በነባሮችና በአዲሶቹ አመራሮች መካከል ግጭት አይታይዎትም?

አቶ ገብሩ፡- በትክክል ግጭት አለ፡፡ አቶ መለስ መተካካት የሚል አቅጣጫ ሲያስቀምጡ እሳቸው ለሚያስቡት ፖለቲካ የራሳቸው ስሌት ነበራቸው፡፡ ምናልባትም ነባሩ ኃይል በአጠገባቸው መኖሩ ለሥራ እንቅፋት ሆኗል የሚል ሐሳብ ይኖራቸዋል፡፡ ከተሃድሶ በኋላ ደካማና የሚገዛ አመራር እንዲኖር ነው ያደረጉት፡፡ በዚህም የረኩ አይመስለኝም፡፡ መተካካት በሚለው ፈሊጥ ነባሮቹን ገለል አድርገዋል፡፡ እሳቸው ግን እዚሁ ቆይተዋል፡፡ ይኼ መተካካት ራሱ ፋይዳ አልነበረውም፡፡ ድርጅቱን ይበልጥ ያዳክም እንደሆነ እንጂ የሚያጠናክርበት ሁኔታ የለም፡፡ ምክንያቱም ኢሕአዴግ ዋናው ችግሩ የሰዎች ማርጀት ወይም ዕድሜ አይደለም፡፡ የሚከተለው ርዕዮተ ዓለሙ ነው ችግሩ፡፡ ወጣቱም ቢመጣ የወጣት አምባገነን ነው የሚፈጠረው፡፡ ስለዚህ ወጣት ይተካል ተብሏል፡፡ ዋናው ነገር የሚመራበት መርህ ምንድነው? የሚለው ነው፡፡ አሁን የበለጠ ተዳክሟል፡፡ ስለዚህ መተካካቱ አልሠራም፡፡ የቀድሞዎቹ ይህ ሁኔታ ያሳሰባቸው ይመስለኛል፡፡ ‹‹ድርጅታችንን ደካማ ለሆኑ ሰዎች አስረከብን›› የሚል ቁጭት አድሮባቸዋል፡፡ ሥራ ማስፈጸም ለማይችሉ አስረክበው መውጣታቸው ፀፀት ውስጥ የከተታቸው ይመስለኛል፡፡ በሚያደርጉት ገለጻ ይህንን አስተውያለሁ፡፡ አሁን ያለውን አመራር መተቸት ጀምረዋል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎና ጓደኞችዎ ፓርቲውን ከለቀቃችሁ 15 ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ ኢሕአዴግም እናንተን ካሰናበተ በኋላ ተሃድሶ ማድረጉን አወጆ ነበር፡፡ ከ15 ዓመታት በኋላ ጉዳዩን ሲያዩ ምን ይታዘባሉ?

አቶ ገብሩ፡- እኔ ሳየው ያኔ ልዩነት የተፈጠረው በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ነው፡፡ ከኤርትራ ጋር ባለው ግንኙነትና አያያዝ ከዚያም አልፎ ከውጭ አገሮች ጋር ስለምንከተለው መርህ ነው፡፡ የኤርትራ መንግሥት በወቅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ጣልቃ ገብነት ነበረው፡፡ በዚያም አልረኩም በኢትዮጵያ የራሳቸውን አሻንጉሊት መንግሥት እስከ መመሥረት ድረስ ፍላጎት ነበራቸው፡፡ ጦርነቱ ኢኮኖሚያዊ መሠረት ነበረው፡፡ በሥራ አስፈጻሚው ይኼ እንደማይሆን ውሳኔ ተሰጠ፡፡ ከዚያ ነው ወደ ጦርነት የተገባው፡፡ ይህ በሆነበት ጊዜ አቶ መለስ ከሻዕቢያ ጋር ያለው ግንኙነት እንዳለ እንዲቀጥል ፈለጉ፡፡ የአቶ መለስ ፍላጎት ለረዥም ጊዜ በሥልጣን ለመቆየት አስፈላጊ ሸሪክ የመፈለግ ጉዳይ እንደበር አሁን ተረድቻለሁ፡፡ እዚህ አገር አንድ ችግር ቢፈጠር ድጋፍ የሚሰጥ ኃይል ሻዕቢያ እንዲሆን በመፈለግ የተቀየሰ አመለካከት ነበር፡፡ ሻዕቢያን አንነካካው የሚል አቋም ነበራቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ሊሆን ይችልም የሚል አቋም ነበር፡፡ ይህ ጉዳይ ሄዶ ሄዶ ሌላ አቅጣጫ ያዘ፡፡ አቶ መለስ በዚያ ወቅት የነበረው አመራር አልተመቻቸውም፡፡ እሳቸው በሚፈልጉት አቅጣጫ ድርጅቱን ለመምራት እንቅፋት በመፈጠሩ ለመጥረግ ተነሱ፡፡ ይህን ለማድረግ ግን ሻዕቢያን መጠቀም አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ጦርነቱ ተካሂዷል፡፡ በወቅቱ በተካሄዱ ስብሰባዎች አቶ መለስ እንደ መፈክር ያነሱት ድርጀቱ በስብሷል፣ በሙስና ተዘፍቋል፣ ዴሞክራሲያዊ ባህሉ ተበላሽቷል የሚል ነው፡፡ እነዚህ መፈክሮች እኛን ለመምታት የተጠቀሙበት እንጂ ከመፈክር ያለፉ አልነበሩም፡፡ በእውነት አሁን ላይ ሆኜ ወደኋላ ስመለከት እኛም በልዩነት የወጣነውም ሰዎች ብንሆን ትክክለኛ ጥያቄዎችን አንስተናል አልልም፡፡ ከኢትዮ ኤርትራ ጉዳዮች ውጪ ያሉ የፖለቲካ ጥያቄዎችን በትክክል አላስቀመጥንም፡፡ የተከራከርነው እኮ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መርህ ነው፡፡ ስለዚህ አብዮታዊ ዴሞክራሲ በሚገባ ሥራ ላይ አልዋለም ማለት አፈናውን በትክክል አላስኬድነውም ከማለት ውጪ ትርጉም የለውም፡፡ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ለማምጣት አንኳር አጀንዳዎች አንተ ያነሳኸው የፓርቲና የመንግሥት ዝምድና፣ የመንግሥት ተቋማት የነፃነት ጉዳይ፣ የሕዝብና የብዙኃን ማኅበራት ነፃነት ጉዳይ፣ የሚዲያ ነፃነት ጉዳይ፣ በነፃነት የማሰብና የመንቀሳቀስ ጉዳይ እነዚህን ሁሉ አንስተን አልተነጋገርንም፡፡ ስለዚህ የተነጋገርነው በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ማዕቀፍ ነበር፡፡

