Saturday, December 9, 2023

ከኢሕአዴግ ግምገማ ምን ይጠበቃል?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በመካከለኛውና በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍሎች ከሌሎች ጊዜያት የተለየና ጠንከር ያለ ደም አፋሳሽ ግጭት ተከስቷል፡፡ ይህ ደም አፋሳሽ ግጭት ተባብሶ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ከተሃድሶ በኋላ ያለፉትን 15 ዓመታት ለመገምገም ተቀምጧል፡፡

በቅደሚያ ከነሐሴ 10 እስከ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ 36 አባላት ያሉት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ግምገማ አካሂዶ መግለጫ አውጥቷል፡፡ በመቀጠል የኢሕአዴግ ምክር ቤት ግምገማ በማካሄድ ላይ ሲሆን፣ በዚህ ግምገማ ላይ የምክር ቤት አባል ያልሆኑ የቀድሞ አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ከዚህ በኋላ በተዋረድ የታችኛው የድርጅት መዋቅር ግምገማ እንደሚቀመጥ ተገልጿል፡፡

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ከተሃድሶ በኋላ የነበሩትን 15 ዓመታት በስድስት ቀናት ውስጥ ገምግሞ ባወጣው መግለጫ፣ በኦሮሚያ በአማራ ክልሎች ስለተነሱ ሕዝባዊ ጥያቄ መንስዔዎች ላይ ሐሳቦቹን ሰንዝሯል፡፡

ድርጅቱ በሰጠው ትንታኔ፣ ‹‹የመንግሥት ሥልጣን የሕዝብን ኑሮ ለማሻሻልና አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል እንዲውል ከማድረግ ይልቅ፣ የግል ኑሮን መሠረት አድርጎ የመመልከት በአንዳንዶቹም ዘንድ የግል ጥቅም ከማስቀደም ጋር የተያያዘ ነው፤›› በማለት ይገልጻል፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ጥያቄዎች ምንጭም ይኼው ያልተገባ ድርጊት የፈጠረው ችግር መሆኑ ተመልክቷል፡፡ ከዚህ በመነሳት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ደረጃውና መጠኑ ምንም ይሁን ምን የመንግሥት ሥልጣንን ያላግባብ ለግል ኑሮ መሠረት ለማድረግ የሚታየው ዝንባሌ መታረምና መገታት እንዳለበት፣ ይህን ለማድረግ የሚያስችሉ ተጨማሪ ዕርምጃዎችም መውሰድ እንደሚገባ ተወስኗል፤›› በማለት የፓርቲው መግለጫ ያመለክታል፡፡

ከዚህ ባሻገር የገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ባወጣው መግለጫ ኢሕአዴግ ውስጡን የሚመለከት ድርጅት መሆኑን፣ ከራሱ ጀምሮ የሚታዩ የጥገኝነትና የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰቦች መገለጫ የሆኑትን ጠባብነትና ትምክህተኝነት በጥብቅ በመታገል፣ ይህ አዝማሚያ እንዲገታ ለማድረግ የሚያስችሉ ዕርምጃዎች እንደሚወሰዱ አስገንዝቧል፡፡

‹‹ድርጅታችን በዚህ ችግር ምክንያት የተፈጠረውን አደጋ መሠረታዊ መንስዔዎች በሌላ በማንም ሳያሳብብ በመንግሥትና በድርጀት ማዕቀፍ እንደሚያይና ይህንኑ ለማስተካከል እንቅስቃሴ ተጀምሯል፤›› በማለት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አመልክቷል፡፡

ኢሕአዴግ በአሁኑ ወቅት እያካሄደውና በየደረጃው በሁሉም ተቋማት ለማካሄድ ያቀደው ግምገማ መሠረት ያደረገው በ1993 ዓ.ም. በተካሄደው ተሃድሶ ላይ ነው፡፡ ይህ ተሃድሶ የተካሄደውም በሕወሓት ውስጥ ያንዣበበው የመሰንጠቅ አደጋ በአቶ መለስ ዜናዊና በቡድናቸው አሸናፊነት ከተደመደመ በኋላ ነው፡፡

አቶ መለስ በወቅቱ ተቀናቃኞቻቸውን ያሸነፉበት ሐሳብ ከ15 ዓመታት በኋላ በሁለቱ ትልልቅ ክልሎች ለተነሳውም ችግር ምክንያት ሆኖ ቀርቧል፡፡ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ድል ማግስት ውስጥ ውስጡን ሲብላላ የቆየው የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ልዩነት ገሃድ ወጥቶ ነበር፡፡

በሕወሓት ላይ ያንዣበበው የመሰንጠቅ አደጋ ፖለቲካውን በቅርበት ለሚከታተሉ ወገኖች ከፍተኛ ሥጋት ፈጥሮ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ምናልባት በሕወሓት ውስጥ የተፈጠረውን ልዩነት ለማጥበብ በተደጋጋሚ የተካሄዱ ስብሰባዎች፣ ልዩነቱን ከማጥበብ ይልቅ ጭራሹን ቅራኔ በማጉላት ተደምድመዋል፡፡

ለ17 ዓመታት የተካሄደውን የትጥቅ ትግል የመሩና ከትጥቅ ትግሉ በኋላም ለአሥር ያህል ዓመታት የአገሪቱን ፖለቲካ ይዘውሩ የነበሩት 12 የሕወሓትና የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚዎች ተገለሉ፡፡

በዚህ ክስተት በአቶ መለስ ዜናዊ የሚመራው ቡድን አሸናፊ ሆኖ ሲወጣ፣ በአቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ይመራ የነበረው ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እናት ድርጅቱን ለቆ ወጣ፡፡

አቶ መለስ በወቅቱ መከራከሪያ አድርገው ያቀረቧቸው ሐሳቦች በግርድፍ ሲታዩ፣ ለተፈጠረው ቀውስ በዋናነት ጥገኛ ዝቅጠት (ኪራይ ሰብሳቢነት) ተስፋፍቷል፣ ድርጅቱ በስብሷል፣ በሙስና ተዘፍቋል፣ ዴሞክራሲያዊ ባህሉ ተበላሽቷል፣ የቦናፓርቲዝም ዝቅጠት አደጋን መጋፈጥ አማራጭ የለውም የሚል ነበር፡፡

በዚህ መነሻነት በዚያው ዓመት የተሃድሶ ንቅናቄ ተጀምሮ አዳዲስ የልማት አጀንዳዎች ተቀርፀው ወደ ሥራ ከመገባቱም በላይ፣ በጥቅሉ ብልሹ አሠራሮችን ለማጥፋት ታቅዶ ወደ ተግባር ተሸጋግሯል፡፡ ነገር ግን አስገራሚው ነገር በወቅቲ አደጋ ናቸው የተባሉት ችግሮች ከመጥፋት ይልቅ ተባብሰው መቀጠላቸው ነው፡፡ ከ15 ዓመታት በፊት ለሥርዓቱ አደጋ ናቸው የተባሉ ችግሮች ከ15 ዓመት በኋላም የሥርዓቱ አደጋ ናቸው መባሉ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡ ‹‹ከመክሰም ይልቅ ለምን ፋፋ?›› ሲሉ ብዙዎች ይጠይቃሉ፡፡

በወቅቱ በልዩነት ከወጡ አመራሮች መካከል አቶ ገብሩ አሥራት ይጠቀሳሉ፡፡ አቶ ገብሩ ወደኋላ 15 ዓመታት አሻግረው ሲመለከቱ፣ ‹‹ድርጅቱ በስብሷል፣ በሙስና ተዘፍቋል፣ ዴሞክራሲያዊ ባህሉ ተበላሽቷል፤›› ብለው ‹‹የቀረቡት ሐሳቦች እኛን ለመምታት እንጂ ከንግግር ያለፉ አይደሉም፤›› ይላሉ፡፡

‹‹እነዚህ ችግሮች ዛሬም ተንሰራፍተው የሚገኙ ናቸው፤›› የሚሉት አቶ ገብሩ፣ ጨምረው እንደሚያስረዱት ኢሕአዴግ አሁን እያካሄደ ካለው ግምገማም ምንም የሚመጣ ለውጥ የለም ሲሉም ምክንያት በማስቀመጥ ይከራከራሉ፡፡

‹‹የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ግምገማውን እንደጨረሰ የሰጠውን መግለጫ አድምጫለሁ፡፡ መግለጫው በኢትዮጵያ ካለው ተጨባጭ እውነታ ጋር ጭራሽ የማይጣጣም ነው፤›› ብለው፣ ‹‹እየተካሄዱ ያሉ ሠልፎች መሠረታዊ ጥያቄዎች አንስተዋል፡፡ ነገር ግን ሥራ አስፈጻሚው ለውጥ እናደርጋለን ሲል አልሰማሁም፡፡ የተለመደውን እብደት ነው የደገመው፤›› በማለት አቶ ገብሩ አስረድተዋል፡፡

ዓመት ሊደፍን ጥቂት የቀረው የኦሮሚያ ክልል የተቃውሞ ትዕይንተ ሕዝብ በአዲስ አበባና ኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላን ዝግጅትን ክስተት ሲያደርግ፣ ወራት ያስቆጠረው የአማራ ክልል ተቃውሞ ደግሞ የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ጉዳይ ክስተት ሆኗል፡፡

በእነዚህ መነሻዎች በጥቅሉ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ ሥራ አጥነት፣ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች መደፍጠጥ የሚሉ ጥያቄዎች ጎልተው ወጥተዋል፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች በማንሳት ሒደት በሠልፈኞችና በፀጥታ አካላት መካከል በሚፈጠሩ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ሕይወት አልፏል፡፡ ለጊዜው የሚመለከተው አካል የሟቾችን ቁጥር ይፋ ባያደርግም በርካታ ዜጎች ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሷል፡፡ በንብረት ላይም እንዲሁ፡፡

በተለያዩ ገጽታዎች ሕዝባዊ ተቃውሞው ቀጥሏል፣ ደም አፋሳሽ ግጭቶችም እንዲሁ ይታያሉ፡፡ ኢሕአዴግ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ውስጡን በመመርመር ዕርምጃ እንደሚወስድ ሲያስታውቅ፣ የውጭና የአገር ውስጥ ፅንፈኛ ኃይሎች ከዚህ ተግባር እንዲታቀቡ አስጠንቅቋል፡፡

ኢሕአዴግ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ባስተላለፈው ጥሪ፣ ‹‹በአገራችን የፈነጠቀውን የልማትና ዴሞክራሲ ጮራ ተማምነው በለመለመ ተስፋቸው ወደፊት በሚመለከቱበት ወቅት፣ በድርጅትና በመንግሥት አካላት ዘንድ የታየው ይህ ስህተት ተስፋቸውን እንዳያጨልም›› በማለት የጠየቀ ሲሆን፣ ‹‹በዚህ አጋጣሚ የውጭና የውስጥ ፅንፈኛ ፀረ ሰላምና ፀረ ልማት ኃይሎች ሕዝቡ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ ትግሉ የገነባውን ሥርዓት በቀጣይነት ለማሻሻል የሚያደርገውን እንቅስቃሴ መጠጊያ አድርገው፣ ሁከትና ትርምስን ለማስፋፋት የሚነሱትን በፅናት መመከት ያስፈልጋል፤›› በማለት ኢሕአዴግ ለሕዝቡ ጥሪ አድርጓል፡፡

የኢዴፓ የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ ልደቱ አያሌው ጉዳዩን ከዚህ በላይ ይወስዱታል፡፡ አቶ ልደቱ በቅርቡ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፣ ለተፈጠረው ችግር ሰፊ መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን ኢሕአዴግ ከራሱ ያልመጣ ለውጥን መቀበል አይፈልግም፡፡

‹‹ዋናው የለውጥ አጀንዳ መሆን ያለበት የፖለቲካ ምኅዳሩን ለሁላችንም ምቹና እኩል እንዲሆን የማድረግ ጉዳይ ነው፡፡ ነፃ ሚዲያ ማቋቋም ላይ ከተስማማን የትኛው አስተሳሰብ አሸናፊ ሆኖ ይወጣል የሚለውን ሕዝብ ይፈርዳል፤›› በማለት አቶ ልደቱ ገልጸው፣ ሁሉን ያሳተፈ የውይይት መድረክ ሊዘጋጅ እንሚገባ ያሰምሩበታል፡፡

ኢሕአዴግ ከዚህ ችግር ባሻገር አገሪቱ በትክክለኛ የዕድገት ጎዳና እየተራመደች እንደሆነ፣ ያለፉት 13 ዓመታት የኢኮኖሚ ዕድገት ባለሁለት አኃዝ መሆኑን በመጥቀስ ይገልጻል፡፡

በእርግጥ ተሃድሶ ከተካሄደ በኋላ የተለያዩ የልማት አጀንዳዎች ተቀርፀው ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ አለመታደል ሆኖ ግን በ1994 ዓ.ም. እና በ1995 ዓ.ም. አገሪቱ ድርቅ ያጋጠማት በመሆኑ የተነደፈው ስትራቴጂ ፍሬ ማፍራት ሳይቻል ቀርቷል፡፡ ከዚህ በኋላ በ1996 ዓ.ም. ጥሩ የዝናብ ሥርጭት ስለነበር አገሪቱ 13 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቧ መነገሩ አይዘነጋም፡፡

ከዚህ በኋላም ለተከታታይ 13 ዓመታት በአብዛኛው ባለሁለት አኃዝ ዕድገት በማስመዝገብ መጓዝ ቢችልም፣ ዕድገቱ ያመጣው ፀጋ ለብዙኃኑ መዳረስ ባለመቻሉ ዛሬ ለተከሰተው ችግር እርሾ ሊሆን እንደቻለ በብዙዎች ዘንድ ይታመናል፡፡

ምናልባት ለመጀመርያ ጊዜ ኢሕአዴግ ይህንኑ ሀቅ አምኗል፡፡ ኢሕአዴግ በመግለጫው እንዳለው፣ ‹‹ባለፉት 25 ዓመታት የአገሪቱ ሕዝብ ቁጥር በእጥፍ ከጨመሩና ሰፊ የወጣት ኃይል ከመፈጠሩ ጋር ተያይዞ፣ ለውጡ ሁሉንም በሚያረካና ተጠቃሚነቱን በሚያረጋግጥ ደረጃ ሄዷል ማለት አይቻልም፤›› በማለት ትንታኔውን አቅርቧል፡፡

አቶ ገብሩ የኢሕአዴግ ዕድገት ጤናማ አይደለም ይላሉ፡፡ አቶ ገብሩ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ‹‹ዕድገትና ልማት የተለያዩ ናቸው፡፡ ዕድገት ተጨማሪ ገቢ የማግኘት ጉዳይ ነው፡፡ አምባገነን መንግሥታት ዕድገት ሊያስመዘግቡ ይችላሉ፡፡ ኢሕአዴጋውያን እንደሚያምኑት የኮሪያና የታይዋን ዕድገት በዴሞክራሲ ማዕቀፍ የመጣ አይደለም፡፡ በአምባገነኖች የመጣ ዕድገት ነው፡፡››

ቀደም ባሉት ጊዜያትም ሂትለርም ሞሶሎኒም ዕድገት አምጥተዋል፡፡ ጣሊያን ገብታበት ከነበረበት የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ አውጥቶ ያንቀሳቀሳት ሞሶሎኒ ነው ይላሉ፡፡

በርካታ የአፍሪካ አምባገነን መንግሥታት ዕድገት እያስመዘገቡ ነው፡፡ ምክንያቱም የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት ወዳልተነካው አካባቢ የሚፈስ በመሆኑ ነው የሚል አስተያየትም አላቸው፡፡

‹‹ልብ ማለት ያለብን ያደጉ አገሮች ካፒታል የሚንቀሳቀሰው ወዳልተበላው፣ ወዳልተነካው አካባቢ ነው፤›› በማለት የሚናገሩት አቶ ገብሩ፣ ‹‹በኢትዮጵያም እየተባለ የለው ኑ መዝብሩ ርካሽ ጉልበት አለ፡፡ ኑ መዝብሩ ያልተነካ የተፈጥሮ ሀብት አለ፡፡ ኑ መዝብሩ ርካሽ ኤሌክትሪክ አለ የሚል ነው፤›› በማለት ይቀጥላሉ፡፡

በእነዚህ ክስተቶች ዕድገት ሊመጣ ይችላል፣ ልማት ግን ሊመጣ አይችልም ብለው፣ ‹‹ምክንያቱም ልማት ቀጣይነት ያለው ነው፡፡ ዜጎች ያመኑበትና ዜጎችን ያሳተፈ ነው፡፡ በዕቅዱም በአፈጻጸሙም ዜጎች የተሳተፉበት ነው፡፡ ከጥቅሙም ዜጎች ተቋዳሽ የሚሆኑበት ነው፤›› በማለት የሚናገሩት አቶ ገብሩ፣ ‹‹ነገር ግን ኢሕአዴግ በሚለው ልክ ባይሆንም በአምባገነንነት ጥላ ሥር ሆኖ ዕድገት አምጥቷል፡፡ ልማት ግን በፍጹም አላመጣም፤›› በማለት አቶ መከራከሪያቸውን ይገልጻሉ፡፡

በአጠቃላይ ባመጣው ዕድገትና ልማት ኢሕአዴግ ደስተኛ ነው፡፡ በግምገማውም ይህንኑ በማንሳት በኢኮኖሚውና በማኅበራዊ ጉዳዮች ለውጥ ማምጣቱን አትቷል፡፡ ነገር ግን ለተፈጠሩት ግጭቶች ግን ኃይል የቀላቀለ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ምልክት ሰጥቷል፡፡

የሪፖርተር ምንጮች እንደሚገልጹት፣ በተለያዩ ቦታዎች ለተነሱት ችግሮች በቀጥታ ተጠያቂ የሚሆኑ አመራሮች ዕርምጃ ይወሰድባቸዋል፡፡ የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በሰጡት መግለጫ እየተፈጠረ ያለው ሁከትና ግጭት ከዚህ በላይ እንዲቀጥል መንግሥት እንደማይፈቅድና ይህን ችግር ማስተካከል የሚያስችል ዕርምጃ ይወስዳል ብለዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -