Monday, April 15, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የሚካሄዱ ተቃውሞዎች ‹ፈታኝ ተግዳሮቶች› ናቸው – አሜሪካ

በቶም ማልኖውስኪ

በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች እየተካሄዱ ላሉ ተቃውሞዎች በምላሹ የኢትዮጵያ መንግሥት የተከተለው ‹ራስን የመፃረር› ስልት ነው፡፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ ደኅንነትን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ናይሮቢ ከመድረሳቸው ቀደም ብሎ የጻፍኩት ይህ ጽሑፍ፣  የአዲስ አበባ ‹ቀጣይ ታላቅ ብሔራዊ ተግባር የፖለቲካ ግልጽነትን ለማስፈን የሚያጋጥሙ ተጋድሮቶችን በሚገባ መወጣት› እንደሆነ ያስረዳል፡፡

አሜሪካና ኢትዮጵያ አንዱ ለሌላው አስፈላጊ መሆኑን ታሳቢ ያደረገ ለዓመታት የዘለቀ ጠንካራ ግንኙነት አላቸው፡፡ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላምና ደኅንነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የምታደርግ፣ አፍራሽ ጽንፈኝነትን በመዋጋት ረገድ የአሜሪካ ዋና አጋር፣ ከየትኛውም አገር በላይ ብጥብጥና ጭቆናን ሸሽተው የተሰደዱ ስደተኞችን በማስተናገድ ለማመን የሚያስቸገር ልግስና ያሳየች አገር ነች፡፡ ኢትዮጵያ ድህነትን ለማስወገድ፣ በአካባቢ ጥበቃና ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ ለምታደርገው ጥረት አሜሪካ ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ ላይ ነች፡፡ 

ሁለቱ አገሮች ባላቸው የጋራ ጥቅምና ወዳጅነት ምክንያት አሜሪካ በኢትዮጵያ ብልፅግና፣ መረጋጋትና ስኬታማነት የራስዋ ድርሻ አላት፡፡ ኢትዮጵያ በመልካም ጎዳና ላይ ስትሆን፤ ሌሎችን ማነሳሳትና መርዳት ትችላለች፡፡ በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ቀውስ ሲከሰት፣ ሁለቱ አገሮች በጋራ ለማሳካት ያለሙትን ግብ ያኮስሳል፡፡

በቅርቡ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች እየተካሄዱ ያሉ ተቃውሞዎች ፈታኝ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ተቃውሞዎች ኢትዮጵያውያን በሕገ መንግሥቱ በሰፈረው መሠረት ለጥያቄዎቻቸው ምላሽ የሚሰጥና የፖለቲካ ብዝኃነትን የሚያሰፍን መንግሥት እንዲኖር መፈለጋቸውን የሚያመለከቱ ናቸው፡፡

በቅርቡ በኢትዮጵያ ባደረግኳቸው ሦስት ጉብኝቶች የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጨምሮ ያገኘኋቸው ሁሉ፣ ኢትዮጵያውያን በበለፀጉና በተማሩ ቁጥር ይበልጥ የፖለቲካ ተሰሚነት እንዲኖራቸው እንደሚፈልጉ ገልጸውልኛል፡፡ ይህ ፍላጎታቸው ደግሞ ሊሟላላቸው ይገባል፡፡ ምንም እንኳን ጥቂቶቹ ተቃውሞዎች ለብጥብጥ መሣሪያነት ቢውሉም፣ አብዛኛዎቹ ተቃዋሚዎች የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ሐሳባቸውን እንዲገልጹ የሰጣቸውን መብት እየተገበሩ እንደሆነ እናምናለን፡፡

አሜሪካ የምትሰጠው ማንኛውም ምክር መፍትሔ ለማስገኘት ያለመ ሲሆን፣ በአክብሮት ጭምር ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በሐምሌ 2007 ዓ.ም. አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት እንደተናገሩት፣ አሜሪካ ፍፁም እንከን አልባ አገር አይደለችም፡፡ የሕዝብን ብሶት ምላሽ በመስጠት ዙሪያ ከተሞክሯችን ጠቃሚ ትምርት እየተማርን ነው፡፡

ኢትዮጵያ ተጨባጭ የሆነ የውጭ ሥጋት እንደተጋረጠባት እንገነዘባለን፡፡ ኢትዮጵያ በድንበሯ አካባቢ የመሸገውን የአልሸባብ አሸባሪ ቡድንን በጀግንነት ተጋፍጣለች፡፡ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖሩና ራሳቸው ለሰብዓዊ መብት ክብር በማይሰጡ አገሮች የሚደገፉ ግለሰቦችና ቡድኖች አልፎ አልፎ በብጥብጥ ለውጥ ለማምጣት ሳይታክቱ ጥሪ ያቀርባሉ፡፡

ኢትዮጵያ እንዲህ ያሉ ድርጊቶችን በአግባቡ ትኮንናለች፣ አሜሪካም እንዲሁ፡፡ ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ተበታትነው የሚኖሩና በኢትዮጵያውያንም ብዙ ተቀባይነት የሌላቸው የጥፋት መልዕክተኞችን በመመከት ረገድ ብዙ ርቀት ተጉዛለች፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለደኅንነቷና ለአንድነቷ እየገጠማት ያለው ችግር ምንጩ ከውስጥ ነው፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በበርካታ ቦታዎች፣ በብዙ ክልሎች ወደ አውራ ጎዳናዎች በመውጣት ሕይወታቸውን በሚነኩ ጉዳዮች ተገቢ ድምፅ እንዲኖራቸው ሲጠይቁ፣ የውጭ ጠላት ሴራ ነው ብሎ ማጣጣል የሚቻል አይሆንም፡፡

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ሠልፈኞቹ አግባብነት ያለው ብሶት እንዳላቸውና ተገቢ ምላሽ እንደሚያስፈልጋቸው አምነው ተቀብለዋል፡፡ በዚህም እንደ ሙስናና በቂ የሥራ ዕድሎች ያለመመቻቸትን ለመዋጋት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ግን የደኅንነት ኃይሎች ከመጠን ያለፈ ኃይል በመጠቀም ኢትዮጵያውያን በሰላማዊ መንገድ እንዳይሰበሰቡ መከልከል፣ በርካቶችን መግደልና ማቁሰል እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ማሰራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በተቃውሞ ሠልፎች ላይ ተገኝተዋል በሚል መሠረተ ቢስ ክስ በእስር እንደሚገኙ፣ አብዛኛዎቹም ለሕግ ያልቀረቡ፣ የሕግ አማካሪ የተከለከሉ ወይም በአግባቡ የወንጀል ክስ ያልተመሠረተባቸው እንደሆኑ እናምናለን፡፡

ይህ ደግሞ ራስን የመፃረር ስልት ነው፡፡ የተቃዋሚ መሪዎችን ማሰርና የሲቪክ ማኅበረሰብ ተቋማትን መገደብ ሰዎችን ተቃውሞ ከማድረግ አያግዳቸውም፡፡ ይልቁንም መንግሥት በሰላም ለመደራደር የማይችልበትን መሪ አልባ እንቅስቃሴ ይፈጥራል፡፡ የኢንተርኔት መስመርን መዝጋት ተቃውሞን አያረግብም፡፡ ነገር ግን የውጭ አገር ባለሀብቶችንና ጎብኚዎችን ሥጋት ውስጥ ይከታል፡፡ ኃይልን መጠቀም ለጊዜው ተቃዋሚ ሠልፈኞችን ቢያረግብም፣ ይበልጥ ንዴታቸውን የሚያባብስና ወደ ጎዳና ተመልሶ ለመውጣት ምንም ነገር ከግምት ውስጥ እንዳያስገቡ ያደርጋቸዋል፡፡

ማንኛውም መንግሥት ዜጎቹን የመጠበቅ ግዴታ አለበት፡፡ ነገር ግን ሕጋዊነት ያለውና ስኬታማ መንግሥት ዜጎቹን ያዳምጣል፣ ስህተቱን ያምናል፣ እንዲሁም ያላግባብ ጉዳት ለደረሰባቸውም ካሳ ይከፍላል፡፡ ትችትን በግልጽነትና በሰላማዊ መንገድ ማስተናገድ በራስ መተማመንንና ጥበብን የሚያሳይ እንጂ ድክመት አይደለም፡፡  በመንግሥት፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በማኅበረብ ውስጥ ነፃ ድምፆች ቢኖሩ፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ተቋማት የብዙኃኑን ችግር በሕጋዊ መስመር ቢያስተላልፉና የፖሊሲ መፍትሔዎችን ቢያቀርቡ ኢትዮጵያ የበለጠ ትጠነክራለች፡፡ መንግሥትን የሚተቹ ሁሉ መፍትሔ በማፈላለጉ ሒደት ኃላፊነትንና ተጠያቂነትን እንዲጋሩ ያደርጋል፡፡ ሥርዓቱን ለማደስ የሚደረግ ሒደትም የሕዝብ ጥያቄዎችን ሙሉ በሙሉ ከመቃወም ወደ መግባባት ያደርሳል፡፡

የኢትዮጵያ ቀጣዩ ብሔራዊ ኃላፊነት የሚሆነውም የኢኮኖሚ ዕድገት እንቅፋቶችን እንዳስወገደ ሁሉ የፖለቲካ ግልጽነት ተግዳሮቶችን መዋጋት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ረሃብና ሽብር ከሰፈነባቸው ጊዜያት የተጓዘችባቸውን ርቀት ከግምት በማስገባት፣ ኢትዮጵያውያን እነዚህን ተግዳሮቶች እንደሚያስወግዱ አሜሪካ ሙሉ ተስፋ አላት፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት ሌላን አገር ለማስደሰት ሳይሆን የራሳቸውን ራዕይ ለማሳካት ነው፡፡ አሜሪካም ሆነች ሌሎች የኢትዮጵያ ወዳጆች እጃቸውን ለመዘርጋት ዝግጁዎች ናቸው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የአሜሪካ የዴሞክራሲ፣ ሰብዓዊ መብትና ሠራተኞች ምክትል ሚኒስትር ናቸው፡፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles