Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ወርቃችንን ለምን በነሀስ እንለውጣለን?

ሰላም! ሰላም! ማንጠግቦሽና እኔ ሰሞኑን እንዲችው ተናንቀን ሰነበትን። መቼም  መተናነቅ  በእኛ  አልተጀመረም፡፡  እንደምታዩት ሕዝብ  ከሕዝብ፣ መንግሥት ከመንግሥት፣ ባል ከሚስት፣ ወላጅ ከልጅ መተናነቁን ቀጥሏል። መጨረሻውን ያሳምረው እንዳንል እንኳን ከመተናነቅ ከመተቃቀፍም ደህና ነገር አልወጣ ብሏል። እንዴት በሉ? እንዴት  ማለት  ጥሩ  ነው። እንዴት የሚሉ የማይተናነቁ ናቸው።  ያልጠበቡ ናቸው። ኧረ ሳቄ መጣ እናንተ። ብለን ብለን እንደ ቦላሌ ጥበትና ስፋት ላይ ገባን። ይልቅ ፖለቲካውን ለቦጥላቂዎች እንተወውና ባንተወውም የተውነው እንምሰልና ማንጠግቦሽና እኔን ምን እንዳስተናተቀን ላጫውታችሁ። ይህቺ የወርቅ ምድር  በዓለም የአትሌቲክ ውድድር በአንድ ወርቅ ብቻ መሸኘቷ አንገበገበኝ፡፡ ሲሆን ሲሆን በቀጣዩ ኦሊምፒክ እወዳደርላታለሁ፡፡ ካልሆነ ደግሞ  ለጤናዬ  ይጠቅመኛል ብዬ ማልጄ እየተነሳሁ ለመሮጥ አሰብኩ። ተጨነቅ ብሎኝ እንጂ ‘ሼፒ ማን’ ነኝ፡፡ ቁዝር ያለች ቦርጭ ብቻ ነው ያለችኝ።

ታዲያላችሁ ማንጠግቦሽ እቅዴን በየት በየት አድርጋ እንደደረሰችበት አላውቅም፣ ሌሊት 11 ሰዓት ላይ ቀስ ብዬ ከአልጋዬ ስነሳ መብራቱን ቦግ አድርጋ “ኡኡ!”  ብላ ጮኸች። እኔ ደግሞ ‘መርዶ በቴክስት መነገር ተጀመረ?’ ብዬ፣  “ማን  ሞተ?” እላለሁ ትራሷ ሥር አንጀቴን ቋጥሬ የገዛሁትን ‘አይፎን’ ስልኳን  እየፈለግኩ። “አትወጣም። ከዚህች ቤት ንቅንቅ የለም ዛሬ፤” አትለኝ መሰላችሁ? “ለምን? እንዲህማ በግለሰብ የመሮጥ መብት ጣልቃ አትገቢም። ሲሆን ሲሆን ለአገርም ለእኔም ወጪ እንዳይበዛ  አስበሽ አሠልጣኝ በሆንሽ፤” አልኳት። “የለም። አንተን የሚያህል ሰውዬ አሁን ቁምጣ ለብሶ ሲሮጥ  . . . ኧረ እባክህ በተከበርኩበት አገር አታወርደኝ አርፈህ ተቀመጥ፤” ስትለኝ በቴሌቪዥን የወሰድኩት የትምህክተኝነት ‘ሌክቸር’ ትዝ ብሎኝ ክው አልኩ። ተሳክቶልኝ በመጪው የቶኪዮ ኦሊምፒክ በቡታንታ ስሮጥ ብታየኝ ልትፈታኝ ነው ማለት ነው? ያኔ በልጅነት በየቀኑ ትጥቅ ስታስፈታኝ  እንዳልኖረች? ወይ ትምክህትና ቁምጣ!

“በገብስማ  ዶሮ  እየተመሃኘ፣ የእኔስ በሽታዬ ሰው ሆኖ ተገኘ” ያለው ማን ነበር? ማንም ቢለው ደግነቱ ሕመማችንን እስከ ገለጸ ድረስ አንቃወምም፡፡ ኋላማ ማንጠግቦሽን “ወግጂ!”  ብዬ ወጥቼ  ዱብ  ዱቤን  ጀመርኩ። (ዱብ ዱብ ባይ በስተርጅና) በዘመኑ የእኩልነትና የመከባበር ባህል መሠረት ይህንን ቃል ለሚስቴ መጠቀም አልነበረብኝም። ግን ደግሞ የመናገርና የመጻፍ መብት በሕገ መንግሥታችን ያለሳንሱር ተደንግጎልኛል፡፡ እንግዲህ ሁለቱን ለማስማማት በጥበብ አስቤ በጥበብ ማውራት ነበረብኝ፡፡ “የዘመኑም ችግር ይኼ ይመስለኛል። በጥበብ አስቦ በጥበብ የሚናገር ሰው ጠፍቷል። እንዳመጣልን ስንለጣጠፍ ሩጫውን  ትተን  በአሉሽ  አሉሽ  ጠበል  ፀዲቅ ስንጠራራ፣ ከኋላ ተነስቶ የሚቀድመን በዝቷል፤” ይለኛል የባሻዬ ልጅ። ወይ ዘንድሮ!

 ይኼን እያሰብኩ በለሆሳስ ‘ወይ ማንጠግቦሽ’ እያልኩ ለብቻዬ እያወራሁ ሳሶመሱም “ቁም!”  አለኝ። “ማን?’’ እንዳትሉኝ። ባለሁበት ቆምኩ። “ወዴት ነው የምትሮጠው? ለምንድነው የምትሮጠው? የማንን አጀንዳ  ለማስፈጸም ነው የምትሮጠው?” የጥያቄ  እንቁላል ፈለፈለብኝ። “ኧረ እኔ ማንም አላከኝም። የምሮጠው ለጥቅሜ . . . ማለቴ ለጤናዬ ነው፤” ብዬ መልሼለት ‘ወዴት ነው የምትሮጠው?’ የሚለውን ምን ብዬ ልመልስ? ወደ ቤቴ ነው የምሮጠው እንዳልለው ቤቴ በጀርባዬ ነው። ወደ ቀኝ እንዳልለው ለእሱ ግራው ሊሆን ነው። ዝም ብዬ እንዳመጣልኝ “ወደፊት ነው የምሮጠው፤” አልኩት። “አምጣ መታወቂያ!” አለኝ። “ቤት ነው አልያዝኩም፤” አልኩት። ያ የደላላ አንደበቴ ከዳኝ። ዘንድሮ የማይከዳ የለም። ለነገሩ የደላላ ሆነ የተላላ፣ የፕሮፌሰር ሆነ የዶክተር የሚያስጥል አፍ ያለ አይመስለኝም። “መታወቂያ የለህም?” ሲለኝ፣ “መታወቂያማ አለኝ። ግን ሰውነቴን ለማጎልመስ  ከቤት ስለወጣሁ አልያዝኩም። ቁምጣዬ ደግሞ ኪስ የለውም፤” ብዬ ስሾፍ ቁምጣዬ ከኋላ ኪስ አለው። መቼም ሲፈጥረኝ ሰው ያምነኛልና መርማሪዬ አመነኝ፡፡ “በል ሁለተኛ ያለመታወቂያ እንዳትሮጥ። ደረትህ ላይም ቢሆን ለጥፈህ ሩጥ፤” ብሎ ሲለቀኝ በመጣሁበት አቅጣጫ ተመልሼ ወደ ቤቴ። ‹ወደ ቤታቸው ያልተመለሱትን ቤት ይቁጠራቸው› ስትሉ ሰማሁ?

እንዲህ እንደ ዋዛ ወጥተን ስንገባ ተመስገን የረሳን ብዙ አለን። ደግሞ ይኼንን  ለምን አመጣኸው በሉኝ፡፡  በሉኝ ግድ የለም። አያችሁ መጠያየቅ ጥሩ ነው። ካለመጠያየቅ ሥልጣኔ  የቀረብን  እኛ  እንጂ  አውሮፓውያን አይደሉም። ታዲያ በሰላም ወጥቶ የመግባትን በረከት ከረሱት መሀል አንዱ እኔ ነበርኩ። ፈጣሪም የመርሳቴን ጥልቀት ዓይቶ ነው መሰለኝ ያ መርማሪ ሲለቀኝ ለወርቅ ሜዳሊያ የማልሮጠውን ሩጫ እየሮጥኩ ወደ ቤቴ ስመለስ ጉድጓድ ውስጥ ከተተኝ። ባሻዬን እንዲህ ስላቸው፣ “ተው ፈጣሪህን አትፈታተን። እሱ ከጉድጓድ አይከትም። እሱ አይፈትንም፤” ሲሉኝ ነበር። “እውነት ነው። ግን አንዳንዴ የመንገዱን ምቾትና ልማት አላውቀው ላለ ሰው ወይም  ሕዝብ  በበረሃ መንገድ አስጉዞ (ልክ ሲና በረሃ ጉዞው) ካላስተማረው እንዴት ሊማር ይችላል?” ብዬ ተከራከርኩ።

ምሁሩ ልጃቸው  ወለምታዬን  ሰምቶ ሊጠይቀኝ  ሲመላለስ ይህንን ማጠንጠኛዬን ሰምቶ፣ “ይኼን ሁሉ ዙሪያ ጥምጥም የምትዞረው ማዘጋጃ  ቤትን  ላለመክሰስ ነው?”  ብሎ በሰው ፊት አያዋርደኝ መሰላችሁ? በጥዝጣዜ  አሳብቤ  አቃሰትኩና  ዝም። አዲስ  አበቤ እንደሆነ በየመንገዱ ብቅ ጥልቅ የሚልባቸውን ጉድጓዶች ለምዷቸዋል። እርግጠኛ ነኝ ከነገ ጀምሮ የመንገድ  ባለሥልጣን (ማን እንደሚመለከተው ጭምር ጠፋን እኮ?) ራሱ አንድ ጉድጓድ እንዳላይ  ብሎ  መድፈን ቢጀምር ነዋሪው ግልብጥ ብሎ (ሰላማዊ ሠልፍ ልል ነበር) ቅር የሚለው ይመስለኛል። ይኼኔ በልባችሁ ‘ግልብጥ ብሎ ቅር ‘ብሎ አነጋገር አለ? ትሉኝ ይሆናል። ለቋንቋና ለባህል መከበር ዘብ ከመቆም አልፎ ታሪክ የሠራው መንግሥታችን ግን በእንደራሴዎቹ  አንደበት  በአማርዝኛ ሲያጨናንቀን ዝም ትላላችሁ። ለነገሩ ሰሚ ጠፍቶ እንጂ እኔም እናንተም ዝም ብለን አናውቅም።  የለንበትም  የምትሉ  ካላችሁ  ‘እኔ የማውቀው ዝም ብዬ አለማወቄን ነው’ ብዬ ራሴን ችዬላችኋለሁ።  እስኪ ለስብራቱም ለአወዳደቁም ራሳችንን እንቻል፡፡

እናለችሁ ወለምታዬ ሙሉ ለሙሉ እስኪሻለኝ አልጠበኩም። ካልተሠራ አይበላም። እንኳን ተኝተን ሮጠንም አልተሳካም። ዋናውም የተሳካው ለጥቂቶች ብቻ ይመስላል። ምክንያቱማ ይኼው በባህር አቋራጭ ዋኝተን ዋኝተን አብዛኞቻችን የተረፈን እትብታችን በተቀበረባት አገራችን የዳያስፖራ ቀን ማክበር ብቻ ነው። እና ይኼን ብዬ አንድ ዳያስፖራ ደንበኛዬ ቦሌ አካበቢ ሁነኛ ቤት ሳገኝ እንድደውል ማዘዛቸው ትዝ አለኝ። ፈጣሪም ሳይደግስ አይጣላ፣ ማዘጋጃ ቤትም ሳያቀባብል ጉድጓድ አይጥል ምን የመሰለ ባለአንድ ፎቅ ዘመናዊ ቤት አግኘሁ። ደወልኩላቸውና መገናኛ አካባቢ ተገናኝተን በመኪናቸው ጫኑኝ። ጉዞ ወደ ቦሌ ሆነ፡፡ መጫወት ጀመርን፡፡ “ወይ ጉድ ይኼ ቀለበት መንገድ መቼ ነው የተሠራው?” በማለት ጠየቁኝ። “15 ወይም 16 አመት ሆነው፤” አልኳቸው። ይደነቃሉ፣ ይገረማሉ። “እንኳን ይኼ ወሎ ሠፈር እኮ ጫካ ነበር፤” ይሉኛል። ከመንገዱ ጨዋታው ረዘመ። ለካ እየሄድን አይደለም። አልሄድ አለ ያለው ለካ ዘፋኙ ወዶ አይደለም። መኪናችን ቆማለች።

