Saturday, April 20, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የጋራ መኖሪያ ቤት 11ኛው ዙር ዕጣ ቢወጣም እኛና ችግራችን ግን ዛሬም አልተፋታንም

በዮሐንስ ኃይሉ

መዲናች አዲስ አበባ ፈርሳ እየተገነባችና አሮጌ ገጽታዋ እየተለወጠ በትልልቅ ዛፎች ፈንታ ትላልቅ ሕንፃዎች ጫካ እየተሞላች ነው፡፡ ለጥቂት ጊዜያት ወጣ ብለው ሲመለሱ የግንባታዎች ፍጥነት ከተማዋን እየቀያየራት የገዛ ሠፈርዎን ለመጠየቅ ካስገደዱ ዋል አደር ብለዋል፡፡

በተለይ በግለሰብ ደረጃ ይገነባሉ ተብለው ለማመን የሚቸግሩ ትልልቅ የሕንፃዎች መንደር 80 በመቶ ለንግድና ለቢሮ፣ 20 በመቶ ለመኖሪያ የሚከራዩ መሆናቸውን እያየን ነው፡፡ በጭቃ ቤት ውስጥ ተወልደን ለዘመናት እዚያው ጭቃ ቤት ውስጥ እየኖርን ከጋራ መፀዳጃ ቤት ወረፋና ከሳፋ ሻወር አልወጣንም፡፡ በተፋፈገ መኖሪያ ቤት ውስጥ ሆነን ቀን በሥራ የደከመ አካላችንን ሌሊት በሰላም እንድናሳርፍ የሚረብሹንን አይጦች ለማጥፋት አልጋ ሥርና የምግብ ማብሰያ ቦታዎች ወጥመድ በማስቀመጥና በማንሳት ተጨማሪ ሥራ የተጠመድን ብዙዎች ነን፡፡ ‹‹መቼ ይሆን ከኪራይ ቤት ወጥተን እንዳቅሚቲ በሆነች የግል መኖሪያ ቤት ፈታ ብለን መኖር የምንጀምረው?›› የሚል ከምኞት ያልዘለለ ሕይወት እየገፋን፣ የፎቆች መሥሪያ ሚስጥሩ ተሰውሮብን ምኞት ስለማይከለከል ብቻ እኛና ምኞታችን ከነቤተሰቦቻችን ጭምር ከኪራይ ወደ ኪራይ እየተገላበጥን ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡

መንግሥት እንደኛ ላሉት ዜጎቹ የመኖሪያ ቤት ችግራችንን በዘላቂነት ለመፍታት በ1996 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ነዋሪዎች ለኪራይ በሚያወጡት ገንዘብ በረዥም ጊዜ ክፍያ የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ለማድረግ ዕቅድ አወጣ፡፡ በዚህም መሠረት የናሙና ሥራዎቹን በ1997 ዓ.ም. በዕጣ ለማስተላለፍ በከተማዋ ባሉ ቀበሌዎች ምዝገባ አካሂዶ በወቅቱ በእኩል የዕጣ ተወዳዳሪነት ሁሉም ተመዝጋቢዎች ቀርበው፣ በዓላማው መሠረት እጅግ ፍትሐዊ በሆነ ዋጋ ቤቶቹን ለባለዕድለኞች ማስረከቡ አይዘነጋም፡፡

በዚህም መሠረት የመጀመርያው የጋራ መኖሪያ ቤት ምዝገባ ከተካሄደ 11 ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም፣ እስካሁን በተካሄዱት 11 ዙር የዕጣ አወጣጥ ሥርዓቶች በየጊዜው የሚፈለሰፉ አዳዲስ አሠራሮችና ድንጋጌዎች አሉ፡፡ ለ11 ዓመታት ዕጣ በወጣ ቁጥር እንደ ዜጋ ከችግራችን አንፃር በከፍተኛ ጉጉት የምንጠብቀውን ተመዝጋቢዎች የቤት ዕጣ ተጠቃሚነት መብታችን በየዙሩ እየተሸራረፉና ቤት የማግኘት ዕድላችን እየጠበበ ተስፋው ወደመጨለሙ ተዳርሰናል፡፡

ከ1997 ዓ.ም. የመጀመርያ ዙር ዕጣ አወጣጥ ጀምሮ በዋጋ፣ በአከፋፈል፣ በእኩል ተወዳደሪነት፣ በጥራት፣ በቦታ ርቀትና በብዙ ተዘርዝረው በማያልቁ ልዩነቶች ተጎጂ የሆነውንና በሰበብ አስባብ ወደኋላ እየተጎተትን ተመዝጋቢዎች አለን፡፡ ከፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና ከእኩል የዜግነት መብት ተጠቃሚነታችን ተገፍተን የበይ ተመልካች ሆነን መኖር ሊያበቃ ስለሚገባ፣ ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅድልን መንገድ ጥያቄያችንን ለመንግሥት በሕጋዊ አካሄድ እናቀርባለን፡፡ የመኖሪያ ቤት ችግራችንን አስመልክቶ ለ11 ዓመታት የተጉላላነው እንዲያበቃና የቤት ግንባታው ዓላማ ከተቋቋመበት ውጪ በየዙሩ እየተጫኑብን የመጡትን አሠራሮች ማስተካከያ እንዲበጅላቸው ጥያቄያችንን ለመንግሥት በጋራ እንድናቀርብ፣ ከሥር በተዘረዘሩ መሠረታዊ ነጥቦች ዋና ዋና ጉዳዮቻችንን ለመነሻት አቅርበናል፡፡

  1. በመጀመርያውና በሁለተኛው ዙር ዕጣ ወቅት የነበረው የቤቶቹ የዋጋ ተመን እጅግ ፍትሐዊና በዝቅተኛና መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ሆኖ፣ በመኖሪያ ቤት ችግር አስከፊ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የነበረውን ሕዝብ የቤት ባለቤት በማድረግ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል በአገሪቱ እንዲኖር መሠረት የጣለ አሠራር ተጀምሮ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ሆኖም የ1997 ዓ.ም. የምርጫ ቀውስና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተፈረጠው የኢኮኖሚ ቀውስ በተለይም በአገራችን እስከ 2000 ዓ.ም. የነበረው የሲሚንቶ፣ የብረታ ብረትና የግንባታ ጥሬ ዕቃ አቅርቦት፣ የባለሙያ የሰው ኃይል እጥረት ግንባታውንም ሆነ የዕጣ አወጣጡን ሒደት ከማጓተቱም በላይ፣ በዋጋ ላይም በመጀመርያዎቹ የቤት ዕድለኞችና አሁን ባሉት የዕጣ ዕድለኞች መካከል በአምስት እጥፍ የዋጋ ልዩነት ጭማሪ እንዲያሳይ ምክንያት ሆኗል፡፡
  2. በመጀመርያዎቹ ዙሮች የነበረውን ሁኔታ ለናሙና ስንመለከት በ1997 ዓ.ም. ለ51 ካሬ ባለሁለት መኝታ ቤት ጠቅላላ ክፍያ 49,000 ብር ከፍሎ መረከብ የሚቻል የነበረ ሲሆን፣ በረዥም ክፍያ ለሚጠቀሙ በ9,800 ብር ቅድመ ክፍያ ቤቱን ተረክበዋል፡፡ ከአራተኛ ዙር ጀምሮ የተመሳሳይ ካሬ ቤት ጠቅላላ ዋጋ 90,095.75 ብር በመሆን ከፍተኛ ልዩነት የተፈጠረ ሲሆን፣ በረዥም ክፍያ ቤቱን መረከብ ለሚፈልጉ ዜጎች 18,019.14 ብር ከፍለው ቤቱን ተረክበዋል፡፡

ከስምንተኛው ዙር ጀምሮ እስከ ዘጠነኛው ዙር የቤቱ ዋጋ ወደ 135,508.18 ብር ከፍ ያለ ሲሆን፣ በቅድመ ክፍያ ለሚረከቡ ብር 27,101.64 ብር በመሆን በከፍተኛ ደረጃ የዋጋ ልዩነት እየፈጠረ ቀጥሏል፡፡ ከላይ በተዘረዘሩት ዙሮች ዕጣው ከወጣ በኋላ ቅድመ ክፍያ ከፍለው የሁለት ዓመት የዕፎይታ ጊዜ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ከዋጋው ጭማሪ ውድነት በቀር ዕጣው ከወጣ በኋላ የሚከፈል የቅድሚያ ክፍያና የሁለት ዓመት የዕፎይታ ጊዜ አሠራር ተቋሙ የተቋቋመለት ዓላማ በትክክል ተግባራዊ የሚያደርግ በመሆኑ፣ የእኛም ተራ ሲደርስ በዜግነታችን እኩል ተጠቃሚ እንደምንሆን በማመን በተስፋ ስንጠብቀውና ስንደግፈው ኖረናል፡፡

ከአሥረኛው ዙር ጀምሮ ግን በዳግም ምዝገባ በቅድመ ክፍያ (ቁጠባ) ሰበብ በርካታ ዜጎች ከወርኃዊ ወጪያቸው በተጨማሪ በኪራይ ቤት እየተጉላሉና በየወሩ የተተመነባቸውን እየቆጠቡ እንዲጠብቁ ከመደንገጉም በላይ፣ ዕጣው ሲወጣ ተመሳሳይ ባለሁለት መኝታ ጠቅላላ ዋጋ በአምስት እጥፍ አድጎ 263,000 ብር ሲሆን፣ ቅድመ ክፍያው ደግሞ ወደ 65,000 ብር ከፍ ብሏል፡፡ በዚህ አሠራር ብዙ ዜጎቻችን ከውድድሩ ውጪ ሆነው የመኖሪያ ቤት ችግራቸው የዕድሜ ልክ ጨለማቸው ሆኗል፡፡

ከላይ እንደተገለጸው የዋጋ ንረት ዋነኛ ምክንያቶች የሲሚንቶ፣ የብረታ ብረት፣ የሰው ኃይልና የአቅርቦት እጥረት የነበረ ቢሆንም፣ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት የቀረጥ ነፃ ዕድል በማመቻቸትና ድጎማ በማድረግ ጭምር አስቸኳይና የአጭር ጊዜ መፍትሔ ተግባራዊ አድርጓል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ደግሞ እንደ ብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ የመሳሰሉ ተቋማትንና ሌሎች የመንግሥት ፋብሪካዎችን ከማቋቋም በላይ፣ በግል ዘርፉም የሲሚንቶና የብረታ ብረት ፋብሪካዎች እንዲበራከቱ ከቀረጥ ነፃ የግብር ዕፎይታና የመሳሰሉ ድጋፎችን በማድረግ፣ እጥረቱን ብቻ ሳይሆን ዋጋውንም ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደርስ አድርጓል፡፡ የሰው ኃይል ችግሩንም ለመፍታት ከቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ጀምሮ እስከ ትላልቅ ሥራ ተቋራጮችን በማኅበር በማደራጀት የጠጠር፣ የብሎኬትና የግንባታ አቅርቦትን ችግር በዘላቂነት በመፍታት አስደናቂ መፍትሔ ሰጥቷል፡፡

ይህ ሁሉ ሆኖ እያለ በርካሽ አቅርቦት የተገነቡትን ቤቶች ሳይቀር እጥረት በነበረበት ጊዜ ከተገነቡት ቤቶች በበለጠ ዋጋ ብቻ ሳይሆን፣ ከተገነቡ በኋላ በሰበብ አስባቡ ከዕጣ ውጪ በማቆየትና ግንባታውንም በማዘግየት ጭምር በቀጣይ ዙሮች በተጋነነ ዋጋ ለተመዝጋቢዎች ማቅረብ፣ ተቋሙ የተቋቋመለትን ዓላማ ያልተገነዘቡና ተቋሙ ሲመሠረት ያልነበሩ ግለሰቦች የተሳሳተ አሠራር እንጂ መንግሥትንም ሆነ የግንባታውን ዓላማ የሚወክል ሊሆን አይችልም፡፡

  1. የመኖሪያ ቤት ችግር እንደ ምግብ፣ ልስብ፣ ጤናና የመሳሰሉት ፍላጎቶች የሁሉም ዜጋ መሠረታዊ ችግር እንጂ በፆታና በሙያ ፈጽሞ የሚፈረጅ አይደለም፡፡ እኛ ለ11 ዓመታት ከዛሬ ነገ ዕጣችን ይወጣል ብለን በተስፋ የምንጠብቅ ዜጎችም እንደማንኛውም ዜጋ የአገራችን ልማትና ዕድገት አካላት እንጂ ሁለተኛ ዜጋ አይደለንም፡፡ ልማትን በተግባር እየደገፍን የተጠቃሚነታችንን ተራ ብንጠባበቅም፣ መንግሥት አሮጌ ሠፈሮችን ባፈረሰ ቁጥር የልማት ተነሽዎች በሚል ሰበብ ተመዝግበው የነበሩም ይሁኑ ያልተመዘገቡትንም ጭምር የቁጠባ ደብተር ሳያሻቸው እየታደላቸው ነው፡፡ እኛ በቆጠብነው የጋራ መኖሪያዎችን ገንብቶ ለእነሱ ማስተላለፍ የእኛን የመፍትሔ ጊዜ በማዘግየት የቤት ጉዳይ ፈጽሞ ተስፋ አስቆራጭ እንዲሆንና ዥንጉርጉ ዜጋ ያላት አገር እንድትሆን ያደርጋል፡፡ በመሆኑም የልማት ተነሺዎችን ጉዳይ ለብቻው ተይዞ ከእኛ ዕጣ አወጣጥ ሥርዓት ውጪ የተሻለ አሠራር ሊበጅለት ይገባል፡፡

ከብዙ በጥቂቱ በእነዚህ ነጥቦች መነሻነት ሌሎች ያልተጠቀሱ ተያያዥ ዝርዝር ጉዳቶቻችንን ለመንግሥት አቅርበን ማስተካከያ እንዲደረግበትና ዘላቂ መፍትሔ ለእኛም ሆነ ለቀጣይ ተመዝጋቢዎች እንጂ ለማድረግ ከፖለቲካ፣ ከሃይማኖት፣ ከጎሳና ሌሎች ከቤት ችግራችን ጋር ተያያዥ ያልሆኑ አጀንዳዎች ርቀን በሰላማዊ መንገድ ተደራጅተን ለችግራችን በጋራ መፍትሔ ማበጀት እንድንጀምር ትክክለኛ ጊዜው አሁን ነው፡፡ ለችግራችን መፍትሔ ለመፈለግ በስብሰባዎቻችን ለመገኘት የነባር ተመዝጋቢ ካርዳችን ብቸኛ መለያችን እንዲሆን ይገባዋል፡፡ ከዚህ ውጪ በየቀበሌያችን ያሉ የየትኛውም አደረጃጀቶች ሆኑ ጥያቄያችንን ተገን አድርገው ለሌላ ዓላማ የሚሰባሰቡ ኃይሎች በዚህ ጉዳይ ላይ ፈጽሞ ጣልቃ እንዳይገቡ ብርቱ ጥንቃቄ እንድናደርግ ያስፈልጋል፡፡

በመጨረሻም ሰባቱ እስከ መቼ? 

  • ለቤት ዕጣ ተመዝግበው በ11 ዓመታት ውስጥ በተስፋ እየጠበቁ ዕጣው ሳይወጣላቸው በመኖሪያ ቤት ጉዳይ እረፍትን እንደናፈቁ ለአንዲት ቀን ሳያገኟት ያለፉ የቤተሰብ ኃላፊዎች፣ ከሞቱ በኋላ ዕጣው ወጥቶ ቤተሰቦቻቸው የዕድሉ ተጠቃሚ መሆን ሳይችሉ ሲቀሩ እስከ መቼ?
  • በሰበብ አስባቡ ግንባታው እየዘገየና በየዙሩ ዋጋ እየጨመረ እስከ መቼ?
  • በፆታ፣ በሙያ፣ በልዩ ኬዝ፣ ነገ በሚፈጠር ሌላ ልዩ ኬዝ እየተባለ የእኩል ዕጣ ተወዳዳሪነታችን ዕድል እየጠበበ እስከ መቼ?
  • ምርጫ በመጣ ቁጥር የተገነቡ ቤቶችን በተስፋ ዳቦነት እየተቁለጨለጭን እስከ መቼ?
  • እኛ እየቆጠብን የተሠሩ ቤቶች ለሌላ እየተላለፉ የበይ ተመልካችነታችን እስከ መቼ?
  • በመጀመርያዎቹ ዙሮች ለዜጎች የተሰጡ ዕድሎችን ተነፍገን እስከ መቼ?
  • መጠለያ፣ ምግብና ልብስ ወዘተ. እኩል የሁሉም ዜጋ ችግር ሆነው ሳለ እስከ መቼ?

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው m[email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles