Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊይቅርታ

ይቅርታ

ቀን:

ጉዳዩ ከተፈጸመ አራት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በአንድ መንደር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በጋራ ግቢ አጠቃቀም፣ በጥበቃና በተለያዩ የጋራ ጉዳዮች ላይ ሙግት ይገባሉ፡፡ አንዱ ወገን የእኔ አካሄድ ትክክል ነው ሲል፣ ሌላው የእናተ ትክክል አይደለም የኛ ትክክል ነው ወደሚል ውዝግብ ይገባል፡፡ በዚህም ቀድሞ በሰላም ይኖሩ የነበሩ ጎረቤታሞች ይበጣበጣሉ፡፡ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ጉዳያቸውን እየያዙ በየጎራቸው ወደ ወረዳው ባለሥልጣናት ያመራሉ፡፡ በሚጣሉበት የግቢ አስተዳደርና በጋራ መጠቀሚያዎች ዙሪያ ወረዳው የመፍትሔ ሐሳብ ቢያስቀምጥም፣ ጎረቤታሞቹ ግን መግባባት አልቻሉም፡፡ መኪና በሚቆምበት ሥፍራ፣ የጥበቃ ዓይን አላማረኝም በሚሉና በሌሎችም በየጊዜው ይነታረካሉ፡፡ ለፀብ ተጋብዘውም ፖሊሲ ጣቢያ የደረሱበት ጊዜ ነበር፡፡ የሠፈሩ ነዋሪዎች አካሄድ ያላማረው ወረዳው፣ ሁለቱንም ወገኖች ጠርቶ ፀባቸውን እንዲያቆሙና ይቅርታ እንዲባባሉ ያደርጋል፡፡ ከዚህ ቀደም የሠፈር ሽማግሌዎች በይቅርታ ሰላም ለማውረድ የሞከሩት ጥረት ከሽፎ የነበረ ቢሆንም፣ የወረዳው ለጊዜው ተሳክቶ ነበር፡፡ ሆኖም ጎረቤታሞቹ ያለፈውን መተው አልቻሉም፡፡ ቂማቸውንም ትከሻ ለትከሻ አሳስሞና ይቅር አባብሎ የሸኛቸውን ወረዳ ገለል አድርገው፣ አንዱ አንዱን ጠልፎ የሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ይጠባበቁ ጀመር፡፡

በየጊዜው መካሰስ ሆነ፡፡ ጉዳዩ ክፍለ ከተማ ደርሶ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እስከተዘጋበት ድረስ ሰዎቹ፣ ክፉ የተነጋገሩበት ለድብድብ የተጋበዙበት ጊዜም ነበር፡፡ ባለመግባባት ከተከፋፈሉት ጎረቤታሞች በአንዱ ጎራ የሚገኙት እንደሚሉት፣ ወረዳው ይቅርታ ሲያባብላቸው ነገሩ ዳግም ለጭቅጭቅ እንደማይዳርግ፣ በየጊዜው በረባ ባልረባ ከሚነታረኩና የሥራ ጊዜያቸውን ፖሊስ ጣቢያ በመመላለስ ከሚያባክኑም ይቅርታው መፍትሔ እንደሚሰጣቸው አምነው ነበር፡፡ ሆኖም እንዳሰቡት አልሆነም፡፡ ‹‹ይቅርታው አፍ ላይ ቀርቷል፤›› የሚሉት እኝህ ሰው፣ በሳቸው ጎራና በሌሎቹ ጎራ ያሉት ሰዎች ተቀያይመውና ተራርቀው እንደቀሩ በጋራ ግቢ ውስጥ የጋራ መጠቀሚያ ቢጋሩም፣ ሰላምታ እንኳን እንደማይለዋወጡ ይናገራሉ፡፡

ይቅርታ የተባባሉ ሰዎች ይቅር የተባባሉበትን ጉዳይ ዳግም ሳያነሱ፣ ከችግሩ ትምህርት ወስደውና ታርመው ቢኖሩ በመካከላቸው ሰላም የሚሰፍን ቢሆንም፣ በይቅርታ ያለፏቸውን ጉዳዮች ዳግሞ እያነሱ የሚናቆሩ፣ ሰላማቸውን የሚያደፈርሱም አይጠፉም፡፡

- Advertisement -

ትዳሯን ከፈታች ስምንት ዓመታትን ያስቆጠረችው አልማዝ (ስሟ ተቀይሯል)፣ ይቅርታን ከልብ መቀበልና ይቅርታ ማድረግ ትዳሯን እንዳላዳነ ትናገራለች፡፡ አልማዝ መጀመርያ ከባለቤቷ መቀያየም የጀመረችው ፍች ከመፈጸሟ አራት ዓመት በፊት ነው፡፡ ባለቤቷ ሊያምናት አልቻለም፡፡ እሷም በፊናዋ ባለቤቷን አታምነውም፡፡ ባለመተማመን በቤት ውስጥ የተጀመረው ጭቅጭቅ ወደ ፀብ አምርቶ ቤቷን ጥላ ትወጣለች፡፡ የጎረቤት ሽማግሌዎች ተሰባስበው ባለትዳሮቹን ለማስታረቅ ወዲህ ወዲያ ማለት ጅመሩ፡፡ በተለይ ቤት ውስጥ ያሉት ሁለት ልጆች እየተጎዱ መሆናቸውን ያዩት ሽማግሌዎች፣ ለልጆቻቸው ሲሉ ይቅር እንዲባባሉ ባለትዳሮችን ማግባባት ጀመሩ፡፡ የማደራደሩ ሁኔታ ወር ፈጀ፡፡ በኋላም አልማዝ ወደቤቷ ተመለሰች፡፡ እሷ እንደምትለው፣ ቤቷ ባትመለስ ይሻላት ነበር፡፡ በወጣች በገባች ቁጥር ቤት ውስጥ ንትርክ ሆነ፡፡ ይቅርታ የተባባሉበትን ጉዳይ እያነሱ እርስ በርስ መነታረኩ በዛ፡፡ ‹‹ከይቅርታ በኋላ ያሳለፍኩት ጊዜ ከባድ ነበር፡፡ እሱም ያለፈ ታሪክ ሲያነሳ እኔም የሱን እያነሳሁ መጨቃጨቅ ሆነ፡፡ ሰላም አልነበረንም፤›› የምትለው አልማዝ፣ እንደዚህ ዓይነቱን ኑሮ ባለመምረጣቸው ሁለቱም በፍቺ ተስማምተው ፍቺ መፈጸማቸውን፣ ልጆቿን እሷ ይዛ እሱ ተቆራጭ እያደረገ እንደሚኖሩ ገልጻለች፡፡

ይቅርታ መጠየቅና ማድረግ በአገራችን ‹‹የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳ›› እንደሚባለው ተፈጽሞ የነበረው ጉዳይ ፍፁም ይረሳል ማለት ባይሆንም በሰዎች መካከል ከይቅርታ በኋላ የመጎዳዳት ሥጋት ይረግባል፣ እፎይታ ያሳድራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም ይቅርታ መጠየቅና ይቅር ማለት ብቀላ እንዳይኖርና ነገሮችን በአዎንታዊ መልኩ ለማየት ይረዳል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ግን በይቅርታ ማግሥት የብቀላ ሰለባ የሆኑ አሉ፡፡

በጅማ ነዋሪ የሆኑ እናት ከሁለት ዓመት በፊት በአካባቢያቸው የተፈጸመውን እንዲህ ያስታውሱታል፡፡

ልጅቷን የሚያውቋት እሳቸው ከሚሠሩበት መሥሪያ ቤት ስትመላለስ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ግን ትጠፋለች፡፡ ምን ሆና ነው ብለው ሲጠይቁ መሞቷን ይሰማሉ፡፡ ወይዘሮዋ የሞተችው በባለቤቷ ጥቃት ተፈጽሞባት ሲሆን የሞተችውም፣ ባለቤቷ በአማላጅ የላከባትን ይቅርታ ተቀብላ ቤቷ በገባችበት ዕለት ነበር፡፡

ከባለቤቷ ጋር መስማማት ባለመቻሏ በተደጋጋሚ ከቤት ትወጣ እንደነበር፣ በተደጋጋሚም ይቅርታ እየጠየቃት ቤት ተመልሳ እንደምታውቅ፣ በኋላ ላይ አምርራ ቤተሰቦቿ ጋር መቀመጧንና ባለቤቷ በላካቸው እምቢ በማትላቸው ሽማግሌ ምክንያት ይቅርታውን ተቀብላ ቤቷ መመለሷን፣ በተመለሰችበት ዕለት ማታም መገደሏን መስማታቸውን ነግረውናል፡፡ ገዳዩ ጠፍቶ የነበረ ቢሆንም፣ በኋላ መያዙንና በኢቢሲ ፖሊስ ፕሮግራም ላይ ጉዳዩ መቅረቡንም ያስታውሳሉ፡፡

ይቅርታ ባይ ደጋግሞ ሲመጣ ይቅርታ አድራጊው እስከመቼ በእንቢታው ሊፀና ይችላል? ይቅርታስ ስንቴ ነው? የት ጋር መቆም አለበት? የሚሉት እንደሰዉ አመለካከት፣ ባህሪ፣ እምነትና በጉዳዩ ዓይነትና ክብደት የሚወሰንም ቢሆንም፣ ብዙ ጊዜ ሰዎችን ይቅርታ ለማባባል ሽምግልና የተቀመጡት አቶ ገብረማርያም ለማ፣ በሁለት ሰዎች መካከል ካንድ ጊዜ በላይ ይቅር መባባል አስፈላጊ እንዳልሆነ ያምናሉ፡፡ ‹‹ጉዳዩ ምንም ይሁን ምን ይቅርታ አንዴ ነው፡፡ ካልሆነ ሞኝነት ይመስላል፤›› የሚሉት አቶ ገብረማርያም፣ የአርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ‹‹የልብን እያደረሱ ይቅር በሉኝ›› የሚለውን ዘፈን በማስታወስ፣ ይቅርታ ገደብ ሊኖረው እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡

ለበደላቸው ይቅር ማለት፣ ወይም የበደሉትን ይቅርታ መጠየቅ እሚከብድ የሚተናነቃቸው፣ ቃሉን ለማውጣት የሚከብዳቸው ብሎም ለይቅርታ ልባቸውንና ጆሯቸውን የዘጉ መኖራቸውን ያህል ይቅር ማለትንና ይቅርታ መቀበልን በደንብ የሚችሉም አሉ፡፡

‹‹ይቅር የማለት ችግር የለብኝም›› የምትለው ወጣት፣ ክፉኛ የበደሏት ሰዎች ይቅርታ ጠይቀዋት ይቅር ያለበችበት አጋጣሚ መኖሩን ታስታውሳለች፡፡ በጣም የምታምናት ጓደኛዋ ክህደት የፈጸመችባት ዩኒቨርሲቲ እያለች ነው፡፡ ጉዳዩ ያበሳጫቸው ጓደኞቿም ልጅቷን ክፉኛ ተናግረዋታል፡፡ አግልለዋታል፡፡ ጉዳዩ ተፈጽሞ ወር እንኳን ሳይቆይ ለበደለቻት ጓደኛዋ ይቅርታ አድርጋ አብረው ምግብ ሲበሉ፣ ለሷ ብለው ከልጅቷ የተጣሉ ጓደኞቿ ያዩዋታል፡፡ ‹‹ጓደኞቼ በሁኔታዬ ተገረሙ፡፡ ለልጅቷም ይቅርታ ይገባታል ብለው አያምኑም፡፡ ማንም ሰው ቢበድለኝና ከምር ቢጠይቀኝ ይቅር ብዬ ግንኙነቴን መቀጠል እችላለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ከዚያ ሰው ጋር በሚኖረኝ ግንኙነት የሆነ የጎደለ ነገር ያለ ያህል ይሰማኛል፤››  

እንደ እሷ አባባል፣ የበደላትን/ቻትን ሰው መንገድ ላይ ወይ በሥራ አጋጣሚ ብታገኝ አትዘጋም፣ አብራ ሻይ ለመጠጣትም ሆነ ምግብ ለመብላት ችግር የለባትም፡፡ ሆኖም በፊት ከነበራቸው እምነት ጎድሎ የሚቀር ነገር አለ፡፡ ይቅርታ ማድረግ ቢቻልም፣ ይቅርታው ተበዳዩ ውስጥ ያለውን ጉዳት ሙሉ ለሙሉ አይሽርም፡፡

የሕግ ባለሙያው አቶ ማሙሽ እጅጉ፣ ይቅርታ በማኅበራዊ መስተጋብር ውስጥ ወሳኝ መሆኑን፣ ሰዎችም ይቅር በመባባልና በመቻቻል አብረው እንደሚኖሩ ገልጸው፣ በዚሁ ልክ ታርቀውና ይቅር ተባብለው እስከመጨረሻው በሰላም መዝለቅ የማይችሉ እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሰዎች በዕለት ተዕት ኑሮዋቸው በተለያዩ ምክንያቶች ስለሚገናኙ ነው፡፡

ቀለል ያሉ ጉዳዮች ማለትም በድንገታዊ ግጭት የሚሰነዘር ስድብ፣ የሥራ ላይ ፀብ ፖሊስ ጣቢያ ከደረሰ፣ በፖሊስ ጣቢያው በእርቅ እንዲያልቅ የተዘረጋ አሠራር ቢኖርም፣ በእርቅ ሊያልቁ የሚችሉ ጉዳዮች ፍርድ ቤት ሲሄዱ እንደሚስተዋሉ፣ አንዳንዶችም ይቅርታ ለመቀበልም ሆነ ለመጠየቅ  እንደሚቸገሩ ይናገራሉ፡፡

በፖሊስ ጣቢያ ጉዳያቸውን ጨርሰውና ይቅር ተባብለው ታርቀው የሄዱ ሰዎች በተደጋጋሚ ፖሊስ ጣቢያ የሚሄዱበት፣ ጉዳያቸው ፍርድ ቤት ሲደርስ ደንግጠው ተከሳሽ ፍርድ ቤት ከመቅረቡ በፊት ጉዳዩ በእርቅና ይቅርታ እንዲያልቅ አማላጅ የሚላክበት፣ ከሳሽም ክስ አንስቻለሁ የሚሉባቸው ብዙ ኬዞች መኖራቸውን፣ በዚህ ሁኔታ ከጨረሱ በኋላ ደግሞ መልሰው የሚጋጩ እንዳሉ ይገልጻሉ፡፡

ሳይኮጆሎጂ ቱዴይ በድረ ገጹ እንዳሰፈው፣ ይቅርታ ማድረግም ሆነ ይቅርታን መጠየቅ ሕይወትን ይቀይራል፡፡ ይቅርታ የተጎዳን ሰው የማዳን ኃይልም አለው፡፡ የተበላሹ ወይም የተቋረጡ ግንኙነቶች እንዲቀጥሉ፣ የተሰበረ ልብም እንዲጠገን ይረዳል፡፡

ይቅርታ ማኅበራዊ መስተጋብር ብቻም ሳይሆን ሃይማኖታዊ ሆኖ ክብርና ሐዘኔታን ለሌሎች ማሳየትም ነው፡፡ ይቅርታ ማድረግ ጥፋተኛ ጥፋቱን መረዳቱን የሚያምንበት፣ ጥፋቱ ችላ ከተባለ ደግሞ አለመግባባት የሚፈጠርበት ነው፡፡

ይቅርታ አንድ ሰው የተጎዳበትን ነገር መልሶ ማዳን ባይችልም፣ ያ መጥፎ ድርጊት መልሶ እንዳይፈጠር የማስቻል ኃይል አለው፡፡

ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ ይቅርታ ማድረግም ሆነ መጠየቅ አካላዊና አዕምሮአዊ ጤናን ይመልሳል፡፡ በተለይ ይቅርታን መቀበል አዎንታዊ የሆነ የአካል ደኅንነት ያመጣል፡፡ የደም ግፊት ይቀንሳል፣ የልብ ምት ይስተካከላል፣ የአተነፋፈስ ሥርዓትም ያስተካክላል፡፡

 

  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...