ወዲያውኑ የሆነው ግን ሙስና ድሮም ከነበረበት አይሎና ገዝፎ የድርጅቱ ዋና መገለጫ የሆነበት፣ በማይታወቅ ሒሳብ በአንድ ሌሊት ሚሊየነር የሚኮንበት፣ የፓርቲ አባልና የመንግሥት ባለሥልጣን ከየት አመጣው በሚያስብል ሁኔታ ትልልቅ ሕንፃዎች የሚሠሩበት ጊዜ ሆነ፡፡ ሙስና ተጠናከረ፡፡ ይኼን ስልህ እኛም ፓርቲ ውስጥ ቀጥለን ቢሆን እንኳ ይህ ክስተት አይቀርም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ክስተቶች፣ ሙስናና ብልሹ አሠራር ከፀረ ዴሞክራሲ ባህሪ የሚመነጩ ናቸው፡፡ በአንድ አገር እነዚህን የምንዋጋበት መንገድ በትክክል እስካልተቀመጠ ድረስ ማለትም የግል ሚዲያዎች ሙስናን ለመታገል በነፃነት ካልተንቀሳቀሱ፣ ፍርድ ቤቶች በነፃነት ካልወሰኑ፣ የፀጥታ ኃይሎች በነፃነት ተደራጅተው ካልተንቀሳቀሱ፣ ብዙኃን ማኅበራት በነፃነት ተደራጅተው ካልሠሩ ሙስናን ማስወገድ አይቻልም፡፡ ብልሹ አሠራርን ማስቀረት አይቻልም፡፡ ይህ ሳይሆን ሙስናን እዋጋለሁ ማለት ከመፈክር አይዘልም፡፡ ስለዚህ ከተሃድሶ በኋላ የሆነውም ይኼ ነው፡፡ ሙስናና ብልሹ አስተዳደር የአገዛዙ መገጫዎች ናቸው፡፡ አንድ መንግሥት በቁርጠኝነት ሙስናን መዋጋትና መልካም አስተዳደር ማስፈን የማይችለው  በእነዚህ ጉዳዮች እጅና እግሩ ሲታሰር ነው፡፡ ራሳቸውም እኮ እያሉት ነው፡፡ በግለሰብ ደረጃ ሳይሆን በቡድን የተደራጀ ሙስና አለ ብለው በሰነድ አስቀምጠዋል፡፡ ከተሃድሶ በኋላ ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የኢሕአዴግ መሥራች የሆኑት ሕወሓት፣ ብአዴን፣ ኦሕዴድና ደኢሕዴን የየራሳቸውን ኢኮኖሚያዊ ኢምፓየር ለመገንባት እንደሚንቀሳቀሱ የሚናገሩ አሉ፡፡ በአመራርና በሥልጣን ላይ ያሉ የእነዚህ ፓርቲ አመራሮች ለሚመለምሏቸው ግለሰቦች ብድርና መሬት እንዲያገኙ በማድረግ ኢኮኖሚያዊ መሠረት ለመያዝ ይንቀሳቀሳሉ ይባላል፡፡ ይህ አሠራር ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን አይንድም? አሁን ለሚፈጠሩ ሕዝባዊ ጥያቄዎችስ መሠረት አይደለም ማለት ይቻላል?

አቶ ገብሩ፡- አሁን ያለው የፖለቲካ አካሄድ የአንድ ፓርቲ ፈላጭ ቆራጭ የመሆን፣ የአንድ ፓርቲ አምባገነን ሆኖ የመሄድ ጉዳይ በአየር ላይ የተንጠለጠለ ሊሆን አይችልም፡፡ ይኼን አገዛዝ ይኼን አምባገነን ሥርዓት የሚሸከም መደብ መፈጠር አለበት፡፡ በትስስርና በትውውቅ የሚፈጠር ካፒታሊዝም (ክሮኒክ ካፒታሊዝም) ይኼ ነው፡፡ አራቱም ድርጅቶች ዕድሉ እስከፈቀደላቸው ድረስ ‹ክሮኒክ ካፒታሊስት› ለመፍጠር ይንቀሳቀሳሉ፡፡ የሥራ ክፍፍል አላቸው፡፡ በንግድና በኢንቨስትመንት የመንግሥትን ሥልጣን የተቆጣጠረም አለ፡፡ እነዚህ ተሳስረው የሚፈጥሩት ካፒታል ነው እየታየ ያለው፡፡ ልማታዊ ባለሀብት እየተባባሉ፣ እየተሞጋገሱ፣ የክርስትና ስም እየተሰጣጡ ሀብት ይፈጥራሉ፡፡ ይኼ ባለሀብት የመንግሥትን ሥልጣን ተጠቅሞ ሊደራጅ ነው የሚፈልገው፡፡ እየሆነ ያለውም ይኼው ነው፡፡ በዚህ ጊዜ እውነተኛ ባለሀብት ይቀጭጫል፣ ይደፈጠጣል፡፡ በኢሕአዴግ ደረጃ ሙስና ነግሷል ሲባል የየራሳቸውን ኢምፓየር ለመመሥረት፣ የራሳቸውን የፖለቲካ ኃይል ለመፍጠር እየሄዱ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ ጅምሩ እኔም ባለሁበት ጊዜ ነበር፡፡ ከፖለቲካ ፍልስፍናው ነው የሚጀምረው፡፡ የአንድ ፓርቲ አምባገነንነት ዝም ብሎ አይቆምም፡፡ የሚደግፈው አካል ይፈልጋል፡፡ የተወሰኑ ባለሀብቶችን እንዲሁ ተመልክተህ እንዴት ነው ሀብት ያፈሩት ብትል፣ ከአንድ ወይም ከሌላ ባለሥልጣን ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ትረዳለህ፡፡ ይኼ በፓርቲ ደረጃ አይነገርም፡፡ በፓርቲ ደረጃ የሚነገረው ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነትን እንዋጋለን›› የሚል ነው፡፡ የአገሪቱን መሬት በብቸኝነት ተቆጣጥረህ፣ የአገሪቱን በጀት ተቆጣጥረህ፣ የአገሪቱን ፈቃድ (ላይሰንስ) ተቆጣጥረህ፣ ውድድር የሚባል በሌለበት ባለሀብት ያድጋል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ከቀበሌ የሚጀምር ነው፡፡ ቀበሌ እንኳ የፉክክር ቦታ ሆኗል፡፡ ከፍተኛ ጥቅም ስለሚያስገኝ ማለት ነው፡፡ የባለሥልጣን ልጆች እኮ እዚህ አገር አይማሩም፣ ውጭ ነው እየተማሩ ያሉት፡፡ ልጆቻቸው ወደ ቻይና እየጎረፉ ነው፡፡ እዚህ ያሉት ሌሎች ደግሞ ተስፋ እየቆረጡ ነው፡፡ ትምህርት የጨረሱ መሐንዲሶች፣ የሕግ ምሁራን ድንጋይ እየፈለጡ ይውላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ቀደም ኢሕአዴግ ግምገማ ተቀመጠ ሲባል ጠንከር ያሉ ዕርምጃዎች እንደሚወሰዱ ይታመን ነበር፡፡ ምክንያቱ አነጋጋሪ ቢሆንም እርስዎን የመሳሰሉ ትልልቅ ነባር ታጋዮችንም እስከማሰናበት ይጨክን ነበር፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብዙና ተከታታይ ግምገማዎችን ቢያካሂድም ጠብ የሚል ነገር አይታይም፡፡ የተዛነፈ ነገር ይኖር ይሆን?

