Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የማኑፋክቸሪንግ ኤክስፖ በአዲስ አበባ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

አፍሪካን በተለይም የኢትዮጵያን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለማስተዋወቅና  በዘርፉ ያለውን እንቅስቃሴ ለማሳደግ እገዛ ያደርጋል የተባለ ዓለም አቀፍ ኤክስፖ ኢትዮጵያ ውስጥ በቋሚነት መዘጋጀት ሊጀምር ነው፡፡  

ሐበሻ ዊክሊ ፕሮሞሽን በተባለው አገር በቀል ድርጅት አዘጋጅነት በየዓመቱ አዲስ አበባ ላይ መካሄድ የሚጀምረው ኤክስፖ ‹‹አፍሪካ ኢንተርናሽናል ማኑፋክቸሪንግ ኤክስፖና ኮንፈረንስ›› የሚል ስያሜ ይኖረዋል፡፡ የመጀመሪያው ኤክስፖም ከጥር 15 እስከ 17 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል፡፡  

በየዓመቱ በቋሚነት የሚዘጋጀው ይህ ኤክስፖ ከ300 በላይ የሚሆኑ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑበት የሐበሻ ዊክሊ ፕሮሞሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ አዶኒ ወርቁ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አፍሪካውያንን በማኑፋክቸሪንግ ምርቶች ለዓለም ለማስተዋወቅና አዳዲስ ገበያዎችን ለማፍራት ያስችላቸዋል የተባለው ይህ ቋሚ ኤክስፖ፣ በአዲስ አበባ በየዓመቱ በቋሚነት ከመካሄዱ ሌላ በሌሎች የአፍሪካ አገሮችም በመዘዋወር የሚካሄድ እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡ እንደ ሐበሻ ዊክሊ ፕሮሞሽን መረጃ ተዘዋዋሪ ኤክስፓውን በተመረጡ የአፍሪካ አገሮች ለማዘጋጀት የሚያስችል ፈቃድ በመውሰድ የሚሠራ ይሆናል፡፡ ተዘዋዋሪ ኤክስፖው የኢትዮጵያን የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች ለማስተዋወቅና ለውጭ ምንዛሪ የገቢ ምንጭ የሚሆንበትን ዕድል የሚያመቻች ነው ተብሏል፡፡

በየዓመቱ ዕድገት እያሳየ የመጣው የአፍሪካ ማኑፋክቸሪንግ ምርት መጠን እ.ኤ.አ. በ2005 73 ቢሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን፣ በ2015 መጨረሻ ላይ 157 ቢሊዮን ዶላር እንደደረሰ የኤክስፖው አዘጋጆች ይገልጻሉ፡፡ ዓመታዊ ዕድገቱ 3.5 በመቶ የደረሰ በመሆኑ ይህንን ዘርፍ የበለጠ ለማሳደግ አንዱ መንገድ እንዲህ ያሉ ኤክስፖዎች ናቸው ይላሉ፡፡

በዚህን ያህል ደረጃ እያደገ ያለውን ዘርፍ በተለይ በኢትዮጵያ የተጀመረውን እንቅስቃሴ ለማሳየት ዘርፉን ለማዘመንና አዳዲስ ኩባንያዎችንም ለመሳብ ኤክስፖው ትልቅ ሚና እንዲኖረው ታስቦ የተቀረፀ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡ ኤክስፖው በተለይ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2025 በቀላል ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ቀዳሚዋ አፍሪካዊ አገር እንድትሆን የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካትም በተለየ ሁኔታ ዘርፉን የሚያስቃኝ ልዩ የንግድ ትርዒት መዘጋጀቱ አስፈላጊ እንደሆነ የገለጹት አቶ አዶኒ፣ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ኢትዮጵያ ያላትን መልካም ዕድልም የምታሳይበት ይሆናል ብለዋል፡፡ የውጭ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ጭምር ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነም የኤክስፖው አዘጋጆች ይገልጻሉ፡፡

ከኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ኩባንያዎች ሌላ በኤክስፖ ላይ የሚሳተፉ የውጭ ኩባንያዎች የማኑፋክቸሪንግ ማሽነሪ አቅራቢዎች እንደሚሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ፕሮግራሙ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚሰማሩ ኢትዮጵያውያን ኩባንያዎች ማሽነሪዎችን በቀላሉ እንዲያገኙ በማድረግ የሚፈጥረው ዕድል እንደሚኖረው ለመረዳት ተችሏል፡፡

የኤክስፖው ትኩረት በማኑፋክቸሪንግ ላይ ይሁን እንጂ በዝግጅቱ ላይ ከ15 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ተቋማትንም የሚያሳትፍ ነው፡፡ የአገር ውስጥም ሆነ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በምሳሌነት ተጠቅሰዋል፡፡

በኤክስፖው እንደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽንና የመሳሰሉት መንግሥታዊ ተቋማት በአጋርነት ይሳተፉበታል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑን ከሐበሻ ዊክሊ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

ከኤክስፖ ጎን ለጎን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍን የተመለከቱ የውይይት መድረኮች እንደሚኖሩ የተገለጸ ሲሆን፣ የኢትዮጵያንም ሆነ የአፍሪካን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የበለጠ ለማሳደግ የሐሳብ ልውውጥ የሚደረግበት ይሆናል ተብሏል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች