Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በእንጀራ ላይ የሚፈጸመውን ውንብድና መቆሚያው መቼ ነው?

ፈጽሞ ለምግብነት ሊውሉ የማይችሉ ባዕድ ነገሮችን በመቀላቀል ‹‹እንጀራ›› በሚል መጠሪያ ለሸማቹ ያቀርቡ ነበር የተባሉ አንድ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ስለማዋላቸው የሚገልጹ ወሬዎችን እየሰማን ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ወሬ ሰሞኑን አዲስ  ቢሆንም ከሰጋቱራና ከሌሎች ባዕድ ነገሮች ጋር በመቀላቀል እንጀራ የማዘጋጀትና በድፍረት ለገበያ የማቅረቡ ተግባር ግን ዛሬ የተጀመረ አይደለም፡፡ ተቆጣጣሪ ጠፋ እንጂ ቀድሞ የነበረ ነገር ነው፡፡

ለሸማቾች ወይም ለተጠቃሚዎች ደንታ የሌላቸው ደፋሮች ሲተገብሩት ቆይተዋል፡፡ አሁን ግን እንደ አዲስ ባዕድን ነገሮችን እንደ ግብዓት በመጠቀም እየተዘጋጀ ያለውን ‹‹እንጀራ›› ገበያውን መያዙን በተደጋጋሚ መስማታችን ደግሞ ችግሩ ሥር እየሰደደ መምጣቱን ያመለክታል፡፡ ለማንኛውም መልካሙ ነገር በዚህ ፀያፍ ተግባር ተሰማርተዋል የተባሉ ግለሰቦች በሕግ ቁጥጥር ሥር እየዋሉ ነው መባሉ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ዕርምጃ የዘገየ ቢሆንም፣ አሁን መጀመሩ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ሕገወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩትን ወደ ትክክለኛው መንገድ ለማምጣት ምን ያህል በቂ ዝግጅት ተደርጓል? የሚለው ጉዳይ ያሳስባል፡፡ ምክንያቱም ብዙ ጊዜ አንድ ሰሞን በዘመቻ የምንጀምራቸውና ቆይተው የሚዘነጉ ጉዳዮቻችን በርካታ ስለሆኑ፣ ሕገወጥ እንጀራ ጋጋሪዎች ላይ እየተወሰደ ነው የተባለው ዕርምጃ በተመሳሳይ የሆነ ቦታ ይቆማል ከሚል ነው፡፡ 

በአሁኑ ወቅት ሸማቾች በየዕለቱ ከሚሸምቷቸው የዕለት ፍጆታዎች መካከል አንዱ እንጀራ በመሆኑ፣ በቀጥታም ከጤና ጋር የተሳሰረ ነውና በልዩ ትኩረት ቁጥጥር ይገባዋል፡፡ ሆኖም ግን ምርቱ ብዙም ትኩረት ሳይሰጠው ቆይቷል፡፡

አሁንም ቢሆን ግን ባዕድ ነገሮችን ቀላቅሎ እየተሰናዳ ያለው እንጀራ ውንብድና እየሰፋ ስለመሆኑ ከመነገሩ አንፃር፣ ከሰሞኑ ሁለትና ሦስት ሰዎችን በማሰር ብቻ የሚታለፍ ያለመሆኑን እንድንገነዘብ ያደርጋል፡፡

የደራውን የእንጀራ ገበያ ከግምት በማስገባት በየመንደሩ ‹‹እንጀራ›› የሚያመርቱና በቀጥታ ለሸማቾች የሚያቀርቡ እንዲሁም ለሆቴሎችና ምግብ ቤቶች የሚያቀርቡ መበርከታቸውን ልብ ይሏል፡፡ ስለዚህ በዚሁ ልክ የቁጥጥር መንገዱ ካልሰፋና አሁን እንደታየው አንድ ሁለት ሰው ብቻ በመያዝ ችግሩ ይወገዳል ማለት ዘበት ነው፡፡

በጊዜ ብዛት ከቤት ውጭ ይዘጋጅ ያልነበረው ‹‹እንጀራ›› አሁን አደባባይ ወጥቶ እንደማንኛውም ሸቀጥ ለገበያ እየቀረበ መሆኑ ባይከፋም፣ ግብይቱም ሆነ አመራረቱ ጤናማ እንዲሆን ግድ ይላል፡፡

የእንጀራ ገበያ እየሰፋ በዚያው ልክ ውንብድና እየበዛበት የመጣ ጉዳይ በመሆኑ፣ እንዲሁም ዛሬ በግልጽ ባናየውም ያለ ጥንቃቄ እየተመረተ ያለው እንጀራ አንድ ቀን ጅምላ የጤና እክል መፍጠሩ አይቀርም፡፡ ስለዚህ የእንጀራ አዘገጃጀት አቀራረብና የማከፋፈል ሥራው ጤናማ እንዲሆን ከታሰበ የቁጥጥር ሥራው የተደራጀ መሆን አለበት፡፡ በተለይም ቁጥጥሩ ያዝ ለቀቅ የሚል ከሆነ ችግሩን ማባባስ እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡ ችግሩ የሰፋ መሆኑን ካመንን በሁለት ሰዎች ላይ ብቻ ዕርምጃ በመውሰድ መፍትሔ ማምጣት ስለማይቻል፣ አሁንም በድፍረት ሥራ ውስጥ ያሉትንም ለመቅጣት ተጨማሪ ዕርምጃዎች ያሻሉ፡፡ ያልተቋረጠ ክትትልም ግድ ነው፡፡

ስለዚህ ጉዳይ ቀደም ብሎ በተላለፉ መልዕክቶች በግልጽ ማስቀመጥ እንደተቻለው፣ በአሁኑ ወቅት እንደ ‹‹ዳቦ›› ያሉ ምግብ ነክ ምርቶች ደረጃና መጠን ተቀምጦላቸው እንዲሸጡ የተቀመጠው ግዴታ እንጀራንም መመልከት እንዳለበት ነው፡፡ ቁጥጥሩን ለማጥበቅ በቀጥታ ወንጀለኞችን ለመለየት እንዲሁም በትክክል ለገበያ የሚቀርበው ‹‹እንጀራ›› አደጋ የሌለው መሆኑን ለማረጋገጥ እንጀራ የራሱ የሆነ የአዘገጃጀት ደረጃ ሊወጣለት ይገባል፡፡

ጤፍ ወይም ሌላ እህል ከእንጨት ፍቅፋቂ ጋር ቀላቅሎ ‹‹እንጀራ›› ሆኖ ለገበያ እንዳይቀርብ ከተፈለገ፣ የመቆጣጠሪያ ዘዴው መስተካከል አለበት፡፡ ቢያንስ እንደማንኛውም ንግድ እንጀራ አቅራቢዎች ማንነት መመዝገብ የመጀመርያው ዕርምጃ መሆን አለበት፡፡

የምርቱ ቦታና አምራቹ ግለሰብም ቢሆን ተመዝግቦ እንዲሠራ ማድረግ ቀዳሚ ዕርምጃ ከሆነ፣ በቀጣይ ሊደረጉ የሚገባቸው የቁጥጥር ሥራዎች ጥሩ መደላድል ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ዛሬ በየቀበሌው ደንብ አስከባሪ በሚል የሥራ ዘርፍ የተመደቡ ተቆጣጣሪዎችም ሆኑ በሌላ የሥራ ዘርፍ የተሰማሩ ሕግ አስከባሪዎች የጎዳናው ላይ ነጋዴዎችን ከማሳደድ ጎን ለጎን፣ እንዲህ ያሉ ጉዳዮችንም እንዲከታተሉ ሥልጣን ቢሰጣቸው ነገሩን ማርገብ ይቻላል፡፡ ዘላቂም ባይሆን ቀላል የማይባል መፍትሔ ይሰጣል፡፡

የእንጀራ ዝግጅት በግለሰብ ቤት ጭምር የሚሠራ በመሆኑ አሁን ባለው ደረጃ ግብር ክፈሉ፣ እንዲህ አድርጉ ማለት ብቻ ሳይሆን የሚሸጡትን እንጀራ እንዴት እንደሚያዘጋጁት መከታተል ነገሩን ያረግባል፤ ሰዶ ማሳደድንም ያስቀራል፡፡

እርግጥ ነው ቢዝነሱ እየሰፋና በኩባንያ ደረጃ ወደማምረት እየተገባ ስለሆነ፣ እንጀራ አቅራቢዎች በግብር ሥርዓት ውስጥ ይግቡ መባሉ አይቀሬ ነው፡፡ እስከዚያ ድረስ ግን ሆዳችንን በሰጋቱራ መሙላት ግን ተገቢ አይደለም፡፡

የሕዝብ ጤንነት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ እንጀራ ከጤፍ ብቻ ሳይሆን ከሌላ ሰብሎችም የሚዘጋጅ በመሆኑ፣ ከምን ከምን እንደሚዘጋጁ እንድናውቅ የመቆጣጠሪያ ሥልታችን ወሳኝ ነው፡፡

ችግሩን ለመቆጣጠር ሌላው አማራጭ ደግሞ ምግብ ቤቶች የሚረከቡት እንጀራ እንዴት እንደተመረተና በምን እንደተመረተ? ጠይቀው የመቀበል ግዴታ እንዲኖርባቸው ማድረግ ነው፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ እንጀራ ጋጋሪዎች ማንነት ታውቆ በሥርዓት የሚያመርቱ ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ መረጃ ሲይዙ ነው፡፡ ተቀባዮችም ይህንኑ አይተው እንዲቀበሉ ማድረግ ነው፡፡ ይህ እጅግ ቀላል ነገር ነውና አንድ ከሁለት ሰዎችን በመያዝ ችግሩን መቅረፍ እንደማይቻል በማመን ምግብ ነክ የሆኑ ነገሮችን የሚቆጣጠረው አካል ወደታች ወረድ ብሎ ተጨማሪ የመፍትሔ ሐሳቦችን መዘርጋት ይኖርበታል፡፡ ነገሩ  የአንድ ሰሞን ሰዶ ማሳደድ እንዳይሆንም እንጀራ አቅራቢዎች ሊያሟሏቸው የሚገባቸውን መስፈርቶች ማስቀመጥና በዚያው አግባብ እንዲሠሩ ማድረግም መልካም ይሆናል፡፡ ስለዚህ ለዘላቂ መፍትሔ የተጠና ሥራ በመሥራት ሸማቾችን መታደግ ያስፈልጋል፡፡

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት