Tuesday, February 27, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የኢሕአዴግ ግምገማ ግልጽነትና ተጠያቂነት በተግባር ይረጋገጥበት!

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ያለፉትን 15 ዓመታት በጥልቀት በመገምገም ባጋጠሙ ችግሮች ላይ የማስተካከያ ዕርምጃዎች ለመውሰድ ስብሰባ ተቀምጧል፡፡ ኢሕአዴግ በሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች ማለትም የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት (ሙስናና ብልሹ አሠራሮች)፣ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ የጠባብነትና የትምክህት አመለካከቶችን በዝርዝር እንደሚገመግም፣ በእነዚህ ችግሮች ሳቢያ በተፈጠረው አደጋ መሠረታዊ መንስዔዎች ላይ ተነጋግሮ ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ አስታውቋል፡፡ በአገሪቱ እያንዣበበ ያለውን አደጋ መንስዔዎች በማንም ሳያሳብብ በመንግሥትና በድርጅት ማዕቀፍ እንደሚያይና ቀዳሚ ችግር መሆኑን በመገንዘብ፣ በተቻለ ፍጥነት ለማስተካከል እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቋል፡፡ ኢሕአዴግ ያለፉትን 15 ዓመታት የስኬትና ተግዳሮት ጉዞዎቹን ሲገመግም፣ ለግልጽነትና ለተጠያቂነት ታይቶ በማይታወቅ መጠን ከፍተኛ ትኩረት መስጠት አለበት፡፡ የሕዝብን የልብ ትርታ ማዕከል ማድረግም ይጠበቅበታል፡፡

ኢሕአዴግ በተጠቀሱት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ግምገማ ሲቀመጥ፣ ሕዝብ የዚህን ግምገማ ውጤት እንደሚጠባበቅ ማወቅ አለበት፡፡ የግምገማው ውጤት እንደተለመደው ልፍስፍስና ፍሬ ቢስ ከሆነ ከሕዝብ ጋር የበለጠ ይቆራረጣል፡፡ ግምገማው ግልጽነትና ተጠያቂነት ይኑርበት ሲባል ኢሕአዴግ ላዩ ላይ ለዓመታት የሠፈረውን ቆሻሻ ያራግፍ ማለት ነው፡፡ በግምገማው ውጤት መሠረት ተጠያቂ መሆን ያለባቸው በሕግ ሊጠየቁ ይገባል፡፡ ከላይ እስከ ታች ባሉ አባላቱ ላይ ተጠያቂነትን በተግባር ማሳየት አለበት፡፡ ከዚህ በፊት በለብ ለብ ግምገማዎች የተወሰኑ ሹማምንት ቢከሰሱም በሕገወጥ ድርጊቶች ላይ የተሰማሩ ብዙ አሉ፡፡ ሥርዓቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ልክ እንደ 1993 ዓ.ም. በዝቅጠት ውስጥ መሆኑን ማመን ይኖርበታል፡፡ ይህ ዝቅጠት ደግሞ አደጋ ደቅኗል፡፡ በሕዝብ ተቀባይነት ያጡ የመንግሥትና የፓርቲ ኃላፊዎችን የሚቀጣ ሥርዓት እንዲፈጠር ግምገማው ሀቀኛ፣ ጠንካራና ርህራሔ አልባ ይሁን፡፡

ይህ ግምገማ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሚሰፍንበት ሥርዓት እንዲመሠረት መሠረት መጣል አለበት፡፡ ለሥርዓቱም ሆነ ለአገር እንቅፋት የሆኑ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ተነቅሰው ወጥተው ሕግ ፊት ከቀረቡ በኋላ ተገቢውን ቅጣት ማግኘት አለባቸው፡፡ ግምገማው ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ወገኖች ላይ ብቻ አነጣጥሮ ተዓማኒነት እንዳያጣ ይታሰብበት፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ የተለመደው የተልፈሰፈሰ ግምገማ የሚካሄድ ከሆነ፣ ኢሕአዴግ ከሕዝብ ጋር ለይቶለት እየተቆራረጠ መሆኑን ይወቀው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የተለያየ ዓላማና ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች ክፍተቱን በመሙላት ሰበብ፣ አገርና ሕዝብን ለትርምስ ለመዳረግ አጋጣሚውን ያገኛሉ፡፡ እንኳን ሕግ ሊከበር፣ ሰላም ሊኖር፣ ልማት ሊቀላጠፍ ይቅርና በሶሪያና በየመን ያየናቸው የሕዝብ ዕልቂቶች፣ ስደቶችና ውድመቶች ይከሰታሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ መመለሻ የማይኖራቸው ውድመቶች ውስጥ ላለመግባት ከኃይል ይልቅ ለውይይትና ለድርድር ራስን የሚያዘጋጅ ሀቀኛ ግምገማ ይደረግ፡፡ ኢሕአዴግ ራሱን አብጠርጥሮ በመፈተሽ ከስኬቶቹ ይልቅ ድክመቶቹ ላይ ያተኩር፡፡ ድክመቶቹን በማመን ከሕዝብ ጋር ይታረቅ፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ለሚረዱ እንቅስቃሴዎች መፈጠር የበኩሉን አስተዋጽኦ ያድርግ፡፡ የግብር ይውጣ ግምገማና ኃይል ላይ ብቻ ማተኮር ከመፍትሔ ይልቅ ለበለጠ ግጭት አስተዋጽኦ ከማበርከት የዘለለ ፋይዳ እንደሌለው ግንዛቤ ይያዝ፡፡

