የሪዮ ኦሊምፒክ በተጠናቀቀ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ የዘንድሮው ዳይመንድ ሊግ ሩውዝ (ሩጫ፣ ውርወራና ዝላይ) ውድድር፣ ባለፈው ሐሙስ (ነሐሴ 19 ቀን 2008 ዓ.ም.) በሎዛን (ስዊዘርላንድ) ቀጥሏል፡፡ ኢትዮጵያዊቷ ገንዘቤ ዲባባ በ3000 ሜትር ሩጫ በ8፡31.84 ደቂቃ በማሸነፍ የቦታውን ሪከርድ አስመዝግባለች፡፡ የሪዮ ኦሊምፒክ የ1500 ሜትር ብር ሜዳሊያ አሸናፊዋ ገንዘቤ፣ ውድድሩ ሊጠናቀቅ 400 ሜትር ሲቀር ተስፈንጥራ በመውጣት፣ ከስድስት ዓመት በፊት በኬንያዊቷ ቪቪያን ቼሩየት የተያዘውን ሪከርድ በሦስት ሰከንድ ግድም አሻሽላዋለች፡፡ የቅርብ ተቀናቃኟ የነበረችው በሪዮ በ5000 ሜትር ብር ሜዳሊያ ተሻሚዋ ኬንያዊቷ ሔለን ኦቢሪ ሁለተኛ፣ ሌላው ኬንያዊት ሜርሲ ቼሮም ሦስተኛ ሆነው ገብተዋል፡፡ እስከ ስድስተኛ ያለውን ቦታ ኬንያውያቱ ሲቆጣጠሩ ኢትዮጵያዊቷ ሀብታምነሽ ፈንታዬ 7ኛ ሆና ፈጽማለች፡፡ ገንዘቤ ባሰባሰበችው 10 ነጥብ ዳይመንድ ሊጉን ስትመራ ኦቢሪ በ6 ነጥብ በሁለተኛነት ትከተላለች፡፡ ዳይመንድ ሊጉ ነሐሴ 21 በፓሪስ የቀጠለ ሲሆን፣ የመጨረሻዎቹ 13ኛ እና 14ኛ ውድድሮች ሐሙስ ነሐሴ 26 እና ጳጉሜን 4 ቀን በዙሪክና በብራስልስ ከተሞች ከተካሄዱ በኋላ እ.ኤ.አ. የ2016 ዳይመንድ ሊግ ይጠናቀቃል፡፡