 “ምንድነው ሰላም አይደለም እንዴ?” አለን አንድ ባለአውቶሞቢል በመስኮት። “እኛ ምኑን አውቀን?” ስንለው ደግሞ አንድ ቀልቃላ ታክሲ ነጂ ያለመስመሩ ተሹሎክሉኮ መጣና አጠገባችን ሲደርስ ሞተር አጥፍቶ ቆመ። ነገር አለ አልኩ። “ከኢምፔሪያል ሞኤንኮ መለስተኛ ሐይቅ ‘ናፕ’ ልውሰድ ብሎ ተኝቶ ነው። እስከዚያ ‘ሜዲቴት’ አድርጉ ተብሏል፤” ብሎ ሳቀ። አዛውንቱ ዳያስፖራ ሳቅ ብለው፣ “ስማ አንጂ። እኛ ስለማንሰማ ነው እንጂ እኮ በየት አገር ነው ወንዝ ጎርፍ ከተማ መሀል ለጥ ብሎ የሚተኛው?” አሉኝ። “አልገባኝም?” ስላቸው፣ “አየህ ልጄ ጠማማው ይቃናል። ዝቅ ያለው ከፍ ይላል። የጎደለው ይሞላል። የሞላው ይጎላል። ለሁሉም ግን  ቁልፉ ያለው ጊዜ ላይ ነው። ይኼን ሁሉ ለዕለት ጉርሱ የተሠለፈ ሠራዊት በዝናብ ውኃ አግቶ ያሰከነው ፈጣሪ ያለምክንያት ይመስልሃል?” ሲሉኝ ባሻዬን መሰሉኝ። እኔስ የ’ስዊሚንግ ፑል’ እጥረት እንዳለብን የውኃ ስፖርት ፌዴሬሽኑን አምርሮ የደፋው ውኃ መስሎኝ ክፉ ልናገር ነበር። ለማንኛውም አጋጣሚው ሲገኝ ቆመን እስኪጎል ከመጠበቅ ስብ ብናቀልጥበት ምን ይለናል? ኦ ለካ ማነው ስሙ. . . አተት  አለ!

በሉ እንሰነባበት። “የሰቆጣ ሞሰብ ይሸጣል ከእነ እፊያው፣ ዓይኔ ዞሮ ዞሮ ካንተው ነው ማረፊያው፤’’ ሆኖባት ማንጠግቦሽ ስትናገር አልሰማ ብዬ በመጣው ጦስ አኩርፋኝ ሰንብታ ታረቀችኝ። እኔም ተራዬን “አውላላው ሜዳ ላይ አዋላኝ አዋላኝ፣ ባባቷ እምላለሁ አባቴን አስክዳኝ፤” ሆኖብኝ  ያለሷ አይሆንልኝም። ምን መሰላችሁ ሚስጥሩ? ከፍቅርም  የከረመ ፍቅር አለ አያችሁ? እንዲያውም በቀደም በዚህ በፍቺ ጭቅጭቅ አሥር ቦታ ሽምግልና እየጠሩ ስልችት ቢላቸው፣ “ልጆቹ ምን ያድርጉ? ያልከረመ ፍቅር ይዘው ድሮስ እንዴት ሊከርሙ ኖሯል?” ሲሉ ነበር ባሻዬ። ታዲያ ባሻዬ እንደምታውቋቸው  ጨረሱ ሲባሉ ማቆሚያ የላቸውም። ጨረሱ ብዬ እግሬን አፍታትቼ ልሄድ ስነሳ፣ “ቆይ ቁጭ በል የት ትሄዳለህ? አንተም እንደ ዘመኑ ሰው ስለከረመ ፍቅር ስለነበተ ሰላም ሲወራ ትሸፍት ጀመር?” ብለው አሳፈሩኝና ቁጭ።

“ይኼውልህ አንበርብር። ‘መጣች ያገሬ ልጅ እንደ ሐረግ ተመዛ፣ ሳይበሉ የሚያጠግብ ትዝታዋን ይዛ’ የተዘፈነበት ጊዜ ተረስቶ ‘ማነህ? ምንድነህ? ምንትስ ነህ? ከወዴት ነህ?’ አስተያየትና ግልምጫ እያየሁ ነው። እንጃ አላማረኝም። ምን ትላለህ አንተ?” ብለው ጠየቁኝ። ባሻዬን ካወቅኳቸው ቀን ጀምሮ ‘ምን ትላለህ?’ በሚል ምክር ጠይቀውኝ አያውቁም። መላ፣ ምክር፣ ዘዴ ከእሳቸው ነበር። ዛሬ ቢጨንቃቸው ወደ እኔ ዞሩ። ድሮስ በከረመ ፍቅር፣ በሰነበተ ሰላም ሲመጡበት ማን መላ ቅጡ አይጠፋው? እኔ ደላላው አንብርብር ምንተስኖት በበኩሌ ጉምጉሙን ትተን በአደባባይ ከተነጋገርንና ከተወያየን ያኖርነው ፍቅር ይከርማል፣ የተከልነው ካስማ ፀንቶ ይኖራል እላለሁ። አለበለዚያ እንዲያው ጉምጉም እያሉ መዝፈን ነው። ወርቃችንን ለምን በነሀስ እንለውጣለን? መልካም ሰንበት!

         

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት