Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርሰላምን እንሻ እንከተላትም

ሰላምን እንሻ እንከተላትም

ቀን:

“ሰላምን የሚሻ ይከተላት” ይላል ታላቁ መጽሐፍ፡፡ ሰላምን የማይሻ ሰው የለም፡፡ ሰው በመውጣቱም በመግባቱም አገር ሰላም እንድትሆን በየእምነቱ ፈጣሪውን ይለምናል፤ ይማጸናል፡፡ እውነት ነው! ሰላም ከሌለ ገበሬው በግብርናው፣ ነጋዴው በንግዱ፣ ተማሪው በትምህርቱ፣ መምህሩም በማስተማሩ፣ የመንግሥት ሠራተኛው በሥራ ቦታው፣ የቀን ሠራተኛውም በሥራ ውሎው፣ በአጠቃላይ ሁሉም ሰው በተሰማራበት መስክ የሚፈልገውን አያገኝም፤ ውጤታማም ሊሆን አይችልም፡፡

የሰውን ህሊና የሚያሳርፈው ገንዘብ አይደለም፤ ንብረትም አይደለም፤ ምክንያቱም ሁሉ ነገር እያላቸው ሰላም ያጡ ሰዎች በሕይወታቸው ደስተኛ ሳይሆኑ በጭንቀት ማዕበል ተውጠው ሲቸገሩ አይተናልና፡፡ ስለሆነም ለህሊና ዕረፍት ሰላምን ገንዘብ ማድረግ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ይሆናል፡፡ ይህ ሰላም ደግሞ እንዲሁ በቀላሉ የሚመጣ አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ግለሰብ በጎ ህሊና ሲኖረውና ለሰላም ሲተባበር ነው፡፡

“ረሃብን የሚያውቀው የተራበ ብቻ ነው” ይባላል፡፡ የሰላምን ምንነትና ዋጋ የሚያውቀውም ሰላም አጥቶ የነበረና ያጣ ሰው/ማኅበረሰብ ነው፡፡ እስኪ ሁላችንም በሰላም እጦት ጊዜ ምን እንደተሰማን ራሳችንን እንጠይቅ? እርግጠኛ ነኝ ኑሮውም፣ ሥራውም፣ አጠቃላይ ሕይወት ያስጠላል፡፡ ያለሰላም ደስታ የለምና!

ሰላም የሁሉ ነገር ቀዳሚ ነው፡፡ ሰላም ያለበት ማኅበረሰብ የመከባበር፣ የመተማመንና ሠርቶ የመኖር ባለቤት ይሆናል፡፡ ሰላም ከሌለ ሕይወትም ይሁን ንብረት የባለቤቱ አይሆንም፡፡ የሰላም አየር በሌለበት እንኳንስ ስለ ልማትና ብልጽግና ማሰብ ይቅርና ወጥቶ ለመግባትም ዋስትና አይኖርም፡፡ ይህንን መረዳት የሚቸግረው ሰው አለ ብሎ ማሰብ እጅግ ከባድ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ያገኘችው ሰላም እንዲህ በቀላሉ የተገኘ አለመሆኑን ጠንቅቆ ማወቅም የሰላምን ዋጋ እንዳንዘነጋው ያደርገናል፡፡ አገሪቱ ነፃነቷን ጠብቃ እንድትቆይ ከማድረግ ጀምሮ አሁን ላገኘችው ሰላም የተከፈለው የሕይወት መስዋዕትነት በዋጋ የሚተመን አይደለም፡፡

መቸም አገሩን እንደነሶሪያ “ሰላም የራቃት ምድር” መባልን የሚሻ ያለ አይመስለኝም፡፡ በአብዛኛው የዓረቡ ምድር በሰላም እጦት ታምሶ የኮሽታ ድምፅ በተሰማ ቁጥር እየበረገገ፣ አገሩን፣ ወገኑን፣ ዘመዱን፣ ንብረቱን ጥሎ እየተሰደደ ከባህሉ፣ ከወጉ፣ ከእምነቱ፣ በአጠቃላይ ከማንነቱ ጋር ከማይመስለው ኅብረተሰብ ጋር ተቀላቅሎ ይኖራል፡፡ ይህም ዕድሜ ለሰጠው ብቻ ነው፡፡ አብዛኛው ደግሞ በስደቱ የዱር አውሬ እራት ሲሆን፣ ሌላው በረሃብ ጠኔ በረሃው ላይ ወድቆ ለአሞራዎች ሲሳይ ሲውል፣ በባህር ላይ የሸሸው ደግሞ ውኃ በልቶት በዛው ሲቀር ሰምተናል፤ ተመልክተናል፡፡ ያሳዝናል፡፡

 የሰላም እጦት ትርፉ ይህ ነው፡፡ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ሰላም አጥተው፣ ዜጎቻቸውን ለሞት ገብረውና የተረፉትንም በየቦታው ለስደት በትነው ለሰቆቃ የዳረጉት አገሮች ለዚህ ነገር ምስክሮች ናቸው፡፡ እነዚህ አገሮች ራቅ አድርገው ማሰብ ተስኗቸው አንዴ ከእጃቸው ያመለጣቸውን ሰላም ለመመለስ ቢታገሉም አልሆነላቸውም፡፡ ይባስ ብሎም “ሰላማቸው መቸውንም የሚመለስ አይመስልም” እየተባለ ሥጋት አዘል መርዶ ይነገርባቸዋል፡፡

ዛሬ እኛም “በእጅ የያዙት ወርቅ ከመዳብ ይቆጠራል” ለሚለው አባባል መተረቻ እንዳንሆን ቆመን ማሰብ አለብን፡፡ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች እያንዣበበ ያለውን ግጭት ልብ ልንል ይገባል፡፡ ከእንጭጩም ለማስወገድ መንግሥት የሕዝቡን የልብ ትርታ ሊያዳምጥ ይገባል፡፡ ሕዝቡም እንደ ቦይ ውኃ ዝም ብሎ መፍሰስ ሳይሆን ሰላማዊ በሆነ መንገድ በእውቀት ላይ በተመሠረተና በሕግ አግባብ ጥያቄውን ማቅረብ ይኖርበታል፡፡  ለሰላም እንቅፋት የሆኑ ነገሮችን አይተን እንዳላየን የማለፍ ሞራሉም ሆነ መብቱም የለንምና፡፡ ምክንያቱም በከባድ መስዋዕትነት የተገኘው ሰላም አንዴ ከእጃችን ካመለጠ ለመመለስ እጅግ በጣም ከባድ ይሆናል፡፡ በቀጣይም ኢትዮጵያንም እንደ ኢትዮጵያነቷ ለማየት ያስቸግራል፡፡

ስለሆነም ሰላም በምንም ዓይነት ሁኔታ በዋጋ ሊተመን የማይችልና ለድርድር ሊቀርብ የማይገባው ጉዳይ ነውና ሁላችንም ስለሰላም እናስብ፤ ሰላምን እንሻ እንከተላትም!! ሰላም ሁኑ፡፡

(ዳዊት ወልደየሱስ፣ ከአዲስ አበባ)   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...