አቶ ገብሩ፡- እኔ በነበርኩበት ጊዜ የነበረ ግምገማ አለ፡፡ ግምገማው ከርዕዮተ ዓለም ጋር ይገናኛል፡፡ በግምገማ ችግሮችን ማጥፋት እንችላለን ብለን ነበር፡፡ እኔ በነበርኩበት ጊዜም የግምገማ ሰለባ የሆኑ ሰዎች አሉ፡፡ ግምገማ መዋቅራዊ ስላልሆነ አንድ አባል ‹‹አንተ ችግር አለብህ›› ካለ መከላከያ የለህም፡፡ ግምገማ ሕግንና የሕግ የበላይነትን ተከትሎ ቢካሄድ፣ መዋቅርን ተከትሎ ቢካሄድ፣ በነፃነት አቤት የምትልበት የይግባኝ ሥርዓት ተዘርግቶለት ቢካሄድ መልካም ነው፡፡ ይኼ በሌለበት አንዱ ወገን ሌላውን የሚያጠቃበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ እንዲያውም ባለፉት 25 ዓመታት ከግምገማ ተለይተን አናውቅም፡፡ እኔ ልዩነቱ ጠንካራ ግምገማና ደካማ ግምገማ በመኖሩ አይደለም ባይ ነኝ፡፡ አንዱን ነገር እየመለስን መሥራት ነው፡፡ አልበርት አንስታይን እንደሚለው፣ ‹‹አንድን ነገር መላልሶ በመሥራት የተለየ ውጤት መጠበቅ እብደት ነው፡፡›› ኢሕአዴግም በትጥቅ ትግሉ የተጠቀመበትንና ለድል ያበቃውን ግምገማ፣ መንግሥት ሆኖም በዚሁ ግምገማ ለውጥ አመጣለሁ ብሎ መከጀሉ እብደት ነው፡፡ በሌላ በኩል ግምገማው በፍትሕና በነፃነት የተመሠረተ ቢሆን ይሻል ነበር፡፡ ግምገማ በማንኛውም ዓለም ያለ ነው፡፡ ነገር ግን ከሙስና፣ ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያያዞ አንድ ቡድን ሌላውን ለማጥቃት የሚጠቀምበት ካልሆነ በስተቀር ያመጣው ለውጥ አይታይም፡፡ እንዲያውም ኢሕአዴግን በከፍተኛ አመራሮች ደረጃ አስቸግሯቸው ያለው ይኸው ይመስለኛል፡፡ በዚህ ዓመት መጀመርያ አካባቢ የመልካም አስተዳደር ጥናት ቀርቦ ነበር፡፡ ምንም ፈቅ ማለት አልቻለም፡፡ በጣም የተተበተበ ድርጅት ሆኗል፡፡ ራሳቸውም በኔትወርክ መተብተቡንና ከነጋዴ ጋር መተሳሰሩን ተናግረዋል፡፡ ድርጅቱን አንድ ዕርምጃ መውሰድ የማይችልበት ደረጃ ላይ መደረሱ እየታየ ነው፡፡ አቶ መለስም ‹እጅና እግራችን ታስሯል› ብለዋል፡፡ አሁን ደግሞ የበለጠ ኢሕአዴግ ራሱን እንዳያይ እጅና እግሩ ተጠፍሯል፡፡ ለውጥ የሌለው ግምገማ ነው፡፡ ዋናው ችግር የርዕዮተ ዓለም ማዕቀፉ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢሕአዴግ እናንተን አሰናብቶ ተሃድሶ ካደረገ 15 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ሰሞኑን ከተሃድሶ በኋላ ያለፉትን 15 ዓመታት የሥራ አፈጻጸም እየገመገመ እንደሆነ ፓርቲው አስታውቋል፡፡ ዕርምጃም እንደሚወስድ ኃይለ ቃል በመጠቀም ጭምር ገልጿል፡፡ እርስዎ ኢሕአዴግን በቅርበት የሚያውቁት እንደመሆንዎ ግምገማው ተዓማኒነትና ተፈጻሚነቱ እስከየት ድረስ ይሄዳል ይላሉ?

አቶ ገብሩ፡- እኔ በዚህ ላይ ያለኝን አቋም ልንገርህ፡፡ በኢሕአዴግ ግምገማ ምንም የሚመጣ ለውጥ የለም፡፡ ሥራ አስፈጻሚው ግምገማውን እንደጨረሰ የሰጠውን መግለጫ አድምጫለሁ፡፡ መግለጫው በኢትዮጵያ ካለው ተጨባጭ እውነታ ጋር ጭራሽ የማይጣጣም ነው፡፡ እየተካሄዱ ያሉ ሠልፎች መሠረታዊ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡ ነፃነት ይኑር፣ በኢሕአዴግ ጫና በ1ለ5 አፈና ከፍቷል፣ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ይካሄድ፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ይኑር የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ አንዳንድ አላስፈላጊ ጥያቄዎች መነሳታቸውም ሳይዘነጋ ማለት ነው፡፡ በዋናነት ሕዝብ ምሬቱን የሚገልጽበት ሠልፍ ነው እየተካሄደ ያለው፡፡ ሙስና ተንሰራፍቷል፣ ብልሹ አስተዳደር ሰፍኗል የሚሉ ብቻ ሳይሆኑ፣ የእነዚህ ችግሮች ምንጭ የሆኑት የነፃነት ዕጦት፣ ፍትሕና የሕግ የበላይነት ጠፍቷል የሚሉ አሉ፡፡ አፈናው በዝቷል፣ አምባገነንነት ነግሷል ነው እየተባለ ያለው፡፡ ከዚህ አንፃር ሥራ አስፈጻሚው ለውጥ እናደርጋለን ሲል አልሰማሁም፡፡ የተለመደውን እብደት ነው የደገመው፡፡ አምና በተካሄደው የሕወሓት ጉባዔ መሠረታዊው ጉዳይ ባይነሳም መገለጫዎቹ ተነስተዋል፡፡ የኔትወርክና የውስጥ ዴሞክራሲ አያያዝ ተነስቷል፡፡ ይህ ከተነሳ ከአንድ ዓመት በኋላ ተመሳሳይ ነገር ነው የሚነገረው፡፡ ይህን እያየህ ግምገማው እንዴት ተዓማኒ ሊሆን ይችላል? ለአገሪቱ ተስፋ የሚሰጥ ነገር እየተናገሩ አይደሉም፡፡

ሪፖርተር፡- እየወጡ ባሉት መግለጫዎች የፀጥታ ኃይሉ ከዚህ በኋላ እንደማይታገስና ይልቁኑም ችግር ፈጣሪ በተባሉት ላይ ጠንከር ያለ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ነው፡፡ ይህ የሚያስተላልፈው መልዕክት ምንድነው?

አቶ ገብሩ፡- በዋናነት ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ ኢሕአዴግ የአገዛዝ ተቀባይነትን (ሌጀትመሲውን) አጥቷል፣ ፖለቲካ መሥራቱን አቋርጧል፡፡ ኢሕአዴግ ‹‹በዚህ አገር ነፃነት አረጋግጫለሁ፣ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ አካሂጃለሁ፣ ፍትሕ አረጋግጫለሁ፣ ዜጎች በነፃነት የሚሳተፉበት አገር መሥርቻለሁ…›› በማለት ሊናገር አይችልም፡፡ ስለዚህ ሌላውን መንገድ ነው የሚመርጠው፡፡ አገዛዙን ለማስቀጠል ሌላ መንገድ ነው የሚመርጠው፡፡ ይኼም ኃይል ነው፡፡ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች እንቅስቃሴ ከመጀመሩ በፊት የተሰጠው መግለጫ እንደ መንግሥት ኃይል አለን የሚል ነው፡፡ በእርግጥ በመንግሥት ሥር ኃይል አለ፡፡ ግን ኃይል ለችግሩ መፍትሔ ሊሆን አይችልም፡፡ ይበልጥ ደግሞ ሕወሓት ውስጥ የምናየው ደግሞ ‹‹ትምክህተኞች፣ ፅንፈኞች፣ ጠባቦች›› የሚሏቸውን ቋንቋዎች እንደገና እያነሱ ነው፡፡ ይኼ እንግዲህ ከ25 ዓመታት የሥልጣን በኋላ የተነሳ መፈክር ነው፡፡ ይኼ የሽንፈት ምልክት ነው፡፡ አሁን በኢሕአዴግ በኩል ያለው ፅንፍ ችግሩን ማየት ተስኖት አንዴ ሻዕቢያ ነው፣ አንዴ የውጭ ኃይሎች ናቸው ይላል፡፡ በእርግጥ እነዚህ ሚና የላቸውም አልልም፡፡ የውጭ ኃይሎች ሻዕቢያን ጨምሮ ሙከራ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ግን በአሁኑ ጊዜ ሻዕቢያ እንደዚህ ዓይነት ማዕበል ኢትዮጵያ ውስጥ ከቀሰቀስ ኢሕአዴግ ከሻዕቢያ አንሷል ማለት ነው፡፡ ሻዕቢያ አምባገነን መንግሥት ነው፡፡ እንኳን ኢትዮጵያ መጥቶ ማመስ ይቅርና በራሱም አገር አፍኖ የሚይዝ አምባገነን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ አንቀሳቃሽ ሊሆን አይችልም፡፡ እንግዲህ በቅርብ ያለው ጠላት እሱ ነው፡፡ ሌሎችም በውጭ ያሉ ኃይሎች የሚባለው ጭራሽ የተሳሳተና ወደ መፍትሔ የማያመጣ አባባል ነው፡፡ ምክንያቱም ኢሕአዴግ 24 ሰዓት የሚለፍፍ ሚዲያ ባለቤት ነው፡፡ ይኼንን ሁሉ ተሰሚነት አጥቶ በውጭ አገር ያለ አንድ ቴሌቪዥን ወይም ራዲዮ ወይም አንድ አነስተኛ ቡድን ይህን ማዕበል አንቀሳቅሷል ብሎ መናገር ራስን እንደ ማጥፋት ይቆጠራል፡፡

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች የሚነሱ ሕዝባዊ ሠልፎችና ጥያቄዎች ባለቤትነት ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ‹የሕዝብ ብሶት የወለደው ነው› ከሚሉ ወገኖች ጀምሮ፣ የውጭና ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ስማቸው እየተነሳ ነው፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያዎችም እንዲሁ ስማቸው ይነሳል፡፡ የእርስዎ ዕይታ ምንድነው? ያልታወቀ የገንዘብ ምንጭም አለ ይባላል፡፡

አቶ ገብሩ፡- አንድ እንቅስቃሴ በተለይ ሚሊዮኖች የሚንቀሳቀሱበት እንቅስቃሴ በውጭ ኃይል ሊመራ አይችልም፡፡ በውጭ ሴራ ተጠንስሶ ሊካሄድ አይችልም፡፡ ሥርዓቱ ውስጥና እዚሁ አገር ውስጥ ችግር ከሌለ በስተቀር ሊነሳ አይችልም፡፡ በእኔ አመለካከት ይኼ አባባል የሚንቀሳቀሰውን ሕዝብና ወጣት መናቅ ነው፡፡ ጥያቄዎቹ ግልጽ ናቸው፡፡ ሥርዓቱም የሚያምንባቸው ጥያቄዎች ናቸው እኮ፡፡ ሥራ አጥነት፣ ሙስና፣ ብልሹ አሠራር ነው እየተነሱ ያሉት፡፡ በእርግጥ እንቅስቃሴዎቹ ግብዓታዊነት ያለባቸው በመሆናቸው፣ ዘረኛ እንቅስቃሴዎች ይታዩባቸዋል፡፡ መሠረቱንና ጽንሰ ሐሳብን ለያይተን ማየት ይኖርብናል፡፡ ባለቤት ወይም ተጠያቂ እኔ ነኝ የሚል ፓርቲ ወይም ማኅበራት በሌሉበት የሚደራጅ እንቅስቃሴ ፅንፉን ሊስት ይችላል፡፡ የቀድሞ ሰንደቅ ዓላማ ወጥቷል፣ በሕዝብ ስሜት ሊወጣ ይችላል፡፡ የዘር ቅስቀሳዎችና የዘር ጥቃቶች ታይተዋል፡፡ እነዚህ መኮነን አለባቸው፡፡ በውጭ ኃይል ገንዘብ ነው ማለት ግን ስህተት ነው፡፡ እኔ እስከዚህ ድረስ ግን የዋህ አይደለሁም፡፡ ሻዕቢያን ጨምሮ ዓረቦች አርፈው ይቀመጣሉ አልልም፡፡ ለነገሩ ሻዕቢያ እንዲጠናከርና እንዲኖር ያደረገው ኢሕአዴግ ነው፡፡ ግን ዋናው ማየት ያለብን ደካማ ሥርዓት በሚኖርበት ጊዜ፣ ዴሞክራሲ በሚጠፋበት ጊዜ፣ ነፃነት በሚጠፋበት ጊዜ ችግር ይፈጠራል፡፡ ለዚህ አገር አደጋ አየፈጠረ ያለው የሚታየውን እንቅስቃሴ የውጭ እጅ ነው፣ ጠባቦችና የውጭ ኃይሎች የፈጠሩት ነው ማለት ለአገሪቱ ችግር የሚፈጥር ነው፡፡ ይህ አደገኛ የኢሕአዴግ ስትራቴጂ ነው፡፡ በዚህ አገር እየተከሰተ ላለው ፅንፈኝነት፣ ከሕግ ውጪ ለሚፈጠረው ክስተት ተጠያቂው ኢሕአዴግ ነው፡፡ እኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ አቅጣጫ እንዳያስት እየሰጋሁ ያለሁበት ከኢትዮጵያ አንድነት ይልቅ ልዩነቶች እያየሉ መምጣታቸው ነው፡፡ የአንድነት እሴቶችና የአንድነት አሠራሮች በጣም ላልተዋል፡፡ ኢሕአዴግ መሠረት አድርጎ የወሰደው የብሔር ብሔረሰቦች መብት በሚል ነው፡፡ ያስጮኸዋል፡፡ ጉዳዩን ከዴሞክራሲ ነጥሎታል፡፡ ኢትዮጵያ የሚለውን እሴት በጣም አዳክሞታል፡፡ ሚዛኑ ጠፍቷል፡፡ ኢሕአዴግ በዚህ ነው እየተጫወተ ያለው፡፡ ትግራይ ውስጥ ለምርጫ ሲቀሰቅስ ትምክህተኞችና ፅንፈኞች አማሮች መጡብህ፣ ኦሮሞች መጡብህ ይላል፡፡ ኦሮሚያ ውስጥ ሲቀሰቅስ አማሮች መጡብህ ይላል፡፡ አማራ ውስጥ ሲቀሰቅስ ጠባቦቹ ኦነጎች መጡብህ ይላል፡፡ በራሱ ለችግሩና ለክፍፍሉ የሚሆን አስጩኋል፡፡ ሌላው ፅንፍ በፍጥነት ሕዝቡን ያስተባብራል፡፡ ከአሁን በፊት አብዛኛው የአማራ ልሂቅ ከአማራ ጉዳይ ይልቅ ለኢትዮጵያ ነበር የሚያደላው፡፡ በኦሮሞ የቆየ ነው፡፡ በትግራይ አሁን በይበልጥ ከ25 ዓመታት በፊት ይነሳ የነበረው በድጋሚ ጎልቶ መነሳት ጀምሯል፡፡ እየመጡብህ ነው፣ ሊያጠፉህ ነው የሚል ጩኸት ይሰማል፡፡

ሪፖርተር፡- በኦሮሚያ ክልል ለተነሳው ሕዝባዊ ጥያቄ መነሻ የሆነው የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላን ነበር፡፡ በአማራ ክልል ለተነሳው ሕዝባዊ ጥያቄ ደግሞ መነሻ የሆነው የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ነው፡፡ እርስዎ የመጀመርያውና ለረዥም ጊዜ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩ ስለሆኑ ጉዳዩን በተሻለ ይረዱታል፡፡ የወልቃይት አከላለል እንዴት ነበር? በወቅቱስ ጥያቄ ተነስቶ ነበር?

አቶ ገብሩ፡- ጥሩ፡፡ በሁለቱም ክልሎች ሲታይ በኦሮሚያ የማስተር ፕላን ጉዳይ፣ በአማራ ደግሞ የወልቃይት ጉዳይ ተነስቷል፡፡ እኔ እነዚህ ጉዳዮች መገለጫዎች ናቸው ብዬ ነው የማምነው፡፡ ክስተቶች ናቸው፡፡ ዋናው ጥያቄ በኦሮሚያ የመሬት ዝርፊያ፣ ምርጫው ትክክል አይደለም፣ የሚያስተዳድሩን ካድሬዎች አምባገነኖች ናቸው፣ ጭራሽ ፍትሕ አጥተናል፣ ኑሯችን ተመሳቅሏል፣ ወጣቶችም ሥራ የለንም፣ የፓርቲ አባል ካልሆንን ሥራ አናገኝም፣ የፓርቲ አባል ያልሆነ ተሸማቆ ነው የሚኖረው የሚሉና የመሳሰሉት ናቸው ጥያቄዎቹ፡፡ በአማራ ክልልም እየጎለበቱ የሄዱት ጥያቄዎች እነዚህ ናቸው፡፡ ግን አንዳንድ እንቅስቃሴ ጎልቶ የሚወጣው በክስተት ነው፡፡ በአማራ ክልል የተነሳው ክስተት የወልቃይት ነው፡፡ እኔ ትግራይን ሳስተዳድር ነበር፡፡ መታየት ያለባቸው ሁለት ጉዳዮች ናቸው፡፡ ስለወልቃይትና ስለአስተዳደሩ ልናገር፡፡ ወልቃይት የተከለለው በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መሠረት ነው፡፡ የፌዴራል አከላለል ቋንቋ፣ ባህል፣ አሰፋፈር የመሳሰሉትን መሠረት አድርጎ ነው፡፡ በዚህ መሠረት የወልቃይት ሕዝብ ትግርኛ ይናገራል፡፡ የፀገዴም ሕዝብ ግማሹ ትግርኛ ይናገራል፡፡ ትግርኛ ተናጋሪው ፀገዴ ወደ ትግራይ ተካሏል፡፡ አማርኛ ተናጋሪው (ጠገዴ) ደግሞ ወደ አማራ ክልል ተካሏል፡፡ ከትግራይም አገውኛ የሚናገር ወደ አማራ ክልል ተካሏል፡፡ አፋርኛ የሚናገሩ አምስት ወረዳዎችም ወደ አፋር እንዲሄዱ ተደርጓል፡፡ መነሻውን ማየት አለብን፡፡ መነሻው የሀብት ወይም የመሬት ዝርፊያ አይደለም፡፡ ይኼን ላረጋግጥ እወዳለሁ፡፡ የመሬት ዝርፊያ ቢሆን ኖሮ፣ የሀብት ቢሆን ኖሮ የጨው ማዕድን፣ የፖታሽ ማዕድንና ሌሎች ውድ ማዕድናት ያሉበት የአፋር ክልል ይበልጣል፡፡ ከሁመራ አካባቢ ይልቅ ማለት ነው፡፡ ግን አፋር ተናጋሪ አፋር ነው ተብሎ ወደ አፋር ተካለለ፣ ወልቃይት ደግሞ ትግርኛ ይናገራል ተብሎ ወደ ትግራይ ተካለለ፡፡ ስለዚህ በዚህ የአከላለል ሥልት ድሮ የነበረው ተለውጧል፡፡ ይኼ አከላለል በትግራይ ብቻ አይደለም፡፡ ኦሮሚያ ድሮ የሸዋ ክፍለ ሀገር፣ ባሌ፣ ሐረርጌ የሚባሉትን ጨምሮ ነው የተካለለው፡፡ አፋርም የተካለለው ከወሎና ከትግራይ ተውጣጥቶ ነው፡፡ እንደ ጥያቄ መቅረብ ያለበት መካለል በዚሀ መሆን አለበት ወይ? የሚለው ነው፡፡ መካለል ያለበት በብሔረሰቦች ወይ በማንነት መሆን አለበት ወይ የሚል መሆን አለበት? ወይስ በሌላ? የሚለው ጉዳይ አነጋጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ወልቃይትም ሌላውም በዚህ መሠረት ነው የተካለለው፡፡ ጥያቄው ከተነሳ በትግራይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ክልሎችም መነሳት አለበት፡፡ ይኼ አከላለል ሕዝብን ይጎዳል አገርን ይጎዳል ከተባለ በሰላማዊ መንገድ ሊነሳ ይችላል፡፡ ሕዝብ የማያምንበት ከሆነ፡፡ አሁን እንግዲህ ጥያቄ ተነስቷል፡፡ ጥያቄው ከተነሳ በሰላማዊና በዴሞክራሴያዊ መንገድ መፈታት አለበት፡፡ የአንድ አካባቢ የማንነት ጥያቄ ከተነሳ የድንበር ጥያቄም ከተነሳ ሕገ መንግሥቱ እየሠራ አይደለም እንጂ በሕገ መንግሥቱ ሊፈታ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ወልቃይት አካባቢ ያሉ ሰዎች አማርኛም ትግርኛም ይናገራሉ፡፡ በሚካለልበት ጊዜ ሕዝብ አልተጠየቀም? ነው ወይስ ከላይ በመጣ ውሳኔ እንዲሁ ነው የተካለለው?

አቶ ገብሩ፡- የተካለለው በአጠቃላይ ፓርቲዎችና በዚያን ጊዜ የተመሠረቱ የክልል መንግሥታት ስምምነት መሠረት ነው፡፡ እያንዳንዱን አካባቢ አንተ ወዴት ነህ? አንተ ወዴት ነህ? እየተባለ አይደለም፣ በሪፈረንደምም አይደለም፡፡ ወልቃይት ሲካለል በአማራ ክልል በኩል ብአዴን፣ በትግራይ በኩል ሕወሓት ነበር፡፡ ሰቆጣ አካባቢ ሲካለልም እንዲሁ፣ አፋር ሲካለልም ሕወሓትና የአፋር ፓርቲ (አብዴፓ) ነበር፡፡ በመንግሥትም በፓርቲም ደረጃ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ አስቀድሞ የቋንቋውን ሁኔታ በማጤን የተወሰነ ነው፡፡ እንዳለ ተወስዶ በአከራካሪ ጉዳዮች ብቻ ነበር ውይይት ይካሄድ የነበረው፡፡

ሪፖርተር፡- የወልቃይት አከላለል በወቅቱ አከራካሪ ጉዳይ አልነበረም?

አቶ ገብሩ፡- አከራካሪ አልነበረም፡፡ በወቅቱ ሕወሓት በዚያ ቦታ የተንቀሳቀሰው መንግሥት ከመመሥረቱ በፊት ነው፡፡ መንግሥት የተመሠረተው ከ1983 ዓ.ም. በኋላ ነው፡፡ ሕወሓት የትግራይን መንግሥት ሲመሠርት የወልቃይትን አካባቢ ጨምሮ ነው፡፡ በምሥራቅ የነበረውን የአፋር ክፍል ትቶ ከመሀል ደግሞ ኮረም፣ ኦፍላና የአላማጣ ትግርኛ ተናጋሪዎችን አጠቃሎ መንግሥት መሠረተ፡፡ ይኼ በኢሕአዴግም የተወሰነና የታየ ነው፡፡ ሌሎችም ወደዚህ ማካለል የገቡት ከ1983 ዓ.ም. በኋላ ነው፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹በአመራሮቻችን የተነሳ የፓርቲያችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል›› አቶ አበባው ደሳለው፣ የአብን አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ከተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመዛኙ የተሻለ ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኘ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ...

‹‹የግሉን ዘርፍ በመዋቅር መለያየት የነበሩ ችግሮችን ከማባባስ ውጪ መፍትሔ አያመጣም›› አቶ ሺበሺ ቤተማርያም፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ

አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በኢኮኖሚክስ፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲና ዕቅድ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማግኘት ለ36 ዓመታት የዘለቀ የሥራ ልምድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በዕቅድና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ በዓለም አቀፍ...

‹‹የኢትዮጵያን የውስጥ ችግሮች ሁሌም የሚያባብሰው ከውጭ የሚመጣ አስተሳሰብ ነው›› ሳሙኤል ነጋሽ (ዶ/ር)፣ በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር

በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር የሆኑት ሳሙኤል ነጋሽ (ዶ/ር) የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር የውጭ ግንኙነት ኃላፊም ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት አሥርት ዓመታት ታሪክ አስተምረዋል፡፡...