በታደሰ ሻንቆ
‹‹በዚህ በዚህ አይደል ሰው የሚተማማ
ሞተችልህ አሉኝ ሕመሟን ሳልሰማ››
ይህ የሕዝብ እንጉርጉሮ ነው፡፡ ከአቶ መለስ ዜናዊ ሞትና ሐዘን በፊት፣ ከእሳቸው መወለድ በፊት፣ ከአቶ መለስ ትውልድ አስቀድሞ የነበረ የሕዝብ የብሶት መግለጫ ሆኖ የቆየ፣ አሁንም አገልግሎቱን የሚሰጥ እንጉርጉሮ ነው፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን መታመም ይፋ ያደረገው ከኢትዮጵያ መንግሥት ይልቅ የአፍሪካ ኅብረት አስተዳደር ነው፡፡ ይህም የሆነው ከሐምሌ 2 ቀን እስከ ሐምሌ 9 ቀን 2004 ዓ.ም. በሊሎንግዌ ማላዊ ሊካሄድ የነበረውን 19ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔን ማላዊ ፈቃደኛነቷን መልሳ በመሳቧ የጉባዔው አስተናጋጅ ኢትዮጵያ እንድትሆን በመወሰኑ አጋጣሚ ነው፡፡
ሰኔ 11 እና 12 ቀን 2004 ዓ.ም. ሜክሲኮ ባስተናገደችው የቡድን 20/2012 ስብሰባ ላይ ለመገኘት ሲሄዱ፣ ተገኝተው ሲመጡ አንዳች የጤና ችግር እንደደረሰባቸው ሕመማቸው ራሱ በሰው ፊት ‹‹ያጋለጣቸው›› አቶ መለስ፣ በ2004/2005 ዓ.ም. የበጀት ሕግ ማፅደቅ ሥርዓት ላይም በፓርላማ አልተገኙም ነበር፡፡ ይኼ ሁሉ ሲሆን የአቶ መለስን መታመም ጉዳዬም፣ የሕዝብ ጉዳይም ብሎ የተናገረ መንግሥትና የመንግሥት ባለሥልጣን አልነበረም፡፡ ከመኃይም እስከ ምሁር ከተራ ሥራ አጥ እስከ ማዕከላዊ መንግሥት አባላት ድረስ የተንሰራፋ ሰፊ ተጠቃሚ ያለው የኢትዮጵያ የዜና ማሠራጨና ምንጭ ደግሞ ዛሬም ሹክሹክታ ነው፡፡ የአቶ መለስን ሕመም ሹክሹክታ ለመላው ኢትዮጵያ አዳርሶታል፡፡ በዚህ መካከል አጋጣሚ ተገኝቶ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታው ስለአቶ መለስ ሕመም ‹‹ወሬ›› ይጠየቃሉ፡፡ ክደው መልስ ይሰጣሉ፡፡ የአፍሪካ ኅብረት 19ኛው መደበኛ ጉባዔ መክፈቻ ላይ ሐምሌ የመጀመሪያ ሳምንት ውስጥ የወቅቱ የኅብረቱ ሊቀመንበር የጠቅላይ ሚኒስትሩን መታመም ለመሪዎች ጉባዔ ይናገራሉ፡፡ ለኢትዮጵያ ያረዳሉ፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ምክትሉ ስለአቶ መለስ ጤንነት ተጠይቀው ወሬውን አስተባብለው መልስ በሰጡ በወሩ አካባቢ አቶ በረከት ስምኦን በመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊነታቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣሉ፡፡ ዋናውና ግንባር ቀደሙ ጥያቄ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የጤንነት ሁኔታ ላይ የተረባረበ ነበር፡፡ ከወር በፊት ጥያቄው ቀርቦ የተሰጠውም መልስ ተነሳ፡፡ ‹‹ስታንዳርድ መልስ›› ነው ተባለ፡፡ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የገዢው ፓርቲ (የድርጅቱ) ወግና ባህል እየተጠቀሰ ይህም ከመንግሥት የአሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነት በላይ ሆኖ በዚያ ልክ ብቻ ማወቅ ያለብን ተነገረን፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውጭ እንዳሉ፣ እንደተሻላቸው፣ ዕረፍትም እንደሚያስፈልጋቸው፣ ከዚህ በተረፈ ሁሉም ደህና እንደሆነ ብቻ ሰማን፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የኢትዮጵያ መንግሥት የአቶ መለስ ዜናዊን ሞት ነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም. በይፋ ገለጠ፡፡ የአገራችን ሕዝብ በጭምጭምታ ሰምቶ የጨረሰው ቢሆንም ብሶቱን ውጦ፣ የአሁኑን ከወደፊቱ አገናዝቦና የአቶ መለስ ዜናዊን ደግ ደጉን አስተውሎ ያዘነው ማዘን ደግሞ ሌላ አስደማሚ ትምህርት የሚሰጥ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የጠብ ፖለቲካ ለዚህ ሕዝብ ምን ያህል እንደጠበበው እንድንገነዘብና ለዚህም አንገታችንን እንድንሰብር ያደረገ ሐዘን ነበር፡፡ ልቦናችንን ካልደፈንን በቀር ትምህርቱና ኃፍረቱ ከላይና ከሥር ያሉትን ፖለቲከኞች ሁሉ የሚመለከት ነበር፣ ነውም፡፡ ከ1967 ዓ.ም. አንስቶ የፍጥጫ ፖለቲካ ውስጥ ከገባን እስከ መለስ ሞት ድረስ 38 ዓመታት አደረግን፡፡ አሁን ደግሞ 42 ሆኖናል፡፡ ሕዝብ ግን ባሳየው ሐዘን በእኛ ፖለቲካ እንደማይመዘንና ከእኛ ፍጥጫ በላይ እንደሆነ አስመሰከረ፡፡ ለሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ብቻ ሳይሆን መተማመኛ ለሌለው ለራሱ ኑሮም፣ ይበልጡኑም ለራሱ ኑሮ አዘነ፡፡ የባሰ እንዳይመጣ፡፡
የማወራለት ሐዘን፣ ከአስከሬን አቀባበል እስከ ቀብር በመንግሥት ስለተቀናበረው ተራ በተራ ቤተ መንግሥት የመድረስ፣ ሠልፍ የመውጣትና በአደባባይ ሻማ የማብራት ምደባ ስለተካሄደበት፣ ፎቶ ያለበት ካናቴራ በመቶ ብር ግዙ እየተባለ ስለታዘዘበት፣ ቅን ሐዘን በፕሮፓጋንዳነት ተጐሳቁሎ ለታለ አይሰጥ ኑሮ ከዚህ በላይ ሲበዛ ተብሎ ስለተተረተበት፣ የሰሜን ኮሪያን የመሰለ የሐዘን ትርዒት አይደለም፡፡ የማወራው በየደረስኩበት የተመለከትኩትን፣ ቀደም ብሎ እህል እየሸመተ እንዴት እንሆን ይሆን እያለ ሲጨነቅ የነበረው ሰው በየቤቱና በየመንገዱ ከልቡ ይገልጽ ስለነበረው ስሜት ነው፡፡ በጣም መራር ብሶት የነበራቸው ሰዎች እንኳን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት ደንግጠው ከእሳቸው የተሻለ ሰው ከቀሪዎቹም ከተቃዋሚዎቹም ማን አለ ብለው ሲጨነቁ ተመልክተናል፡፡ ከአቶ መለስ ያልተጠበቀ ሞት በኋላ እንዴት እንሆናለን የሚል ጭንቀት የፈጠረው በሕዝብ ውስጥ ብቻ አልነበረም፡፡ የመንግሥትም የፓርቲም ሰዎች ጭንቅ ውስጥ እንደነበሩ የሚጠቁሙ ምልክቶች ነበሩ፡፡ የሞቱን ካልሆነም የሕመሙን ተደብቆ መሰንበት ወይም መክረምና ሌላ ሌላውን ትተን የሕዝቡ በጐ ምላሽ የፈጠረባቸው ግርምትና እፎይታ ብቻውን ለማሳያ ያህል በቂ ነው፡፡
የሕዝቡም ሆነ ሥልጣን ላይ ያለው ቡድን ጭንቀት አልፎ ሂያጅ ንፋስ አልነበረም፣ አይደለምም፡፡ እውነታዊ መሠረት ያለውና ዛሬም ያላበቃለት ነው፡፡ ይልቁንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እየተባባሰ መጥቶ ዛሬ የደረሰበት አደገኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ከዝምታችን፣ ከሰላማችንና ከመቻቻላችን ሥር በቁጥጥርና በፕሮፓጋንዳ እየተድበሰበሰ የቆየ ረመጥ አለ፡፡ ለሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ስለታዘነ፣ ሐዘኑ ለፕሮፓጋንዳ ሽመና ውሎ የስም ግንባታ ሐውልት ኅብረተሰቡ ህሊና ውስጥ ለማነፅ ወይም በአቶ መለስ የመሐንዲስነት ውዳሴ ውስጥ ለመቀጠል ስለተሞከረ፣ ከሰባትና ከስምንት ዓመታት ወዲህ (ያኔ እሳቸው ሲሞቱ) የመጣ ልማት የ21 ዓመት ወይም የ25 ዓመት እንዲመስል ተደርጐ ስለቀረበና