ኢሕአዴግ ከላይ በተጠቀሱት ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ግምገማ ሲቀመጥ መረሳት የሌለባቸው በጣም ጠቃሚ ጉዳዮች አሉ፡፡ የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የጠባብነትና የትምክህት አመለካከትን በተመለከተ በፓርቲው መዋቅር ውስጥ ራሱን የቻለ የተለመደ አሠራር እንዳለው ይታወቃል፡፡ በየትኛውም መንገድ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ግምገማ ቢያደርግ ጥያቄ ላይነሳበት ይችላል፡፡ ይህም ግምገማ የሚካሄደው በድርጅቱ ሕገ ደንብ መሠረት በገዛ አባላቱ ላይ ስለሆነ የውስጥ አሠራሩን የሚመለከት ይሆናል፡፡ ነገር ግን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን በሕገ መንግሥቱ ማዕቀፍ የመተርጎም ግዴታ፣ ገዥው ፓርቲን ጨምሮ በሁሉም ወገኖች ላይ መሆን አለበት፡፡ ይሁንና እጅግ በጣም የተመረጡና ኢሕአዴግ እኔን ይጠቅሙኛል የሚላቸውን ነገሮች ብቻ በማንሳት፣ በዚሁ ተመሳሳይ አጀንዳ ላይ ሌሎች አካላት የሚያቀርቧቸውን ጥያቄዎች ግን የሕዝብ አይደሉም የሚለው አካሄድ ዕርምት ይፈልጋል፡፡ መወገድም አለበት፡፡

በሕዝቡ ውስጥም ሆነ በአገሪቱ ጉዳይ ያገባናል በሚሉ ወገኖች የሥልጣንና የሀብት ክፍፍል መዛባት፣ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሠፈሩትን የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች አለመከበር፣ የሕግ የበላይነትን መጋፋት፣ የፍትሕ ሥርዓቱን ገለልተኝነት መፈታተንና ማዳከም፣ የዴሞክራሲ ተቋማት የፓርቲ መገልገያ መሣሪያ መሆን፣ የወጣቶች ተስፋ መቁረጥ፣ የኑሮ ውድነትና የመሳሰሉትን ‹‹የጥቂት ፀረ ሰላም ኃይሎች›› ጥያቄዎች አድርጎ ማየት የበለጠ ቅሬታ፣ ምሬት፣ ብጥብጥና ግጭት ከማስነሳት በስተቀር ፋይዳ የለውም፡፡ በአገሪቱ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት አይረዳም፡፡ ይልቁንም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተፈጠሩትን ዓይነት ደም አፋሳሽ ግጭቶች በመቀስቀስ የበለጠ ሞት፣ ጉዳትና ውድመት መጥራት ነው፡፡ ግምገማው የሕዝብን ፍላጎት ማዕከል ማድረግ ሲሳነው የግልጽነትና የተጠያቂነት መርሆች ይጣሳሉ፡፡ የሚያንዣብቡት አደጋዎች እርግጠኛ ይሆኑና ለአገር መፍረስና ለሕዝብ ሰቆቃ የበለጠ ማጠናከሪያ ይሆናሉ፡፡

በፓርቲ ደረጃ የሚደረጉ ግምገማዎች ጥንካሬ ካላቸውና በግልጽነትና በተጠያቂነት መርህ የሚከናወኑ ከሆኑ ጠቃሚነታቸው አያጠያይቅም፡፡ ነገር ግን ግምገማዎቹ ከድክመትና ኃላፊነትን በብቃት ካለመወጣት ባሻገር የወንጀልና የፍትሐ ብሔር ኃላፊነቶች መኖራቸው እየተረጋገጠ፣ በፖለቲካዊ ውሳኔዎች ለማለፍና የፍትሕ ሥርዓቱ የራሱን ሚና እንዳይጫወት መገደብ ገዥው ፓርቲ ቆሜለታለሁ ከሚለው የሕግ የበላይነት ጋር ይጋጫል፡፡ በሌሎች አገሮች እንደተለመደው ሥልጣን ላይ ያለ ኃይል በሚዲያ፣ በሲቪል ማኅበረሰቦች፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና በሙያ ማኅበራት ሳይቀር ያለማቋረጥ ይገመገማል፡፡ ገዥው ፓርቲ የእኔ ግምገማ ብቻ አውነት ያመጣል የሚለውን ግትርነት በመተው እነዚህ አካላት አሁን ካሉበት አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ወጥተው ከኅብረተሰቡ የሚያገኙዋቸውን ተጨባጭ ማስረጃዎች በመጠቀም የሚያመጡዋቸውን የግምገማ ውጤቶች ሙሉ በሙሉ ችላ ባይባል ይመከራል፡፡ ኢሕአዴግ በዚህ ግምገማው እነዚህ ከኅብረተሰቡ ግብዓት ለማግኘት የሚረዱ ተቋማት እንዲጠናከሩና የተሻለ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የሚረዳ ውሳኔ ቢያስተላልፍ ጠቃሚ ነው፡፡

አገሪቱ ላለፉት ዘጠኝ ወራት በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ውስጥ በተፈጠሩ ሁከቶች እየተናጠች ነው፡፡ የተቃውሞ ሠልፎች በተካሄዱባቸው ሥፍራዎች በርካታ ዜጎች ተገድለዋል፣ አካላቸው ጎድሏል፣ ለእስር ተዳርገዋል፣ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ የአገር ሀብት ወድሟል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአገሪቱን ሕዝብ ጭንቅ ውስጥ የከተተ የሥጋት ደመና አንዣቧል፡፡ ከመፍትሔ ይልቅ ሁከቱ እየተባባሰ ለሰላምና ለመረጋጋት ጠንቅ ተፈጥሯል፡፡ ኃይል መቼም ቢሆን ለሰላም አማራጭ ካለመሆኑም በላይ የመፍትሔ መንገዶችን ይዘጋጋል፡፡ ሕዝብ ጥያቄ ባነሳባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ በሰከነ ሁኔታ መነጋገር የወቅቱ ጥያቄ ነው፡፡ አሁንም የሕዝብ ድምፅ መሰማት አለበት፡፡ ለታይታና ለማስመሰል የሚደረግ ተራ ግምገማ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ ይልቁንም የሕዝብን ፍላጎት ማዕከል በማድረግ ለመሠረታዊ ለውጥ የሚበጁ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት ግምገማ ላይ ትኩረት ይደረግ፡፡ ሕዝብ ግምገማው የሚያመጣው ለውጥ የለም ብሎ እንዳይደመድም በተጨባጭ ተግባራዊ ዕርምጃዎች ይወሰዱ፡፡ በመሆኑም ግምገማው ግልጽነትንና ተጠያቂነትን በተግባር ያረጋግጥ!

      

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...

ሕወሓት በትግራይ ጦርነት ወቅት በፌዴራል መንግሥት ተይዘው ከነበሩት አባላቱ መካከል ሁለቱን አሰናበተ

በሕወሓት አባላት ላይ የዓቃቤ ሕግ ምስክር የነበሩት ወ/ሮ ኬሪያ...

የኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ ለመሸጥ የሚያስችል ስምምነት ለመፈጸም የመንግሥት ውሳኔ እየተጠበቀ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን የሚያስችለውን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...

የበራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረከበ

በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት (1967-1983) ዘመን የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ የየካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን ተሸላሚ የነበሩ የአየር ኃይል ጀት አብራሪው የብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ...

የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ዘላቂ መፍትሔ ይበጅለት!

ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በተጠናቀቀ ማግሥት፣ መንግሥት ልዩ ትኩረት የሚሹ በርካታ ጉዳዮች እየጠበቁት ነው፡፡ ከእነዚህ በርካታ ጉዳዮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው...