Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉልብ ያለው ልብ ይበል

ልብ ያለው ልብ ይበል

ቀን:

በሳሙኤል ረጋሳ

እንደ አገር አሁን እየተጓዝንበት ያለው ሰፊ ጎዳና የት እንደሚያደርሰን ያልገባን ብዙዎች ነን፡፡ የሰላም ዋጋ ርካሽ በመሆኑ ሁሉም ሰው በቀላሉ ሊገዛው ይችላል፡፡ በእጃችን ሲኖር ሰላምን እንደ መዳብ እንቆጥረዋለን፡፡ ሲያመልጠን ግን ዋጋውን መገመት ያስቸግረናል፡፡ መልሶ የማግኛው ዋጋ እጅግ ውድ በመሆኑ ከመጀመሪያው እንዳያመልጠን ያስፈልጋል፡፡

በእጅ ያለው የሰላም ዋጋ ርካሽ የሚሆነው በትዕግሥት፣ በመቻቻልና በመወያየት ብቻ በመሀላችን ያለውን ችግር መፍታት ሳንችል ነው፡፡ ጠንካራ የበሰለ አመራርና አስተዋይ ሕዝብ ያለው አገር ይህንን በቀላሉ የሚተገብረው በመሆኑ የተስፋ እንጂ የሥጋት አገር አይኖረውም፡፡ ነገር ግን ሕዝብና መንግሥት አንድ አካል አንድ አምሳል ሳይሆኑ ቀርተው በ‘እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ’ እልህ ተጋብተው ወደ አላስፈላጊ ቅራኔ ከተገባ የሚከፈለው ዋጋ እጅግ በጣም ውድ ነው፡፡ አሁን አሁን ግን ምንም ያህል ውድ ዋጋ ቢከፈልበት መልሶ ሰላምን ማግኘት ያልተቻለበት አጋጣሚ በጣም ብዙ ነው፡፡ አሁን ያለንበት የዓለም ሁኔታም የሚያሳየን ይኼንን ነው፡፡ ኢራቅ፣ ሶሪያ፣ ሊቢያ… ያጡትን ሰላም ለመመለስ እየከፈሉት ያለው ዋጋ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ሕይወት እንኳ ሊመስላቸው አልቻለም፡፡

ታዲያ ይኼ በሌሎች ላይ የምናየው ችግር ለጊዜው በሰላም የምንኖር በመሆኑ ብቻ በእኛ አይደርስም ብሎ ማሰብ ከየዋህነትም በላይ ነው፡፡ በኦሮሚኛ አንድ ተረት አለ፡፡ ‹‹ደራሽ ውኃ ሞልቶ ከወንዙ ተርፎ ሜዳ ላይ ወጥቷል፡፡ ውኃው ከደጋው አገር አግበስብሶ ያመጣውን የሰዎችና የእንስሳት አስከሬን እያገላበጠ ሲያልፍ አንዱ መንገደኛ ከዳር ቆሞ ይኼን ጉድ ያያል፡፡ ውኃው እየሞላና እየጨመረ ወደ እግሩ ተጠጋ፡፡ ሰውዬው አሁንም በመገረም ይመለከተዋል፡፡ ታዲያ ወንዙ ለሰውዬው ‘በልቼ አሳየሁህ፣ ጮኼ አሰማሁህ ከዚህ በላይ ማስጠንቀቅ የለም’ ብሎ እሱንም ገፍቶ ከመሀል አስገብቶ ይዞት ሄደ፤›› እኛም አሁን የምንጓዝበት ጐዳና ወደዚያ ላለማምራቱ ምንም መተማመኛ የለንም፡፡ መላ ሳናበጅለት ችግራችንን ከዳር ቆመን ስናይ ከመከራ ባህር ውስጥ እንዳንሰምጥ፡፡

በተለይ መንግሥት ይኼን አስከፊ ጎዳና ሕዝቡ እንዳይጓዝበት ለማድረግ ቀዳሚ ኃላፊነትና ተጠያቂነት አለበት፡፡ ታዲያ መንግሥትም ቢሆን ይኼን የሚያደርገው የጉዞው መጨረሻ ምን እንደሆነ ለራሱም ቢሆን ገብቶት ከሆነ ነው፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሌጋሲያቸውን (ፈለጋቸውን) እንከተላለን የሚሏቸው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አሁን ያለንበትን ሁኔታ የሚገልጽ ምሳሌ ነግረውን ነበር፡፡ ሐሳቡን ቃል በቃል ባልይዘውም መንፈሱ እነሆ፣ ‹‹አንድን እንቁራሪት ቀዝቃዛ ብረት ምጣድ ላይ አድርገው እሳት ላይ ቢጥዷት ሙቀቱ ቀስ በቀስ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ነገር ግን እንቁራሪቷ የሙቀቱ መጠን በፈለገው ያህል ቢጨምር ለውጡ አይሰማትም፡፡ በዚህ ሒደት ሙቀቱ እየጨመረ እሷም በሒደቱ ሳታውቀው ተጠባብሳ ትሞታለች፤›› የሚል ነው አባባሉ፡፡ አቤት እሳቸውማ ሲያሳምሯት፡፡

በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አሁን ብረት ምጣዱ የተጣደ ይመስላል፡፡ መንግሥትና ሕዝብም ብረት ምጣዱ ላይ ተጥደዋል፡፡ ሙቀቱ የተሰማቸው ጥቂቶች ካሉ ሳናውቀውና ሳይሰማን ተጠባብሰን ከመሞታችን በፊት ከሁለቱም ወገን መፍትሔ ይምጣ፡፡ ያኔ እንቁራሪት ሳንሆን ሰዎች መሆናችንን ከሰዎችም እንደ ወትሮው አገራችንን ሊታደጓት የሚችሉ ብርቱ ዜጐች ያሏት መሆኑን ለዓለም እናሳያለን፡፡

ብዙ ጊዜ መንግሥት እሱ የማያምንበትንና የእሱን ፖሊሲ የሚጣረስ ምንም ዓይነት ጥሩ ነው የሚባል ሐሳብ ቢሆንም ተቀብሎ በሥራ ላይ ማዋል ቀርቶ መስማት አይፈልግም፡፡ ቢሰማም በፀረ ሕዝብነት ነው የሚፈርጀው፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት ላለፉት 25 ዓመታት ሲከተለው የነበረ በሒደት እንኳ ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር የማይለወጥ ችክ ያለ አቋም ነው ያለው፡፡ አሁን መመለስ ያለበት አንድ ወቅታዊ ጥያቄ አለ፡፡ መንግሥት ከማንኛውም አቅጣጫ የሚቀርብለትን ጥያቄ እንዴት ለማስተናገድ ተዘጋጅቷል? እስከ መቼ ሁሉም እኔ ባልኩት ይሁን ይላል፡፡ ይኼ ግትር አቋም እንዳለው የሚያውቁ ጠንካሮች አብረው መዝለቅ አይችሉም፡፡ ስለዚህ መንግሥት የአድር ባዮችና የአስመሳዮች፣ እንዲሁም የሙሰኞች ስብስብ ይሆናል፡፡

የሌሎችን ሐሳብ ተቀብሎ ሚዛን የሚደፋውን መተግበርና ያ ሐሳብ የሌሎች መሆኑንም ማሳወቅ መንግሥትን ያስከብረዋል እንጂ አያዋርደውም፡፡ መንግሥት ሁሉንም መንገድ ዘግቶ እሱ በሚያውቃት ጠባብ መንገድ ላይ ብቻ የአንድን አገር ሕዝብ እመራለሁ ማለት የትም እንደማያደርሰው ማወቅ አለበት፡፡ ሰዎች የተለያዩ አማራጮችንና መንገዶችን ማየት ይፈልጋሉ፡፡ ስለዚህ መንግሥት አማራጭ መንገዶቹ ምንም ይሁኑ ምን፣ በተቃዋሚዎችም ሆነ በሌሎች ሲቀርቡለት የሁሉንም ሐሳቦች ተቀብሎ የጋራ ውይይት በሚፈልገው ደረጃ ማድረግ አለበት፡፡ ውጤቱ የሚያለያይም ሆነ የሚያቀራርብ ለሕዝብ በግልጽ መንገርም ይኖርበታል፡፡ ያኔ ፍርዱ የሕዝብ ይሆናል፡፡

ለአብነት የወልቃይትን ጉዳይ በተደጋጋሚ ለመንግሥት ያቀረበ አካል መኖሩን የተለያዩ ሚዲያዎች ዘግበውታል፡፡ የቀረበው ጥያቄ ለመንግሥት የማይጥመውና የማይቀበለው ሊሆን ይችላል፡፡ ግን አቅራቢ ኮሚቴዎችን ከመግፋት ይልቅ በክብር ተቀብሎ ጊዜ የወሰደ ውይይት አድርገው በመጨረሻም የሚደርሱበትን ውጤት በጋራ ለሕዝቡ ቢገልጹ፣ ይኼ ጉዳይ አሁን የደረሰበት ደረጃ የመድረስ ተስፋው የመነመነ ነበር፡፡

ኦሮሚያ ውስጥም በተደጋጋሚ ሕዝብና መንግሥት ቅራኔ ውስጥ የሚገቡበት አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ችግሮች በተፈጠሩ ቁጥር የእሳት ማጥፋት ሥራ ነው የሚሠራው፡፡ መንግሥት ችግሮቹን ይፈቱልኛል ብሎ የሚያስበው ችግሩ ከተፈጠረበት አካባቢ መጥተው በሥልጣን ላይ ያሉትን የፌዴራልና የክልል ባለሥልጣናትን ነው፡፡ እነዚህ ባለሥልጣናት ሕዝብ ውስጥ ገብተው የማረጋጋት ሥራ እንዲሠሩ ይነገራቸዋል፡፡ ባለሥልጣን ሆነው አዲስ አበባ ከመኖራቸው ውጪ ከሕዝቡ ጋር ስለማይተዋወቁ የሕዝቡ ተቃውሞ እነሱንም ያጠቃልላል፡፡

እነዚህ ሹመኞች በአካባቢው የሚገኙትን የድርጅታቸውን አባላትና ተገደው እንዲወጡ የሚደረጉ የመንግሥት ሠራተኞችን ሰብስበው ስለተቃዋሚዎች፣ ስለሻዕቢያ አፈጣጠር የተለመደውን ንግግር አድርገው አጨብጭበውና አስጨብጭበው ይመለሳሉ፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ በምንም ሁኔታ የእነሱን ሐሳብ የሚቃወም መስሎ የታያቸውን ወይም በተቃዋሚ ድርጅትነት የሚጠረጠሩ ሰዎች ድርሽ አይሉም፡፡

ይኼንን ችግር መፍታት የነበረባቸው ትክክለኛ ባለቤቶቹ የዞንና የወረዳ አመራሮች መሆን ነበረባቸው፡፡ አብረው የሚኖሩና በቅርብ ችግራቸውን ያውቃሉ ተብሎ ስለሚገመት፡፡ ለነገሩማ እነሱም የሕዝብ ተመራጭ እኮ ናቸው፡፡ ስለዚህም መሠረታዊ የችግር አፈታት ሥራ ስለማይሠራ በየዓመቱ ችግሩም ሁከቱም ያገረሻል፡፡ ይኼንን ሁከት ለማስወገድ በአንዳንድ አካባቢዎች በቋሚነት በሚመስል ሁኔታ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን የሚቆጣጠሩት ከፌዴራል የሚላኩ የፀጥታ ኃይሎች ናቸው፡፡ ይኼ አማራጭ የሌለው ጊዜያዊ መፍትሔ ነው፡፡ ግን እስከ መቼ?

ነገር ግን ይኼን ችግር መፍታት ያለባቸው የአካባቢ፣ የዞንና የወረዳ መስተዳድሮችን ሕዝቡም አያውቃቸው፣ እነሱም መንግሥትን ወክለው እንደሚሠሩ ሆነው ለመታየት አይፈልጉም፡፡ ተወደደም ተጠላ መንግሥት የተቃዋሚንም ሆነ የተራውን ሕዝብ ሐሳብ ተቀብሎ መደራደር የሚገባው ጊዜ ላይ ደርሷል፡፡ ጠንካራ ተቃዋሚዎች የሉም እንጂ ከተገኙ ግማሽ መንገድ ሄደን እንቀበላቸዋለን የተባለው መተግበር ያለበት አሁን ነው፡፡ ነገር ግን በተቃራኒው የተቃዋሚን መኖር ያለመፈለግ አዝማሚያ እየታየ ነው፡፡

በፓርላማው ውስጥ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ፓርላማው ተቃዋሚዎች ከነበሩበት ጊዜ ይልቅ አሁን በተሻለ ሁኔታ እየሠራ ነው የሚል ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡ ይኼ ገዥው ፓርቲ እኔ ብቻ መግዛት አለብኝ፣ በአገሪቱ (ፓርላማ) ሌላ ተቃዋሚ አስተያየት መኖር የለበትም የሚል ሐሳብ እንዳለው አመላካች ነው፡፡ ፓርላማ የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ድርጅቶችና ፓርቲዎች በተለያየ አቋም የሚከራከሩበትና አብላጫው ድምፅ የሚያሸንፍበት እንጂ፣ ከቀድሞው የተሻለ ምርት አግኝቼበታለሁ የሚባልለት ፋብሪካ አይደለም፡፡ መንግሥት የተለመደውን የፖለቲካ አቋሙን ይዞ ምንም ሳያድግ እዚያው ቀንጭሯል፡፡ ስለዚህም የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ከልማቱ ጋር ሲታይ በተቃራኒ አቅጣጫ እየሄደ ነው፡፡

በሕዝብ በኩልም የመደገፍና የመቃወም መብታችን እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ስለምንቃወመው ነገር ጠለቅ ያለ እውቀትና ባንቃወመው በሕዝብ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት፣ ብንቃወመው የምናስገኘውን ጥቅም በአግባቡ ማወቅ አለብን፡፡ በተለይም ተቃውሞውን እንደ አጀንዳ የያዘውን ክፍል ማንነትና ከበስተጀርባው ምንም ዓይነት ሕዝባዊ ያልሆነ ተልዕኮ እንደሌለ ማረጋገጥ አለብን፡፡

ተቃውሞዎች በሰላማዊ ሠልፍ ደረጃ መመራት ያለባቸው ሕዝባዊ ወገንተኝነት ባላቸውና በምናውቃቸው ኢትዮጵያውያን ዜጐች ነው፡፡ ስለኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ምንም የማያውቁ ዳያስፖራዎች ውጪ ሆነው በሪሞት የሚቆጣጠሩት መሆን የለበትም፡፡ እኛስ ከእልቂታችንና ከመከራችን ተካፋይ መሆን የማይችሉ ወይም የማይፈልጉ በመሀላችን የማይገኙ ሰዎች በሚያስተላልፉልን የጦር አውርድ ቅስቀሳ የምንመራው እስከ መቼ ነው?

ባለፉት ሳምንታት ከተከሰቱት አደገኛ ሁኔታዎች መማር ያለብን ብዙ ቁም ነገር አለ፡፡ ኦሮሚያን የሚያህል ሰፊ ክልል ውስጥ በአንድ ቀን በሁሉም ቦታ በተመሳሳይ ሰዓት የተቃውሞ ሠልፍ እንዲደረግ፣ በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾች በተወሰኑ ግለሰቦች ሲነገረን ከርሟል፡፡ በተወሰነ ደረጃም ተተግብሯል፡፡

ለመሆኑ ይኼን መልዕክት ሲያስተላልፉ የነበሩት አካላት በአንድ ጊዜ በአጠቃላይ ኦሮሚያ ውስጥ የሚካሄደውን ሠልፍ የሚመራ፣ የሚቆጣጠር፣ ሥርዓት የሚያስይዝና የሚያስከብር ሌላው ቀርቶ በሠልፈኞቹ መካከል እንኳ ችግር ቢፈጠር አመራር የሚሰጥ አካል አስቀምጠዋል? አስቀምጠናል እንኳ ቢሉ በመላው ኦሮሚያ ውስጥ መተግበር እንደማይችል ይታወቃል፡፡ የተቃውሞው አጀንዳስ ምን ነበር? መቅረብ ያለባቸው ጥያቄዎችና መፈክሮች ምንድናቸው? ወይስ የኦሮሚያ ሕዝብ በሙሉ በየግሉ የሚፈልገውን መፈክር ይዞ አደባባይ እንዲወጣና ግርግር ፈጥሮ እንዲማገድ ነው? መንግሥትን በዚህ ዓይነት በአንድ ሌሊት ማስወገድ ፈልገው ከሆነ ትርፍና ኪሳራው ተጠንቷል? እያንዳንዱ ሰው ጊዜ ሰጥቶ ስለሠልፉ ቢያሰላስል በምንም ሁኔታ በትክክል ለኦሮሚያ በሚያስብ ሰው የቀረበ ጥሪ ነው ማለት ይከብዳል፡፡ ከጀርባው ያሉትን አካላት መመርመርና መገመትም አይከብድም፡፡

የአማራው ክልል ሠልፍም ቢሆን ከኦሮሚያው በተሻለ ሁኔታ ተካሂዷል እንኳ ቢባል፣ በአንድ ቀን ሳይሆን በተለያዩ ቀናት በመሆኑና የሠልፉም አጀንዳ በዋናነት ከወልቃይት ጥያቄ ጋር በመያያዙ ነው፡፡ ይኼ ምናልባት ውስን አጀንዳ ስላለው የተለየ ሊመስል ይችላል፡፡ የተነሱት ጥያቄዎች በሰዎች አዕምሮ ውስጥ ያሉ በመሆናቸው መጠየቃቸው ተገቢ ነው፡፡

የሚገርመው ነገር ግን በጉራ ፈርዳና በተለያዩ ቦታዎች በአማራ ብሔረሰቦች ላይ የተፈጸመው እንግልትና መፈናቀል እንዲሁም የንብረት መውደም ሲቃወም የነበሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች፣ በአማራ ክልል ውስጥ ያሉ ሌሎች ብሔረሰቦች በአማሮች ሲገደሉ ሲሰደዱና ንብረታቸው ሲወድም ትክክል ነው የሚል ህሊና እንዴት ይኖረናል? እነዚህ የውጭ አገር አራጋቢዎችም ሲሉት የነበረውን ሁሉ ረስተው እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት ደግፈዋል፡፡ ለዚህ ሁሉ በዋናነት የዋህ ሕዝብ አግኝተው በፈለጉት መንገድ እየመሩ የራሳቸውንና የዘመናት ጠላቶቻችንን ዓላማ ለማስፈጸም የተዘጋጁ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊነታቸውን እንደ እባብ ቆዳ ገፈው ጥለው በትውልድ እዚህ በመፈጠራቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊነት ብቻ የቀራቸው ሰዎች የሚያመጡት የእርስ በርሳችን መጠፋፊያ መንገድና የጠላቶቻችንን ድብቅ አጀንዳ ተቀብለው የሚያስተናግዱ መሆኑን ሁላችንም ልናጤነው ይገባናል፡፡ መርዙን የሚረጩልን ዘመኑ በፈጠረው ቴክኖሎጂና ረቂቅ ሚዲያዎች በመሆኑ የሚደርሰን በሪሞት ነው፡፡ እንዳይደርሰን ለመከላከልም ለመቀበልም ያስቸገረ ነው፡፡ የዚህ ሴራ ጠንሳሾች በውጭ የሬዲዮና የቲቪ ፕሮግራሞች መጥፊያችንን አዘጋጅተዋል፡፡

በርካታ የአገራችን ሕዝቦች ሕወሓት/ኢሕአዴግን ሊቃወሙ ይችላሉ፡፡ ለተቃውሞአቸውም በቂ ምክንያት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ተቃውሞአችንን የምንገልጸውና ዓላማችንን የምናስፈጽመው ግን እንደ እንቁራሪት ግለቱ እየጨመረ በሚሄድ፣ ግን የግለቱ መጨረሻ ምን እንደሆነ ሳናውቀው በሚገለን ብረት ምጣድ ላይ ተኝተን መሆን የለበትም፡፡

አሁን እየተካሄደ ያለው ትግል መንግሥትን ከሥልጣን ከማስወገድ በመለስ፣ የቀረቡትን ጥያቄዎች ብቻ በመመለስ የሚያበቃ አይመስልም፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴና ደርግም የብረት ምጣዱ ሙቀት ሳይሰማቸው ነው የከሰሙት፡፡ ለሩብ ምዕተ ዓመት ተደላድሎ ሥልጣን ላይ በመቆየቱና ሕዝቡም በአስተዳደሩ ዝርክርክነትና በመልካም አስተዳደር ዕጦት በመማረር ሌላ መንግሥት ቢፈልግ አይፈረድበትም፡፡ ነገር ግን ይኼ ምኞትና ፍላጐት እንዲፈጸም ከተፈለገ ቀዳሚና ተከታይ ሁኔታዎችን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ጥልቅ ግምትና እውቀት፣ በቂ ጊዜና ሁሉንም የሚያግባባ ድርድር፣ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለው የኢትዮጰያዊነት ትርጉም ቀዳሚና ሁላችንም ልንግባባበት የሚገባን ጉዳይ ነው፡፡

እስከዚያው ግን ከኢሕአዴግ የተለየ አማራጭ አለኝ የሚል ካለ ይንገረን፡፡ መንግሥትም በእስካሁኑ ዓይነት የምርጫ ሒደት መቶ በመቶ አሸንፌ እቀጥላለሁ ካለ የሚያስኬድ አይመስልም፡፡ መጪው ጊዜ ግለቱ እየጨመረ ከሚሄደው ብረት ምጣድ ላይ ወርደን በአዲስ መንፈስ ስለአገራችን አጠቃላይ ሁኔታ የምንወያይበት፣ የምንከራከርበትና መፍትሔ የምናስቀምጥበት መሆን አለበት፡፡ አሁን በሕዝብም ሆነ በመንግሥት እየተኬደበት ያለው የጥፋት መንገድ መሆኑን ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

         

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...