ልማቱን የማፋጠን ተግባር ለራሳችን ሳይሆን፣ የሟቹ ራዕይ ከንቱ እንዳይቀር ብለን የምንሠራው እስኪመስል የተጠናገረ ቃል ኪዳን ያጐረፈ የፕሮፓጋንዳ ስጋጃ ስለተሸከሸከ ከሥር ያለው ረመጥ አልጠፋም፣ አይጠፋምም፡፡ ትናንትም ዛሬም ከጥላቻ ፖለቲካ ጋር የተወሳሰበ ብሶት እየተንተከተከ በአደባባይ ድምፁ መሰማት ከጀመረ በኋላ እንኳን፣ ይህንን ችግር እንደበፊቱ ፕሮፓጋንዳ አልብሰን ቁጥጥር አጥብቀን እንከላከለዋለን እንገላገለዋለን ማለት ዓይነት እንቅልፍ ውስጥ እንገኛለን፡፡ ድንገቴዎቹ መቼ እንደሚከሰቱና ምን ይዘው እንደሚመጡ እንደማይታወቅ የአቶ መለስ ሞት ምስክርና አፍ አውጥቶ የተናገረ፣ ሕዝቡንም አመራሩንም እንደ ፍጥርጥራቸው (ከፍ ሲል እንደተገለጸው) ያስደነገጠ ማስጠንቀቂያ ነበር፡፡
እንዲያም ሆኖ ግን መንግሥትና ገዥው ፓርቲ በፀጥታው መረቡና በፕሮፓጋንዳ ምርቱ ተውጦ እንዳለ፣ ተቃዋሚዎችም በኢትዮጵያ ችግሮች የዴሞክራሲ ኃይል መሆን ያስቻለ ብቃትና አቋም ሳያገኙ የአራተኛው ምርጫ ቀሪ ሦስት ዓመት በዋዛ ፈዛዛ አለፈ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሌሉበት የተደረገው የመጀመሪያው የአገር አቀፍ ምርጫ ውጤትም ሥልጣንና ትክክለኛነት የእኔ ብቻ ነው የሚለውን የኢሕአዴግን ‹‹ትምክህት›› በይፋ አወጀ፡፡ ገዥው ፓርቲም ከመጀመሪያው ዙር ምርጫ አንስቶ እስከ አምስተኛው ምርጫ ድረስ ለ‹‹አጋር›› ፓርቲዎች ከተመደበው ወይም ‹‹ጥብቅ›› ሆኖ ከተያዘው 45 መቀመጫ በስተቀር መቶ በመቶ አሸናፊ ሆነ፡፡ አምስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛውን የሥራ ዘመን ከመጀመሩ ገና ሁለት ወር እንኳን ሳይሞላ፣ ከፕሮፓጋንዳው ስጋጃ ሥር የሚንተከተከው ብሶትና ጥላቻ ጥፋቱንም ማሳየት ጀመረ፡፡ የአቶ መለስ ዜናዊ አራተኛ የሙት ዓመት ከፊል – ኦፊሴላዊ መታሰቢያ በሚከበርበት ሰሞን ውስጥ የሕዝቦችን መተማመንና ተፋቅሮ መኖር ሲቦረቡር የኖረው፣ ከዚያም በላይ የአጠቃላይ መተላለቅና መበታተን ማቀጣጠያ ሆኖ ፕሮፓጋንዳ ለብሶ የቆየው ከጥላቻ ጋር የተለወሰው ብሶት፣ በአብዛኛው የኢትዮጵያ አካባቢዎች መልከ ጥፉ ገጽታውን እያስመዘገበ ነው፡፡ ተቃውሞው ኦሊምፒክ አደባባይ ላይ እስኪመሰከር ድረስ ታይቶ የማይታወቅ ሪከርድ አስመዝግቧል፡፡
የዚህ ሁሉ መነሻ ከፕሮፓጋንዳ ስጋጃው ሥር ከፀጥታ መረቡ መጋረጃ በስተጀርባ የሚንተከተከው ችግራችን ነው፡፡ ይኼ ምንድነው? ዋና ዋናዎቹን እናመላክት፡፡
በቤት ኪራይ፣ በቀለብ፣ በትራንስፖርት፣ በጤና፣ ወዘተ፣ ወዘተ. ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ዋጋዎች የሚያረጁበትና ሰው ምኑን ከምኑ እያደረገ ነው የሚኖረው ያሰኘው የኑሮ ውድነት አገሪቱን የወጠረ አንድ ዓብይ የብሶት ምንጭ ነው፡፡ ስንዴና ዘይት በሸማቾች ሱቆች በማከፋፈል፣ ዘርፈ ብዙ ውድነትን ለማስታገስ ‹‹መሞከር›› እና የየወሩን የዋጋ አጨማመር ካለፈ ዓመት ጋር እያነፃፀሩ ‹‹ንረት ቀነሰ›› እያሉ መለፈፍ፣ በዚያ ልፊፋም ውስጥ ሙልጭ ያለ ውሸትን እውነት አስመስሎ ማቅረብ በሚብላላ፣ በሚነድና በሚቃጠል እሳት ላይ ተጋድሞ ከመዘባነን አይለይም፡፡ ብሶቱ እንዳይወጣ የቱንም ያህል ፕሮፓጋንዳና አፈና ቢካሄድ የኑሮ ውድነቱ እየጨመረ መሄድ የብሶቱንም ክረት ስለሚያሳድግ ሄዶ ሄዶ አፈና የሚዘነጠልበት ቀን መምጣቱ አይቀርም፡፡ እየሆነ ያለውም ይኸው ነው፡፡ ከዚያ በፊትና አሁንም ውድነትን የምር የሚያቃልል መፍትሔ ማበጀት ብልህነት ነበር፡፡ አሁንም ነው፡፡ ምንጩ ብዙው የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት አዙሪቱ እያሽከረከረ ማዳፋቱን ቀጥሎ ሳለ የመንግሥት አውታሩ የቀበጠ የፀጥታና የፕሮፓጋንዳ ወጪ ጭምር ገበያውን የሚተናነቅ አንድ ችግር መሆኑ ሳያንስ፣ ሚዲያው ኑሮ ውድነት/ንረት ቀነሰ እያለ ላታላችሁ ሲል ደግሞ የበለጠ ያማል፡፡
ከመንግሥት ተቀጽላነት የወጣ ነፃ የሕዝብ እንቅስቃሴን በቀሰፈ አጠቃላይ የመብቶች አፈና ውስጥ ከሌሎች የነፃነት ብሶቶች ይበልጥ አገራችን ውስጥ ቀድሞም፣ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሞት አካባቢም፣ አሁንም ፊት ለፊት የሚወራጨው በሃይማኖቶች ውስጥ ባለው የመንግሥት ጣልቃ ገብነትና ጥልቅ ባይነት የተመረረው ብሶት ነው፡፡ ይህንን ብሶት በተለመደው የፀጥታ አፈናና ‹‹ከጥያቄዎች በስተጀርባ ፖለቲካዊ ዓላማ አለ››፣ ‹‹ሃይማኖትን ሽፋን አድርጐ አመፅ ለማነሳሳት ነው›› ወይም ‹‹የአክራሪነት አደገኛ እንቅስቃሴ ነው›› እያሉ ስም በመለጠፍና በማሰር መታገል፣ በኦርቶዶክስ ክርስትናም ሆነ በእስልምና የእምነት መሪዎች አመራረጥም ውስጥ እጅን በቀጥታም ሆነ በእጅ አዙር ሰዶ አቦካለሁ ቢባል ውጤቱ መመለሻ ላይኖረው ይችላል፡፡ ኃላፊነት የሚሰማውና አስተዋይ አዕምሮ ያለው አንድ የሆነ ግጭትና ግድያ ምን ያህል የጣጣ ሰበብ ሊሆን እንደሚችል፣ የንድ ብሶት ፍንዳታ ከሌሎች ብሶችች ጋር ተላልሶ ሊያጥለቀልቅ እንደሚችል መመልከት አለበት፡፡
እኔ የፈቀድኩልህን እምነት፣ አለባበስና አኗኗር ካልተከተልክ ወዮልህ የሚል ሃይማኖታዊ አፋኝነት ኅብረተሰብን እንዳያብጥ መከታተል ኃላፊነት ነው፡፡ ግዴታም ነው፡፡ ሃይማኖትን ያነገበ አፋኝነት አገራችን ውስጥ ገብቶ ከዚህ በፊት ጥፋት እንደደረሰም ይታወቃል፡፡ ወደፊትም ምዕራባዊ ጣልቃ ገብነትም ሆነ ውስጣዊ ኋላቀርነትና መናጨት የሚፈጥረውን አለመረጋጋት መራቢያ እያደረገ መፈታተኑ አይቀርም፡፡ ለዚህ ማገጃ ቢሆነን ብሎ አፈናን መጠቀም የ‹‹አክራሪነት›› ረዳት ከመሆን አይተናነስም፡፡ የሃይማኖት ሰላምን ለማረጋገጥም ሆነ ወደ መካከለኛው ዘመን ሊመልስ የሚሞክር ‹‹አክራሪነት››ን መጠጊያ ለማሳጣት መድኃኒቱ ሃይማኖቶች መንግሥት የጠላውን እንዲያወግዙ፣ የወደደውን እንዲያወድሱና እንዲያሞግሱ (አጨብጫቢ እንዲሆኑ) ከማድረግ መራቅና አደረጃጀትና እንቅስቃሴያቸውን ከመቆጣጠርና ከመዘወር መቆጠብ፣ የእምነቶችን እኩልነትና መከባበር በተግባር ማረጋገጥ (እንደ ኋላቀር እየታዩ ‹‹ባህላዊ እምነት›› ለሚባሉት ጭምር) ነው፡፡ ብዙ ሃይማኖቶች ባሉበት አገር ይቅርና አንድ ሃይማኖት ባለበት አገርም ቢሆን፣ መንግሥትና ሃይማኖት ተጋብተው ንዑስና ክፍልፋይ እምነቶች በእኩልነት አስተናግደው የማያውቁበትን የትናንትናም ሆነ የዛሬውን ታሪካዊ ሀቅ በማኅበራዊ ግንዛቤነት ፅኑ መሠረት ማስያዝ ነው፡፡ ፀረ ምዕራብ አሸባሪነት በአንድ በኩል፣ ምዕራባዊ ጣልቃ ገብነትና እስልምናን እንደ አደጋ የመመልከት አባዜ በሌላ በኩል እየተነካከሱ አንዳቸው ሌላቸውን በሚያባብሱበት ዓለም ውስጥ እጅግ ብርቅ የሆነው የአገራችን የሃይማኖት ሰላም መዝለቅ የሚችለው በተገለጸው ዓይነት ዴሞክራሲያዊ አያያዝ ነው፡፡ ከአፈና ወጥቶ እዚህ ዴሞክራሲያዊ አያያዝ ውስጥ አለመግባት የአገሪቷ ሰላም እንዲቆስል መተው ይሆናል፡፡
በራሳቸው ለማጥለቅለቅ አቅም የሌላቸው የሚመስሉ የግርግር አጋጣሚና አራጋቢ ካገኙ ግን በቀላሉ የማይፈለግ ውስብስብ ሊፈጥሩና አቅጣጫ ሊያስቱ የሚችሉ ችግሮችም አሉብን፡፡ ማኅበራዊ ተዛምዶንና አናሳ ጉድኝትን ከልማት አቅም ሥርጭት፣ ተግባብቶ ከመተዳደርና ከማደግ ዕድል ጋር ያገናዘበ፣ ሕዝብና ምሁራን በደንብ የመከሩበትና በሒደትም የሚቃና የአስተዳደር አከላለል ተፈጥሮ ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ የተቃውሞ ምንጭና ለገዥዎችም ‹‹እኔ ሥልጣን ላይ ከሌለሁ…›› እያሉ ማስፈራሪያ የሆኑ እዚህ ወይም እዚያኛው ክልል የተካተቱ ሥፍራዎች መፋለሚያ ባልሆኑ ነበር፡፡
ከተዛባ አገዛዝ የበቀሉ ክልል ገብና ክልል ዘለል ተገፋን፣ ተበለጥን የሚሉ የብሔር/የጐሳ ቅሬታዎች፣ ‹‹መጤ›› እና ‹‹ነባር›› ወይም በቀል የሚሉ ግልብ ፍረጃዎች አሉ፡፡ አድልኦዎቹና ከፋፋይ አመለካከቶቹ እስካልተቃኑ ድረስም ቅሬታዎቹ የውስጥ ለውስጥ ኑሮአቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ሲንተከተኩ ቆይተውም በራሳቸው መንገድ መኖራቸውን ያስታውቃሉ፡፡ የረሱንን ሰዎች አልረሳናቸውም ይላሉ፡፡ የወሰንና የመሬት ይዞታን፣ ‹‹የይዞታ ካርታን›› የተመለከቱ ውዝግቦች ከሰፋፊና ከሰፋሪ መሬት ኪራይ ጋር የተያያዙ ቅሬታዎችም ተጠምዝዘው ከብሔር/ጐሳ ነክ ቅያሜዎች ጋር ሊቀላቀሉና የግጭት ማሳበቢያና መክፈቻ ለመሆን የተጋለጡ፣ ሲፈነዳም የታዩ ናቸው፡፡
ከዚህ እልፍ ሲልም ዘመናቸው ያለፈና በፖለቲካ የመርታት አቅማቸው የከሰረ ቢሆንም የመገንጠል ዓላማ ያላቸው እንቅስቃሴዎችም አልታጡም፡፡ አሉ፡፡ ለመገንጠል ትግል መክሰር ከዛሬዋ ኤርትራና ከኦነግ ታሪክ በላይ ተጨማሪ ማሳያ አያስፈልግም ነበር፡፡ ከኦነግና ከአሮጌ መንገዱ መንኮታኮት በኋላ ተመሰቃቅላ የመከራና የሥርዓት አልባነት ምርጥ ምሳሌ የነበረችው የሶማሊያ ልምድ የዓመታት ትምህርት እየሰጡም ሳለ፣ በነፃነት ስም በጠመንጃና በፈንጂ የኦጋዴንን ሰላም የሚያምስ ቡድን ማኅበራዊ መደበቂያ ማግኘት አልነበረበትም፡፡ ያልነበረበት እንዲኖር እስትንፋስ ሲሰጥ የቆየው አገዛዙ ነው፡፡ የንግግር መፍትሔን፣ የተቃውሞ ነፃ እንቅስቃሴንና ነፃ የምርጫ ውድድርን በመሰነግ፡፡ ከዚህ ቡድን ጋር የሚደረገውም ድርድር ዘላቂ የሰላም ውጤት የሚያስገኘው ስነጋው ከተፈታ ብቻ ነው፡፡
ለቁርሾና ለጠብ አራጋቢዎች የተመቹ ታሪክ መሳይ አስተሳሰቦችም የበኩላቸውን ሥራ ህሊና ላይ ይሠራሉ፡፡ ለአብነት የሚነሱ ተጠቃሽ ማስረጃዎች አንዱ ሃይማኖታዊው ሲሆን፣ ሌላው ብሔር/ብሔረሰባዊ ነው፡፡ እነዚህ አስተሳሰቦች ኅብረተሰብ ውስጥ መርዝ የማበጀት አቅም ላይኖራቸው የሚችለው ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ አስተዳደር እየተሟላ መምጣት ከቻለና አብሮም የሚያጋልጣቸው የታሪክ ማረሚያ ከኖረ ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ደም ግባት ለመስጠትም ሆነ የነገሥታትን ዝና ለመካብ ሲባል ቆርጦ ቅጠላ የተደረገበት የታሪክ ጽሑፍ ችግር ኢትዮጵያ የለባትም፡፡ ዘመናዊ በመሰለ፣ ግን ከፖለቲካ ፍላጐት ተመዝዞ በተጻፈ ድርሰታዊ ታሪክም እስከ ዛሬ የተወላገደው ታሪካችን አያንሰንም፡፡ በይለይለት ዕይታና በጮርቃ ጀብደኝነት በደሎችን ከዘመናቸው አውጥተው፣ ስለመዘዛቸው ሳይጨነቁ በዛሬ ዓይን እየፈረዱና እያግለበለቡ ደም ያንተከተኩና ግጭት የጠሩ ትንታኔዎች ይበቁናል፡፡ ዛሬ የሚያስፈልጉን የታሪክ ትንታኔዎች የታሪክ ክንዋኔዎችን በዘመናቸው ባህርይና ውስንነት ውስጥ የሚረዱና ዛሬ ያሉንን አገራዊና አካባቢያዊ የህልውና ጉዳዮችን ላለማድማት የሚጠነቀቅ አስተዋይነትን ከሀቀኛነት ጋር ያዛመዱ ናቸው፡፡ በዚህ በኩል ክፍተት የዘጋ የታሪክ ሙያተኞች እንቅስቃሴ አለ ከማለት ይልቅ፣ ሙያተኞቹ ለጠበኛ የፖለቲካ ፍጥጫ አንገት ደፍተዋል ቢባል እውነት ይሆናል፡፡ ፍጥጫው ቢናጋና ቢፈርስ ዘራፍ ባይ ሳይኖር በሰከነ ስሜት ታሪካችንን ለመመርመርና ለማደራጀት ምን ያህል እንደሚቀልና መነቃቃት እንደሚኖር ማሰብ ነው፡፡
በአጠቃላይ አሁን ወደምንገኝበት አደገኛ የገሞራ መሰናዶ ውስጥ እያሳሳቀና እያስጠጋ ያቀረበን አንድ ቀን ለይቶለት ለሚፈነዳ ውስብስብ ችግር፣ አገሪቷንና ሕዝቦቿን እያጋለጠ ያመጣት ከላይ የተጠቀሱት ዓይነት ችግሮችን ከአፈናና ከፕሮፓጋንዳ ምንጣፍ ሥር አስተጃጅሎ የማኖር ፖሊሲያችን ነው፡፡
አቶ መለስ በነበሩበት ወቅትም ሆነ አሁን ዛሬ የሚያስተማምን የፖለቲካ ሰላም እንዳልተፈጠረ መካድ ጥቅም የለውም፡፡ ሕዝብን በጥቅሉ የረታ ፓርቲ በሌለበት የጥላቻ ፖለቲካ ከሁለት በኩል የትኛውንም ድንጋይ አንስቶ የሚወረወር በሆነበት እውነት ላይ ምንም ዓይነት ድንገቴ ነውጥ በጭራሽ አይጓጓለትም፡፡ የድንገቴው የውጤት ዕድል እንደምንም ወደ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ከመዞር አንስቶ የታጠቀውን መንግሥታዊ ኃይል በገዥና በአማፂ ወገን/ወገኖች እየተቆራቆሱ ጦሱ ለአገር የሚተርፍና መድረሻው የማይታወቅ አውዳሚ ውጊያ ውስጥ እስከመግባት የሰፋ ነው፡፡
ችግሮች መዘዝ ሳያመጡ እንዲመክኑ አንድ ‹‹የፖለቲካ መሐንዲስ›› ላይ ብቻ ላለመጠምጠም፣ እሱ አንድ ነገር ቢደርስበትና የሚገዛው ፓርቲ ቢዝረከረክ መሄጃ እንዳይጠፋን፣ ብሶቶች እየከረሙ የማይንጡበትና አክራሪነት-አሸባሪነት መለምለሚያ አፈርና ውኃ የማያገኝበት ምዕራፍ ውስጥ ለመግባትና ካሮጌ የአገዛዝና የፖለቲካ ባህል ለመላቀቅ፣ የመጀመሪያው ጥርጊያ መንገድ ከየፖለቲካ ጎራዎች አጥር ወጥቶ ጠበኛነትን ማፍረስ ነው፡፡
ከጠብ ፖለቲካ በመውጣት ከተቃዋሚ በላይ ተጠቃሚው ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ነው፡፡ በመዘርጠጥ ጭንቅ ተጠምዶ ሁሉን ነገር ሚስጥራዊ ከማድረግና የተቃውሞ ንፋስ ከማሳደድ አዙሪት የመላቀቅ ዕድል ይከፈትለታል፡፡ እንደ ዳንኪራ እየተደረሰ የሚከናወን ክስና ፍርድ ማካሄድንና የአፈና እውነታን ለመደበቅ የፕሮፓጋንዳ ስጋጃ እየሸመኑ ሲያነጥፉ የመዋል ባህልን ሙጥኝ የሚያስዝ ምክንያት ይቋረጥለታል፡፡ ሁሉን ነገር (ሐዘንን ጨምሮ) በድርጅታዊ መንገድ ከማቀናበር ይድናል፡፡ ከሕዝብ ነፃ እንቅስቃሴ ጋርም ከልብ ለመገናኘት በር ይከፈትለታል፡፡ እንዳይፈነዳ የሚያስፈራራ እምቅ ብሶት አይኖርምና ከማድባትና ከመንጫጫት ይልቅ ይህንን እንሥራ እያሉ በሐሳብና በተግባር መተጋገዙ ያይላል፡፡ የዚህ ዓይነት የእርቅ ፖለቲከኛነትና የእርቅ መንግሥትነት ሁኔታ ውስጥ መግባት፣ ለአገሪቱ የዴሞክራሲና የልማት እመርታ ዓብይ ትርጉም ያለው ነው፡፡
የእርቅ ፖለቲከኝነትንና የእርቅ መንግሥትነትን ጥያቄ ሥልጣን በአቋራጭ የማግኛ ዘዴ ወይም የሥልጣን ተራ እኛም ደርሶን እንቅመስ ማለት አድርጎ ገዥው ፓርቲ ሲወስደው ቆይቷል፡፡ በተቃዋሚዎችም በኩል የሽግግር መንግሥት ወይም የተውጣጣ መንግሥት ካልተመሠረተ በቀር የተሻለ ለውጥ እንደማይመጣ አድርገው የሚያስቡ፣ ከዚያም አልፎ የሽግግር መንግሥትን በሥልጣን ማቋረጫነት ለመጠቀም የሚፈልጉ እንዳሉ ዕውቅ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ለማንኛውም ተዘጋጅተን እንጠብቅ በሚል ዓላማ ተብሎ የሽግግር ምክር ቤት እንደተቋቋመ ሰምተን ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አንገብጋቢ ጉዳይ ክፍተት ወይም ትርምስ ከተፈጠረ ሥልጣን ለመያዝ ተዘጋጅቶ መጠበቅ ሳይሆን፣ ትርምስ መንገድ እንዳያገኝ ያሉትና መጪዎቹም ፓርቲዎች የተቻቻለ ዴሞክራሲያዊ ሕይወት ውስጥ እንዲገቡ፣ የመወነጃጀልና የጠላትነት ፖለቲካዊ ግንቡ ይናድ ነው፡፡ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በአመፅ በማፍረስ››፣ በ‹‹ሽብርተኛነት›› ወይም ‹‹ሽብርተኛ በመርዳት›› ስም የተካሄዱ ውንጀላዎች፣ ፍርዶችና እስራቶች ሁሉ ተነስተው በኢትዮጵያ ልማትና ዴሞክራሲ ግንባታ ውስጥ የተሻለ ሕይወትን የሚያስቡ ሁሉ መቀራረብ፣ መነጋገርና ድርሻ ማዋጣት የሚችሉበት በር ይከፈት፡፡ ወደ ውይይት ከመምጣትም በላይ ላሉት ሕጋዊ ፓርቲዎችም ሆነ ተንጠባጥበው ወደፊት ለሚመጡ ሰላም ፈላጊዎች ሁሉ ያለማሳበቢያ ክፍት የሆነና ሕይወት ያለው የምክክር ሸንጎ ይደራጅ ነው፡፡
‹‹የሽግግር መንግሥት ይቋቋም ወይም ሥልጣን አጋሩን›› የሚል ጥያቄ (አሁን ባለው የገዥና የተቃዋሚ የፖለቲካ ሚዛን ሁኔታና በሕግም ጭምር) የማይጨበጥና ያንኑ የኢሕአዴግን አሰልቺ ማሳበቢያ የሚጠቅም፣ እንዲያውም ዛሬ ዓለም ትኩረት ከሰጠው ሕገ መንግሥታዊ የሥልጣን ቅብብል ጎን ሆኖ ለማምታታት የተመቸ ነው፡፡ ይህንን ያስተዋለና በቋፍ ያለውን የአገሪቱ ብሶተኛነት የጠየቅነው ካልተሟላ የራሱ ጉዳይ ከሚል ድርቅና መውጣትን የሚፈልግ መሆኑን የተገነዘበ፣ እርቃዊ ሁኔታው እየሰመረ ከሄደ ሥልጣን መቋደስም ቢሆን የፖለቲካ ደመና ለውጡ ከሚያመጣቸው መልካም ነገሮች ውስጥ በጣም ትንሹ ነገር እንደሆነ የገባው የፖለቲካ ሰውም የሚያነጣጥረው፣ ከሁሉ በፊት ጠብ ይፍረስ በሚል ዒላማ ላይ ነው፡፡ ኢሕአዴግ የሽግግርን መፍትሔ ካልተቀበለ ጉድ ይፈላበታል የሚል ዓይነት ዛቻ የሚያሰሙም ዛቻና ጥያቄያቸውን በተግባራዊነት እርባናው ቢመዝኑት ይመከራል፡፡
በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥትም ለራሱና ለአገሪቱ ብሎ ጠብ ለማፍረስ፣ ሲሆን በራሱ ተነሳሽነት፣ ካልሆነም ልመና ቀረሽ ሲጠየቅ ያደርገው እንደነበረ በትዕቢት መሳለቁንና እንዳይታማ ያህል የይስሙላ ፈቃደኝነት አሳይቶ የመግፋት ዘዴውን ትቶ የምር ተግባር ውስጥ መግባት ይጠበቅበታል፡፡ ‹‹ዛሬ 80 ሚሊዮን ሕዝብ መለስን እንደተካው አይተናል›› ያለና በኢትዮጵያ ሕዝብ የተገረመ መንግሥት የተናገረውን የሚያምንበት ከሆነ፣ ወደኋላ ለማለት ሰበብ አይኖረውም፡፡
በተቃዋሚዎችም በኩል ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እርቅ ሲጠየቅ ብናይም (በተለይ መድረክ በተደጋጋሚ ለመነጋገር ጠይቆ ሰሚ እንዳጣ ይታወቃል)፣ ብዬ ነበር ለማለት የሚሆን መግለጫ ከመወርወር ያለፈ ነገር አልታየም፡፡ ዛሬም ከመግለጫ ባለፈ እርቅ ፈላጊ ተቃዋሚዎች እርቅና መቀራረብን አመለካከታቸውና እንቅስቃሴያቸው እስካላደረጉትና እንቅስቃሴያቸው የመበራከት ክብደት ካልፈጠረ ዋጋ የለውም፡፡ ስለሰላም መጨነቅ ተንበርካኪነት የሚመስላቸውና ከአቋሜ ወይ ፈንክች የሚሉም ወገኖች፣ ‹‹ከፀረ ሰላም ጋር ድርድር የለም›› የሚል ሰበበኛነትን በመጥቀም ረገድ ጠላቴ ለምለው መንግሥት የምርጥ ወዳጅ አገልግሎት እየሰጠሁ ይሆን ብለው ራሳቸውን ቢጠይቁ መልካም ነው፡፡ የዴሞክራሲ ትግሉ ኃጢያት ከመከመርና ማንም የሚያውቀውን (መለስ ራሰ-በራ ነበር ከማለት የማይሻል) ነገር ከመደጋገም የዘለለ የአስተሳሰብ ፍሬያማነትን (ሴንስቢሊቲ) ይፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ የጊዜው ፖለቲካ ላይ አንዳችም አሻራ ማሳረፍ የማይችሉትን የደርግ ባለሥልጣናትን ለማስፈታት የባከነው የሃይማኖት መሪዎች እርቅና ምሕረት ጠያቂነትም አገራዊ ፋይዳ ያለው ሚና መጫወት የሚችለው አሁን ነው፡፡
ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚዎች ሊያጤኑት የሚገባ አንድ ሀቅ አለ፡፡ ዛሬ የምንገኝበት ወቅት ከ1997 ዓ.ም. በጣም የተለየና የባሰ ነው፡፡ በ1997 ዓ.ም. በተቃዋሚው በኩል የነበረው የቆሙበትን መሬት በውል ያላስተዋለ፣ በአንድ የምርጫ ጀንበር ሥልጣን የመላፍ ችኩልነትና የገዥውን ክፍል ጥምብ እርኩስ የማውጣት አባዜ ከነንቀቱና ስላቁ፣ ገዥው ክፍል ከሥልጣን ወርዶ በመፈጥፈጥ ፍርኃት ደንብሮ፣ ለአጭር ጊዜ ያየናትን የዴሞክራሲ ሁኔታ ሥር ሳትይዝ እንዲያጠፋት ማመካኛ እንደሆነ የሚታወስ ነው፡፡
ዛሬ ከአንድ ፓርቲ ገዥነት መዳፍ የምትገኝ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ምን ያህል ተሰባሪ ሸክላ እንደሆነችና ምን ያህል እንክብካቤ እንደምትሻ ትምህርት ተገኝቷል፡፡ የዴሞክራሲ መብትን መጠቀምና ሳያስመነትፉ የማቆየት ነገርም መንገድ እየወጡ ከመንጫጫት በላይ አስተዋይነትንና ዘዴኛነትን የሚጠይቅ እንደሆነ፣ ተቀራርቦ ለመነጋገር ያልፈቀደ ግትር አቋም የቱን ያህል መቀመቅ እንደሚከት የሰሜን አፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ ትኩስ ልምድ ትምህርት ይሰጣል፡፡ በአካባቢያቸው ተፅዕኖ ፈጣሪ የነበሩት ሊቢያና ሶሪያ በይፋና በሥውር ጣልቃ ገብነት እገዛ በተካሄደ/እየተካሄደ ባለ የሞት ሽረት ጦርነት እንዳይሆኑ ሆነዋል፡፡ ሊቢያ ከጋዳፊ ጋር የነበረባትን ጦርነት ብትጨርስም ፍርስራሽ እንደታቀፈች ልዩ ልዩ የታጠቁ ቡድኖችና ንዑስ ፍላጎቶች ገና ይፍተለተሉባታል፡፡ ሶሪያ ውስጥ ከጉድም በላይ ጉድ እየተመሰከረ ነው፡፡ የበርማ ገዥዎችና ተቃዋሚዎች እየሸሹት ያሉት ይህንን የመንኮታኮት መንገድ ነው፡፡ የመንኮታኮቱ አዙሪት በኢትዮጵያ ዕውን እንዳይሆን መፍትሔው ገዥም ሆነ ተቃዋሚዎች በጊዜ ከግትርነት ወጥተው መደራደር መቻላቸው ነው፡፡ ኪሳራው ከበዛ ትርምሳም የመንግሥት ለውጥ ይልቅ በእጅ ባለ ልማት ላይ ፖለቲካዊ እርቅ የሚያመጣቸውን በጎ ነገሮች መጨመር የብዙዎች ኢትዮጵያውያን የዛሬ ፍላጎት መሆኑን ሁሉም ወገን ያጢነው፡፡ ከዚህ አኳያ ከአራት ዓመት በፊት የአቶ መለስ ሞት ሲነገረው ገዥውንም ተቃዋሚውንም ያስገረመው የኢትዮጵያ ሕዝብ በእርቅ ሁኔታ ውስጥ የነፃ እንቅስቃሴ ዕድል ቢያገኝ ደግሞ ከግርምትም ግርምት እንደሚፈጥር አያጠራጥርም፡፡
ቅኝ ተገዥነትን እምቢ ያለና ያሳፈረ ታሪክ ያለው ሕዝብ፣ ከፋሽስት ጣሊያን ጋር ባካሄደው የአርበኝነት ትግል ጊዜ እንኳ ግፍ ያዘንብበት ለነበረ የፋሽስት ምርኮኛ ፍርድ ያለመንፈግ የትግል ቅርስ ለነበረው ሕዝብ፣ በታሪኩ መሪውን ቀብሮ የሚያውቅ የአቶ መለስ ዜናዊን መልካም ጎን አይቶ በደግ የመሸኘት ጨዋነት ላስተማረ ሕዝበ የጠብ ሸለቆን ተሻግሮ ይችን ታህል የፖለቲካ ሰላም እንዲጎናፀፍ ዕድል መስጠት እጅግ ቢያንሰው እንጂ አይበዛበትም፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